Print this page
Saturday, 20 April 2019 13:51

የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ይናገራሉ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)

 የመሬት ወረራ---የባለሥልጣናት ጫና---የደላሎች ዛቻ---የደህንነት ስጋት

            የቀድሞው የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጋትሉዋክ ቱትኮት፣ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ክልሉን በተለያዩ የሃላፊነት ደረጃዎች አገልግለዋል፡፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርም ነበሩ፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ከሥልጣን እስኪወርዱ ድረስ ጋምቤላን ለ2 ዓመት ያህል በፕሬዚዳንትነት መርተዋል፡፡
በእነዚህ ሁሉ የሥልጣን ዓመታት ለክልላቸው ምን አስገኙ? ምንስ አሳጡ? ብዙ ስለሚነገርለት የክልሉ የመሬት ወረራ ምን ይላሉ? ከሥልጣን የወረዱት ወደው ነው በተቃውሞ? በአሁኑ ወቅት ለምን የደህንነት ስጋት ተጋረጠባቸው? ቤትና መኪናስ ለምን ተነጠቁ? አዲሱ ሥራቸውን ያልጀመሩበት ምክንያት ምንድን ነው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሠላም ገረመው፣ ከአቶ ጋትሉዋክ ቱትኮት ጋር  ያደረገችውን ቃለ ምልልስ እነሆ፡-   


                እርስዎ  ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ በክልሉ የነበረው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዴት ይገለጻል?
ከእኔ በፊትም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፤ “ኑ እና በጋራ ጋምቤላን እናልማ” የሚል ጥሪ ተላልፎ ኢንቨስተሮች ወደ ክልሉ እየገቡ ነበር፡፡ ብዙ ኢንቨስተሮችም ከተለያዩ  ክልሎች ገብተዋል:: ይሄንን እንደ በጐ ነገር መውሰድ እንችላለን:: ነገር ግን የሚያሳዝነው አፈፃፀማቸው ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም ከክቡር ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ እንዲሁም ከግብርና ሚኒስቴርና ከኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ተወካዮች ጋር የተቀናጀ ቡድን ይዘን ሥራቸውን ገምገመናል:: ከ882 ኢንቨስተሮች መካከል 269 ያህሉ አፈፃፀማቸው በጣም ዝቅተኛ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ዝም ብለው መሬት ወስደው፣ የባንክ ብድር ማግኛ ከማድረግ ውጭ ማሽነሪ ገዝተው ወደ ስራ በመግባት፣ ለወጣቱ የስራ ዕድል አልፈጠሩም፡፡
ባለሃብቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ያለ አግባብ ከባንክ መበደራቸው ይነገራል:: አስተዳደርዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እርምጃ ወሰደ?
በ2008 ዓ.ም ለጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ፣ ”ኪራይ ሰብሳቢነት ይቁም” በሚል ጉዳዩን የሚያጣራ  ቡድን ተዋቅሮ እንዲላክልን ጥያቄ አቅርቤያለሁ፡፡ በወቅቱም ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከኢንቨስትመንት ኤጀንሲ፣ ከጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤትና ከክልሉ ከተውጣጡ ቡድኖች ጋር በተደረገ ማጣራት፣ 269 የሚሆኑ አልሚዎች ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ከባንክ መውሰዳቸው ተረጋግጧል:: ይሄ እንዲጣራ ያደረግሁት  እኔ ነኝ፡፡
በጫና ለባለሃብቶች መሬት ትሰጡ ነበር ይባላል፤ እውነት ነው?
ቀደም ሲል ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚደረጉ ጫናዎች ነበሩ፡፡ መሬት ያለ አግባብ ለመውሰድ የሚደረግ ሩጫም ነበር፡፡ እነዚህ ሩጫዎች ሲያስቸግሩን መሬቱን እንዲያስተዳድርልን ለፌደራል መንግስት አስተላለፍን፡፡ ምክንያቱም ፌደራል ላይ አቅም ያላቸው ባለሙያዎች አሉ:: ዝም ብለን መሬት የምንሰጥ ከሆነ ህዝቡ ስለሚበዘበዝ፣ ይሄን ለማስቀረት ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስነው:: ፌደራል መንግስት መሬቱን ከሰጠ በኋላ እከሌ ለሚባል ባለሀብት ተሰጥቷል ብሎ ለክልሉ መንግስት መረጃ ይልካል፡፡
መሬት ከተነጠቁት አልሚዎች  ውስጥ በጫና መሬት የወሰዱ ነበሩ?
ሙሉ በሙሉ በጫና ነው የወሰዱት ማለት ይቻላል፡፡ ግን ጫናም ቢኖር መሬቱን ስንሰጣቸው፣በቀጥታ ወደ ልማት ገብተው ክልሉን ያለማሉ በሚል እምነት ነበር፡፡  አፈፃፀማቸው ሲገመገም ግን ደካማ ሆኖ ተገኘ:: ጫና የሚፈጥሩት አካላት የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች ቤተሰቦች ስለነበሩ ለስማቸው ይጠነቀቃሉ፤ እነሱም ይቆጣጠራሉ ብለን አስበን ነበር፡፡ ሆኖም ያለአግባብ መደጋገፍ በመሆኑ ከፍተኛ ችግር ነበር የፈጠረብን:: ጫና የሚያደርጉት ሰዎች ጉልበትም ነበራቸው፡፡ እነዚያ 269 አልሚዎች ላይ እርምጃ ስንወስድ፣ እኔ ላይ ከባድ ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሶብኛል::  ብሔርን ከብሔር የማጋጨት ጥረትም ነበር:: ለምሳሌ እኔን “የደቡብ ሱዳን ኑዌር ነው” በማለት ከህዝብ ጋር ሊያጣሉኝ ሞክረዋል፡፡ “አንተን ከስልጣን ካላወረድንህ ታያለህ” ብለው የዛቱብኝም ነበሩ፡፡  
ዛቻው ከመንግስት ኃላፊዎች ነው ወይስ መሬቱን ከተነጠቁት ግለሰቦች?
ከሁሉም ነው የነበረው፤ ደላሎችም ነበሩ:: በተለይ ከትግራይ ክልል የመጡ 19 የሚሆኑ ደላሎችን እስከ ማሠር የደረስንበት ጊዜ ነበር፡፡ ደላሎቹ የራሳቸውን ስምሪት አድርገው ካመቻቹ በኋላ መሬት እዚህ አለ በማለት የራሳቸውን ክልል ሰዎች ጠርተው አምጥተዋል፡፡ ስለዚህ መሬቱን ሲነጠቁ በእኔ ላይ በተደጋጋሚ ዝተዋል፤ ህይወትህን እናጠፋለን እስከ ማለት ሁሉ ደርሰው ነበር፡፡ ደላሎች እስከ ፌደራል የሚደርስ ረጅም ገመድ ነበራቸው:: መሬቱን የመበዝበዝ ሙከራ ብቻ ሳይሆን በጣም መጥፎ የሆኑ ስራዎችን ሲሰሩ ነበር፡፡
የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት በጀት በአግባቡ የመጠቀም ችግር አለበት ይባላል፤ ከቀጣይ አመት ብድር ይወስዳል፤ ያልተከፈሉ እዳዎች አሉበት፤ ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ በሰአቱ አይከፍልም ወዘተ ትችቶች ይሰነዘርበታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
አንደኛ የሠራተኛ ቁጥር ብዛት ችግር አለብን፣ ትንሽ ክልል ሆኖ ከ21ሺህ በላይ የሰው ሃይል ነው ያለን፡፡ ይሄ ቀላል  በጀት አይደለም የሚወስደው:: በተለይ ወረዳዎች ያለ አግባብ የሰው ሃይል ምደባ ያደርጋሉ፡፡ ይሄ አንዱ ችግር ሲሆን ሌላው ባለሙያዎች አካባቢ የበጀት አጠቃቀም ችግር መኖሩ ነው፡፡ ከእቅድ ውጪ ያለ አግባብ የማውጣት ችግሮች ነበሩ፡፡ ሌላው ትልቁ ችግር፤ ገቢያችንን ሙሉ በሙሉ ያለመሰብሰብ ነው፡፡ በቴክኖሎጂ ተደግፎ የገቢዎች ግብር በተገቢው ሁኔታ አይሰበሰብም፤ ሠርቨር አለ፤ ተገዝቷል፤ ስራው ይጀመርና ተበላሽቷል ተብሎ ይቆማል:: የካሽ ሬጅስተር ስለሌለ አየር በአየር ስራ ለማስቆም አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ክልሉ ማግኘት ያለበትን ገቢ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ይሄም እንደ በጀት ነው የሚቆጠረው፡፡ እንደ ማንኛውም ክልል ገቢ ትሰበስባላችሁ ተብለን፣ በጀታችን ላይ አንድ ቢሊዮን አምስት መቶ ሚሊዮን ብር ይደመራል፤ ነገር ግን መሰብሰብ ያለብንን ባለመሰብሰባችን ችግር ውስጥ እንገባለን ማለት ነው፡፡ ወረዳዎችም ዞኖችም መሰብሰብ ያለባቸውን ስለማይሰበስቡ  ብድር ይጠይቃሉ::  ይህንን ጥገኝነት ለማስቀረት የተቸገርንበት ሁኔታ ነበር፡፡ ብድርን አንሠጣችሁም ቢባል ደግሞ ዞኑ፣ ወረዳው መዘጋቱ ነው ማለት ነው::
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ የክልሉ መንግስት ለውጡን አልተቀበለም ብለው ነበር፡፡ እውነት ነው?
ይሄ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ለውጡ እንዲመጣ ከታገሉ ሰዎች ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ፡፡ በተለይ በጋምቤላ ክልል፣ እንደ ጋህዴን፣ ለውጡ ሲመጣ በአካልም ነበርኩ፡፡ ክቡር ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ሲመረጡ በቦታው ላይ ነበርኩ፡፡ በኦሮምያ ክልል ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት እያሉ ጀምሮ ነው የምንተዋወቀው፡፡ በተመረጡ ወቅትም ይሄን ሀገር ይለውጣሉ የሚል ትልቅ እምነት ነበረኝ፡፡ አሁንም እምነቴ አልተቀየርም፡፡  ለውጡ ማለት እኛ ያለንበት ለውጥ ነው፡፡ ሌላ ሰው ያመጣው ለውጥ አይደለም:: በኢህአዴግ ውስጥ የተፈፀመ ለውጥ ነው፡፡ የቀድሞው ክቡር ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ መልቀቂያቸውን ሲያስገቡ በአካል ነበርኩ፡፡ በወቅቱ ሦስት ጊዜ እድል ተሰጥቶኝ ንግግር አድርጌያለሁ:: እኛ የምንፈልገው ለኢትዮጵያ ህዝብ ሠላም የሚያመጣ መሪ ነው ብያለሁ፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ ተጨናንቆ ነበር፤ ወደ ጋምቤላ ለመሄድ እንኳን በመኪና ፈርቶ በአውሮፕላን ከአቅሙ በላይ እየከፈለ የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ነበር፡፡ እኛ አብዛኛውን ነገር  ከአዲስ አበባና ከኦሮምያ ነበር የምናገኘው፤ሠላም ስለሌለና መንገድ ባለመኖሩ ተቸግረን ነበር፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር መፍትሄ ይሆናል  ያልኩት ደግሞ ዶ/ር ዐቢይን ነበር፤ ይሄን መቶ በመቶ መናገር እችላለሁ:: ሌላው ልማት የሚያመጣ መሪ ነው ብያለሁ:: ይህቺ ሀገር እንደ ሌሎች የአፍሪካና የአለም አገራት እንድትሆን ጉጉት አለው፡፡ ይሄንን አውቃለሁ፤ መመስከርም እችላለሁ፡፡  
በእኔ በኩል የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆነው አቶ ኦባንግ ሜቶ በሽግግር ወቅት አይደለም ከአገር የወጣው፤ ቆይቷል አገር ከለቀቀ፡፡ ከሽግግሩ ወቅት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በየአካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በትክክል የሚያውቅ አይመስለኝም:: አንድ ሰው ትችት በሚያቀርብበት ወቅት የማያውቀውን ነገር መናገር የለበትም:: በክልሉ ውስጥ ሳይኖሩ መተቸት በጣም ያስቸግራል:: አቶ ኦባንግ ከአሜሪካን ነው ቀጥታ አዲስ አበባ የገባው:: ያየው ነገር የለም፡፡ ውጭ ሆኖ ተቃዋሚ ነበር፤ መቃወሙ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ተደምረን መስራት ነው ያለብን እንጂ እኔ ነኝ ይሄንን ለውጥ ያመጣሁት የሚለው አይሰራም:: ምክንያቱም እሱ ያመጣው ለውጥ አይደለም፤ ሁላችንም እንደ ኢትዮጵያዊ ያመጣነው ለውጥ ነው፡፡
እርስዎ ከስልጣን የለቀቁት በፈቃድዎ እንደሆነ ቢናገሩም በተቃውሞ ነው የለቀቁት የሚሉ ወገኖች አሉ---
ወቅቱ የወለዳቸው ችግሮች ነበሩ፡፡ የወጣቶች ጥያቄም ነበር፤ “ለውጥ እንፈልጋለን” የሚል:: በፌደራል ደረጃ የተጀመረው የሪፎርም ስራ ጋምቤላ መድረስ አለበት የሚል አጀንዳ ተይዞ ነበር፡፡ ሌላው የወጣቶች ተጠቃሚነት ጉዳይ ነው፡፡ የስራ ዕድል ፈጠራ በነበረን የበጀት ዕጥረት ምክንያት ብዙ ርቀት ያለመሔድ ችግር ገጥሞት ነበር፡፡ ስለዚህ ወጣቶች ማግኘት የነበረባቸውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አላገኙም፡፡      
የፀጥታ ችግር በተለይ በአቅራቢያችን ከኦሮሚያ ክልል በኩል የኦነግ እንቅስቃሴ እስከ ጋምቤላ የደረሰበት ሁኔታ ነበር፡፡ በክልሉም ውስጥ የኑዌርና አኝዋክ ብሔረሰቦች እርስ በእርሳቸው የመገዳደል ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ በ2008 ዓ.ም በእንደዚህ አይነት ሴራዎች ብዙ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲከሰት ህዝቡ በየጊዜው ከሚሞት ስልጣን መልቀቅ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ::  
ሌላው የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ናቸው:: የሠራኋቸው በጐ ስራዎች ቢኖሩም የሕዝቡ ጥያቄ አልተመለሰም ነበር፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ለምን አዲስ አመራር አላስረክብም ብዬ በራሴ ፍላጐት ነው ስልጣን ያስረከብኩት እንጂ ከፌደራል መንግስት ከጠ/ሚኒስቴር ቢሮ ውረድ የተባልኩበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ በሌላ በኩል በክልሉ ውስጥ ስልጣን በአቋራጭ ለመያዝ የሚፈልጉ ወገኖች ነበሩ፤ በጣም ከፍተኛ ፍትጊያ ለማድረግ የተነሱ፡፡ በእነሱ ምክንያት ሌላው ህዝብ ለምን ይሞታል ብዬ ነበር የማስበው:: በነገራችን ላይ እነዚህ የስልጣን ጥመኞች አሁንም አሉ፤ የተመኙትን ስልጣን አላገኙም እንጂ፡፡ አሁንም አዲሶቹ ላይ ሴራ እያሴሩ ነው፤ ዘመቻ እያካሄዱ ነው፡፡ ለውጥ አልመጣም ይላሉ፡፡ ምንድነው ያልተለወጠው የሚለውን ግን መግለፅ አይችሉም:: ለውጥ እንደሌለ በተጨባጭ ማሳየት አይችሉም፡፡ መንግስት ለይቶ እርምጃ ካልወሰደባቸው ሌላ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡
ከጋምቤላ ርዕሰ መስተዳደርነትዎ ከለቀቁ በኋላ ምን እየሰሩ ነው?
ከየካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በህንድ ሀገር ሞምባይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንጽላ ጽ/ቤት ውስጥ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ሆኜ ተመድቤያለሁ፤ ነገር ግን ደሞዝ ይከፈለኛል እንጂ በውጪ ጉዳይ በኩል ስራውን  አልጀመርኩም፡፡
ደሞዝዎ ምን ያህል  ነው?
አምስት ሺህ ሰባት መቶ ስልሳ አራት  ብር ነው የሚከፈለኝ፡፡
የደህንነት ስጋት  እንዳለብዎ ሲናገሩ  ሰምቻለሁ…
ብዙ ችግሮች ያጋጠሙኝ በማህበራዊ ህይወቴ ዙሪያ ነው፡፡ ከስልጣን ስወርድ ተሽከርካሪ አስረክቤያለሁ፤ ተለዋጭ መኪና ስላልተሰጠኝ የህዝብ ትራንስፖርት ነው የምጠቀመው፡፡ በስልጣን ላይ በነበርኩ ጊዜ ውሳኔ ሰጪ አካል ነበርኩ፡፡ ስለዚህ በመጥፎም ሆነ በክፉ የሚያየኝ ሰው ይኖራል፡፡ እኔ ደህንነቴን የምጠብቅበት አጃቢ እንኳ የለኝም፡፡ በራሴ ሰላማዊ ሰው ነኝ ብዬ ባስብም፣ ለደህንነቴ ስጋት ውስጥ የገባሁበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሌላው አዲስ አበባ በምመጣበት ጊዜ የማርፍበት  የመንግስት ቤት ነበር፡፡ ይሄንን ቤት እንዳስረክብ ተደርጌያለሁ:: ስለዚህ ከልጆቼ ጋር ማረፊያ ቦታ የለንም፡፡ በግለሰብ ቤት ውስጥ በኪራይ ነው የምንኖረው::  አምስት ልጆች አሉኝ፤ አዲስ አበባ ነው የሚማሩት፤ ባለቤቴ ነፍሰጡር ናት፡፡ ሁላችንም በችግር ላይ ነን፡፡ የቤት ጉዳይን በተመለከተ የክልሉ አዲሱ አመራር ለጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት የድጋፍ ደብዳቤ ጽፎልኛል፤ ግን መልስ አልተሰጠኝም፡፡ ልጆቼ ትምህርታቸውን አቋርጠው መሔድ አይችሉም፡፡ እኔ ስራ ብጀምር እንኳን እስከዚያው የሚያርፉበት ቦታ የላቸውም:: ሌላው እኔ ከፍተኛ የጉሮሮ ህመም አለብኝ፡፡ ከአገር ውጭም ወጥቼ የታከምኩበት ጊዜም ነበር:: አሁን ግን ለህክምና እንኳን የሚሆን ገንዘብ አጥቼ  ተቸግሬያለሁ፡፡ የእኔ ምክትል የነበሩት አቶ ሠናይ በሌላ ኃላፊነት ላይ ተመድበው፣ ጥቅማ ጥቅም ተከብሮላቸው እየሠሩ ነው የሚገኙት፡፡
በአንድ ወቅት ለህክምና ከመንግስት በጀት አንድ ሚሊዮን ብር እንደተሰጠዎ ተገልፆ ነበር …
ገንዘቡ እንዲሰጠኝ መወሰኑን የሠማሁት ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ የክልሉ ፋይናንስ ውሳኔውን የሠጠው እኔ በሌለሁበት ነበር፤ ግን ገንዘቡን አልወሰድኩም፡፡

Read 6501 times