Saturday, 27 April 2019 10:36

የሁሉም ነገር ትንሳኤ ይሁንልን!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው አደረሳችሁማ!
ዋዜማ ነው፡፡ ዛሬ ምሽት ከተማዋ ያው እንደለመደባት፣ (ምናልባትም አዳዲስ ልምዶችን ጨምራ!) በ‘አውራ ጣቷ’ የምትቆምበት ነው፡፡ ነገና ከነገ ወዲያ የሌሉ ይመስል፣ ሲነጋ የዓለም ፍጻሜ ይመስል… ይጠጣል፣ ይበላልም፡፡ ከመስከረም ጀምሮ.. አለ አይደል… “በቀን ሦስቴ መመገብ እንደናፈቀኝ ነገር…” ስንል የነበርነው ሁሉ የሆነ በዓል ሲመጣ… “ገንዘቡን እንዲህ ከሚረጨው ምናለበት የሆነች ሱቅ ቢጤ ቢከፍትባት…” ሊያስብለን ምንም በማይቀረው ‘ቸርነት’ ብሩን ስንመዘው አምሽተን እናድራለን::
የምር ግን፣ …“ኑሮ አደቀቀን፣ ሰበረን፣ አነካከተን…” ስንል ከርመን በዓል በመጣ ቁጥር “ከበር መልስ  የእኔ ሂሳብ ነው…” የሚያሰኘን ፈራንካ… በዚያ ፍጥነት ከየት እንደሚመጣ እስካሁን ያልተደረሰበት ሆኗል፡፡ ይሁና…እንግዲህ ምን ይደረጋል፡፡ አረረም፣ መረረም ምናልባት ለአንድና ለሁለት ቀናት ብቻ እንኳን ቢሆን ከገባንበት ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ፋታ ማግኘትማ አንድ ነገር ነው፡፡ እናማ… ደስታ እየራቀን ይመስላል:: የተፈጥሮ ሳቃችን እንኳን አየጠፋ ‘ሳብ ብሎ ግጥም’ በሚል ፕላስቲክ ሳቅ እየተተካ ነው፡፡ ደስታችንም ቢሆን ፈረንጅ እንደሚለው ‘ስኪን ዲፕ’ ወይም ‘ላይ ላዩን’ እየሆነ ነው፡፡ በዚህ የትንሳኤ ሰሞን ሙሉ ደሰታ የምናገኝበትን ጊዜ ያፋጥንልን እንላለን፡፡
ስለ ደስታ ካነሳን አይቀር ይቺን እዩልኝማ…በአንድ መንደር አንድ ሰማንያ ዓመት ሊሞላቸው የደረሱ አዛውንት ነበሩ፡፡ ታዲያ አንድም ቀን ደስ ብሏቸው አያውቅም፣ ሁልጊዜም አቤቱታ እንዳቀረቡ ነው፣ እንደተነጫነጩ ነው:: መንደረተኛው ሁሉ በእሳቸው ነገር ምርር ብሎታል፡፡ ማንኛውም ሰው እሳቸውን ባየ ቁጥር ፊት ለፊት ላለመገናኘት መንገድ እያሳበረ ነበር የሚሄደው፡፡
አንድ ቀን ልክ ሰማንያኛ ዓመት ሲሞላቸው አስገራሚ ነገር ተከሰተ፡፡ ወሬው ወዲያው ተዛመተ፡፡ “ሽማግሌው ምን አግኝተው ነው ዛሬ ደስ ብሏቸዋል:: ስለምንም ነገር አያማርሩም:: ፈገግታ በፈገግታ ሆነዋል፣” ተባለ:: መንደረተኛውም አዛውንቱ ወዳለበት ሄደ፡፡ “ምን ተገኝቶ ነው እንዲህ የሆኑት?” አላቸው:: አዛውንቱ ምን ቢሉ ጥሩ ነው… “የተለየ ነገር የለም፡፡ ለሰማንያ ዓመታት ደስታን ሳሳድድ ኖርኩ፡፡ ግን አልተሳካልኝም፡፡ አሁን ደስታን ማሳደድ ትቼ ኑሮዬን ለማጣጣም ወሰንኩ፡፡ ለዚህ ነው ደስተኛ የሆንኩት፣” አሏቸው፡፡
ስሙኛማ… በቀደም አንድ ወዳጃችን የሆነ ዘመዱ ያገኘውና የባጥ የቆጡን ሲያወሩ ይቆያሉ:: ከዛላችሁ…ዘመድ ሆዬ ምን ይለቀዋል….
“እስካሁን ቤት አልሠራሁም እንዳትለኝ!”
ወዳጃችን ብሽቅ” ቢልም ንዴቱን ይውጥና… “አልሠራሁም…” ይላል፡፡ ይሄኔ ዘመድ ሆዬ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“አንተ ሰውዬ፣ ገንዘቡን ምን እያደረግኸው ነው?”
ወዳጃችን “በቃው” እንደሚባለው፣ አንገቱ ይደርስበታል፡፡ እሱ ለራሱ ወር ከወር እንዴት እንደሚደርስ እሱና ቤተሰቦቹ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ እናላችሁ… ከመናደዱ የተነሳ በጽሁፍ ሊሰፍሩ የማይችሉና ከወዳጃችን አንደበት ይወጣሉ ተብሎ የማይገመት የስድብ ናዳ ያዘንብበታል፡፡ “ሁለተኛ እንዳትደርስብኝ!” ብሎም ዝምድናውን በጥሷል ፡፡
እኔ የምለው…ዘመድ ተብዬውስ ልክ እሱ ፔይሮል ላይ እሚያስፈርመው ይመሰል… “ገንዘቡን ምን እያደረግኸው ነው?” ብሎ ‘ሀራስመት’ ምን ማለት ነው፡፡ ልክ ወፈር ብላ የታሰረች ‘ዶላሬዋን’ በ’ፎርቲ፣’ በ’ፎርቲ፣’ ያስቆጠራችሁ ይመስል… አለ አይደል… “ብቻ እስከ ዛሬ መኪና አልገዛሁም እንዳትለኝ…” ሲላችሁ የምር ቀሺም ነው፡፡ አንዳንዶቻችን ‘ወሬ አማረልኝ’ ብለን፣ ወይም ነገርዬው የለበጣ መሆኑን እየተዋወቅንም ሰውየው ደስ ይለዋል ብለን፣ “እንዴት ጥሩ ብታስብልኝ ነው ‘አንዲት ራቭ ፎር ግዥ እንጂ!’ አለችኝ” ትለናለች ብለን፣ እንዳመጣልን የምንናገረው ነገር ውሎ አድሮ ትዝብት ላይ ባይጥለን ነው!
እናላችሁ…አንዳንዶቻችን ሰው ሁሉ እንደኛ ህብረተሰቡን በጠላትና በወዳጅነት ለሁለት የሚከፍል፣ ከእኛ ወገን ስላልሆነ ብቻ የእኛ ጠላት ነው ማለት (ፈረንጅ ‘ባይ ዲፎልት’ እንደሚለው ማለት ነው…) ደስ አይልም፡፡ መማማር አኮ አሪፍ ነው...በራሱ የሚተማመን ሰው ስህተቱን ሲነግሩት “ስለነገራችሁኝ አመሰግናለሁ…” ምናምን ብሎ ብሎ ለማስተካከል ይሞክራል፡፡
እናላችሁ…አሁን ችግሩ ሰዎች የሆነ ነገር ተናግረው ‘ሊሉ በፈለጉትም’ ‘ሊሉ ባልፈለጉትም’ እየተኮነኑ ነው፡፡ “እሱ እኮ ድሮም ቢሆን…” አይነት ነገር ሰዎች ሀሳባቸውን እንዳይገልጹ እያሸማቀቃቸው ነው፡፡ በግልጽ መነጋገር ካልቻልን፣ ሀሳባችንን በዚህ ይተረጎምብኛል፣ በዛ ይታሰብብኛል ሳንል ፊት ለፊት ለመለዋወጥ ካልቻልን ነገራችን ዞሮ፣ ዞሮ እዛው ነው የሚሆነው፡፡
 እግረ መንገዴን አንዲት ነገር መጥቀስ ፈልጌ ነው:: ደገምገም ስለተደረገች ዝም ብዬ ላለማለፍ እንጂ ለመመላለስ አይደለም:: የሆነ ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ አማርኛ ፕሮግራም ላይ አንድ የተረጎምኳት የታሪክ መጽሀፍ ላይ ሲያወሩ፣ የሆኑ ነገሮች ሳይካተቱ የቀሩት እኔ ሆነ ብዬ የሆኑ ህብረተሰብ ክፍሎችን ታሪካቸውን ለማዛነፍ እንደሆነ አድርገው ሲናገሩ ነበር:: የሆነ ሥራን ቀሺም ነው ማለት አንድ ነገር ነው፣ ለሠሪውም ትምህርትም እርምትም ነው፡፡ ሳይካተቱ የቀሩ ነገሮች ካሉ ቀጥታ ከትርጉሙ ስራ ባህሪይና አካሄድ ጋር በተያያዘ፣ ወይንም በትርጉምም ሆነ በአርትኦት ወቅት በተርጓሚው የተፈጠሩ ስህተቶች ይሆናሉ፡፡ ከዛሬው ድክመት ለነገው ሥራ ትምህርት ይወሰዳል፡ በቃ ይኸው ነው፡፡ እና…ጠላት በማብዛት ፖለቲካ ‘የሌለ ገመድ መጎተት’ ትክክል አይደለም! ደግሞ “የእኛ…” የምንለው ያልሆነው ሰው ሁሉ አእምሮ በሴራ ፖለቲካ የተበከለ ነው ብሎ ማሰብ ደግ አይደለም፡፡ ይህኛውን ‘እዳው ገብስ ነው’ እንበለውና ሌላም ይበልጥ አስገራሚ ‘ክስ ቢጤም’ ነበረች፡፡
ከአስራ ምናምን ዓመታት በፊት በአንድ መንግስታዊ ጋዜጣ ላይ የወጣ ነገር ነበር:: ነገርዬው እንደ ግጥም ሆኖ የስንኞቹ የመጀመሪያዎቹ ፊደላት ቁልቁል ሲነበቡ ከሆነ ከዘር ጋር የተያያዘ መልእክት ነበራቸው፡፡ (እግረ መንገድ… እኔ በወቅቱ እለታዊው እንግሊዝኛው ጋዜጣ ላይ ነበርኩ፡፡) እናማ በወቅቱ ያ ጽሁፍ ከፍተኛ ነውጥ ፈጥሮ፣ ጻፉት የተባሉ ሰዎችም ችግር ገጥሟቸው ነበር፡፡ እና የተባለው ቴሌቪዥን ላይ የዚህን ሥራ ‘ኮፒራይት’ ነገር ወደ እኔ አዙረውታል፡፡ (“ዘይገርም ሻሸመኔ” የተባለው ከምን ጋር ተያይዞ ነው!)
ደግሞላችሁ ነገርዬው የቀረበው “ድሮም ቢሆን ሰውየው እኛ ላይ…” ምናምን ተብሎ እንደ ምናምነኛ የከሳሽ ኤግዚቢት ሆኖ ነው፡፡ (ጊዜው ራሱ በወራትና በዓመታት ቢቆጠር እኮ “ዘ ሎንገስት…” ምናምን የሚል ‘ፈረንጂኛ’ ሊገባበት ይችል ነበር!) ይቺን ለመጻፍ የተገደድኩት ‘ራስን ለመከላከል’ ምናምን አይደለም፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ፕሮግራሙ ከተላለፈ በኋላ ከዚቹ ከአዲስ አበባና ጣቢያው ካለበት ከተማ ጉዳዩን የሚያውቁና ትንሽ ግራ የገባቸው ወዳጆች ደውለው ይነግሩኛል፡፡ ስንት ሚዲያው የሚያነሳቸውና ሊያነሳቸው የሚገቡ የሀገር አጀንዳዎች ባሉበት በዚህ በተወጠረ ጊዜ በ“ሶ ሁዋት!” አይነት አልፌው ነበር፡፡ በቃ ይሄ ግላዊ ጉዳይ ነው፡፡ ረቡእ እለት ፕሮግራሙ ሲደግሙት ሌሎች ወዳጆች ይነግሩኛል፡፡ ለዚህ ነው…አንዳንዴም ዝምታ ወርቅ ስለማይሆን፣ አንድ ሁለት ቃል ጣል ማድረጉ ከፋት የለውም በሚል ትንሽ ጣል ማድረጉ ክፋት የለውም በሚል ትንሽ ለማለት የፈለግሁት፡፡
ስለሆነም የተባለው ጣቢያ ላይ ራሳቸው በመጠኑት ብሩሽና ራሳቸው በመረጧቸው ቀለማት ለሳሉኝ ሰዎች አንዲት ነገር ለመናገር ብቻ:: (ለአንባቢዎች… ይህንን እንዳልተለመደ ‘ተራ መታበይ’ አይነት እንዳትውስዱብኝ:: መባል ስላለበት ብቻ እለዋለሁ እንጂ በዚሀ አይነት ቅላጼ ማውራቱ ለአኔም ምቾት የሚሰጠኝ ሆኖ አይደለም::) …እናማ ለሰዎቹ… “እናንተ የጠቀሳችሁት አይነት እኩይነት፣ አንዱን የህብረተሰብ ክፍል አውርዶ ሌላኛውን ሰማይ የሚያደርስ የድንጋይ ዘመን ጎጠኝነት፣ እናንተ እንደምታስቡት ሲፋቅ ብቅ የሚል ሴረኝነት፣ በሚታየው እጅ ጽጌረዳ አስይዞ፣ በማይታየው ሳንጃ የሚያስጨብጥ የኢያጎ ስነልቡና… የመሳሰሉት ጸረ ማህበረሰብ ባህሪያት በተሰራሁበት ዲ.ኤን.ኤ. ውስጥ የሉም፡፡ ይኸው ነው፡፡ ( ሰውየው በሆነ ነገር የልባቸው ሲደርስ “እሰይ፣ እሰይ… እግዜር ይስጥሽ” አይደል ያሉት!) እኔ የምለው…ደግሞ ፎቶዬ ላይ በቀይ ‘ኤክስ’ አድርጋችሁ ጣቢያው ግድግዳ ላይ ስቀሉት አሉ! ቂ…ቂ…ቂ… (በነገራችን ላይ በዚህ አይነት ነገር ስትከሱኝ — ‘ወቀሳ’ ስላልነበረ — ከአፍሪካም አንደኛ፣ ከዓለምም አንደኛ መሆናችሁን ስገልጽላችሁ፣ ቢያንስ ለትብብሬ ልታመሰግኑኝ ይገባል! ቢያንስ አንድ ታሪክ ነው!) እግረ መንገድ…የስንትና ስንት ስልጣኔ መሰረትና መነሻ በሆነ አካባቢ ሆናችሁ ዶማ ይዛችሁ ‘መካሰሻ’ ከምትቆፍሩ በእውቀት በዳበረ አእምሮና በቅንነት በጠራ ልብ የበኩላችሁን ታሪክ ስሩ፡፡ (ብችልበት ኖሮ እንደ እናቶቻችን ወገቤን ይዤ “ምነው ሸዋ!” እል ነበር፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… )
ዋዜማችሁን አበላሸሁትሳ፡፡  መልካም የበዓል ሰሞን፡፡ የሁሉም ነገር ትንሳኤ ይሁንልንማ!
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 2106 times