Saturday, 02 June 2012 09:03

“ጎበዝ ሴት ልጆችን በሽልማት ማትጋት የሚያስገኘውን ጥቅም እያየን ነው”

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ነኢማ በከር ዘንድሮ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በኮምቦልቻ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ አምና በኢጀግና ት/ቤት የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስዳ 99.97 ውጤት አምጥታ ነው ያለፈችው፡፡ የጐበዟ ተማሪ ውጤት በት/ቤቷ፣ በወረዳና በዞን ደረጃ ተወዳዳሪ ስላላገኘ፣ በሦስቱም ደረጃ መሸለሟን የኮምቦልቻ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ሽፈራው ገልጿል፡፡ አሁን ሁሉንም ትምህርት እየተከታተለች ያለው (ከኦሮምኛ ቋንቋ በስተቀር) በእርግሊዝኛ ነው፣ ለአካባቢውና ለት/ቤቱ ተማሪዎችና አስተማሪዎች እንግዳ፣ … ብትሆንም፣ ጉብዝናዋ ዛሬም አልተለያትም - እያበበና እየፈካ ነው፡፡ በዘንድሮ ውጤቷም፣ ከክፍሏና በት/ቤቱ ውስጥ ካሉ 461 ሴት ተማሪዎች መካከል 1ኛ መሆኗን፣ በት/ቤቱ ካሉ 1727 አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል 3ኛ ኮከብ ተማሪ መሆኗን አቶ አብርሃም በኩራት ይናገራል፡፡

አክሽን ኤድ ከሚንቀሳቀስበት ዘርፎች አንዱ  በተለይ የሴቶችና የሕፃናት ትምህርት  በመሆኑ፣ በአካባቢው እንቅስቃሴ ከጀመረበት ከስድስት ዓመት አንስቶ የሴት ተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ ለማበረታታት፣ በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ያመጡትን ሴት ተማሪዎች በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚሸልም የአክሽን ኤድ የኮምቦልቻ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ የሺጥላ ዓለሙ ተናግሯል፡፡ በዚህ ዓመትም ድርጅቱ በሚንቀሳቀስባቸው 12 ቀበሌዎች ከ1ኛ-3ኛ ለወጡ ሴት ተማሪዎች ከ69ሺ ብር በላይ ወጪ አድርጐ መሸለሙን ጠቅሶ፤ “ነኢማ ሁልጊዜ ከክፍሏ 1ኛ ስለምትወጣ ያልተሸለመችበት ጊዜ የለም፡፡ ጐበዝ ሴት ተማሪዎችን በመሸለም ማትጋት፣ ምን ጥቅም እንዳለው እሷ ጥሩ ማሳያ ናት” ብሏል፡፡ እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ በኮምቦልቻ ወረዳ አንድም መሰናዶ ት/ቤት አልነበረም፡፡ 10ኛ ክፍል ጥሩ ውጤት ያመጡ ልጆች የነበራቸው ዕድል ሁለት ነው፡፡ አንዱ፣ የቤተሰቦቻቸው የኢኮኖሚ አቅም ጥሩ ከሆነ፣ ወደ ሌላ ወረዳ ሄዶ ቤት ተከራይቶ ወይም ዘመድ ካለ እዚያ ተጠግቶ መቀጠል ነው፡፡ ሌላው ደግም ቤት መቀመጥ፡፡ ይኼ በጣም መጥፎ ነው - በተለይ ለሴት ልጅ፡፡ በአካባቢው ቡና ስላለ ገንዘብ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን ት/ቤት (በተለይ ሴት ልጅ) መላክ አይወዱም፡ “የምትማሪው ለገንዘብ አይደል! ሳትማሪም ገንዘብ ማግኘት ስለምትችይ አርፈሽ ቁጭ በይና ባል አግብተሽ ልጅ እየወለድሽ መኖር ነው…” የሚሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ አቅሙ ቢኖራቸውም ወደ ሌላ ወረዳ ልከው የሚያስተምሩት በጣም ጥቂት ወላጆች ናቸው፡፡ መሰናዶ ት/ቤት እንዳይከፈት ችግር የሆነው የክፍል እጥረት ነበር፡፡ አክሽን ኤድ ይህን ችግር እያየ ዝም ብሎ አልተቀመጠም፡፡ ከወረዳው ት/ቢሮና ከት/ቤቱ ጋር በመመካከር በ2001 ዓ.ም ከ750ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ 4 ክፍሎች ያሉት አንድ ብሎክ ሠርተው የ150 ወንበሮች ማሠሪያ ድጋፍ ስላደረገላቸው የመሰናዶ ትምህርት መጀመራቸውን አቶ አብርሃም ተናግሯል፡፡ “አራት ክፍሎች ያሉት ሌላ ተጨማሪ ብሎክም ሠርቶልናል፡፡ የሚኒ ሚድያ መሳሪያዎችም ገዝቶ አስረክቦናል” ብሏል ዳይሬክተሩ፡፡ አክሽን ኤድ በኮምቦልቻ ወረዳ በስፋት ከሚንቀሳቀስባቸው ዘርፎች አንዱ ትምህርት ነው፡፡ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ት/ቤት እንዲሠራላቸው ወይም የክፍል ጥበት ሲያጋጥማቸው ለድርጅቱ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ጥያቄውን ተቀብሎ፣ ያለውን ችግር አጥንቶ በሚችለው አቅም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የቢሊሱማ ቀበሌ ከኮምቦልቻ ከተማ 3ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ቀበሌው ቢሊሱማ 1ኛ ደረጃ የሚባል ት/ቤት ያለው ሲሆን ብዙ ተማሪዎች የሚያስተናግድ በመሆኑ ከፍተኛ የክፍል ጥበት አጋጠመው፡፡ ስለዚህ የት/ቤቱ ኮሚቴ አክሽን ኤድ ድጋፍ እንዲያደርግለት ጥያቄ አቀረበ፡፡ በዚህ መሠረት አራት ክፍሎች ያሉት የአንድ ብሎክ ማሠሪያ ድጋፍ አደረገላቸው፡፡ አቶ ጀማል ሼክ አህመድ የት/ቤቱ ኮሚቴ አባልና  የሂሳብ ሹም ናቸው፡፡ አክሽን ኤድ ነው ይህን ት/ቤት የሠራላችሁ?

አይደለም፡፡ ልጆቻችን ከ1ኛ ክፍል እስከ 4ተኛ ክፍል የሚማሩበት ት/ቤት ድሮም ነበረን፡፡ በኋላ ላይ ግን የተማሪው ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ የክፍል ጥበት አጋጠመን፡፡ ተማሪዎች በፈረቃ ነው የሚማሩት፡፡ ስለዚህ ሕዝቡን አወያይተን አክሽን ኤድ ድጋፍ እንዲያደርግልን ጠየቅን፡፡ የት/ቢሮው፣ የሕዝቡና የአክሽን ኤድ ድጋፍ ምን ያህል እንደሆነ አውቀን ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡

አዲሱን ብሎክ ማነው የሠራው?

ሕዝቡ ነው፡፡ አክሽን ኤድ አራት ክፍሎች ያሉት አንድ ብሎክ ማሠሪያ 431,524 ብር  ድጋፍ አደረገልን፡፡ ከዚያም እኛ 5 ሰዎች ያሉት ኮሚቴ መርጠን ፕሮፎርማ ሰብስበን ቅናሽ ካገኘንበት ነጋዴ ቆርቆሮ፣ ሚስማር፣ ብረት፣ በር፣ መስኮት፤ … በአጠቃላይ አስፈላጊ ነገሮች ገዛን፡፡ ሕዝቡ፣ መሬት በመቆፈርና በመደልደል፣ ሽንት ቤት በመቆፈር እንጨትና ውሃ በማቅረብ የጉልበት አስተዋጽኦ አደረገ፡፡ ኮሚቴው ጥቁር ሰሌዳ አሠርቷል፡፡ የ80 ተማሪዎች መቀመጫም እየተሠራ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ 386 ሺህ 325.44 ወጪ ሆኗል፡፡ አሁን 45,198.56 ቀሪ አለ፡፡

አቶ ኃይሌ ሰርቤሳ የቢሊሱማ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕስ መምህር ነው፡፡ “ቀደም ሲል ት/ቤቱ የሚያስተምረው ከ1-4ኛ ክፍል ነበር፡፡ አክሽን ኤድ አራት ክፍል ያለው አንድ ብሎክ ማሠሪያ ድጋፍ ስላደረገልን በዚህ ዓመት 5ኛ ክፍል ከፍተን እያስተማርን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 881 ወንዶች፣ 673 ሴቶች በአጠቃላይ 1554 ተማሪዎች አሉን፡፡ አስተማሪዎች ደግም ወንድ 21፣ ሴት 5 በአጠቃላይ 27 መምህራን አሉን፡፡ ት/ቤቱ የቦታ ጥበትና የቤተ መጻሕፍት ችግር አለበት ብሏል፡፡ የአራንብዬ ቀበሌ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ከአሁን ቀደም ሁለት ት/ቤቶች (ከ1-4 እና ከ5ኛ-8ኛ) አሉት፡፡ መንደሮቹ ያሉት በጣም ተራርቀው ስለሆነ ሕፃናት በመንደሮች መኻል ያለውን ጭቃ አቋርጠው፣ ወይም 5ኪ.ሜ ርቀት ተጉዘው መማር አልቻሉም፡፡ ስለዚህ የአካባቢው ነዋሪዎች አክሽን ኤድ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ፡፡

አክሽን ኤድም ችግራቸውን ተረድቶ እያንዳንዳቸው 4 ክፍሎች ያላቸው ሁለት ብሎኮች እንዲሠራ የገንዘብ ድጋፍ አደረገላቸው፡፡ ነዋሪዎቹም ኮሚቴ መርጠው፣ ቁሳቁስ ገዝተው፣ የጉልበት ድጋፍ አድርገው ት/ቤቱን አሠሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት በት/ቤቱ ከ400 በላይ (አብዛኞቹ ሴቶች) ሕፃናት እየተማሩ ነው፡፡

በለገሃማ ቀበሌ የሚኖሩ 25 ድሃ ሴቶች በ1999 ዓ.ም ተደራጅተው አክሽን ኤድ እንዲያቋቁማቸው ጠየቁ፡፡ ድርጅቱ ጥያቄያቸውን ቢቀበልም፣ ዝም ብሎ ገንዘብ አልሰጣቸውም፡፡ ድጋፍ ቢያገኙ ምን እንደሚሠሩበት ጠየቃቸው፡፡ በተለያየ ንግድ እንደሚሠማሩበት ገለጹ፡፡ ይሁን እንጂ ከተለምዷዊ አሠራር በስተቀር ስለ ዘመናዊ የንግድ አሠራር ልምድ የላቸውም፡፡ ስለዚህ አክሽን ኤድ ኮምቦልቻ ከተማ እንዲመጡ አድርጐ አበል ከፍሎ ለአንድ ሳምንት ስለ ዘመናዊ ንግድ አሠራር፣ ስለ ቁጠባ፣ … አሠለጠናቸው፡፡

ሴቶቹ ከ500 ብር በስተቀር ምንም ገንዘብ አልነበራቸውም፡፡ ይሁን እንጂ ለአበል ከተከፈላቸው ገንዘብ ላይ ቆጥበው፣ በ3000 ብር ሐረር በሚገኘው የኦሮሚያ ቁጠባ ባንክ ሂሳብ ከፈቱ፡፡ አክሽን ኤድም፣ የመነሻ ገንዘብ (Seed money) 10ሺህ ብር ጨምሮላቸው፣ በ13ሺህ ብር ወደ ሥራ መግባታቸውን የማኅበሩ ሊቀመንበር ወ/ሮ ኤኒ መሐመድ ተናግረዋል፡፡

ያ ማኅበር ታዲያ በአሁኑ ወቅት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ከሰረ ወይስ አተረፈ? የማኅበሩ አባላትስ ተለወጡ? ወይስ …? የማኅበሩ አመራሮች ወ/ሮ ኤኒ መሐመድና ወ/ሮ መሊካ ዑመር ከሌሎች አባላት ጋር ይናገራሉ፡፡

ወ/ሮ ኤኒ መሐመድ ስለ አሠራራቸው ሲገልጹ፣ ከሊቀ መንበሯ ጀምሮ እስከ ተራ አባሏ ድረስ እኩል ተበደርና ያዋጣናል ባልነው ንግድ ተሰማራን፡፡ ከአባሎቻችን መካከል፣ ለውዝ፣ ፍየል፣ ቡና፣ … የሚነግዱ አሉ፡፡ በትርፉ ተጠቅመው ወለድም ይከፍላሉ፡፡ ተጠቅመናል፣ ተለውጠናል፡፡

ጥቅማችሁንና ለውጣችሁን እንዴት ነው የምትገልፁት?

ቤት የሌላቸው ባለቤት ሆነዋል፡፡ የቁጠባን ጥቅም ባለማወቅ የተበደርነውን በከንቱ እናባክን ነበር፡፡ አሁን ግን የቁጠባን ጥቅም ስላወቅን እንቆጥባለን፡፡ ምንም ገንዘብ ስላልነበራቸው መታከም የማይችሉ ሰዎች ከብድር ባገኙት ገቢ ታክመው ሕይወት ማትረፍ ችለዋል፡፡ በዚህ ዓይነት ሕይወታችን እየተለወጠ ነው፡፡

የቀድሞው አኗኗራችሁ ምን ይመስላል?

ድሮ ሲቸግረን የምንበደረው ከባለሀብት ነበር፡፡ ከእርሻ ምርት የምናገኘውን ገቢ ዕዳችንን እንከፍልበት ነበር፡፡ ቁጠባ ስለማናውቅ የተበደርነውንም ገንዘብ ቁም ነገር ላይ አናውልም ነበር፡፡  አክሽን ኤድ ካሠለጠነን በኋላ ግን ንግድ አወቅን፣ ቁጠባም ተማርን፡፡ መበደር ስንፈልግ ደግሞ ከማኅበራችን እንበደራለን፡፡ በዚህ መልኩ ብዙ ጥቅም አግኝተናል፡፡

ማኅበራችሁ በጐጂ ባህላዊ ድርጊቶች ላይ ይመክራል?

አዎ እንመካከራለን፡፡ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋ፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻ የመሳሰሉ ጐጂ ባህሎች ነበሩ፡፡ ሥልጠና ካገኘን በኋላ ንቃተ ኅሊናችን ጨምሯል፡፡ በማኅበር መደራጀታችንም በጣም ጠቅሞናል፤ መብታችንን እንድናውቅ ረድቶናል፡፡ ለምሳሌ በጋብቻ ላይ ጋብቻ የፈፀመ ሰው፣ አዲሷን ሚስት በዕለቱ እንዲፈታ አድርገናል፡፡ ጐጂ ባህላዊ ድርጊቶች በአሁኑ ወቅት በዚህ አካባቢ ቆመዋል ማለት ይቻላል፡፡ ወ/ሮ መሊካ በበኩላቸው ስለ ማኅበሩ አባላት ተጠቃሚነት ሲገልፅ፤ አንድ አባላችን 700 ብር ተበድራ ሽንኩርት ገዝታ 2040 ብር ሸጠች፡፡ ከዚያም አንድ ላም ገዝታ ላሟም ወልዳላታለች፡፡ ኑሮዋ በደንብ ተሻሽሏል፡፡ ምንም ገንዘብ ያልነበራት ሌላዋ አባላችን ደግሞ ከኛ ተበድራ ባገኘችው ትርፍ ልጇን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወስዳ አሳክማለች፡፡ ቤትም አልነበራትም፤ አሁን የቤት ባለቤት ሆናለች፡፡ ሌላዋ አባላችን ደግሞ 500 ብር ተበድራ፣ ቡና ትነግድ ነበር፡፡ አሁን 40ሺህ ብር ያህል ካፒታል አላት፡፡ ከብቶችም እያረባች ነው፡፡

አሁን ምን ያህል አባላት አላችሁ? ካፒታላችሁስ ስንት ደርሷል?

አባሎቻችን 75 ደርሰዋል፡፡ ካፒታላችን ደግሞ ባለፈው ዓመት 110ሺህ ብር ነበር፡፡ ዘንድሮ በቅርቡ ኦዲተር መጥቶ ሂሳብ አድርጐ ነበር፡፡ ውጤቱን አልሰማንም፡፡ (አቶ የሺጥላ 170ሺህ ብር ያህል መሆኑን ጠቁመዋል)

የወደፊት እቅዳችሁ ምንድነው?

ብዙ ዕቅድ ነበረን፡፡ ለገሃደ በቡና የታወቀች ናት፡፡ ቡና እየገዛን ወደ አዲስ አበባ የመጫን፣ ከዚያ ደግሞ ስንዴ ወደ ለሃገማ የማምጣት ዕቅድ ነበረን፡፡ ነገር ግን ትልቅ እንቅፋት የሆነብን ነገር የመንገድ ችግር ነው፡፡ ቀበሌያችን ዙሪያውን በተራሮች የተከበበ ነው፡፡ ይኼው እንደምታዩት ገደል፣ ቀጥ ያለ ዳገትና ቁልቁለት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ገብቶ የሚጭንልን መኪና የለም፡፡ ጥርጊያ መንገድ ቢሠራልን በጣም እንለወጥ ነበር አሉ ወ/ሮ መሊካ በቁጭት፡፡  የከተማው አስተዳደርም አክሽን ኤድ ከተለያዩ ዘርፍ (በትምህርት፣ በውሃ፣ በሴቶች፣ …) ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት መንግሥት ባወጣው ዕቅድና ስትራቴጂ መሠረት፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ከምሥጋና ጋር ተቀብሎታል፡፡

የወረዳው ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጋሻው ካሣሁን፤ አክሽን ኤድ መንግሥትን ወክሎ ሳይሆን መንግሥት  በአሁኑ ወቅት ማሟላት ያልቻላቸውን የሕብረተሰቡን ጥያቄዎች በማሟላት ረገድ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክሽን ኤድ በራሱ ዕቅድ ሳይሆን መንግሥት በዘረጋው የአምስት ዓመት የትራንፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት በተለይ ከወረዳው ራቅ ያሉትን ቆላማ ቀበሌዎች በመድረስ በትምህርት፣ በውሃ፣ በሴቶችና በሕፃናት ዙሪያ የሚጫወተው ሚና ቀላል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

 

 

Read 19997 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 11:27