Saturday, 20 April 2019 13:51

ቃለ ምልልስ “የጠባብ ብሔርተኝነት መሰረቱ ህውሓት ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 ህገ መንግስቱ ሰዎች የፃፉት እንጂ ከሰማይ የወረደ አይደለም
                          · ጠ/ሚኒስትሩ የህዝብ አመኔታን መልሰው ማግኘት አለባቸው
                          · ዛሬም መሬት ለአራሹ ሳይሆን ለመንግስት ነው የሆነው

             ለትምህርት ወደ አሜሪካ የተጓዙት ገና በአፍላ የወጣትነት ዕድሜያቸው መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡
በትምህርት ላይ ሆነው  ኢህአፓን ለመመስረት ሲወጠን ተሳትፈዋል፡፡ በአሜሪካ የኢህአፓ ህዋስ አመራር አባል ነበሩ፡፡ ኢህአፓ የራሱ ታጣቂ ኃይል እንዲኖረው መወሰኑን ተከትሎ፣ የታጣቂ ሃይሉን የማደራጀት ሚና ተሰጣቸው፡፡ ይኸኔ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ትግራይ በማቅናት የኢህአፓን ጦር ማደራጀት ጀመሩ፡፡ በዚህ ወቅትም ከህውሓት መስራቾች ጋር ድርድር ለማድረግ መሞከራቻን ያወሳሉ፤ ምንም እንኳን ባይሳካም፡፡ ለምን ይሆን ያልተሳካው?  ያብራሩታል፡፡
ለ7 ዓመት የኢህአፓ ጦርን ሲያደራጁ ከቆዩ በኋላ ወደ አሜሪካ ተመልሰው ያቋረጡትን የታሪክ ትምህርት የቀጠሉት ታጋይና  ፖለቲከኛው፤ በአሜሪካ የሚገኝ የስደተኛ ማቋቋሚያ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፡፡
ከ45 ዓመታት የውጭ ሃገራት ቆይታ በኋላ ለውጡን ተከትሎ የኢህአፓን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በአገር ቤት ለማሳለጥ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት አቶ መሃሪ ረዳኢ፣ በጽንፈኛ ብሄርተኝነት፣ በለውጡ ተግዳሮቶች፣ በፌዴራሊዝምና ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡


              ኢህአፓን ስትመሰርቱ ይዛችሁ  ከተነሳችሁት የፖለቲካ ጥያቄዎች ውስጥ ምን ያህሉ ምላሽ አግኝተዋል?
ኢህአፓ እንግዲህ ከተመሰረተ ጀምሮ በጣም አንገብጋቢ የሚላቸውን ጥያቄዎች ነው ያነሳው:: በሚገርም ሁኔታ ዛሬም እነዚያ አንገብጋቢ ጥያቄዎች አሉ፡፡ አልተመለሱም፡፡ እንደ ድርጅት ያኔ ስንመሰረት ያነሳናቸው ጥያቄዎች ዛሬም የሚጠየቁ ናቸው፡፡ እነሱን አንግበን ነው አሁንም የምንጓዘው፡፡
አልተመለሱም የሚባሉትን ጥያቄዎች ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
አዎ! መሬት ለአራሹ ትልቁ ጥያቄያችን ነው:: እኛ መሬት ለአራሹ ይሁን ነው ያልነው፡፡ ነገር ግን ከደርግ መንግስት ጀምሮ መሬት ለመንግስት ነው የሆነው፡፡ አሁንም መሬት ለአራሹ ሳይሆን ለመንግስት ነው የሆነው፡፡ ስለዚህ መሬት ለአራሹና ለህዝብ መሰጠት አለበት በሚለው አቋም እንቀጥላለን፡፡ ምክንያቱም መሬት ለአራሹ አልሆነምና፡፡ አራሹ የተሰጠውን መሬት በፈለገው መንገድ የመጠቀም ሙሉ ነፃነቱ መከበር አለበት፡፡ ያለ መንግስት ተፅዕኖ መሬቱን ሊጠቀምበት፣ ባለቤት ሆኖ ሊሰራበት ይገባል:: ይሄ ፅኑ አቋማችን ነው፡፡ ገበሬውም ሆነ ዜጋው መሬቱን በሚያመቸው መንገድ መጠቀም አለበት:: መሸጥ መለወጥ መቻል አለበት፡፡ መብቱ እዚህ ደረጃ ነው መድረስ ያለበት፡፡ ሌላው የዲሞክራሲ ጉዳይ ነው፡፡ የዲሞክራሲ ጥያቄ እስካሁንም ምላሽ አላገኘም:: ደርግ ያወጣቸው የሰብአዊ መብት ገደብ አዋጆች የመሰብሰብ፣ የመደራጀት፣ የመናገር ክልከላዎች ዛሬም ሙሉ ለሙሉ አልተነሱም:: እነዚህ ተጨማሪ ትግል የሚጠይቁ ናቸው:: አሁን የምናያቸው ውጥረቶች የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ምላሽ ያለማግኘታቸው ውጤት ናቸው፡፡ በተፈጥሮ ለሰው ልጅ የተሰጡ መብቶች ስለሆኑ፣ ሙሉ ለሙሉ ተረጋግጠው የህብረተሰቡ መደበኛ ባህል መሆን አለባቸው፡፡
በህዝቡ ዘንድ ተስፋ የፈነጠቀውን  የለውጥ ሂደት የአንድ ዓመት አካሄድ  እንዴት ይገመግሙታል?
እስካሁን እኛም ሆነ ህዝቡ ያመነው የመሪውን ንግግሮች ነው፡፡ መሪው ደግሞ በሚናገሯቸው ነገሮች ልንደግፋቸው የሚገቡ ናቸው፡፡ ነገር ግን ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊፈፀሙ ይገባቸው የነበሩ ጉዳዮች በዚያው ልክ አሉ:: ለምሳሌ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ከውጭ ወደ ሃገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ እዚህም ያሉ ነበሩ:: በእርግጥ ብዙዎቹ ወያኔ የጠፈጠፋቸው  ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጥቂቶች ናቸው:: እንደዚያም ሆኖ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደተለያዩ ውይይቶች ከመግባታቸው በፊት የእርስ በርስ እርቅ ማውረድ ይገባቸው ነበር:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄ እውን እንዲሆን ሊያደርጉ ይገባል:: እኔ ለምሳሌ ከትዴት ሊቀ መንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ጋር ተታኩሻለሁ:: በሁለት ዓላማ ተሰልፈን ተታኩሰናል:: ብዙዎቻችን ደሞ ተቃብተናል፡፡ እንደዚህ ደም የተቃቡ ሃይሎች ዝም ብለው በሙሉ መተማመንና ልበ ሰፊነት የተሳካ ውይይት ያደርጋሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ እኔ በግሌ ከዶ/ር አረጋዊ ጋር ዛሬም ሆነ በውጭ ቆይታዬ ችግር የለብንም፤ ወዳጆች ነን ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የተደራጀ የእርቅና የሰላም ጉባኤ መደረግ አለበት፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ልባችንን ከፍተን ሁላችንም በንፁህ ህሊና ልንወያይ የምንችለው:: እኔ አሁንም ድረስ የተወሰኑ ግለሰቦችን በጎን አይቼ ሳላናግራቸው ነው የማልፋቸው፡፡ ይሄ መሆን የለበትም ነበር፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የእርቅና ብሔራዊ መግባባት ኮሚሽን ማቋቋማቸው መልካም ነው፤ ነገር ግን በሚገባው ልክ የሚጓዝ ኮሚሽን አልመሰለኝም፡፡ እስካሁንም ብዙ እንቅስቃሴ አላየንም፡፡ አሁንም መሰራት ያለበት በዚህ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የተጀመሩ ውይይቶች በጣም ጠቃሚ ናቸው፤ መቀጠልም አለባቸው፡፡
በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ሰላምና መረጋጋት የጠፋው ለምን ይመስልዎታል?
ሰላምና መረጋጋት የጠፋው ከብሄር አክራሪነት የተነሳ ነው፡፡ ፅንፍ የወጣ ብሄርተኝነት ያመጣው ችግር ነው፡፡ የብሄርተኝነትን ውጤት ነው አሁን እየተመለከትን ያለነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ተጠያቂ ህውሓት ነው፡፡ ሌላ ማንም አይደለም፡፡
ህውሓትን ዋነኛ ተጠያቂ ያደረጉበት ምክንያት ምንድን ነው?
ህውሓት ከተመሰረተ ጀምሮ እስካሁን ሲመራ የቆየው በብሔርተኝነትና በጠባብነት ነው:: ጠባብነትን ወደ ፖለቲካ መድረኩ ያመጣው የመጀመሪያው የፖለቲካ ሃይል ህውሓት ነው፡፡ ይሄን በማስረጃ መናገር እችላለሁ፡፡ እኛ ራሳችን ከህውሓት ጋር በበረሃ ካደረግነው ድርድር ተነስቼ መረጃ መጥቀስ እችላለሁ፡፡ (ሰነዱን እያሳዩ) ይሄ ጥቅምት 26 ቀን 1968 ዓ.ም ሩቅሶ የሚባል ቦታ ላይ ያደረግነው የመጀመሪያው ስብሰባችን ቃለ ጉባኤ ነው፡፡ በኛ በኩል ፀጋዬ ገ/መድህን (ደብተራው)፣ አብደሳ (ሮባ) እና እኔ ነኝ ኢህአፓን ወክለን በቦታው የተገኘነው፡፡ በእነሱ በኩል ደግሞ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሐዬና ሌላ አንድ ህውሓትን ደደቢት ላይ እግሯን እንድትተክል ያደረጉ ሰው ነበሩ (ስማቸው በቃለ ጉባኤው ሰነዱ አልሰፈረም)፡፡ በእኛ በኩል በደንብ ተዘጋጅተን የፓርቲ ፕሮግራማችንን ይዘን፣ አራት የስምምነት ነጥቦችን አውጥተን ነበር የሄድነው፡፡ የመጀመሪያው ነጥብ፡- እኛም እነሱም ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ከሆንን ለምን አንዋሃድም የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ውህደቱ ካልሆነ ለምን ግንባር አንፈጥርም የሚል ነበር፡፡ ሦስተኛው ነጥባችን ደግሞ ውህደቱንም ሆነ ግንባሩን ካልተቀበሉ ትብብር መፍጠር የሚል አማራጭ  ነበር፡፡ ትብብሩ በአንድነት  የጋራ ጠላትን ማጥቃት የሚል ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የማይሆኑ ከሆነ አራተኛ መደራደሪያ ነጥባችን፤እነሱም እኛን፣ እኛም እነሱን እንዳንነካ መስማማት የሚል ነው፡፡ የእነሱ መልስ ግን አስደንጋጭ ነበር፡፡ ሲጀመር ይዘውት የመጡት የስምምነት ነጥብም አልነበረም፡፡ የፖለቲካ ፕሮግራምም አላቀረቡም፡፡ ስንጠይቃቸው፤ ገና እየተረቀቀ ነው የሚል ምላሽ ነበር የሰጡን፡፡ አሁን ስለ ታሪካቸው ሲናገሩ፣ ገና አዲስ አበባ እያለን በረሃ ሳንገባ ነው የፖለቲካ ፕሮግራማችንን ያወጣነው ይላሉ፡፡ ያኔ ግን ለኛ የነገሩን፣ ገና እየፃፍነው ነው ብለው ነው፡፡ እንግዲህ በውይይታችን ይዘን የቀረብናቸው የመጀመሪያዎቹ ማለትም ውህደት፣ ግንባርና ትብብር በእነሱ በኩል ተቀባይነት ሲያጡ፤ “በቃ እርስ በእርስ አንነካካ” ስንላቸው፣ እነሱ የመጨረሻ መፍትሄ ብለው የነገሩን “ኢህአፓ ትግራይን ጥሎ መውጣት አለበት” የሚል ነበር፡፡ እብሪት የጀመሩት በዚህ የመጀመሪያ ውይይት ላይ ነው፡፡
በወቅቱ ያንን ያሉበት ምክንያታቸው ምን ነበር?
ኢህአፓ አማራ ነው በሚል ነበር፡፡ ትግርኛ ተናጋሪ የሆነውን አባላት ደግሞ (ኮርኩራ አማራ) “የአማራ ቡችሎች” ነበር የሚሉን፡፡ ስለዚህ እነ ስብሃትና አባይ ፀሃዬ፤ ከትግራይ ለቃችሁ ውጡ ነው ያሉን:: “እኛ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ድርጅት ነን፤ በኢትዮጵያ የትኛውም አካባቢ ሆነን መታገል እንችላለን፣ ውጡልን ልትሉን አትችሉም፤ መብታችን ነው” ብለናቸው ነው የተለያየነው፡፡ ህውሓት እንግዲህ ሲጀመርም ጠባብ ብሔርተኛ ድርጅት እንደሆነ ይሄ ማሳያ ነው፡፡ የመገንጠልና ጠባብ ብሔርተኝነት ንፋስም በሃገሪቱ የዘራው ህውሓት ነው፡፡ ዛሬም ድረስ በሃገሪቱ የምናየው የጠባብ ብሄርተኝነት ሁኔታ መሰረቱ ህውሓት ነው፡፡ ኦነግም ራሱ የተማረው ከነሱ ነው፡፡
ቀዳሚው ብሔርተኛ ድርጅት ማነው?
ህውሓት፤ ኦነግ የነበረውን ለዘብተኛ አቋም አስቀይሮታል፡፡ ብሔርተኛነትን እንዲያከር አድርጎታል፡፡ አክራሪ ብሔርተኝነትን ለሃገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች ያስተማረው ህውሓት ነው:: ጠባብነትን የፈጠረው ህውሓት ነው:: የ”እኔ እና አንተ” የሚል የተራራቀ ፖለቲካን የፈጠሩት ህውሓቶች ናቸው፡፡ ዛሬ አወዛጋቢ የሆኑ ተቀጣጣይ የጠባብነት ቦንቦችን በየቦታው የተከለው ህውሓት ነው፡፡ አዲስ አበባን የውዝግብ ማዕከል ያደረገውን ቦንብ የተከለው ህውሓት ነው፡፡ ለዚህ ምንም ማስተባበያ የለውም፡፡ በወቅቱ አብረውት የነበሩ የአማራውም፣ የኦሮሞውም፣ የደቡቡም ድርጅቶች ተጠፍጥፈው የተሰሩት በራሱ ነው:: ይሄንንም በደህናው ጊዜ በኩራት ሲነግሩን አዳምጠናቸዋል:: ስለዚህ አሁን የሃገሪቱ ቁልፍ ችግር መፈልፈያ ለሆነው የብሄርተኝነት ጉዳይ ተጠያቂው ህውሓት ነው፡፡
የእናንተ ድርሻስ በዚህ ውስጥ አልነበረም?
እንዲያውም የኛ ደካማ ጎን የምለው፣ ህውሓት በወቅቱ ምን ዓይነት መጥፎ ድርጅት እንደነበር ለህዝባችን አለማጋለጣችን ነው፡፡ ከትግራይ እስከ ቤኒሻንጉል ከእነሱ ጋር ተዋግተናል ደም ተቃብተናል፤ ግን የህውሓትን የጠባብነት ደረጃ ለህዝባችን በወቅቱ አለማስተማራችን የኛ ደካማ ጎን ነበር፡፡
የወቅቱ ጥያቄ የብሄሮችን መብት የማስከበር ነበር የሚሉ መከራከሪያዎች ይቀርባሉ፡፡ የእናንተ የማርክሲስት ሌኒኒስት አስተሳሰብም በዚህ የተቃኘ ነው … እናንተስ እንዴት ከተጠያቂነት ታመልጣላችሁ?
እኛም የብሄሮች መብት መከበር አለበት ብለን ነው የተነሳነው፡፡ እኛ ያንን ስንል ግን ብሄሮች በራሳቸው ቋንቋ ይማሩ፣ ይግባቡ፤ ብሄሮች ሙሉ መብት ይኑራቸው ነው፡፡ የመንግስት ስርአቱም ቢሆን ከላይ ወደ ታች ሳይሆን ከታች ወደ ላይ በሚመጣ ፌደራሊዝም መርህ እንዲዋቀር ነበር አላማችን፡፡ አሁን ግን ፌደራሊዝሙ ከላይ ተሰርቶ ነው ወደ ህዝብ የወረደው እንጂ ከታች ተሰርቶ ወደ ላይ የመጣ አይደለም፡፡
ከጠባብ ብሄርተኛ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ያቀነቅን የነበረውን ደርግ መፋለማችሁን በመጥቀስ ተጠያቂ የሚያደርጓችሁ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?
ይሄ የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ በምሳሌ ላስረዳ:: ሻዕቢያ እኛን ወደ ትግራይ ባሻገሩን ወቅት በ1968 ዓ.ም 600 ወታደር ብቻ ነው የነበራቸው፡፡ ከ6 ወር በኋላ እኔ ወደ ሻዕቢያ ተመልሼ ድርድር እንዳደርግ ስላክ 600  የነበሩት ወታደሮች በሁለት አንጃ ማለትም በአንደኛው 30ሺህ፣ በሌላኛው 30ሺህ አጠቃላይ 60 ሺህ ሰው እያሰለጠኑ ነው ያገኘኋቸው፡፡ ይሄ የሆነው በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው እነሱ ቅስቀሳ ድርገው ሳይሆን የደርግ እርምጃ ጠቅሟቸው ነው፡፡ ቀይ ሽብር ኤርትራ ውስጥ መፋፋሙ ሻዕቢያን በ6 ወር ውስጥ ጠንካራ ሃይል አድርጎታል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን ለወያኔ እና ለሻዕቢያ ያስረከበው ደርግ ነው፡፡ ለዚህ ሌላ ተጠያቂ የለም፡፡ ያኔ ጀነራል አማን አንዶም በጀመሩት የሰላም መንገድ ደርግ ቢሄድ ኖሮ፣ ዛሬ ሻዕቢያም ወያኔም አይኖሩም ነበር፡፡ ነገሮች ሌላ መልክ ይኖራቸው ነበር፡፡
ከጽንፈኛ ብሔርተኝነት በመውጣት አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አንደኛ፤ የተጠናከረ ኢትዮጵያዊነት ላይ የተመረኮዘ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል:: ጠባብነትን በሚፋለም መልኩ ቅስቀሳና ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ እኔ እዚህ በነበረኝ የወራት ቆይታ የታዘብኩት፣ ህዝቡ ከምንም በላይ አንድነትን የሚሻ፣ ብሔርተኝነትን የሚፀየፍ መሆኑን ነው:: ስለዚህ ጠባብነትን ገፍቶ ለመጣል ብዙ ጉልበት አያስፈልግም:: ቅስቀሳና ትምህርት መስጠት በቂ ነው፡፡ ስለዚህ በተግባርም በንድፈ ሀሳብም ትምህርት መስጠት ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት፡፡ ህዝቡ በጠነከረ ሁኔታ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዳለው ከ40 ዓመት በኋላ ወደ ሃገሬ ስመለስ በሚገባ አስተውያለሁ፡፡
አሁን ለሚታዩች ችግሮች መንስኤው የፌደራል አወቃቀሩና ህገ መንግስቱ ነው የሚል ሙግት ይቀርባል፡፡ በዚህ ላይ  የእርስዎ ምልከታ ምንድን ነው?
ሲጀመር ይሄ ህገ መንግስት ሰዎች የፃፉት እንጂ ከሰማይ የወረደ ቅዱስ መፅሃፍ አይደለም፡፡ የማይቀየር ነገር አይደለም፤ መቀየር የሚያስፈልግ ከሆነ  መቀየር አለበት፡፡ የፌደራል አወቃቀሩን በተመለከተ አንድ እውነት አለ፡፡ ይህ ዛሬ በቋንቋ ላይ የተመሰረተው ፌደራሊዝም፣ ወያኔዎች ፈፀሙት እንጂ በፋሽስት ጣሊያን ወራሪ ኃይል የተዘጋጀ ነው:: በጣሊያንኛ በመፅሐፍ ተዘጋጅቶ አግኝቸዋለሁ:: ካርታው አወቃቀሩ ከጣልያኑ የከፋፍለህ ግዛ አወቃቀር ጋር ተመሳሳይ ነው:: መሆን የነበረበት የኢትዮጵያን ህዝብ ትስስር ባማከለ መልኩ የተዋቀረ ፌደራሊዝም ነው:: የተፈጥሮ ወሰኖችን፣ የኢኮኖሚ ትስስሮሽን፣ የህዝብን ቋንቋ ሳይሆን ስነ ልቦናን በማካተት ነበር መዘጋጀት የነበረበት፡፡ አሁንም በዚህ መንገድ ክልልም እንበለው ክፍለ ሀገር 15 እና 16 የፌደራል አካላት እንደገና መዋቀር አለባቸው:: የፌደራል መንግስቱ መስራቾች በርከት ማለት አለባቸው፡፡ አወቃቀሩም ከላይ ወደ ታች የሚወርድ ሳይሆን ከታች ወደ ላይ የሚመጣ መሆን አለበት፡፡
ይሄ ለውጥ ሊቀለበስ ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
የመቀልበስ ስጋቱ በእርግጥ አለ፡፡ እሱ እንዳይመጣ ነው ስብሰባዎች እያካሄድን ያለነው:: እነዚህ ስብሰባዎች በቀላሉ መታየት የለባቸውም:: ለውጡ እንዳይቀለበስ የሚያደርገው ውይይት ነው፡፡ ይሄ ውይይት ደግሞ ተጀምሯል፡፡ ስለዚህ አሁንም ተከታታይ የፖለቲካ ውይይቶች መኖር አለባቸው:: በዚህ መንገድ ሰክነን ለውጡንም ማስከን አለብን:: በፓርቲዎች መካከል የውይይት ሃሳቦችን የማቻቻል ባህል መዳበር አለበት፡፡ አሜሪካኖች አንድ የምወድላቸው አባባል አለ፡- “Our union is not perfect” (ውህደታችን የተሟላ አይደለም) ይላሉ፡፡ እውነት ነው እኛም ዘንድ  ያለው ይሄው ነው፡፡ ሁሉም የየራሱን ሂደት ይፈልጋል፡፡ የተሟላ ነገር የለንም፤ አሁን ሊኖረንም አይችልም፡፡ ነገር ግን ወደዚያ የሚያደርሰን በሩ ተከፍቷል፡፡ ያ በር እንዳይዘጋ ሁላችንም መከላከል አለብን፡፡ ያንን በር ተጠቅመን ሌላ በር መክፈት አለብን፡፡ በዚህ መንገድ ነው መሄድ ያለብን፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቅድሚያ ሰጥተው ቢሰሯቸው የሚሏቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
አንደኛ እንግዲህ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለን ወደ ሃገር ቤት የገባነውም ሆንን እዚህ ሃገር ቤት የነበርን የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል መተማመን እንዲፈጠር ማድረግ አለባቸው:: ሌላው ዜጎች በመንግስቱ ላይ የነበራቸው እምነት በጥቂት ወራት ውስጥ ሲያሽቆለቁል መመልከት ለኔ አስደንጋጭ ነው፡፡ ብዙ ሰው ዛሬ እምነት ማጣት ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ህዝቡ ከዚህ እምነት ማጣት ወጥቶ በድጋሚ ለውጡን እንዲያምን ማድረግ አለባቸው፡፡ የህዝቡን እምነት ማምጣት ካልቻሉ ችግር ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን፡፡ ህዝብ ካላመነህ ምንም ነህ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የህዝብ አመኔታን መልሰው ማግኘት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል የመፈናቀል ጉዳይ አለ:: ለዚህ ፈጣን መፍትሄ ያስፈልጋል:: ህዝብ በዚህ ተስፋ ማጣት የለበትም፡፡ እነዚህ ሦስቱ ጉዳዮች ለኔ ወሳኝ ናቸው፡፡ 

Read 1585 times