Saturday, 13 April 2019 13:29

ቃለ ምልልስ “አሁን የምሰራው ተተኪ ትውልድን መገንባት ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)


                    ተወልዶ ያደገው መሀል አዲስ አበባ ቅድስተ ማሪያም አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአፄ ካሌብና ሱሉልታ ወረዳ ጫንጮ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የተማረ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒልክ ተከታትሏል፡፡ ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በጂኦግራፊ የትምህርት ዘርፍ ዲፕሎማውን ያገኘ ሲሆን ከአለማያ ዩኒቨርሲቲ በዚሁ ዘርፍ ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡ ከዚያም በትምህርት አስተዳደር ማስተርሱን አግኝቷል - የቀድሞው ጋዜጠኛ ክፍለገብርኤል ወልደተንሳይ፡፡ ጋዜጠኛው በጅግጅጋ ትምህርት ቤት ከፍቶ ፊቱን ወደ ትምህርት ኢንቨስትመንት ካዞረ ከ17 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ባለፈው ሳምንት ለሥራ ወደ ሶማሌ ክልል ተጉዛ የነበረችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ዘመናዊ ት/ቤቱን ጎብኝታ ከቀድሞው የ”ጦማር” ጋዜጣ ምክትል
አዘጋጅ ክፍለገብርኤል ወልደተንሳይ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡                እንዴት ነበር ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ የገባኸው?
ጦማር ጋዜጣ ላይ መሥራት የጀመርኩት ለጋዜጠኝነት በነበረኝ ጥልቅ ፍቅር ነው:: በቆይታዬ ለማህበረሰቡ ትክክለኛ መረጃ በማድረስ፣ ወገንተኝነቴን ለማህበረሰቡ አድርጌ፣ ኃላፊነቴን ተወጥቼአለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት ደረጃም ደርሻለሁ፡፡  
የሚዲያ ነፃነት በእናንተ ጊዜ የተሻለ ነበር  ይባላል?
የሚዲያ ነፃነት የሚባለው ምኑ መሰለሽ፣ ብዙ ጋዜጦችና መፅሄቶች ገበያ ላይ ይውሉ ነበር:: ያ ማለት ግን መረጃ እንደ ልብ ይገኛል ማለት አይደለም፡፡ በወቅቱ ኢንተርኔትም ፌስ ቡክም ፍንጭ በመስጠት ደረጃ እንኳን እንደ አሁኑ አያግዝሽም፡፡ ኢንተርኔት አልነበረም:: በዚያ ላይ አንባቢው የፊት ገፅ አንባቢ ነበር፤ በአብዛኛው የአምድ አንባቢ አልነበረም፡፡ ይሄ ማለት ተሟሙተሽ ተጋግጠሽ፣ ትኩስ ዜና ፊት ለፊት ገፅ ላይ ማውጣት ይጠበቅብሻል፡፡ በዚያ ላይ ያኔም ሥርዓቱን የመጥላት ነገር ስለነበር ደፈር ብለሽ መንግስትንም መኮነን አለብሽ:: ይሄ ማለት ጋዜጦች በአንባቢው ፍላጎትና ቅኝት የመጎተትና የመመራት አዝማሚያም ነበረባቸው፡፡
ስለዚህ ሚዲያውን የሚመራው ባለሙያው ሳይሆን ህዝቡ ነበር ማለት ነው?
አዎ! ለምን? ህዝቡ ስሜታዊ አንባቢ ነበር፤ ከተወሰኑት ጋዜጦች በስተቀር አብዛኛዎቹ የህዝቡን የልብ ትርታ ማለትም ፍላጎት ተንተርሰው የሚሰሩ ነበሩ፡፡ ፅንፍ ይዘው የወጡ ጋዜጦችም ነበሩ፡፡ ይገርምሻል በሳል፣ ምክንያታዊና ለሃገር የሚበጁ ፅሁፎች በጋዜጦች አምዶች ላይ እያሉ፣ ህዝቡ ተረጋግቶ ያንን ማንበብ አይፈልግም ነበር፡፡ ይህም የገበያውን ሁኔታ ይወስነው ነበር፡፡ ለምሳሌ የህዝቡን ፍላጎት ተንተርሰው ሴንሴሽናል አድርገው ዜና በመስራት ለገበያ የሚያቀርቡ ጋዜጦች እስከ 30ሺህ ኮፒ ሲሸጡ፣ የበሰለ ሀሳብ ለልሂቃኑ ክፍል ፅፈው የሚያስነብቡ ጋዜጦች 3ሺ ኮፒ እንኳን አይሸጡም ነበር፡፡ አሁን ማህበራዊ ሚዲያው የተሟላም ባይሆን በየሰዓቱ መረጃዎች  ስለሚያወጣ፣ ህዝቡ የአምድና የጥልቅ ሀሳብ አንባቢ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የሆነ ሆኖ አሁንም ጥልቅና ረጅም ሀሳብ አንባቢ ገና አላበዛንም:: መፅሀፍት ይፃፋሉ፤ ከ3 ሺህ ኮፒ በላይ አይታተሙም፡፡ ይሄ ወደ ትምህርት ቤትም ሲመጣ፣ ንባብ ላይ ገና መስራት የሚገባን የቤት ስራ እንዳለ ያሳያል፡፡ ተማሪዎች ላይ አጫጭር ነገርን የማየት እንጂ ማጣቀሻ መፅሐፍትን የማገላበጥ ልምድና ፍላጎት ብዙ አላይም፡፡ ያው ትምህርት ላይ ስለተሰማራሁ አውቀዋለሁ፡፡
ጋዜጠኝነት በቀላሉ የሚላቀቁት ሙያ አይደለም ይባላል፡፡ እንዴት ከሙያው በቀላሉ  ወጣህ?
እኔ በእርግጥ አሁንም ከሙያው የወጣሁ አይመስለኝም፤ ምክንያቱም ጋዜጠኝነትም የማስተማር ስራ ነው፡፡ አሁንም እየሰራሁ ያለሁት የማስተማር ስራ ነው፡፡ ልዩነቱ የማስተምራቸው ሰዎች እድሜ ነው፡፡ ያኔ አዋቂዎችን በህይወታቸው በአገራቸውና በዓለም ላይ ስለሚከናወነው አጠቃላይ ጉዳይ መረጃ በመስጠት ማንቃትና ማሳወቅ፣ ያው ማስተማር ነው፡፡ አሁን የምሰራው ተተኪ ትውልድን መገንባት ነው፡፡ ስለዚህ ሁለቱም አገር የመገንባት፣ ትውልድና ማህበረሰብን የመገንባት ስራዎች ናቸው፡፡ የተነጣጠሉ የሚመስሉ ግን ተያያዥነት ያላቸው ሙያዎች ናቸው ብዬ ነው ይበልጥ ወደ ተማርኩበት መስክ የገባሁት፡፡
እዚህ ጅግጅጋ ከተማ በ6ሺህ ካ.ሜ ቦታ ላይ “The Spark” የተሰኘ ከ1ኛ- 12ኛ ክፍል የሚያስተምር  ትምህርት ቤት ከፍተሃል፡፡ እንዴት ከአዲስ አበባ እዚህ ድረስ መጥተህ ት/ቤቱን  ልትከፍት ቻልክ?
እርግጥ ነው በጋዜጠኝነቱም እየሰራሁ በነበረበት ወቅት በትምህርት ዓለም ተሰማርቼ የማስተማርና ትውልድ የመገንባት ህልም በውስጤ ነበረ፡፡ ይህንን ህልሜን እውን ለማድረግ ለት/ቤት የሚሆን ግቢ መፈለግ ጀመርኩና አንድ ቦታ ተጠቁሜ፣ መገናኛ  እርሻ ምርምር አካባቢ ሄድኩኝ፡፡ እዚያ አንድ ሰው አገኘሁ፡፡ ይህን ሰው በአጋጣሚ አሶሳ ነበር የማውቀው፡፡ ጦማር በምንሰራበት ጊዜ  የስራ ባልደረባዬ ብርሃኑ ሞረዳ ስለ ቤኒሻንጉል አንድ ዜና ሰርቶ፣ ባለስልጣናትን አጋልጦ ነበር:: የቤኒሻንጉል ባለስልጣናት መጥተው ከአዲስ አበባ አፍነው አሶሳ ወስደው አሰሩት፡፡ አየሽ፤ ያኔ የክልል ባለስልጣናት ሳይቀሩ ጋዜጠኛ እያፈኑ ወስደው የሚያስሩበት ጉልበት ነበራቸው፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ ባልደረባዬ  ምግብ የሚያቀብለው፣ የሚጠይቀው ማንም ሰው ስላልነበር፣ ቢያንስ ምግብ እንኳን ላቀብለው ብዬ ስሄድ፣ እኔንም ለአራትና አምስት ሰዓታት ያህል አስረው ለቀቁኝ፡፡ ይሄም በጦማር ላይ ወጣና መነጋገሪያ ሆኖ፣ ከተማው ውስጥ መወራት ጀመረ፡፡ ከዚያ አንድ ሰው ቀረብ አለኝና፤ “ለከተማው አዲስ ነህ?” አለኝ “አዎ” አልኩት፡፡ እንደዚህ እንደዚህ ነው የምትሰራው ሲለኝ መለስኩለት፡፡ “እንግዲያውስ አሁን ከተማው ላይ ከሚወራው አንፃር፣ አንድ ነገር ሊያደርጉህ ስለሚችሉ የምታድርበትን ቦታ ቀይር” ብሎ ሌላ አልጋ ያዘልኝ፡፡ ከዚህ ሰው ጋር በዚያ አጋጣሚ ተዋውቀን ወዳጆች ሆንን፡፡ ያ ሁሉ አልፎ ቤት ኪራይ ፍለጋ አዲስ አበባ፣ እርሻ ምርምር አካባቢ ስሄድ፣ እግዚአሔርአብ አጠገብ አገኘሁትና ለምን እንደመጣሁ ጠየቀኝ፡፡ ሀሳቤን ነገርኩት፡፡ “እዚህ ከምትሰራ ጅግጅጋ በጣም ክፍተት ስላለ እዚያ ብትሰራ ጥሩ ነው” ብሎ መከረኝ፡፡ ጊዜ ሳላጠፋ ከባለቤቴ ጋር ጅግጅጋ ገብቼ፣ ጥናቶችን ሳደርግና መጠይቆችን ስበትን፣ በእርግጥም ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን ተረዳሁ፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት በ1995 ዓ.ም፣ ከ17 ዓመት በፊት ነው “The spark”ን የከፈትኩት፤ ስያሜው የብርሃን ፍንጣቂ ማለት ነው፡፡
ት/ቤትህ እጅግ ትልቅና በመጻህፍት የተደራጀ፣ በርካታ ኮምፒዩተሮችን የያዘ፣ ኢ-ላይብረሪ አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ  ቤተ መጻህፍት አለው፡፡ ክፍሎቹም ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የገንዘቡ ምንጭ ምን ነበር?
በጣም ትንሽ በሆነ ገንዘብ ነው የጀመርነው፤ ትልቅና ሰፊ የሆነ ፍላጎትና ራዕይ ግን ነበረን፡፡ አገሩንና ስራውን እየለመድን ስንሄድ፣ ለልማት ባንክ ድሬደዋ ቅርንጫፍ ሶስትና አራት ወረቀት ፕሮፖዛል አስገባን፡፡ ህልማችንንና አቅማችንን  በማየት፣ የቅርንጫፉ ስራ አስኪያጅ  ብድሩን ፈቀዱልን፡፡ በዚህ ብድር (2 ሚ. ብር ነበር) ይሄን የምታይውን ኮምፓውንድ ዘመናዊ ቤተ መጻህፍት፣ በርካታ ኮምፒዩተርና ምቹ የመማሪያ ክፍሎችና ወንበሮች አሟላን:: ግቢውን በማስዋብም ደረጃ ብዙ ስራ ሰርተናል፡፡ ቦታውም የኪራይ ሳይሆን የገዛነው የራሳችን ንብረት ነው፤ጥሩ ስራ እየሰራን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድሩን ሲፈቅድልንም አንድም በከተማው ያለውን ክፍተት በማየት፣ ሁለትም እዚሁ ት/ቤታችን ድረስ መጥተው ጅማሮውን በማየት ነበር፡፡ አሁን በዚህ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፤ ተጨማሪ ማስፋፊያዎች ለማድረግ እቅድ አለን፡፡ ብድራችንንም ከፍለን ጨርሰናል፡፡ ከዚህ ውጭ የኬጂ ት/ቤት እዚሁ ከተማ ውስጥ ሌላ ቦታ አለን፡፡ የኬጂውም ይሄም የመቀበል አቅማቸውን  ለማሳደግ ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡
በት/ቤታችሁ ውስጥ በአጠቃላይ ምን ያህል ተማሪዎች አሉ? መምህራንስ? እስካሁን በ10ኛና በ12ኛ ክፍል ለምን ያህል ጊዜ አስፈትናችኋል? የተማሪዎቻችሁ ውጤትስ እንዴት ነው?
በሁለቱም ግቢዎች ከ1200 በላይ ተማሪዎች አሉን፤ 63 መምህራንና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ያሉን ሲሆን ለነዚህ ሰራተኞች 372 ሺህ 340 ብር ደሞዝ እንከፍላለን፡፡ እነዚህ ሰራተኞች ደግሞ ለመንግስት 107ሺ ብር የስራ ግብር ይገብራሉ:: 63 ሰራተኞች በነፍስ ወከፍ በአማካኝ አራት ቤተሰብ ቢኖራቸው፣ የትየለሌ ነው ቁጥሩ፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፤ ከት/ቤታችን ተማሪዎችን በኮንትራት የሚወስዱ ወደ 300 የሚጠጉ ባጃጆች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ተቋሙ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለበርካታ ሰው እንጀራ የከፈተ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እስካሁን ከ10ኛ ክፍል 5 ጊዜ፣ ከ12ኛ ክፍል ሁለት ጊዜ አስፈትነናል፡፡ 12ኛ ክፍል ከተፈተኑት የመጀመሪያው 580 ነጥብ በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበና ት/ቤቱን ያስጠራ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ላይ አንዱ ተማሪያችን 576 ነጥብ በማምጣት አኩርቶናል::
እስካሁን ከት/ቤታችን ተፈትነው ዩኒቨርሲቲ ከገቡት 40 ተማሪዎች ውስጥ 25ቱ የህክምና ትምህርት በዶክትሬት ደረጃ እየተከታተሉ ሲሆን ሶስቱ በኮምፒዩተር ሳይንስ፣ ቀሪዎቹም በተለያዩ መስኮች እያጠኑ ይገኛሉ፡፡ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የምንገኘው፤ በስራችን በውጤታችን ደስተኞች ነን፡፡
አንተም ሆንክ ቤተሰብህ እዚህ ለረዥም ዓመታት ቆይታችኋል፤ ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ የመመለስ ሃሳብ አላችሁ?
እኛ አላማችን በዚህ ከተማ አሁን ከምንሰራው የበለጠ ሰርተን፣ ትውልድን ገንብተን፣ ክልሉን በበጎ ማስጠራት ነው፡፡ ተመልሰን አዲስ አበባ የመኖሩን ሀሳብ አንስተነውም አስበነውም አናውቅም፡፡ አሁን ከዚህ ክልል የተማሩ፣ የበቁ የነቁ ልጆችን እያፈራን፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ነው ማሻገር የምንፈልገው፡፡ በዚህ ክልል የተሻሉ ልጆችን በማፍራት ደረጃ የነበረውን ክፍተት በመሙላት፣ ከባለቤቴ ጋር እየሰራሁ ነው:: ከባለቤቴ ከወ/ሮ ኤልሳቤት ጋር እቅዳችን፣ እዚሁ ጠንክረን መስራት ብቻ ነው፡፡


Read 656 times