Saturday, 27 April 2019 10:23

ቃለ ምልልስ መፅሐፍ ቅዱስ ስለ ዘረኝነትና ጎሰኝነት ምን ይላል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 “--እስረኞች ተፈቱ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ሠፋ። ከዚህ በኋላ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያቱ ምንድን ነው? እኔ ካልነገስኩ
ነው? ይሄ ከሆነ የህግ የበላይነትን ማስከበር ያስፈልጋል፡፡ በየትኛውም ዲሞክራሲያዊ በሚባል ሀገር ውስጥ ህግ ቀጭን ነው፡፡
ከተጐተተ ይበጠሳል፤ ስለዚህ ሳይበጠስ በጣሹን ለህግ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡--”

             ሰሞኑን ዓመታዊ ጉባኤዋን ያካሄደችው የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ቤተ ክርስቲያን፤ “ክርስትና እና ብሔርተኛነት” በሚል ርዕስ በጥናት ላይ የተመሰረተ ውይይት አድርጋለች፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ ፓስተር ፀድቁ አብ፣ በመድረኩ ላይ የራሣቸውን ጥንታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ለመሆኑ መፅሐፍ ቅዱስ ስለ ዘረኝነትና ብሔርተኝነት ምን ይላል? አማኝነትና ብሄርተኝነት ምንና ምን ናቸው? በአገራችን የሚታየውን ግጭትና ማፈናቀል ለመግታት ከሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች ምን ይጠበቃል? በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ፓስተር ጸድቁ አብን አነጋግሯቸዋል፡፡


            ሰሞኑን በቤተ ክርስቲያናችሁ ስለተካሄደው ጉባኤ ይግለፁልኝ?
በየአመቱ መደበኛ ጉባኤ እናካሂዳለን:: እንደ ሁኔታው አጀንዳዎች እናስቀምጣለን:: የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው አጀንዳው አሳሳቢ ጉዳይ ላይ ማተኮሩ ነው፡፡ “ብሔርተኝነት እና ክርስትና” የሚል ነበር የአጀንዳው ርዕስ:: በዚህ ርዕስ ላይ አራት ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ አንደኛው፤ ከስነ ሰብ (አንትሮፖሎጂ) አንፃር ብሔርተኝነትን እንዴት ነው የምንረዳው የሚል ነው፡፡ ብሔር ለግጭት መንስኤ ይሆናል ወይ? በዚህ ላይ ሁለት ምሁራን ጥናት አቅርበዋል፡፡ ጥናት አቅራቢዎቹ የግጭት አፈታት ምሁራን ናቸው፡፡ አንደኛው፤ በጉጂና በጌዲኦ የተከሰተው ችግር ላይ ጥናት አድርገዋል፡፡ ጥናቱ፤በግጭቱ እነማን ተሳተፉ? እንዴት ተፈጠረ? የሚሉትን ይዳስሳል፡፡
የጌዲኦና ጉጂ ግጭት እንዴት ለጥናት ተመረጠ?
እንደሚታወቀው በደቡብና በአዋሳኙ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ይበዛሉ:: በዚያ ግጭት ውስጥ በብዛት ተሣታፊ የነበሩት እነማን ናቸው? የየትኛው እምነት አባላት ናቸው? የሚለው ይታወቃል ማለት ነው:: ፕሮቴስታንቶች ይበዙበታል በሚባል አካባቢ፣ ይሄ ከተከሰተ ምን ማለት ነው? የሚለው ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ እንዴት ነው ክርስቶስን እያመለኩ፣ የእርቅ መልዕክት ወንጌል (መጽሐፍ ቅዱስን) እያወቁ፣ ሰዎች ከሌላው ጋር ግጭት ውስጥ የሚገቡት? የሚለው አሳሳቢ ስለሆነ ነው ጥናቱን በዚያ አካባቢ ያደረገው፡፡ ሁለተኛው የውይይት መነሻ የጥናት ወረቀት፣ ብሔር እና ወንጌላዊ እምነታችን እንዴት ነው የሚጣጣሙት? ብሔርን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር እንዴት እንረዳለን? የሚል ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከስነ-መለኮት አንፃር ጥናት ያቀረብኩት እኔ ነበርኩ፡፡ ቄስ ዶ/ር ገለታ ደግሞ በተግባር የሚታዩ ችግሮች ምንድን ናቸው? የሚል ነው ያቀረቡት፡፡
እርስዎ ባደረጉት ጥናት፣ መጽሐፍ ቅዱስ  ስለ ብሔርተኝነት ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ብሔርተኝነት ምን ይላል የሚለውን ከዘፍጥረት ጀምሮ ነው የተመለከትኩት:: እንደምናየው፤ በአንድ በኩል ልዩነትን ያለመቀበል፣ በሌላ በኩል ልዩነትን ከልክ በላይ የማጉላት ዝንባሌዎች በተግባር አሉ፡፡ አንዳንዱ ልዩነትን ከልክ በላይ ያጐላውና ህብረትን ወይም አንድነትን የሚያኮስስ ነገር ይፈፀማል፡፡ ሌላው ደግሞ አንድነትን ያጐላና የሰው ልጅ ምንም ልዩነት እንደሌለው አድርጐ ያቀርባል፡፡ በተለይ በወንጌላውያን አማኞች ውስጥ ብሔርን አስመልክቶ ሁለት ዋልታ ረገጥ አመለካከቶች እንዳሉ በጥናቱ ተረድተናል:: አንደኛው “እኔ ክርስቶስን ተቀብያለሁ፤ ከላይ ተወልጃለሁ፤ ስለዚህ ብሔር የለኝም” የሚል ቡድን ነው፡፡ ሌላው ቡድን ደግሞ “የኔን ብሔር ማንነት ያልተቀበለውን ክርስቶስን ራሱ አልቀበለውም” የሚል አክራሪ ነው:: እነዚህ ልዩነቶች በዋዛ የሚታዩ አይደሉም:: እነዚህ ልዩነቶች መኖራቸውን ስናውቅ ነው፣ ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን እንዴት ነው የሚመለከተው ወደሚል የተመለስነው። እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ፤ እግዚብሔር ሰውን በአምሳሉ ፈጠረው ይላል:: ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠራቸው፡፡ ለምሣሌ ዘፍጥረት ቁጥር አምስት ላይ “የአዳም የትውልድ መጽሐፍ ይህ ነው፤ እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን እግዚአብሔር ምሣሌ አደረገው፡፡ ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠራቸው ባረካቸውም፡፡ ስማቸውንም በፈጠራቸው ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው” ይላል:: በእንግሊዝኛውም ተመሳሳይ ትርጉም አለው:: አዳምና ሄዋንን እግዚብሔር ሰው (አዳም) ብሎ ነው የጠራቸው፡፡ ስለዚህ በሃጢያት እስከ ወደቀበት ድረስ አዳምና ሄዋን ምንም አይነት የፆታ የበላይነት አልነበራቸውም፤ ሰው ነበሩ፤ በሰውነታቸው እኩል፡፡ ሰውን ሰው በሚያሰኝ ጉዳይ ልዩነት አልነበራቸውም::
የፆታ ልዩነት እንዲኖር የተፈቀደበት ምክንያት፤ እንዲባረኩ እንዲወልዱ እንዲበዙ ነው እንጂ አንዱ ሌላውን በፆታው እንዲያጠቃ አይደለም:: በሃጢያት ሲወድቁ ነው አዳምና ሄዋን የእርስ በእርስ ክስ የጀመሩት፡፡ “ከአጥንቴ የሰጠኸኝ ሴት ነች ያሣሣተችኝ” በሚል ነው አዳም ክስ የጀመረው:: ሰውም እርስ በእርሱ መወነጃጀሉ የመጣው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው:: ሌላው በፍጥረት ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር የባህር አሶችን በየአይነታቸው፣ ወፎችን በየአይነታቸው ፈጠረ ይላል፡፡ ስለዚህ አሶችና ወፎች ሲፈጠሩም ጀምሮ የተለያዩ ነበሩ ማለት ነው፡፡ እስከ ሃጢያት ውድቀት ድረስ በእነዚህ መሃልም መጠቃቃት መበላላት አልነበረም:: ከሃጢያት ውድቀት በኋላ ነው አቅም ያለው፣ አቅም የሌለውን ማጥቃት መብላት የተጀመረው:: ስለዚህ ፍጥረት በሙሉ ከሃጢያት ውድቀት በፊት ልዩነት ነበረው፡፡ በልዩነቱ ምክንያት ግን ግጭት አልነበረውም። ከሃጢያት ውድቀት በኋላ ያ ልዩነት ለፀብ ምክንያት ሆነ፡፡ ክፋት ሲገባ ፀብ አብሮ መጣ፡፡ የፀብና አለመግባባት አፈጣጠሩ ይሄ ነው፡፡
ብዙ ሰዎች ዘፍጥረት ምዕራፍ 11 ላይ የተቀመጠው፣ የባቢሎን ግንብ ገንቢዎች ቋንቋ መደበላለቅ ታሪክ ነው፣ በሰው ልጆች ላይ ሁሉ ልዩነት ያመጣው ይላሉ፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፤ ነገሮች መከፋፈል የጀመሩት ከኖህ ልጆች ነው፡፡ ለምሣሌ የሴም ልጆች በየነገዳቸው በየቋንቋቸው ይላል፡፡ ኩሾችንም ያስቀምጣል፡፡ ስለዚህ የነገዶች አመጣጥ ከኖህ ዘመን ነው እንጂ ከባቢሎን ግንብ በኋላ አይደለም፡፡ ወደ አዲስ ኪዳን መጥተን ደግሞ ያ በፊት እንደ እርግማን ይቆጠር የነበረው እግዚአብሔር የደበላለቀው ቋንቋ በኋላ ደግሞ በልዩ ቋንቋ ጭምር ሰዎች እንዳመሰገኑ ይነግረናል፡፡ እርግማን ነው የተባለው የቋንቋ መደበላለቅ፤ በኋላ ላይ በተለያየ ቋንቋ እግዚአብሔርን ለማመስገን ሰዎች እንደተጠቀሙበት ማየት እንችላለን:: ስለዚህ አንድ ቋንቋ ከሌላው በላይ ቅዱስ አለመሆኑን፣ ሁሉም በፈጣሪ የተወደዱ እኩል ተቀባይነት ያላቸው መሆኑን ያሳየናል፡፡ ታዲያ ለምን ዛሬ በቋንቋ የኔ ይበልጥ ያንተ እየተባባልን እንጣላለን? ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናየው፤ ብሔር (ነገድ) በራሱ ችግር አይደለም፡፡ የራስን ብሔር መውደድም ሃጢያት አይደለም፡፡ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ ስለሚል፣ ልክ እኔ ለራሴ የምሰጠውን ክብር፣ ለሌላውም ብሔር መስጠት አለብኝ፡፡ ሌላውንም እንደ ራሴ ብሔር አባል መውደድ አለብኝ፡፡ የራስን ብቻ መውደድ ጥሩ አይደለም፡፡ በፈጣሪ ዘንድም ዋጋ ያስከፍላል፡፡
ዘረኝነትን እርስዎ እንዴት ይገለጹታል?
ዘረኝነት ንፁህ አይደለም፡፡ የበታችነት ስሜት ነው፡፡ እኔ ነኝ የበላይ ከሚል ስሜት የሚመጣ ነው፡፡ እኔ ነኝ መኖር ያለብኝ፤ ሌላው አያስፈልግም ከሚል የሚመጣ ችግር ነው፡፡ ለዚህ አይነቱ አስተሳሰብ መገለጫው የአዶልፍ ሂትለር አቋም ነው፡፡ ወይም ሁቱዎች ቱትሲዎች ላይ የተከተሉት አቋም። አይሁዶች በአህዛብ ላይ ያላቸው አቋም ነው፡፡ በነገራችን ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አይሁዶች ራሳቸው የዘር ልዩነት ነበራቸው። የገሊላ አካባቢ አይሁዶችና የይሁዳ አይሁዶች እርስ በእርስ ይናናቃሉ:: ሁለቱ በጋራ ደግሞ ሄሌኒስቲክ የሚሏቸው ማለትም የግሪክን ቋንቋና ፍልስፍና የተማሩ አይሁዶችን ይጠሏቸዋል፡፡ ሦስቱም የአይሁድ ወገኖች በእጅጉ ይጠላሉ ነበር፡፡ በሌላ በኩል አይሁዶችና ሠመራውያን እርስ በእርስ ይጣሉ ነበር፡፡ የይሁዳ አይሁዶች ወደ ገሊላ ለመሄድ የሠመራውያን መሬትን ረግጠው ላለመርከስ ዙሪያ ጥምጥም ነበር የሚጓዙት፡፡ ክርስቶስ ግን ይሄን አፍርሶ በቀጥታ ነበር ወደ ሠመሪያ የሄደው፡፡ የሠመራውያንን ሰዎች አነጋግሯል፡፡ ይሄን ሲያደርግ ክርስቶስ ብዙ የጥላቻ ግንቦችን ነው የደረመሰው:: አይሁዳዊ ወንድ ከሠመራዊ ሴት ጋር መነጋገር አይችልም ነበር። ክርስቶስ ግን ይሄን ጥሷል:: ሠመራዊቷን ሴት  አስተምሯል፡፡ ሠመራዊያንን ከለምፃቸው ፈውሷል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ከጥንቱም ዘረኝነትና ጐሰኝነት እንዳለ ይነግረናል፤ በዚያው ልክ ተገቢ አለመሆኑንም ያስተምረናል፡፡ በክርስቶስ የዘር ሀረግ ውስጥ በማቴዎስ ወንጌል የተጠቀሱት ከጌታችን እናት ማሪያም በስተቀር አራቱ ከአህዛብ ወገን ናቸው:: ይሄ ምን ያሳያል? አይሁዶች አህዛቦችን መናቅ እንደሌለባቸው ማስተማሪያ ነው፡፡ አብርሃምን የባረከው ካህኑ መልከፀዴቅ፣ ከአይሁድ ወገን አልነበረውም፡፡ ሙሴን የመከረው አማቱ ዮቾር ከአይሁዳውያን አይደለም፡፡ ይሄ የሚያሳየን በብሔርና በዘር መከፋፈል ከጥንትም የነበረ፤ ነገር ግን በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ነው::
ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሃገር ነች ይባላል፤ በዚያው ልክ ለሞራልና ስነ ምግባር ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች ይፈፀማሉ፡፡ ይህ ለምን የሚሆን ይመስልዎታል?
የልብ እምነት ስለሌለን ነው፡፡ እምነት የልብ ካልሆነና ዝም ብሎ የእይታ ከሆነ አደገኛ ነው:: እኛም በጥናታችን የለየነው አንዱ ችግር ይሄ ነው፡፡
የሃይማኖት ተቋማትና የእምነት አባቶች ለዚህ ተወቃሽ ናቸው የሚሉ ወገኖች አሉ …
ይሄ እንደ ሁኔታው ይወሰናል፤ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ አሉ፤ የማይወጡም አሉ:: እንደውም አንዳንዶቹ ከምዕመኑ አንሰው በዘር ግጭት ተሣታፊ ሲሆኑ እንመለከታለን፡፡ እኛም በምልክታችን ያስተዋልነው ሃቅ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ንስሃ ያስፈልገዋል፡፡
ለምንድነው የሃይማኖት አባቶች የሀገሪቱን ግጭቶች መፍታት የተሳናቸው?
እውነቱን ለመናገር የሃይማኖት አባቶች ብዙ ስራ ሠርተዋል፡፡ ለምሣሌ በአማራና በትግራይ ወጥነት በነገሠ ጊዜ የሁለቱን ክልል ፕሬዚዳንቶች ማገናኘት ችለናል፡፡ ሁለቱም በወቅቱ ለህዝባቸው ቃል ገብተዋል:: ቃላቸውንም ከሞላ ጐደል ፈጽመዋል:: ብዙ መሠራት አለበት ከተባለ ግን ትክክል ነው:: በዚያው ልክ በሀገሪቱ ውስጥ የሃይማኖት አባቶች ሚናቸውን እንዳይወጡ የሚሠሩም አሉ፡፡ ብጥብጡን ሁከቱን የሚፈልጉ አሉ:: እነዚህ አካላት የተለያየ ዘመቻ በመክፈትና የግጭት ክብሪት በመጫር፣ ሂደቶችን ሲያበላሹ ተመልክተናል፡፡ አለመተማመንን በመዝራት የተካኑ በርካቶች አሉ፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላም ዋናው መፍትሔ መተማመን መፍጠር ነው፡፡
በጌዲኦና በጉጂ ግጭት ውስጥ የገባው አብዛኛው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ነው ብለዋል:: ችግሩን ለመፍታት በእናንተ በኩል ምን ጥረት እየተደረገ ነው?
አብዛኛው ተልዕኮአችን ማስተማር ነው:: በብሔርተኝነትና በሠላም ጉዳይ ለማስተማር ለአራት አመት የሚቆይ ፕሮጀክት ቀርፀናል:: አምስት አካባቢዎች ላይ ጥናት ተደርጐ ተጠናቋል:: በኦሮሚያ ሶስት አካባቢዎች፣ በደቡብ ሁለት አካባቢዎች ማለት ነው፡፡ ደቡብ ላይ የጌዲኦ ዞን ከተሞች፣ ዲላና ሚዛን ቴፒ አካባቢ፣ ኦሮሚያ ደግሞ አዳማና ጉጂን ጨምሮ ትምህርት እንሠጣለን፡፡ በጉዳዩ ላይ ውይይቶች እናደርጋለን፡፡ ስለ እርቅና ሠላም እናስተምራለን:: በቅርቡ ውይይቶችና ትምህርታዊ ኮንፈረንሶች ይኖሩናል፡፡ ጠንከር ብለን በዚህ ጉዳይ ለመስራት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡
ማህበረሰባችን የሞራልና የስነምግባር ውድቀት አጋጥሞታል የሚሉ ምሁራን አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
አንዳንድ የምናያቸው ነገሮች በእርግጥም አጋጥሞናል የሚያስብሉ ናቸው፡፡ ሰውን ዘቅዝቆ መስቀል ከየት የመጣ አረመኔያዊ ድርጊት ነው? ሰውን በቁሙ ማቃጠል ከየት የተማርነው ጭካኔ ነው? እኔ በእድሜ ዘመኔ ያላየሁትን ጭካኔ ነው ባለፈው አንድ አመት ያየሁት:: ይሄን ከየት አመጣነው? ይሄ አደገኛ የሞራል ውድቀት ምልክት ነው፡፡ ከዚህ ወደ ከፋ ሁኔታ መሄድ የለብንም፡፡ ለዚህም ማህበረሰባችንን ማስተማር፣ በስነምግባር ማነጽና ወደ ፈጣሪ መፀለይ አለብን፡፡
አማኝነትና አክራሪ ብሔርተኝነት እንዴት ይታረቃሉ?
ሁለቱ በፍፁም አብረው የሚሄዱ አይደሉም:: አንድ ሰው እነዚህን ሁለት ጽንፎች አብሮ ማስኬድ አይችልም፡፡ አንዱን መምረጥ አለበት:: ወይ መጽሐፍ ቅዱሱን መተው ነው አሊያም ወደ መጽሐፍ ቅዱሱ መመለስ ነው፡፡ ምርጫው ይሄ ብቻ ነው፡፡
በየቦታው የሰው ህይወት እየቀጠፉ ያሉ ግጭቶች እንዴት ይቆማሉ? ከመንግስትና የሃይማኖት መሪዎች ምን ይጠበቃል?
መንግስት ከዚህ በኋላ የህግ የበላይነት ማስከበር ላይ አትኩሮ መስራት አለበት፡፡ እኛ ደግሞ ማስተማር አለብን፡፡ ለሀገራችንም አብዝተን መፀለይ አለብን:: መንግስት ግን በዋናነት ህግን ማስከበር አለበት:: እስረኞች ተፈቱ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ሠፋ። ከዚህ በኋላ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሚሆነው ጥያቄ ምንድን ነው? እኔ ካልነገስኩ ነው? ይሄ ከሆነ የህግ የበላይነትን ማስከበር ያስፈልጋል፡፡ በየትኛውም ዲሞክራሲያዊ በሚባል ሀገር ውስጥ ህግ ቀጭን ነው:: ከተጐተተ ይበጠሳል፤ ስለዚህ ሳይበጠስ በጣሹን ለህግ ማቅረብ ያስፈልጋል:: የመንጋና የቡድን አስተሳሰብ መንገሱ አደገኛ ነገር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም  መንገኝነት ተጠቅሷል:: “ብዙዎቹ ሰልፍ ወጥተው ስለሚጮሁበት ጉዳይ አያውቁም ነበር” ይላል መጽሐፍ ቅዱስ። አሁንም የምናየው እንደዚያ አይነቱን ነው፡፡ ለውጡ በጣም ፈጣን ነገሮችን አሳይቶናል፡፡ ይሆናል ተብሎ የማይጠበቅ የሆነበት ለውጥ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን መስከን አለበት፡፡ ነገሮች ሰክነው ተቋማዊ መስመር መያዝ አለባቸው፡፡
የትንሣኤ በዓል ነውና ለህዝቡ ምን ይላሉ?
በዓሉ እንግዲህ በርካታ መንፈሣዊ ትርጉሞች አሉት፡፡ አንዱ “የሚያደርጉትን አያውቁምና አባት ሆይ ይቅር በላቸው” ብሎ ክርስቶስ የፀለየው ነው:: በደል ተፈጽሞበት እያለ፣ ስለ እኛ ስለ በደለኞች የማለደው እርሱ ነው። የፍቅር፣ ይቅር የመባባል በዓል ስለሆነ፤ በደልን በምህረት በይቅርታና በፍቅር አልፈን፣ አንዳችን ከሌላው ጋር ታርቀን፣ በሠላምና በደስታ እንድናከብር እጠይቃለሁ:: በአሉን ከኛ እኩል ለማክበር አቅም ለሌላቸው ደግሞ ተገቢውን ድጋፍ እንድናደርግ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ::  


Read 8788 times