Saturday, 13 April 2019 13:43

ያሬዳዊው ሥልጣኔ ክፍል- ፲፯ የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(0 votes)


                ‹‹የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት›› የሚባለው ያሬዳዊውን ሥልጣኔ የማዘመን ፕሮጀክት ሲሆን፣ ይሄም ጥረት የተጀመረው በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ግልፅ እንዳደረኩት፣ እኔ የኢትዮጵያን የዘመናዊነት ሙከራዎች የምመለከተው ከአስተዳደርና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎች አሊያም ከፖለቲካ አንፃር ሳይሆን የአውሮፓ ህሊና ከነባሩ የሀገራችን ባህል (የተአምራዊነቱና የብህትውናው ባህል) ጋር ከነበረው መስተጋብር አንፃር ነው፡፡
በዚህም መነፅር በክፍል-15 ፅሁፌ ላይ፣ የአፄ ምኒሊክን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ከቴክኖሎጂ ፍልስፍና አንፃር በመመልከት፣ የተአምራዊነቱና የብህትውናው ባህል ለንጉሱ የዘመናዊነት ፕሮጀክት እንዴት እንቅፋት እንደሆነባቸው አይተናል፡፡ በዛሬው ፅሁፌ ደግሞ፣ በተመሳሳይ መነፅር የአፄ ቴዎድሮስን የዘመናዊነት ፕሮጀክት እንመለከታለን፡፡
አፄ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጎልተው እንዲታዩ የሚያደርጋቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለማምጣት በነበራቸው ቁርጠኝነትና ስኬት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ፣ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ መዘመን አለበት›› በሚል የህዳሴ (የትንሳኤ) ፕሮጀክት የለኮሱ መሪ በመሆናቸው ነው፡፡
ባለፈው ጊዜ፣ የአፄ ምኒሊክን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ስናነሳ፣ ቴክኖሎጂ ከላይ ከላይ ስናየው እንደሚመስለን የቁስ አካል ስብስብ ሳይሆን የተሰራበትን ሀገር ባህልና ህሊና ተሸካሚ እንደሆነ፣ ሆኖም ግን አፄ ምኒሊክ ቴክኖሎጂን የቁስ አካል ስብስብ ብቻ አድርገው በመመልከታቸው፣ የአውሮፓን ህሊና (ቴክኖሎጂ) በብዛት ወደ ሀገር ቤት በማስገባት፣በኢትዮጵያውያን የመንፈስ (የተአምራዊነትና የብህትውና) መንገድ ላይ እንዳስቀመጡት ተመልክተናል፡፡ ይሄም መንገድ የባህል ቅራኔን በመፍጠር የንጉሱ ዕቅድ በርካታ መሰናክሎች እንዲገጥሙት አድርጓል፡፡
የአፄ ምኒሊክ የዘመናዊነት ፕሮጀክት በሀገር ውስጥ ከፈጠረው የባህል ቅራኔ አንፃር ካየነው፣ የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት አካሄድ በጣም የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ የአፄ ቴዎድሮስ ፕሮጀክት ቴክኖሎጂ የማምረት ሂደቱን በሙሉ በሀገር ውስጥ እንዲከናወን ነው ያደረጉት፡፡
በዚህም የተነሳ፣ የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ከአፄ ምኒሊክ ፕሮጀክት በሁለት መሰረታዊ ነገሮች የተለየ ነው፡፡ የመጀመሪያው፣ ምንም እንኳ አፄ ምኒሊክ ያለቀለትን ቴክኖሎጂ ከአውሮፓ በማስመጣት ፕሮጀክታቸውን ተግባራዊ ያደረጉት ቢሆንም፣ አፄ ቴዎድሮስ ግን ብረት ከማቅለጥ ጀምሮ ያሉትን ሂደቶች በሙሉ በሀገር ውስጥ እንዲከናወን ማድረጋቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ ንጉሱ ጎን ለጎን ቴክኖሎጂ የማምረት ቴክኒካዊ ሂደቱን ለተማሪዎች ማስተማርን ዓላማ አድርገው ማከናወናቸው ነው፡፡ ይሄንንም ጋፋት ላይ አድርገውታል፡፡
እዚህ ላይ አንድ ማስታወስ ያለብን ነገር፣ አፄ ቴዎድሮስ ያንን ያህል የሚንገበገቡለት የቴክኒክ ዕውቀት (ብረት ማቅለጥ፣ የብረት ቁሳቁሶችንና መርከቦችን መስራት፣ ተደራራቢ ፎቆችን መገንባት) በጥንት አክሱማውያን ዘንድ እጅግ የዳበረና የተከበረ ሙያ እንደነበረ ነው፡፡ ይህ እውቀትና ሙያ የብህትውና አስተሳሰብ መስፋፋትን ተከትሎ ተንቋል፣ በስተመጨረሻም ተቋርጧል፡፡
ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት በ17ኛው ክ/ዘ ላይ ይሄንን ሙያን የማጥላላት ብህትውናዊ ስነልቦናን ክፉኛ ተችተው ፅፈዋል፡፡ ይሄንን ፍልስፍናዊ ትችት በኋላ ላይ አፄ ቴዎድሮስ የፖለቲካ መልክ ሰጥተውታል፡፡ እናም በዘመናዊነት ፕሮጀክታቸው ውስጥ አፄ ቴዎድሮስ ያደረጉት ነገር የተቋረጠውን የቴክኒክ ሙያ ዳግም እንዲያንሰራራ ማድረግ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን፣ አፄ ቴዎድሮስ ጋፋት ላይ ለከፈቱት የቴክኒክና ሙያ ት/ቤት ሰልጣኞችን ሲመለምሉ የነበረው በባርነት ከተሸጡና ከዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች (ገባሮች) መሆኑ በወቅቱ ገዥ ስለነበረው የብህትውና ባህል ሁለት ነገሮችን ያመላክተናል፡፡
የመጀመሪያው፣ ሙያን ማጥላላት በብህትውና አስተሳሰብ ለተያዙት ለመሳፍንቱና ለመኳንቱ እንደ ክብር ሲቆጠር እንደነበረ ነው፡፡ ይሄንን ማስረጃ ደግሞ በ18ኛው ክ/ዘ ከተፃፈው የወልደ ህይወት ሐተታ ምዕራፍ 18 ላይም እናገኘዋለን፡፡ ወልደ ህይወት እንደዚህ ይላል፤ ‹‹የእጅን ሙያ ለድሆችና ለሰራተኞች፣ ለአንጥረኞችና ለአናፂዎች፣ እንዲሁም ለገባር ልጆች እንጂ ለታላላቆችና ለከበርቴ ልጆች አይገባም አትበል፡፡››
ለዚህም ነው ንጉሱ የሙያ ተማሪዎችን ከመሳፍንቱና ከመኳንቱ አካባቢ ለማግኘት የተቸገሩት፡፡ ይሄም የብህትውና አስተሳሰብ ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን በተቆጣጠሩት በላይኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የበለጠ የሰረፀ እንደነበረ ያመላክተናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ አፄ ቴዎድሮስ በሀገራችን በጣም የቆየና ጥንታዊ ሥርዓተ ትምህርት መኖሩን እያወቁ፣ በጎን ሌላ አውሮፓዊ ት/ቤት መክፈታቸው፣ ጥንታዊው የሀገራችን ሥርዓተ ትምህርት ከእሳቸው ‹‹የዘመናዊነት ፕሮጀክት ጋር ሊጣጣም አይችልም›› የሚል መደምደሚያ ላይ መድረሳቸውን ያሳያል፡፡
ይሄ ሳያንስ፣ በጥንታዊው የሀገራችን ሥርዓተ ትምህርት የተነሳ ራሳቸውን የሊቃውንት ሀገር እያሉ የሚጠሩ መምህራን በበዙበት ሀገር ላይ ንጉሱ ለእንግሊዟ ንግስት ቪክቶሪያ ‹‹እኛ እውሮችና ደንቆሮዎች ነን፣ ጥበበኛ ልከው አይናችንን ያብሩልን›› እያሉ የተማፅኖ ደብዳቤ ማዥጎድጎዳቸው (ባህሩ 2003፡ 40) እና በዚህም ለራሳችን የነበረንን የተጋነነና የተኮፈሰ ምስል ማፈራረሳቸው፣ በኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ውስጥ ጥንታዊው ትምህርት ያለው ድርሻ ምንም እንደሆነ ገና ከመጀመሪያው ፖለቲካችን አቋም መውሰዱን ያሳየናል፡፡
ከአፄ ቴዎድሮስ በኋላ የመጡት ነገስታትና መሪዎችም ይሄንን አስተሳሰብ ገፍተውበት ታይተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ፣ በዘመናዊነት ፕሮጀክቶቻችን ውስጥ ሁሉ ጥንታዊው የሀገራችን ሥርዓተ ትምህርት በነገስታቱና በመሪዎች የመገፋት ዕጣ ፋንታ ገጥሞታል፡፡
በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች፣ የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ለረጅም ዘመናት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የባህል የበላይነትን በመያዝ ተንሰራፍቶ የነበረውን የብህትውና አስተሳሰብ የሚቀናቀን ሆኖ ታይቷል፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ንጉሱ ‹‹የብህትውናው አስተሳሰብ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የባህል የበላይነቱን ይዞ፣ የዘመናዊነት ፕሮጀክትን ማስፈፀም አይቻልም›› የሚል መደምደሚያ ላይ የደረሱ ይመስላሉ፡፡ ለዚህ ድምዳሜም ሁለት ማሳያዎች አሉ፡፡
የመጀመሪያው፣ የአብነት ት/ቤቶችን የሚገዳደሩ ዓለማዊ ት/ቤቶች ከገዳማቱ ውጭ ማቋቋማቸው ነው፡፡ ይሄም የገዳማቱን የባህል ማዕከልነትና ሥልጣን የሸረሸረ እርምጃ ነበር፡፡ ከአፄ ቴዎድሮስ በኋላ የመጡ ነገስታትም ይሄንን አካሄድ ይበልጥ ገፍተውበታል፡፡ አውሮፓውያን፣ በ13ኛው ክ/ዘ ዩኒቨርሲቲዎችን የከፈቱት የገዳማቱን ት/ቤቶች በማስፋፋትና በማጠናከር ቢሆንም፣ ይሄ ነገር ግን በእኛ ሀገር ሊደገም አልቻለም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ ሰፋፊ የመሬት ይዞታዎችን ከገዳማቱ መውረሳቸው ነው፡፡ ‹‹ይሄም የሚያሳየው ንጉሱ፣ ሃይማኖት በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ሚና መጠየቅ መጀመራቸውንና ተፅዕኖውም እንዲቀንስ ፍላጎት እንደነበራቸው ነው›› ይላሉ ፕ/ር አንድርያስ እሸቴ (2002)፡፡
ከዚህ ሁሉ ነገር ሁለት ማጠቃለያዎችን ማውጣት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው፣ የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት በሀገሪቱ ከተንሰራፋው የብህትውና ባህል ጋር በተቃርኖ የቆመ መሆኑን ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ አፄ ቴዎድሮስ ስለ ዘመናዊነት የነበራቸው አመለካከትና ፕሮጀክቱንም ለማስፈፀም የተከተሉት መንገድ፣ እንዲሁም ‹‹ዘመናዊነት ከነባሩ ትምህርት ጋር በተቃርኖ የሚቆም ነው›› የሚለው አመለካከታቸው ከእሳቸው በኋላ የመጡ ነገስታትና መሪዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 993 times