Saturday, 20 April 2019 14:57

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(2 votes)

 ክፍል-፲፰ ‹‹ያገሬ ሰው ሥርዓት ያዝ ብለው ተጣላኝ!!››
                                    
                 በክፍል-17 ፅሁፌ ላይ የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት በሀገሪቱ ከተንሰራፋው የብህትውና ባህል ጋር በተቃርኖ የቆመ መሆኑንና ንጉሱ በዘመናዊነትና በነባሩ የሀገራችን ትምህርት መካከል ያለውን መስተጋብር በተመለከተ የነበራቸው አመለካከት ከእሳቸው በኋላ የመጡ ነገስታትና መሪዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተመልክተናል፡፡ ዛሬም ያንኑ ሐተታ በመቀጠል፣ አፄ ቴዎድሮስ ዘመናዊነትን ከ‹‹ሥርዓት›› ጋር ያስተካከሉበትን ሐሳባቸውን እንዳስሳለን፡፡
አፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ራሳቸውን ከማጥፋታቸው በፊት ለጄኔራል ናፒየር የላኳት አጭር መልዕክት፣ ለሀገራቸው የነበራቸውን የመጨረሻውን ራዕያቸውን የሚገልፅ ነው:: እንዲህ ነበር ያሉት ንጉሱ፡- ‹‹ያገሬን ህዝብ ገብር ብለው፣ ሥርዓት ያዝ ብለው ተጣላኝ፤ እናንተ ግን በሥርዓት የተመራ ህዝብ ስላላችሁ አሸነፋችሁኝ›› (ባህሩ 2003፡ 33)፡፡ በዚህ የንጉሱ ርዕይ ውስጥ ‹‹ሥርዓት›› (Discipline) የሚለው ሐሳብ ጎልቶ ይታያል፡፡
በዚህ የአፄ ቴዎድሮስ እሳቤ መሰረት ‹‹መዘመን ማለት ሥርዓት መያዝ›› ማለት ነው፡፡ በመሆኑም፣ አፄ ቴዎድሮስ ለሀገራቸው የነበራቸው የመጨረሻው ርዕይ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ ሥርዓት እንዲኖረው ማድረግ›› ነው:: ሆኖም ግን፣ ንጉሱ ‹‹ሥርዓት›› ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? ‹‹ሥርዓት›› ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም ማለት ነው?
ለዚህ ጥያቄ የሚሆን መልስ ከሁለት ምንጮች ማግኘት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው፣ ከእዚያው ከንጉሱ ንግግር ውስጥ ነው፡፡ ንጉሱ ‹‹ያገሬን ህዝብ ገብር ብለው፣ ሥርዓት ያዝ ብለው ተጣላኝ›› ነው ያሉት፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ‹‹ገብር ብለው ተጣላኝ›› ሲሉ፣ ስለ ‹‹ግብር ሥርዓት›› ብቻ አይደለም እያወሩ ያሉት - አጠቃላይ ስለ ዘመናዊነት ፕሮጀክታቸው እንጂ - ስለ ኢኮኖሚው፣ ስለ ሚሊታሪው፣ ስለ ተቋማቱ፡፡
ሁለተኛው ደግሞ፣ ንጉሱ ቋሚ ወታደር ከመለመሉ በኋላ ወታደሮቹን፣ ወታደራዊ የሰልፍ ሥነ ሥርዓት ያለማምዷቸው ነበር፡፡ አፄ ቴዎድሮስ፣ በወታደራዊ ሥነ ሥርዓት ላይ የነበራቸው ርዕይ ምናልባት ከእሳቸው ህልፈት በኋላ በ1903 ዓ.ም ለእንግሊዙ ንጉስ ጆርጅ በዓለ ሲመት የታደመው በደጃዝማች ካሳ ኃይሉ የተመራው የአፄ ምኒሊክ የልዑካን ቡድን፣ በሎንዶን ከተመለከተው የህዝቡና የፖሊሱ መስተጋብር ጋር ሳይመሳሰል አይቀርም:: ብላታን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ ታሪኩን እንዲህ በማለት ያወጉናል፡-
‹‹በጉብኝታቸው ማጠቃለያም፣ ንጉስ ጆርጅ፣ ደጃዝማች ካሳን ‹‹ካዩት ነገር ሁሉ በጣም ያስገረምዎት ምንድን ነው?›› ብለው ጠየቋቸው:: ደጃዝማች ካሳም ‹‹ሁሉም ነገር ግሩም ነው፣ የፖሊሱ ነገር ግን ይበልጥ አስገራሚ ነው። 700 ሺ የሚሆነውን የሎንዶን ህዝብ በእጁ እንኳ ዱላ ያልያዘ አንድ ፖሊስ ያዘዋል፣ ሂድ ሲለው ይሄዳል፣ ቁም ሲለውም ይቆማል። ያን ሁሉ ህዝብ ፖሊሱ እጁን እየዘረጋ፣ በዓይኑ እየጠቀሰ በሥርዓት ያኖረዋል።›› ንጉስ ጆርጅም ቀበል አደረጉና ‹‹እውነት ነው፤ ፖሊሶቹ በብዙ ትጋት ህዝቡን ይጠብቃሉ። ዳሩ ግን ህዝቡም ስለሚረዳቸውና ስለሚታዘዝላቸው እንጂ ፖሊሱ ኃይል ስላለው አይደለም፤›› ብለው መለሱላቸው።›› (ኅሩይ ወ/ሥላሴ 2009፡ 41-43)
አፄ ቴዎድሮስ ‹‹ያገሬ ሰው ሥርዓት ያዝ ብለው ተጣላኝ›› ያሉት እንደዚህ ዓይነቱን የህዝብና የተቋማት መናበብ ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባሩን ሥርዓት ከአውሮፓውያኑ ሥርዓት ጋር ሲያነፃፅሩት ኋላ ቀር ሆኖባቸዋል፡፡ ነባሩ ሥርዓት የቆመው ሺህዎች ዓመታት ላይ በቆየ ‹‹ልማድ›› ላይ እንጂ ‹‹አመክንዮ›› ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ እናም የንጉሱ ርዕይ፣ ልማዳዊውን የፖለቲካል ኢኮኖሚ አስተሳሰቦች እንደገና በአመክንዮ ማዋቀር (the rationalization of the political-economy) ነው፡፡
የንጉሱን ፕሮጀክት ከዚህ ተቋማትን ‹‹አመክንዮአዊ (rationalize)›› ከማድረግ ሐሳብ አንፃር ካየነው፣ የአፄ ቴዎድሮስ፣ የገብረ ህይወትና የፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ሐሳብ ተመሳሳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ልዩነቱ የትኩረት አቅጣጫ ብቻ ነው፤ ዘርዓያዕቆብ ባህሉ ላይ ሲያተኩር፣ ገብረ ህይወትና አፄ ቴዎድሮስ ደግሞ ፖለቲካል ኢኮኖሚው ላይ ያተኩራሉ፡፡
በሌላ አነጋገር፣ የንጉሱ ርዕይ ልማድ ላይ የተቀረቀሩትን የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተቋማት መንጭቆ ማውጣት ሲሆን፣ የዘርዓያዕቆብ ርዕይ ደግሞ በብህትውናና በተአምራዊነት ባህል ውስጥ ተዘፍቆ የኖረውን አስተሳሰብ በአመክንዮ ማንቃት ነው፡፡ ንጉሱ አመክንዮአዊ ተቋማትን ሲፈልጉ፣ ዘርዓያዕቆብ ደግሞ አመክንዮአዊውን ሰው ይፈልግ ነበር፡፡
ሆኖም ግን፣ በዚህ ‹‹የአመክንዮአዊ ተቋማት›› (Rational Institution) ፍለጋቸው ላይ ንጉሱ አንድ ነገር ስተዋል፤ ይሄውም፣ ‹‹አመክንዮአዊ ተቋማትን›› የሚያቋቁመውም ሆነ የሚያስኬደው ‹‹አመክንዮአዊው ሰው›› መሆኑን አለመረዳታቸው ነው፡፡ በዚህም ንጉሱ ቅደም ተከተሉን አዛቡት፡፡ ‹‹አመክንዮአዊውን ሰው›› ሳያዘጋጁ ‹‹አመክንዮአዊ ተቋማትን›› ማቋቋም ፈለጉ፡፡ ከአውሮፓ የዘመናዊነት ፕሮጀክት አንድ የምንማረው ነገር ቢኖር፣ ፖለቲካል ኢኮኖሚውን ለማዘመን በመጀመሪያ በሰው ልጅ ችሎታ የሚተማመንና በአመክንዮ የሚያምን ሰው መፍጠር እንዳለብን ነው፡፡
የነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝን የዘመናዊነት ሐሳብ ከንጉሱና ከዘርዓያዕቆብ ለየት የሚያደርገው ሐሳቡ ‹‹ሁለንተናዊ›› (Holistic) መሆኑ ነው:: ዘርዓያዕቆብ ባህሉ ላይ፣ አፄ ቴዎድሮስ ደግሞ ፖለቲካል ኢኮኖሚው ላይ ሲያተኩሩ፣ ገብረ ህይወት ግን ሁለቱም ላይ ትኩረት አድርጎ ፅፏል፡፡
ገብረ ህይወት፣ የተአምራዊነትና የብህትውና ባህልን በተቸበት ፅሁፉ ላይ ከዘርዓያዕቆብ ጋር ያለውን የመንፈስ አንድነት ሲያሳይ፤ አመክንዮአዊ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተቋማትን የመገንባት አስፈላጊነትን በጠቆመበት ፅሁፉ ላይ ደግሞ ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ያለውን የመንፈስ ዝምድና አሳይቷል:: ደግሞም የአፄ ቴዎድሮስን መንገድ አድንቆ ፅፏል፡፡ በመሆኑም፣ የዘርዓያዕቆብ—አፄ ቴዎድሮስ—ገብረ ህይወት የዘመናዊነት መንገድ ኢትዮጵያን በባህል፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ለመለወጥ የተሟላ ሐሳብ ያለው መንገድ ነበር፡፡
ሆኖም ግን፣ በሀገራችን የብህትውናውና የተአምራዊነቱ ባህል በእያንዳንዱ ግለሰብ ስነ ልቦና ውስጥ በጣም ሥር የሰደደ ስለነበር የዘርዓያዕቆብ—አፄ ቴዎድሮስ—ገብረ ህይወት መንገድ እንዲህ በቀላሉ የሚሳካለት ሆኖ አልተገኘም፡፡
የተአምራዊነት ባህልና ሥርዓት አልበኝነት
የተአምራዊነትና የብህትውና ባህል ዋነኛ ችግሩ፣ ለአካልና ለዓለም ካለው ንቀት የተነሳ ለዓለማዊ ህጎችና ተቋማት ዕውቅናን መንፈጉ ነው፡፡ ሲጀመር፣ ተአምራት ከዓለማዊ ህግና ከአመክንዮ ውጭ የሆኑ ክስተቶች ናቸው፡፡ እናም በተአምራዊነት ባህል ውስጥ ያለ ህዝብ፣ ለዓለማዊ ህግና ተቋማት ካለው እምነት በላይ ለተአምራትና ለተአምራት ተናጋሪዎች ያለው ተአማኒነት ከፍ ያለ ነው፡፡
ይሄም፣ በህዝቡ ዘንድ መንግስታዊ ተቋማት የቅቡልነት ችግር እንዲገጥማቸው ያደርጋል:: አፄ ቴዎድሮስም ያጋጠማቸው ችግር ይሄው ነበር፤ የተአምራት መምህራን፣ ንጉሱ ላቆሟቸው አዳዲስ ህጎችና ተቋማት ህዝቡ ዕውቅና እንዳይሰጣቸው አደረጉ፤ ‹‹የያዙትን መንገድ ተውትና እንደ ጥንቱ ያስተዳድሩን›› አሏቸው ንጉሱን፡፡
የተቋማት የቅቡልነት ችግር ዋነኛው ጦስ ደግሞ ሥርዓት አልበኝነትንና ሽፍታነትን ማስፋፋቱ ነው:: መሪራስ አማን በላይ፤ በኢትዮጵያ የብህትውና ባህል መስፋፋት፣ መንግስትን በማዳከም ሽፍታነት እንዲጠናከር ማድረጉን እንዲህ በማለት ያስረዳሉ፣ ‹‹ከአፄ ካሌብ በኋላ ብህትውና በመሳፍንቱና በመኳንንቱ ዘንድ በመስፋፋቱ የአክሱም ታላቅነት እየደከመ ሄደ፡፡ በዚህም ሽፍታነትና ሥርዓት አልበኝነት እየተስፋፋ ሄደ›› (አማን 2009፡ 103)፡፡
አፄ ቴዎድሮስ የተነሱት፣ የብህትውናና የተአምራዊነት ባህል ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበትና መንግስታዊ ተቋማት በቅቡልነት ችግር በተሽመደመዱበት፣ በዚህም ሽፍታነትና ሥርዓት አልበኝነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት ነበር፡፡
‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ›› በሚል ርዕስ በተከታታይ የማቀርባቸውን ፅሁፎች ወደ ማጠናቀቂያው ደርሻለሁ፡፡ በሚቀጥለው ፅሁፌ የማጠቃለያ ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆን በኢሜይል አድራሻው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1025 times