Saturday, 27 April 2019 10:16

የፋሲካ እንግዳ - ጎሳዬ ተስፋዬ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

 ለዳግም ትንሳኤ ኮንሰርቱ ልምምድ ጀምሯል

      • ፖለቲከኞች አንድ ሆነው አንድ እንዲያደርጉን እፈልጋለሁ
      • ወደ ቀልባችን ካልተመለስን፣ወደ ከፋ ችግር እንገባለን

             ከ11 ዓመት በኋላ በቅርቡ “ሲያምሽ ያመኛል” የተሰኘ አዲስ አልበሙን ለአድናቂዎቹ ያደረሰው ዝነኛው ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ በዳግም ትንሳኤ ዋዜማ ምሽት በጊዮን ሆቴል ለሚያቀርበው ኮንሰርት፣ ከቅላፄ ባንድ ጋር ልምምድ መጀመሩን ይናገራል፡፡ ድምጻዊው በሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን አዘጋጅነት የሚቀርበውን “ሲያምሽ ያመኛል” የተሰኘ ኮንሰርቱን በተመለከተ ባለፈው ረቡዕ፣ በሀያት ሬጀንሲ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከአድናቂዎቹ ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ከጋዜጣዊ መግለጫው በኋላ አርቲስቱ ከባለቤቱ ጋር በመሆን በቀጥታ ያመራው፣ ዲአፍሪክ አካባቢ ወደ ሚገኘው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ የካንሰር ህሙማን እንክብካቤ ማዕከል ነበር፡፡ በዚያም ህሙማንን የጎበኘ ሲሆን ህፃናትን አቅፎና በጊታር ታጅቦ “ያኔ ልጅ እያለን” የተሰኘ ዘፈኑን አቀንቅኗል፡፡ ከባለቤቱና ከሀበሻ ዊክሊ ጋር በመተባበርም፣ ለህሙማን መድሃኒት መበጥበጫ የሚያገለግል ማሽን ገዝቶ ለማዕከሉ ለመለገስ ቃል ገብቷል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫውና በጉብኝቱ ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከአርቲስት ጎሳዬ ተስፋዬ ጋር በአዲስ አልበሙ፣ በኮንሰርቱ፣ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችና በሌሎችም ዙሪያ አነጋግራዋለች፡፡

           ጠፍተህ ጠፍተህ ከ11 ዓመት በኋላ ነው ብቅ ያልከው፡፡ በእርግጥ ከ40 በላይ ዘፈኖችን ሰርተህ፣ 15 ያህሉን በአዲስ አልበምህ አውጥተሃል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ኮንሰርት ስታቀርብ ወይም ሌላ ሥራ ስትሰራ አልታየህም:: ይህን ሁሉ ዓመት ታዲያ በምን ነበር የምትተዳደረው?
ገቢን በተመለከተ ምንም  አልነበረኝም፡፡ ያው እንደሚታወቀው የስቱዲዮ ስራ ወጪ ብቻ ነው፡፡ ለግጥም፣ ለዜማ፣ ለደራሲ፣ ለስቱዲዮ ---- ትከፍያለሽ፡፡ እንደገና ደግሞ የከፈልሽበትን ዘፈን ጥለሽ ወደ ሌላ ዘፈን ትሄጃለሽ፤ብዙ ውጣ ውረድ አለው፡፡ አንቺ 40 ዘፈን ሰርተሀል አልሽ እንጂ እኔ ወደ 57 ገደማ ነው ሰርቼ ያጠናቀቅኩት:: “ሲያምሽ ያመኛል” ውስጥ ያካተትኩት ግን 15 ዘፈኖች ብቻ ነው፡፡ የቁጥሩ መብዛት በራሱ ፈተና ይሆንብሻል፡፡ አየሽ ---- አስቸጋሪ ነው፡፡ በአጠቃላይ ገቢ የሚባል አልነበረም፡፡
ቤተሰብ መሥርተሃል፤ ሁለት ልጆችም አፍርተሃል፤ ከዚህ አንጻር ያለ ገቢ መኖር ከባድ ይመስለኛል፡፡ በዚያ ላይ የአርቲስቶች ኑሮ  ወጪ ይበዛዋል ይባላል---
እውነት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታዬ የወንደላጤነት ህይወት የምመራ ብሆን፣ እንዴት እሆን እንደነበር ሳስበው ከባድ ነው፡፡ እኔ በስራው ካለመርካቴ ጋር ተዳምሮ፣ በጣም አስቸጋሪ ህይወት ሊኖረኝ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር መልካምና የተባረከች ሚስት ሰጥቶኛል፡፡ እየተረዳዳን እየተደጋገፍን፣ ለልጆቻችንና ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ሁሉ ማሟላት ችለናል፡፡  
አዲሱ አልበምህ (“ሲያምሽ ያመኛል”) የጠበቅከውን ያህል ተቀባይነት አግኝቷል ብለህ ታምናለህ?
እዚህ ላይ አንድ ስሜት የሚሰጥ ነገር ልናገር:: አንዳንድ ጊዜ 11 ዓመት መጠበቅ ማለት--- ያውም በናፍቆትና በጉጉት መጠበቅ--- ፈጣሪ የመወደድ ፀጋ ካልሰጠሸ በስተቀር የሚሆን አይደለም፡፡ በ11 ዓመት ውስጥ ያውም በዚህ ሞያ፣ እንኳን ያባትሽ ያንቺም ስም እስከመረሳት ሊደርስ ይችላል:: የትኛውም ዓለም ላይ ቢሆን ነው የምልሽ:: ከጊዜው ርዝመትና ብዙ ከመጠበቄ አንጻር፣ አልበሙ ያለው ግብረ-መልስ ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ሌላው እንድትገነዘቢ የምፈልገው ነገር፣ ሁልጊዜ የሚደመጥ ስራ የመስራት ባህሪ ነው ያለኝ:: ምናልባት እነ ሙሉቀን መለሰንና ቴዎድሮስ ታደሰን የሚያስወድደኝም ነገር ይሄ ይመስለኛል:: በራሴም የሚደመጡ ስራዎች ብዬ በካታጎሪ የምከፋፍላቸው ስራዎች አሉ፡፡ እኔም በዚያ ካታጎሪ ውስጥ እንዳለሁ ስለሚሰማኝ፣ ረጋ ብዬ ቀስ በቀስ የምደመጥ ነኝ፡፡ አንቺም እንግዲህ ቀስ እያልሽ እንድታጣጥሚው እጋብዝሻለሁ፡፡
አዲሱ አልበምህ ምን ያህል ተሸጠ? ለኮንሰርቱስ ምን ያህል ተከፈለህ? በእርግጥ የኮንሰርቱን ክፍያ በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫው ይለፈኝ ብለህ ነበር …
ልክ ነሽ--- ይለፈኝ ብዬ ነበር፡፡
አርቲስቶች ብዙ ጊዜ ስለ ገንዘብ ሲጠየቁ አይወዱም፡፡ ምን ያህል ተከፈላችሁ ሲባሉ “ይለፈን” ይላሉ፡፡ በሌላው ዓለም ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው፤ ስኬታቸው የሚለካው በአልበማቸው ሽያጭና ከኮንሰርት በሚያገኙት ገቢ ስለሆነ አይደብቁም፡፡ እዚህ አገር ለምንድን ነው የማትናገሩት? ምንድን ነው የሚያስፈራችሁ? ግብር ነው ወይስ ሌላ ነገር አለ---?
እንደውም አንቺ ይህን አልሽ እንጂ እዚህ አገር 50ሺ ብር ተከፍሏቸው 1 ሚ. ተከፈለን ብለው የሚያስወሩ እንዳሉ ሰምቻለሁ:: ያገኘውን መናገር የማይፈልግ እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡ በእኔ በበኩል ግን የመናገር ችግር ኖሮብኝ አይደለም፡፡ ለሀገሬ ታክስ ከፋይ ሆኜ፣ አርቲስትነቴ በይፋ ታውቆ፣ በዩቲዩብ እንዲሁም በአይቲዩንስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቅኩ አይነት አርቲስት ብሆን ደስ ይለኛል:: የአገራችን መንግስት ግን ከአርቲስቱ ጋር በቅርበት በመነጋገር ይሄንን አድርጓል ለማለት ይከብደኛል፡፡ ለምሳሌ ማህበራዊ ዋስትና የለንም፡፡ እኛ ፈግተን እዚህ ደርሰን አወቃችሁን እንጂ በየምሽት ክበቡ አቅም ያላቸው፣ ወጥተው መታወቅ የሚገባቸው በርካታ ወጣት አርቲስቶች አሉ፡፡ ግን በቅጂ መብት ያለመከበር ዝርክርክነት ሁሉም አርቲስት ተጎጂ ነው፡። አንድ ሲዲ ሲወጣ 50 ፍላሽ ተከትሎት በሚወጣበት አገር ላይ ስለ ገንዘብ የምንወያይበት ምክንያት የለም፡፡ በዚህ አጋጣሚ መንግስትም ሆነ ሌላ የሚመለከተው አካል፣ የዚህን የቅጂ መብት አለመከበር ጉዳይ ቢያስብበት ደስ ይለኛል፡፡ የእኛ መብት ይከበር፣ የድካማችንን እናግኝ፤ ከዚያ በኋላ ስለ ገንዘብ እንነጋገራለን፣ እንወያያለን ማለት ነው፡፡
አሁን የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ያለበትን ሁኔታ እንዴት ትገልጸዋለህ?
የሙዚቃውን ኢንዱስትሪ ስመለከተው በአልበም ሳይሆን በተለይ በነጠላ ዜማዎች በጣም እየሞቀ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡ ኢንዱስትሪውን ህጉ ብዙ ባይደግፈውም፣ሙያተኛው በራሱ ትግል ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደውም አሁን እንደማየው፣ ብዙዎቹን ወጣት ድምፃዊያን እየጠቀማቸው ያለው አይቲዩንስና ዩቲዮብ ነው፡፡ ወጣቶች የተፈጠረውን አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ያ የሚያስከፋ አይደለም:: ነገር ግን የበለጠ መንግስት ቢተባበር፣ ብዙ ነገሮች መልካም ይሆናሉ፤ ኢንዱስትሪው የበለጠ ልቆ ሙዚቃው አድጎ፣ ሁሉም ተጠቃሚ ሆኖ ማየት ምኞቴ ነው።
ጎሳዬ ብዙ ጊዜውን  ቤት ውስጥ ነው የሚያሳልፈው፣ ከቤት አይወጣም ይባላል፡፡ ለመሆኑ ከሳምንት እስከ ሳምንት ቤት ውስጥ ምንድን ነው የምትሰራው?
(በጣም ረጅም ሳቅ…) ይገርምሻል-- በተፈጥሮዬ ከትዳር በፊትም ሆነ በትዳር ውስጥ ሆኜ፣ ከቤት መውጣት ለምን እንደሚከብደኝና ደስ እንደማይለኝ አላውቅም፡፡ በቃ ምክንያቱን አላውቀውም፡፡ ለራሴም ይገርመኛል፡፡ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው ልበል፡፡ እኔ እንጃ ብቻ --- ብዙ ውጭ መውጣት ደስ አይለኝም፡፡ በትዳር ውስጥ ስትሆኚና ልጆች ሲመጡ ደግሞ በተለይ በፍቅር የተሞላ ህይወት ካለሽ --- ብዙ ጊዜሽን ቤት ማሳለፍ እጅግ የሚያስደስት ነው፡፡
ግን  ምን እየሰራህ ነው ጊዜህን የምታሳልፈው?
በዋናነት ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው ሙዚቃ በመስራት ነው፡፡ ከሙዚቃ ቀጥሎ ደግሞ አንዳንድ በጣም መፅሐፍ የሚያነቡ ጓደኞችና ወዳጆች ስላሉኝ መፅሀፍ ያመጡልኛል፡፡ መፅሐፍ አነባለሁ፤ ፊልምም በደንብ አያለሁ፡፡ በተረፈ ከልጆቼና ከባለቤቴ ጋር እጫወታለሁ፤ ቆንጆ ጊዜ አሳልፋለሁ፡፡
“የጎሳዬ አድራጊ ፈጣሪ ባለቤቱ ናት፤ የልብ ምቱን ሳይቀር ትቆጣጠራለች” ይባላል፡፡ እውነት ነው? እውነት ከሆነ፣ ይህን የምታደርገው በፍቅር ነው  በአምባገነንነት?
(ረጅም ሳቅ…) እኔ ይሄን ነገር እንደ አዲስ ነው የሰማሁት፤ እንደዚህ እንደሚባል አላውቅም ነበር፡፡ እኔ ይህንን ያህል ጊዜ ስለፋና ስደክም:: አንዱን ዘፈን ወርውሬ በሌላ ዘፈን ስቀይርና ይህን ሁሉ ጊዜ ስፈጅ እያንዳንዱን ሌሊት ስፈጋ አድሬ ሌሊት 11 እና 12 ሰዓት ነው የምገባው:: ያ ሁሉ ሰዓት ምን ያህል ፈተና እንደሆነ አስቢው፡፡ የምወዳት ባለቤቴ ገኒ ግን ይህንን ሁሉ ተቋቁማ፣ ልጆቿን ተንከባክባ፣ ቤቷን መርታ በማህበራዊ ህይወት ግንኙነቴ በኩል ያሉትን ክፍተቶች ሞልታ፣ በትዕግስትና በፍቅር የምትንከባከበኝ የምታጎብዘኝ፣ ብርቱና የፍቅር እመቤት ናት፡፡ ቀደም ሲልም እንደነገርኩሽ፣ በትዳሬ እድለኛ በመሆኔ ነው  በሥራዬ ስኬታማ የምሆነው፡፡ በነገራችን ላይ ከቤት አልወጣም ያልኩሽ ቀን ቀን ነው እንጂ ሌሊት ስቱዲዮ ባልሄድ፣ ይህንን ሁሉ ስራ መች ትሰሚ ነበር፡፡ እና ይሄን ሁሉ ተቋቁማ ነው እዚህ ያደረሰችኝ:: ያውም በሙዚቃ ሙያ ውስጥ አይደለችም:: ተመልከቺ----ትዕግስቷንና ፍቅሯን፡፡ እንደውም እድሉን ከሰጠሽኝ፣ በዚህ አጋጣሚ፣ አድናቆቴንና ፍቅሬን ብገልፅላት ደስ ይለኛል፡፡
በሚገባ ትችላለህ …
ገንዬ ትዳሬ፤ እጅግ አከብርሻለሁ አደንቅሻለሁ፡፡ ባንቺ ሁሌም ደስተኛ ነን፡፡ በዚህ አጋጣሚም ልጆቼ-- ገብርኤል ጎሳዬና አሜን ጎሳዬ --- ትዕግስታችሁን አደንቃለሁ፣ እወዳችኋለሁ፤ ኑሩልኝ፡፡
አሁን ደግሞ ስለ አገር እናውራ፡፡ በአንተ አመለካከት በአገሪቱ ላይ ለውጥ መጥቷል ብለህ ታስባለህ? ከዚሁ ጋር ተያይዞ “ሲያምሽ ያመኛል” የሚለው ዘፈንህ፣ ለሴት ፍቅር ብቻ ሳይሆን ለአገርም እንደተዘፈነ ይነገራል፡፡ እንደዚያ አስበህበት ነው የዘፈንከው?
እግዚአብሔር ይስጥሽ፡፡ እንግዲህ “ሲያምሽ ያመኛል” ዘፈኔን በተመለከተ አንቺን ጨምሮ ብዙ ሰዎች፣ ይሄ ዘፈን ለፍቅረኛ፣ ለእናት ወይም ለእህት ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ጭምር ነው ይሉኛል፡፡ ትክክልም ናቸው፡፡ አገሪቱ ላይ ለውጥ አለ ለሚለው እምም… እኔ በተደጋጋሚ የምናገረው ነገር አለ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ኢትዮጵያ ፍቅር ለመናገር አድዋን ብናነሳ ደስ ይለኛል፡፡ አጥንታቸውን የከሰከሱላት፣ ደማቸውን ያፈሰሱላት እናት አባቶቻችን ናቸው፣ ዛሬ እኔና አንቺ እዚህች የቆምንባት ቦታ ላይ ሆነን፣ በነፃነት ቃለ ምልልስ እንድናደርግ እድል የሰጡን፡፡ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ማለቴ ነው። ዛሬ ደግሞ በዘርና በሃይማኖት የምንናከስበትና በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ የጎሪጥ የምንተያይበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡ ይሄ የምር ያመኛል:: እንግዲህ እንነጋገር ካልሽ እናውራ፡፡ እኔ የመርካቶ ልጅ ነኝ፡፡ ለእኔ ኢትዮጵያዊነት መርካቶነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
እንዴት ማለት?
በጣም ጥሩ! እኛ መርካቶ ስናድግ --- ኦሮሞው ቤት ተጫውተን፣ ትግሬው ቤት ተልከን፣ አማራው ቤት በበዓል የተቆረሰ ዳቦ ተቀብለን በልተን፣ ወላይታው ቤት ዞረን አኩኩሉ ተጫውተን፣ አደሬው ቤት ፍራሽ ላይ ዘልለን ጨፍረን ነው---፡፡ የዚህን ሁሉ ማህበረሰብ ህብርና አንድነት እያየሁ አድጌ፣ዛሬ እየሆንን ያለውን ነገር ስመለከት ያሳፍረኛል፡፡ አሁንም ቢሆን ወደ ቀልባችን ካልተመለስን፣ወደ ከፋ ችግር እንገባለን የሚል ስጋት አለኝ፡፡
ለመንግስት ለተቃዋሚዎችና ለአክቲቪስቶች መልዕክት የማስተላለፍ ዕድል ብሰጥህ ምን ትላቸዋለህ?
እኔ በተናጠል ከማስተላለፍ ይልቅ በጋራ ባስተላልፍ ነው የሚሻለኝ፡፡ ኢትዮጵያዊነት አሁን ከላይ ለጠቀስሻቸው አካላት የምር ከገባቸው፣ እንደ ኢትዮጵያዊ የቀደመ አንድነታችን፣ እነሱም አንድ ሆነው፣ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ የሚበጅ ሥራ እንዲሰሩ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ አንድ ሆነው አንድ እንዲያደርጉን እፈልጋለሁ፡፡
ከህዝቡስ ምን ይጠበቃል?
ህምምም … የእናት አባቶቻችን ምርቃትና ትሁትነት፣ የእነሱ ፀሎትና የእግዚአብሔርም ረጂነት ነው ህዝቡን  በትዕግስትና በፍቅር ያቆየው እንጂ ከየትኛውም አካል አንድነትንና መተሳሰብን የሚገነባ ነገር አግኝቶ አይደለም፡፡ እንደውም አጋጣሚውን ካገኘሁ፣ ይህንን ታጋሽ ፈሪሃ እግዚአብሔር የተላበሰ፣ ሥነ ስርዓት ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ማመስገን እፈልጋለሁ:: ወገኔ! ክብር ይገባሃል እላለሁ፡፡ ያለ ማንም ድጋፍ ነው እርስ በእርሱ ተቃቅፎና ተዋድዶ እየኖረ ያለው:: በተረፈ አገራችንን በእጅጉ ሰላም ያድርግልን፡፡
ይህን ቃለ ምልልስ የምናደርገው የካንሰር ህሙማን ማዕከል ለጉብኝት መጥተህ ነው፡፡ ታማሚዎችን ስታይ ምን ተሰማህ?
በጣም ነው ያዘንኩት--- አስቢው የሦስት አመት ልጅ በካንሰር ሲያዝ! እኛ አገር የችግራችን ቀዳዳ አንድ ብቻ አይደለም፡፡ በርካታ ክፍተቶች አሉብን፡፡ ለዚህ ችግራችን ዋናው መፍትሄ መረዳዳት ነው፡፡ ይህን የምለው ከልቤ ነው፡፡ አገራችን ላይ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ ባለሀብቶች አሉን፡፡ ቁጥራቸው ብዙ ባይሆንም፣ በጎና ሰውን ቀና ማድረግ የሚፈልጉ፣ ልበ ቅን ሰዎች አሉ፤ መበርከት አለባቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ እነዚህን ህሙማን እንዲጎበኟቸው፣ ፍቅር እንዲሰጧቸውና እንዲያግዟቸው ጥሪ አስተላልፋለሁ፡፡ ችግሩ ነገ የማንን በር እንደሚያንኳኳ አናውቅም፡፡ ብንረዳዳ ብንደጋገፍ ታሪክ መስራት እንችላለን:: መረዳዳት መጠያየቅና መደጋገፍ ---- የቆየ ባህላችን ነው፡፡ ይሄ ባህላችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ እነዚህን ህሙማን ቢያንስ እዚህ ማዕከል መጥተው፣ ጎብኝተው፣ እግዜር ይማራችሁ እያሉ እንዲመለሱ በእግዚአብሔር አምላክ ስም እማፀናለሁ፡፡
ለኮንሰርቱ ልምምድ ጀምረሃል? ምን ያህል ዘፈን ታቀርባለህ? ከኮንሰርቱስ ምን ትጠብቃለህ?
ልምምዱን በተመለከተ አሁን አንቺ እዚህ ባታግቺኝ፣ እስካሁን እዚያ ደርሼ ነበር:: ለኮንሰርቱ በደንብ እየተለማመድኩ ነው፡፡ ከቀድሞውም ከአዲሱም አልበሜ፣ ባንዱ 23 ያህል ዘፈኖችን አጥንቷል፡፡ ሌሎች ሰርፕራይዞች እንዳሉ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ሰምተሻል፤ ላንቺ ጋዜጣ በጓሮ በር መጥቼ ሰርፕራይዙን አልናገርም፡፡ በኮንሰርቱ ብዙ ደስታ፣ ብዙ ፍቅር ከአድናቂዎቼ እጠብቃለሁ፡፡ በጣም ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ናፍቆታችንን ስለምንወጣ፣ ሚያዚያ 26  በጊዮን ሆቴል እንገናኝ  እላለሁ፡፡
በመጨረሻ የበዓል መልዕክት አስተላልፍና ጨዋታችንን እንቋጭ----
በዓሉን የሰላም የፍቅር የመተሳሰብ ያድርግልን፤ የጎሪጥ የማንተያይበት የማንገፋፋበትና አንዱ ሌላውን  የማይጥልበት ይሁንልን እላለሁ፡፡ አድናቂዎቼ፤ ስለ እልህ አስጨራሽ ትዕግስታችሁና ጥበቃችሁ እጅግ አመሰግናችኋለሁ፤ ከዚህ በኋላ እንዲህ በመጥፋት በናፍቆት አልቀጣችሁም፤ቶሎ ቶሎ እከሰታለሁ፡፡ መልካም በዓል!



Read 1659 times