Print this page
Saturday, 20 April 2019 13:56

ወቅታዊው ፈተና - መንስኤውና የመፍትሄ ሀሳብ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“--ጥላቻና ዘረኝነት ለማንም አይበጅም፤ ሁሉንም ነው የሚያጠፋው፡፡ በጥላቻና በዘረኝነት ቅስቀሳ አንድን የህብረተሰብ ክፍል (ዘር) አነሳስቼ፤ ስልጣን ይዤ በሰላም እኖራለሁ ማለት፤ ከንቱ ህልም (ቅዠት) ነው፡፡--”


              ውድ አንባቢያን፤ ሁላችንም እንደምናውቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በአሁኑ ወቅት ትልቅ ተስፋን በያዘና ፈተናና ተግዳሮት በበዛበት ወሳኝ የለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች፡፡ ለአንድ ችግር ትክክለኛ መፍትሄውን ለመፈለግ፤ በቅድሚያ ትክክለኛ መንስኤውን ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ለመሆኑ የወቅታዊው የሀገራችን ችግር መሰረታዊ መንስኤው ምንድን ነው? የመፍትሄ መንገዱስ? ይህቺ አጭር ጽሁፍ ለነዚህ ጥያቄዎች ጠቅለል ያለ መልስ ትሰጣለች ብዬ አስባለሁ፡፡
ወቅታዊው ችግርና መሰረታዊ መንስኤው
“የእገሌ ብሄር ጥያቄ”  ወይም “የእገሌ ህዝብ ፍላጎት”  የሚለው ቃል፤ የዘር ፖለቲካ በማቀንቀን ስልጣን ለመያዝ በሚያልሙ የሀገራችን ፖለቲከኞች ሲዘወተር እንሰማለን፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞች ይህን ቃል የሚጠቀሙት፤ አርቆ ሳያስብና ነገሮችን ሳያስተውል፤ በስሜታዊነት የሚገፋፋውን የህብረተሰብ ክፍል በማነሳሳትና ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት፣ ከተቻላቸውም በማለያየት፤ ስልጣን እንይዛለን ብለው እኩይ ሃሳብ በማሰባቸው እንጂ፤ ለህዝብና ለሀገር በጎ በማሰብ አለመሆኑን ተግባራቸው ይመሰክራል:: እንደ እውነቱ ከሆነ የማንኛውም ህዝብ ፍላጎት ግልጽ ነው - ሁሉም የሚፈልገው ሰላምን፤ ፍትህን፤ እኩልነትን፤ ብልጽግናንና በተከበረች ሀገር በአንድነት መኖርን ነው፡፡ የከንቱ ስልጣን ፍላጎትና የጥላቻ ልብ ካላቸው ዘረኛ ግለሰቦችና ቡድኖች በስተቀር፤ ማንኛውም ህዝብ/ህብረተሰብ አንድነትን እንጂ መበታተንን ወይም መለያየትን አይፈልግም:: “አንድነት” ማለት “አንድ ዐይነት” ማለት ሳይሆን “አንድነት በብዝሀነት” (Unity with Diversity) ማለት ነው፡፡  
ህዝብን ከህዝብ በማጋጨትና የተለያዩ እኩይ ተግባሮችን በመፈጸም ለውጡን ለማጨናገፍ መሞከር፤ በሀገርና በህዝብ ላይ የሚፈጸም፤ እንደ አጥፍቶ መጥፋት የሚቆጠር፤ ትልቅ ስህተትና በደል ነው፡፡ እስኪ ቆም ብለን በጥሞና አርቀን እናስብ፡፡ እንበልና ይህ እኩይ ፍላጎት ቢሳካና ለውጡ ቢጨናገፍ ምንድን ነው በሀገራችን ሊከሰት የሚችለው? ከመቶ ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት፤ ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባትና አንዱ ዘር ከሌላው ተጋብቶና ተዋልዶ፤ በደምና ስጋ ተዋህዶ በአንድነት የሚኖርባት ትልቅ ሀገር ብትፈርስ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም፤ እያንዳንዱ ዜጋ ተጎጂ ነው፡፡ በአንድነትና በእኩልነት መኖር ግን ለሁሉም ይበጃል እንጂ፤ ማንንም አይጎዳም፡፡ ያለን ወቅታዊ ምርጫ ሁለት ብቻ ነው፡-
አንደኛው፤ የተጀመረውን ለውጥ በመደገፍ፤ በተከበረችና በበለጸገች ትልቅ ሀገር ውስጥ በሰላም፤ በእኩልነት፤ በፍቅርና በአንድነት መኖርና ሉአላዊት ሀገርን ለትውልድ ማሻገር፤  
ሁለተኛው፤ ደግሞ ለውጡን በማጨናገፍ በፈረሰች ሀገር (failed state) ውስጥ በጦርነትና በረሃብ መሰቃየት ነው፡፡ በትክክል የሚያስብ ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው፤ ሁለተኛውን መንገድ ይመርጣል ብዬ አላስብም፡፡ የኢትዮጵያ አምላክና የኢትዮጵያ ህዝብም ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር አይፈቅዱም፡፡
ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት በሃገራችን የተከሰቱት ችግሮች መሰረታዊ መንስኤያቸው ምንድን ነው? ይህንን ጥያቅ በትክክል ለመመለስና ወደ መፍትሄ ለመሄድ፤ እውነቱ ሳይሸፋፈንና ሳያድበሰበስ በግልጽ መነገር አለበት ብዬ አስባለሁ - በአሁኑ ወቅት ለተስፋፋው በዘር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካና  በተለያዩ አካባቢዎች ለሚታዩት ግጭቶችና የህዝብ መፈናቀሎች መሰረታዊ መንስኤያቸውና ምክንያታቸው ከ27 ዓመት ወዲህ በሀገራችን ፖለቲከኞች የተፈጠረውና በጻፉት ህገ መንግስት ተደግፎ፣ ሀገራችን ስትመራበት የቆየችው፣ በአለም ብቸኛ የሆንበት የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርዓት (Ethnic based federalism) ነው፡፡ ለዚህ የጎሳ ፌዴራሊዝም መጠንሰስ ምክንያት የሆነው ደግሞ፤ በ1966 ዓ.ም. በሀገራችን የተከሰተውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ፤“የእገሌ ህዝብ ነጻ አውጪ”  በሚል ሰበብና ስያሜ የተደራጁ፤ የስልጣን ፍላጎትና የጥላቻ ልብ ያላቸው ዘረኛ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚከተሉት አስተሳሰብና አካሄድ ነው፡፡ እስኪ ቆም ብለን እናስብ፤ ማንን ከማን ነው ነጻ የሚያወጡት? ተጋብቶና ተዋልዶ በአንድነት የኖረን ህዝብ ማለያየት ወይም ማጣላት ነጻ ማውጣት አይደለም፤ ይልቁንም ማኮሰስና ማክሰር እንጂ፤ ለከንቱ ስልጣን ፍላጎት ብሎ ሀገርንና ህዝብን መበደልም ነው:: ማንኛውም ህዝብ አንድነትን፤ እኩልነትን፤ ሰላምንና ብልጽግናን ይሻል እንጂ፤ መለያየትን ወይም መጣላትን አይፈልግም፡፡
አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ የሀገራችን ፖለቲከኞች “እኔ የእገሌ ህዝብ ብሄረተኛ ነኝ” ብለው አፋቸውን ሞልተው በይፋ በሚዲያ ሲናገሩ ስሰማ ይዘገንነኛል:: አንድ ሰው እንደዚህ ሲያስብና ሲናገር፤ በሌላ አገላለጽ ዘረኛ (Racist) መሆኑንና ራሱ ከመጣበት ዘር በስተቀር ለሌላው ኢትዮጵያዊ ደንታ እንደሌለው ወይም ጥላቻ እንዳለው ነው የሚያሳየው፡፡ አንዳንድ የሀገራችን ፖለቲከኞች “ዘር” በማለት ፋንታ “ብሄር” “ዘረኛ” በማለት ፋንታ “ብሄረተኛ” ሲሉ እንሰማለን:: ነገር ግን “ብሄር” ወይም “Nation” የሚባለው ቃል ትክክለኛ ትርጉሙ “ሀገር” ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ብሄራዊ መዝሙር (National Anthem)፤ ብሄራዊ ቡድን (National Team) ይባላል:: ይሁን እንጂ የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርዓቱን የመሰረቱት የሃገራችን ፖለቲከኞች በሚከተሉት ርእዮተ ዓለምና በጻፉት ህገ መንግስት፤ የአንድ ሀገር ህዝብን በጎሳ ለመከፋፈል፤ ካስፈለገም ለማለያየት እንዲያመች ተደርጎ የተለየ ትርጉም ተሰጥቶት ቆይቷል፡፡
ጥላቻና ዘረኝነት ለማንም አይበጅም፤ ሁሉንም ነው የሚጎዳው ወይም የሚያጠፋው:: በጥላቻና በዘረኝነት ቅስቀሳ አንድን የህብረተሰብ ክፍል (ዘር) አነሳስቼ፤ ስልጣን ይዤ በሰላም እኖራለሁ ማለት፤ ከንቱ ህልም ወይም ቅዠት ነው፡፡ እዚህ ጋ ከ25 ዓመት በፊት የተከሰተውን የሩዋንዳን አስከፊ ታሪክ ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል - በወቅቱ አገዛዝ ላይ የነበሩት ፖለቲከኞች ባቀነባበሩት ሴራ፣ ህዝብን በህዝብ ላይ በማስነሳትና አንዱ ዘር ሌላውን እንዲጨፈጭፍ በማድረግ፤ አለምን ያሳዘነና የሀገሪቱን ታሪክ ለዘላለም ያጎደፈ ተግባር ፈጸሙ:: ሆኖም ትንሿ የምስራቅ አፍሪካ ሀገር፣ ከሰቆቃው በኋላ ከዘረኝነት የጸዳ መሪና መንግስት በማግኘቷ ዛሬም እንደ ሀገር ቆማ ቀጥላለች፡፡ የተበዳዮቹ ወገኖች ይቅርታ ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል፡፡ የግፉ ፈጻሚ ወገኖች ግን ለዘላለም ከህሊና ቁስል፤ ከሀፍረትና ከጸጸት ሊላቀቁ አይችሉም፡፡
የመፍትሄ ሀሳብ
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፤ በምንመኛት የበለጸገች ታላቅ ሀገር በሰላም፤ በፍትህ፤ በእኩልነትና በአንድነት ለመኖርና፤ የተከበረች ሉአላዊት ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ እንችል ዘንድ፤ እንደ አንድ ዜጋ የሚከተለውን የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡
1ኛ. የሀገራችን ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ሁሉ ልባችሁን ከጥላቻ፤ ከቂምና ከዘረኝነት አጽድታችሁ፤ ፍቅርን፤ ይቅርታንና አንድነትን/ኢትዮጵያዊነትን ተከተሉ፡፡ ወደ ፊት እንጂ፤ ወደ ኋላ አታስቡ፡፡
2ኛ. የሀገራችን ፖለቲከኞች ሁሉ የግል ስልጣን ፍላጎታችሁን ትታችሁ፤ ለራሳችሁ ዘር ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምን፤ ፍትህን፤ እኩልነትን፤ አንድነትንና፤ ብልጽግናን ለማስፈን ተባበሩ፡፡
3ኛ. በተለያዩ ሚዲያዎች የጥላቻና የዘረኝነት ወሬ በማሰራጨት፣ በህዝብ መሃል ጥላቻና ግጭት ለመፍጠር የምትጥሩ ሰዎች፤ ከዚህ እኩይ ተግባራችሁ ተላቅቃችሁ፤ ህሊናችሁን ለማይወቅስ በጎ ተግባር፤ ለሀገር ሰላምና አንድነት ስሩ፡፡
4ኛ. የአምላክ በጎ ፈቃድ ሆኖ፤ በአሁኑ ወቅት ለሃገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ራእይ ያላቸው፤ ኢትዮጵያንና ህዝቧን የሚወዱ፤ ከፍተኛ ችሎታና ብቃት ያላቸው፤ ዘረኝነትን፤ ሌብነትና ግፍን የሚያወግዙ፤ ፍትህን፤ ፍቅርንና ይቅርታን የሚከተሉና፤ ለሃገር አንድነትና ብልጽግና የሚተጉ፤ የለውጥ መሪዎች አግኝተናል:: በወቅታዊው ወጀብና ፈተና ውስጥ ሆነው እንኳን፤ ሀገርን ለማሳደግ የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጥረት እያየን ነው፡፡ ስለዚህ ዜጎች ሁሉ ከመሪዎቻችን ጎን ሆነን፣ ለተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ መሳካት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ!!

Read 2370 times
Administrator

Latest from Administrator