Saturday, 20 April 2019 13:48

የወር አበባ አስቀድሞ የሚቋረጥበት ምክንያት

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(10 votes)

ሴቶች በተፈጥሮ በአማካኝ በወር አንድ ጊዜ የሚያዩትን እና ልጅ ለመውለድ የሚያስችላቸውን የወር አበባ የሚያጡበት menopause እድሜ ከ45-55 አመት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ እስከ 60 አመት ድረስም ሊዘገይ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ እድያቸው ሳይደርስ ገና ከ30-40 አመት በሚደርስበት ጊዜም menopause የወር አበባ ሊቋረጥ እንደሚችል ባለሙያዎች ይመሰክራሉ፡፡ የወር አበባ ለመቋረጥ ትክክለኛው እድሜ ነው ከሚባለው በተለየ እድሜያቸው ሳይደርስ ለምን ይቋረጣል የሚለውን በዚህ እትም እናስነብባችሁዋለን፡፡ ምንጫችን Web-Med..ድረገጽ ነው፡፡
በተለያዩ የህመም አጋጣሚዎች የሚሰጡ ሕክምናዎች በምክንያትነት የሚጠቀሱበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌም ልጅ በመውለድ እድሜ ላይ ያለች ሴት ማህጸንዋ በጤና እክል ምክንያት በቀዶ ሕክምና ቢወገድ ወዲያውኑ ወደ ወር አበባ መቋረጥ menopause ይገጥማታል፡፡ ይህም በቀዶ ሕክምና ምክንያት የተከሰተ menopause ይባላል::  ሴትዋ የወር አበባዋ በዚህ መንገድ የተቋረጠ ከሆነ በእድሜያቸው የወር አበባ መቋረጥ እንደሚገጥማቸው ሴቶች አስቀድሞ menopause ሳይደርስ ለወራት ወይንም ለአመታት የሚኖረው ሂደት ወይንም ስሜት አይኖ ራትም፡፡ የወር አበባው ከተቋረጠ በሁዋላም ቢሆን በእድሜያቸው እንደተቋረጠባቸው ሴቶች ሳይሆን በመጠኑ አንዳንድ ስሜቶች ሊኖሩአት ይችላሉ፡፡
የሴትዋ ማህጸን uterus በኦፕራሲዮን በሚወገድበት ወቅት ሙሉ ለሙሉ ሳይሆን አንደኛው ሳይወጣ ከቀረ ምንም እንኩዋን የወር አበባ ማየት ባትችልም የሴትየዋ አካል ሆርሞን ማምረቱን ይቀጥላል፡፡ ይህ ሂደትም ሴትየዋ በእድሜዋ የወር አበባ ከሚቋረጥበት እስክትደርስ የሚቀጥል ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ነው፡፡
የካንሰር ሕክምና(chemotherapy)
አንዲት ሴት በካንሰር ሕመም ምክንያት የሚሰጠውን ተከታታይ ሕክምና chemotherapy  ወይም የጨረር ሕክምና በሚወሰድበት ጊዜ የወር አበባ መቋረጥ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተፈጥሮ ለእርግዝና ዝግጁ የሆነች ሴት ይህንን ህክምና በምትወስድበት ወቅት ልክ እድሜያቸው ደርሶ የወር አበባ ሊቋረጥ በሂደት ላይ እንዳሉት ሴቶች ስሜቱ ይጀምራታል፡፡ የወር አበባ መቋረጥም የካንሰር ሕክምናው መደረግ ከጀመረ ወይንም ምልክቶቹ መታየት ከጀመሩበት ከተወሰኑ ወራት በሁዋላ የወር አበባ መቋረጥ ሊከተል ይችላል፡፡
የብቃት ማነስ
ከቤተሰብ በሚወረስ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ወይንም በተፈጥሮ ምክንያት የወር አበባ ካለጊዜው የሚቋረጥበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ እድሜያቸው 40 አመት ሳይሞላ የወር አበባ የሚቋረጥባቸው ሴቶች 1 ከመቶ የሚሆኑ ሴቶች ላይ ይስተዋላል፡፡ ይህ ሁኔታ አንዳድ ጊዜ ተፈጥሮአዊ አቅምን በሚቀንሱ ሕመሞች ሊመጣ ወይንም በቀር ሊወረስ የሚችል ነው፡፡
menopause በምን መንገድ ምርመራው
ሊካሄድ ይችላል?
ምርመራው የሚካሄድበት የሆርሞን መጠን ከአንድዋ ሴት የሌላዋ የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡ ከአንዱዋ ሴት ሌላዋ ሴት ብቻም ሳይሆን በአንድዋ ሴት ብቻም ከቀን ቀን መጠኑ ከፍና ዝቅ ሊል ይችላል፡፡ ሴትየዋ ወደ ወር አበባ መቋረጥ ወቅት እየሄደች ነው ወይንም ኤደለም የሚለውን ለማወቅ የሚረዳ ውስን የሆነ የደም ምርመራ የለም፡፡ ስለዚህ ሁኔታው አስቸጋሪ ስለሚሆን የወር አበባ መቋረጥን ለማወቅ ምርመራ ከማድረግ ይልቅ የወር አበባ መዛባትን ለማስተካከል ምርመራ ማድረግ ወይንም የህክምና አገልግሎት መስጠት ይመረጣል፡፡ የወር አበባ መቋረጥ menopause ይከሰታል ወይንስ የሚለውን ለማወቅ ብቸኛው መንገድ ሌላውን ሕክምና እያደረጉ ለ12/ወራት ያህል በትእግስት መጠበቅ ብቻ ነው፡፡
Menopause የወር አበባ መቋረጥ የሚደረግለት
ሕክምና አለ?
የወር አበባ መቋረጥ ሕመም ሳይሆን ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው፡፡ ስለሆነም ምንም አይነት ሕክምና መደረግ አለበት ተብሎ አይመከርም፡፡ በእርግጥ ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች የሚታዩ የጤና መጉዋደሎች ካሉ አስፈላጊው ሕክምና ሊደረግ ይችላል፡፡
የወር አበባ መቋረጥን በሚመለከት መታወቅ ያለባቸው ነገሮች በሚል የህክምና ባለሙያዋ ዴብራ ሮዝ ዊልሰን የመከሩት ወይንም ሁሉም ሴት ሊያውቀው የሚገባው ነገር ያሉትን እናስከትል፡፡
የመጀመሪያው ሁሉም ሴቶች ያሉበትን እድሜ ምንጊዜም ማስተዋል እና መዘጋጀት እንዳለባቸው የሚጠቁም ነው፡፡ ማንኛዋም ሴት እድሜዋ ከ45-55 አመት ሲሆን የወር አበባ መቋረጥ እንደሚኖር በመገመት የሚሰሙ አንዳንድ ስሜቶችን ተፈጥሮአዊ ብሎ ማስተናገድ ይገባል፡፡
ሁለተኛው የወር አበባ ከመቋረጡ በፊት እና ሲቋረጥ ያለውን ልዩነት ለይቶ መገንዘብ ነው፡፡ ቅድመ የወር አበባ መቋረጥ ሰውት የወር አበባ መቋረጥን ለማስተናገድ የሚዘጋጅበት ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ በሰውነት ውስጥ የሚመረተው የሆርሞን መጠን እየቀነሰ በመሄድ ላይ ነው ማለት ነው፡፡ የወር አበባ መዛባት፤ ሙቀትና ላብ፤ የመሳሰሉት ስሜቶች ይታያሉ፡፡
ሶስተኛው የሆርሞን መጠን መቀነስን ምክንያት በማድረግ የሚሰሙ ስሜቶች ምን እንደሆኑ ማወቅ ነው፡፡ ወደ 75 ከመቶ የሚሆኑ ሴቶች ሙቀትና ወበቅ እንዲሁም የማላብ ስሜት አላቸው፡፡ አንዳንድ ሴቶች የጡንቻዎችና የመገናኛ አካላት ሕመም ሊሰማቸው ይችላል፡፡
በአራተኛ ደረጃ በድንገት የሚሰማ ሙቀት
በሰውነት ላይ መኖሩን ማወቅ
በመላ ሰውነት ላይ በድንገት ወበቅ ሲሰማ የሰውነት ሙቀት ልክም አብሮ ይጨምራል፡፡ ይህ ሙቀት የላይኛውን የሰውነት ክፍል ማለትም እንደፊት እና ደረት ያሉ አካባቢዎችን ከለር በማቅላት ወይንም በማበለዝ ሊለውጥ ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ መጨነቅን፤ የልብ ምትን ማፍጠን ወይንም በትክክል እንዳይመታ ማድረግ፤ የድብርት ስሜት፤ የመሳሰሉትን ሊፈጥር ይችላል፡፡ በእንደዚህ ያለው ወቅት አልኮሆል መጠጣት፤ ቡናን ማብዛት፤ ቅመም እና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦችን መመገብ፤ አካባቢው ሞቃታማ በሆነ ስፍራ መኖር የመሳሰሉትን ማስወገድ የተሸለ ስሜት እንዲኖር ይረዳል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ ክብደትን እና ሲጋራ መጤስን ማስወገድም ይመከራል፡፡
በአምስተኛ ደረጃ ማስታወስ የሚገባው የወር አበባ መቋረጥ ከአጥንትና ከልብ ሕመም ጋር የሚገናኝባቸው መንገዶች መኖራቸውን ነው፡፡ ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቀሰው ኢስትሮጂን የተባለው ንጥረ ነገር በሰውነት ውስጥ መመረቱ የሚቀንስት እድሜ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ወቅት አጥንት ጥንካሬውን የሚቀንስበት ወቅት ይሆናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የወር አበባቸው የተቋረጠ ወይንም menopause የደረሱ ሴቶች የልብ ምት ፈጠን የማለት ወይንም የመደበር ሁኔታን ሊያሳይ ይችላል፡፡ የኢስትሮጂን መቀነስ የልብን መስመሮች እንደልብ እንዳይታዘዙ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ደም በሰውነት ውስጥ ያለውን ምልልስ ሊያውክ ይችላል፡፡ ስለዚህም አመጋገብን ማስተካከል፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፤ ሲጋራ አለማጤስ፤ ክብደትን መቆጣጠር ጤንነትን ለመጠበቅ ያስችላል፡፡
ዴብራ ሮዝ ዊልሰን በስድስተኛ ደረጃ ያስቀመጡት ምክር ክብደትን የሚመለከት ነው፡፡ በሰውነት ውስጥ ሊኖር የሚገባው የሆርሞን መጠን መቀነስ በራሱ ክብደትን ሊያመጣ እንደሚችል ማሰብ ይገባል፡፡ እድሜ መጨመር በራሱም ክብደትን ሊያመጣ እንደሚችል ሳይንሱ ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህም ከላይ የተጠቀሱትን የጤና አጠባበቅ መርሆዎች መከተል ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨ ማሪ በሳምንት እስከ 150 ደቂቃ የሚደርስ መካከለኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወይንም በሳምንት /75/ደቂቃ ያህል ጠበቅ ያለ እንቅስቃሴ መለትም እንደ ሩጫ የመሳሰሉትን ማድረግ ይጠቅማል፡፡
ባጠቃላይም የወር አበባ መቋረጥ menopause ተከትለው የሚመጡ አንዳንድ ስሜቶችን ለማስተካከል ሲባል የሚሰጡ ህክምናዎች ቢኖሩም ተመራጩ ግን በተፈጥሮአዊ መንገድ ማስተካከል መሞከር ነው:: በመድሀኒት የታገዘ አኑዋኑዋርን ከመመስረት ይልቅ የአኑዋኑዋርን መንገድ በመቀየር፤ ክብደትን በመቀነስ፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ፤ የመኖሪያ አካባቢን ከሙቀት በማግለል፤ የመኝታ ክፍልን ሙቀት በመቆጣጠር፤ አለባበስን ቀለል በማድረግና ከጥጥ የተሰሩ ልብሶችን በመምረጥ…ወዘተ በmenopause ወቅት የሚከሰትን ወበቅና ሙቀት መከላከል ይቻላል፡፡

Read 12551 times