Saturday, 20 April 2019 13:54

ቃለ ምልልስ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ግስጋሴ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

· በዩኒቨርሲቲው ረብሻና ብጥብጥ ተቀስቅሶ አያውቅም
               · ለአርብቶ አደሮች ነፃ የመድኃኒት አገልግሎት እንሰጣለን
               · የጅግጅጋ ነዋሪን የሚያገለግል ሪፈራል ሆስፒታል ገንብተናል

          በ1999 ዓ.ም የተመሰረተው ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ፤ በሁለት ኮሌጆችና በ60 መምህራን ነበር ስራ የጀመረው፡፡ ባለፉት 12 ዓመታት በብዙ ዘርፎች ራሱን እያሳደገና እየገነባ መጥቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ከ25ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ ከሦስት ዓመት ወዲህ አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ ጋር ተያይዞ በተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪ ግጭቶችና ሁከቶች ቢቀሰቀሱም፣ በዚህ ዩኒቨርሲቲ ምንም ዓይነት ግጭትና ረብሻ አልተነሳም፡፡ ምስጢሩ ምን ይሆን?
ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያለውስ ግንኙነት ምን ይመስላል? ሌሎች እንቅስቃሴዎቹስ? በሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በቅርቡ ለስራ ጅግጅጋ የተጓዘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ የዩኒቨርሲቲው የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና ማርኬቲንግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንዲሁም የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ሥራ አመራር መምህር ከሆኑት አቶ ጀማል አሊ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-

                በዚህ ዩኒቨርሲቲ ለምን ያህል ጊዜ አገለገሉ?
በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው ለዘጠኝ ዓመት በመምህርነት አገልግያለሁ፡፡ አሁንም የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ስራ አመራር መምህር ነኝ፡፡ ወደ ኮሙኒኬሽን የመጣሁት ከአምስት ወር በፊት ነው፡፡ አሁን በሁለቱም ዘርፍ ዩኒቨርሲቲውን እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡
በአሁኑ ወቅት የዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ዩኒቨርሲቲው በ1999 ዓ.ም ሲጀምር በሁለት ኮሌጆችና በ60 መምህራን ነበር፡፡ በዚያን ወቅት አጠቃላይ የሰው ኃይሉ 250 ያህል ብቻ ነበር፡፡ ባለፉት 12 ዓመታት ዩኒቨርሲቲው ብዙ ለውጦችን ያመጣና ራሱን ያስፋፋ ሲሆን አሁን 1150 መምህራንን አቅፏል፡፡ ከነዚህ መካከል ፒኤችዲ ያላቸውና በማስተርስ የተመረቁ እንዲሁም ቢኤ ዲግሪ ያላቸውም መምህራን አሉን፡፡ 2500 ያህል የአስተዳደር ሰራተኞች አሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማሩ ሂደት ስኬትን ለማምጣት በርትቶ እየሰራ ሲሆን በአሁን ወቅት በቅዳሜና እሁድ በርቀትና በማታው የትምህርት ዘርፍ የሚማሩትን ሳይጨምር፣ 13ሺህ ከመላው ኢትዮጵያ የመጡ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛል:: ዩኒቨርሲቲው ከከተማው ውጭ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሰባት ማዕከላትን ከፍቶ በርቀት ትምህርት አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ማዕከላቱ በደገሀቡር፣ ቀብሪደሀር ፊቅ ሽንሌ፣ ጎዴና በቶጎጫሌ ይገኛሉ:: እንግዲህ ከመደበኛው 13ሺህ ተማሪዎች በተጨማሪ በቅዳሜና እሁድ፣ በክረምትና በርቀት የሚማሩ 12 ሺህ 500 ያህል ተማሪዎች አሉን፡፡ በጠቅላላ 25ሺህ 500 ተማሪዎችን እያስተማርን እንገኛለን፡፡
ዩኒቨርሲቲው በምን ያህል የትምህርት ክፍሎች  እያስተማረ ይገኛል?
በአጠቃላይ በ51 አንደር ግራጁየትና 22 ዲፓርትመንቶች ፖስት ግራጁየት (የማስተርስ) ትምህርት እንሰጣለን፡፡ በፒኤችዲ ትምህርት ለመጀመር የተለያዩ ሂደቶችን እየተጓዝን ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲያችሁን በጥሩ ጎኑ ከሚያስጠራው አንዱ ሪፈራል ሆስፒታላችሁ መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች ነግረውኛል፡፡ እስኪ ስለ ሆስፒታሉ ይንገሩኝ?
እውነት ነው፤ ከ7 ሚ. በላይ የጅግጅጋ ከተማን ነዋሪ የማገልገል አቅም ያለው ሪፈራል ሆስፒታል አለን፡፡ በዚህ ሆስፒታል በርካቶች እየተገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ለህዝቡ በምንሰጠው አገልግሎት የድርሻችንን አስተዋጽኦ እያደረግን  ነው፡፡ ከሆስፒታሉም በተጨማሪ በክልሉ የተለያዩ የምርምር ማዕከላት ያሉን ሲሆን ለአርብቶ አደሮች ነፃ የመድኃኒት አገልግሎትም እንሰጣለን፡፡ ብቻ በዩኒቨርሲቲ በርካታ የጥናትና የምርምር የማህበረሰብ አገልግሎቶች ይሰራሉ፡፡
ከሦስት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ከተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ ጋር ተያይዞ በአብዛኞቹ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ረብሻና ግጭቶች ተፈጥረዋል፡፡ በአንጻሩ በናንተ ዩኒቨርሲቲ ምንም ሁከትና ብጥብጥ አለመነሳቱን ሰምቼአለሁ፡፡ የተለየ ምክንያት አለው?
ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ ምክንያቱም ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በምሳሌነት መጠቀስ ያለበት ተቋም ነው፡፡ የሰማሺውም እውነት ነው:: ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አንድም ረብሻና ብጥብጥ ተከስቶበት አያውቅም፡፡ ትንንሽ የሚባሉ ግጭቶች እንኳን ተነስተው አያውቁም:: እርግጥ አንዳንዴ የውጭ ተፅዕኖዎች ይኖራሉ፡፡ ያንን ተፅዕኖ የተማሪ ተወካዮች ከዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች ጋር በቅርበት በመስራት ያስተካክሉታል፡፡ በዘንድሮ የትምህርት ዓመት ለምሳሌ አዳዲስ ተማሪዎችን ስንቀበል፣ ትንሽ ጥሩ  የማይመስሉ ስሜቶች  ነበሩ፡፡ ያንን ያመጣው በሌላው አካባቢ ያለው ተፅዕኖ ነው:: ነገር ግን ይህንን ጥሩ ያልሆነ ስሜት ወዲያው  በመረዳት፣ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ከክልሉ ም/ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ መህሙድ ጋር በመገናኘት፣ በቁጥጥር ስር አውለውታል፡፡ በነገራችን ላይ ለሁለት ቀናት ብቻ ነበር ችግሩ የቆየው፤ትምህርትም አልቆመም ነበር፡፡ ሁለት ተማሪዎች ምግብ ቤት አካባቢ በፈጠሩት አለመግባባት ነበር የተፈጠረው፡፡ ቀደም ሲልም የዩኒቨርሲቲው አመራርና መምህራን፤ ተማሪውን በማንቃትና በማስተማር፣ የዩኒቨርሲቲው ሰላም ተጠብቆ እንዲቆይ አድርገዋል፡፡
በከተማዋ በሐምሌ 28ቱ ግጭት በርካታ የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተከስቷል፡፡ ያኔ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፍርሃት አላደረባቸውም? እንዴት አለፋችሁት?
እንግዲህ የሐምሌ 28ቱ ችግር ከባድ ነበር፡፡ ብዙ ንብረት የወደመበትና ህይወትም የጠፋበት ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲያችን ከ3400 በላይ የኦሮሞ ልጆች እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ እውነት ለመናገር በተፈጠረው ችግር እንደ ማንኛውም ሰው ሊፈሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አንድም የደረሰባቸው ችግር የለም፤ ፈርተው የሄዱት በጣም ትንሽ ቁጥር ያላቸው ልጆችም ተመልሰው ትምህርታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በአጠቃላይ ያ ግጭት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ብዙ ተፅዕኖ አልፈጠረም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ያው ክረምት እንደመሆኑ የክረምት ተማሪዎች ነበሩና አንድም ቀን ትምህርት አልተቋረጠም፡፡ ያኔ መምህራን እዚህ ግቢ አይኖሩም ነበር፤ በሰርቪስ እያመጣን እየመለስን፣ በግቢ ውስጥ ምንም ሳይፈጠር ነው ያለፍነው፡፡ ሶሻል ሚዲያ ላይ የሚለቀቀው ወሬ ነበር ያስቸገረን፡፡ ተማሪዎቹ በጣም ተረብሸው ነበር፡፡ በርካታ ጥረት ተደርጎ ነው መረጋጋቱና መማር ማስተማሩ የቀጠለው፡፡ ወላጆች፤ በፌስ ቡክ የሰሙትና እዚህ ለማረጋገጥ ሲመጡ ያዩት በጣም የተለያየ  ሆኖ ነው ያገኙት፡፡
አሁንም  ህንፃዎች እየተገነቡ ነው፡፡ አዲሶቹ ህንጻዎች ለምን ዓላማ የሚውሉ  ናቸው?
ዩኒቨርሲቲው በስፋት ደረጃ የሚስተካከለው ያለ አይመስለኝም፡፡ 51 ዲፓርትመንቶች ያሉት ሲሆን 8 ኮሌጆች፣ አንድ ት/ቤትና ሁለት ኢንስቲቲዩት አቅፎ የያዘ ነው፡፡ በግቢው ውስጥ ካሉት ኮሌጆች ብዙውን ቁጥር የሚይዙት የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የኢንጂነሪንጉ ክፍል ነው፡፡ ለብቻው ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ይባላል፤ በሱ ስር 10 ት/ቤቶች አሉ:: ኢንስቲቲዩት ኦፍ ሶማሌ ላንጉጅ የተባለ ተቋምም ራሱን ችሎ ይገኛል፡፡ የወንድና የሴት መኝታ ህንፃዎች፣ የመምህራን ቤቶች፣ አዳዲስ ካፌዎች፣ አዳዲስ ተጨማሪ ቤተ መፃህፍት፣ 25 ሺህ ያህል ሰዎችን የሚያስተናግድ ሚኒ ስታዲየምና ሌሎችም በመገንባት ላይ ናቸው፡፡
ዩኒቨርስቲውን ስጎበኝ ያገኘኋቸው መምህራን፣ እዚሁ ግቢ፣ ቤት ተገንብቶላቸው እንደሚኖሩ ነግረውኛል፡፡ እስቲ በዚህ ላይ ማብራሪያ ይስጡኝ …
እውነት ነው፡፡ የትምህርት ጥራትን ከሚያጓድሉ ነገሮች መካከል አንዱ ለመምህራን ምቹ ከባቢን አለመፍጠር ነው፡፡ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት መምህራንን ከቤት ችግር፣ ከቦታ ርቀትና እንግልት ለማዳን፣ እስከ 6 ክፍል ያላቸው ቤቶችን ገንብቶ በማስረከብ፣ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ እስካሁን 168 መምህራን ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አሁን ግቢው ውስጥ ከምታያቸው ግንባታዎች አንዱና ዋነኛው የመምህራን ቤት ነው፡፡ በቀጣዮቹ አምስት አመታት 1150ዎቹም መምህራን በግቢው ውስጥ ቤት ይኖራቸዋል፡፡ አንድ መምህር ከቤቱ ተነስቶ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የሚመጣበትን አቅምና ጊዜ በመቆጠብ ከነሙሉ ጉልበቱና ጥሩ መንፈሱ ወደ ማስተማሩ ይሄዳል፡፡ አስተምሮ ሲጨርስም እዚያው ይገባል፡፡ ለማንበብ ለሁሉም በቂ ጊዜና ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ሌላው ከኢኮኖሚ ጫና ይወጣል:: በዚህ ወቅት ከቤት ኪራይ መገላገል ቀላል አይደለም፡፡ ይሄ ሁሉ በመማር ማስተማሩ ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ቀደም ብለው ቤት ካገኙ መምህራን እያየነው ነው፡፡
በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ኮሚዩኒቲ ት/ቤቶች የሚያስተምሩት የመምህራንና የአስተዳደር ሰራተኛ ልጆችን ብቻ ነው፡፡ የእናንተ  ከዚህ ይለያል?
የእኛን ለየት የሚያደርገው በከተማው ካሉ ት/ቤቶች በውጤታቸው ብልጫ የሚያሳዩ ተማሪዎች ገብተው የሚማሩበት ሞዴል ት/ቤት መሆኑ ነው፡፡ ከኬጂ እስከ 12ኛ ክፍል ነው የምናስተምረው፡፡ በትምህርት አሰጣጡም ሆነ በሁሉም ነገር የተሟላ እንዲሆን ሁሉም ነገር ተዘጋጅቶ ተጠናቅቋል፡፡ የመምህራንና የአስተዳደር ሰራተኛ ልጆችም የሚማሩበት ነው፡፡   
ዩኒቨርሲቲው የራሱ የሆኑ በርካታ ኢንተርፕራይዞች እንዳሉት ሰምቻለሁ…
እውነት ነው፡፡ ከማተሚያ ቤት ጀምሮ የእንጨትና ብረታ ብረት፣ የወተት፣ የዶሮና ከብት እርባታ፣ የችግኝ  ማፍያ ጣቢያ (ነርሰሪ)፣ የችቡርድ ስራ፣---እንጀራ ሁሉ ከዚሁ ነው የምንጠቀመው፡፡ ለዩኒቨርሲቲው የሚያስፈልጉ የአልጋ፣ ወንበር፣ የሼልፍ፣ የቁምሳጥንም ሆነ ማንኛውም የቁሳቁስ ስራ በዩኒቨርሲቲው ኢንተርፕራይዝ ነው የሚሰራው፡፡ ማተሚያ ቤቱን ብትወስጅ ከመታወቂያ ጀምሮ ባነር፣ የተለያዩ መፅሐፍት፣ የመመረቂያ መፅሄቶችም ሆነ ሌሎች ስራዎች በራሳችን የማተሚያ ኢንተርፕራይዝ ይሰራሉ፡፡ ከከብትና ከዶሮ እርባታው ለተማሪዎች ካፌ ስጋ፣ እንቁላልና ወተት ይቀርባል፤ ምንም ነገር ከውጭ ድርጅቶች በጨረታ አይገባም፡፡ አሁን በግቢው እየተገነቡ ካሉት መካከል የመዝናኛና የምርምር ማዕከላት ይገኙበታል፡፡ እነዚህን ማዕከላት ለማስዋብና ግቢውን አረንጓዴ ለማድረግ ችግኝ ከውጭ  አንገዛም፡፡ እዚሁ ከሚገኘው ችግኝ ጣቢያ ነው የምንጠቀመው፡፡ በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው አቅሙ እንደ ሁለተኛ ሳይሆን የመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ነው፡፡
ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነትና አጋርነት እንዳለውም ይነገራል---
ትክክል ነው፡፡ ከበርካታ የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር መልካም ግንኙነትና የትብብር ስምምነት አለን፡፡ ለምሳሌ ከስዊዘርላንድ ዩኒቨርሲቲ ጋር One Health Incentive የሚባል ፕሮጀክት አለን፡፡ ለመምህራን ከማስተርስ እስከ ፒኤችዲ ደረጃ ነፃ የትምህርት ዕድል ይሰጠናል፡፡ ለዩኒቨርሲቲያችንም በምርምር እገዛ ያደርጋል፡፡ የስዊዘርላንድ መንግስት ፕሬዚዳንት እዚህ መጥተው ጉብኝት አድርገዋል፡፡ አሁን ኮሚዩኒቲ ት/ቤቱን የምንመራው በአሜሪካ ቴክሳስ ከሚገኘው ቴክሳስቴክ ዩኒቨርሲቲ ጋር ባለን ግንኙነት ነው፡፡ ከህንድ፣ ማሌዢያ፣ ኢንዶኔዢያና የመሳሰሉ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጥናትና ምርምር፣ በልምድ ልውውጥና በስኮላርሺፕ አብረን እንሰራለን፡፡  
ዩኒቨርሲቲው ከለውጡ ጋር ተያይዞ ያመጣው የአሰራር ለውጥ አለ ብለው ያስባሉ?
ዩኒቨርሲቲው አገሪቱ ላይ ከመጣው ለውጥ ጋር አብሮ ራሱን የለወጠ ተቋም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በፊት እንደምታውቂው ዩኒቨርሲቲዎች በቦርድ ነበር የሚተዳደሩት:: የቦርዱ ሰብሳቢ ራሱ የክልሉ ፕሬዚዳንት አብዲኢሌ ነበር፡፡ ቦርዱ የራሱ ኃላፊነቶች አሉት:: ሱፐርቫይዝ ማድረግ መገምገም መምራትና መሰል ተግባራትን ማከናወን አለበት:: የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ለወጡ ከመጣ በኋላ ከአዲሶቹ  የቦርድ አመራሮች ጋር አራት ጊዜ ተገናኝተናል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው ቦርድ በአምስት ዓመት አንዴ ነበር የሚመጣው፡፡ ችግሮች አጋጥመውን ለመወያየት ሲጠሩ እንኳን እሺ ብለው አይመጡም ነበር፡፡ አሁን ግን ቦርዱ በሚመለከተው ሰው ነው የሚመራው: የኛን የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ ናቸው የሚመሩት: ለምሳሌ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ አህመድ ሺዴ ናቸው፡፡ አሁን ቦርዱ የሚመራበት ሁኔታ ከፓርቲና ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ይሄ በዜጋና በአገር ግንባታ ላይ የራሱን እሴት ይጨምራል ብዬ አስባለሁ የእኛም ዩኒቨርሲቲ በአገርና በወገን ግንባታው ላይ የራሱን አሻራ ለማኖር  የበኩሉን ድርሻ ጠንክሮ ይወጣል ብዬ አምናለሁ፡፡

Read 1991 times