Saturday, 13 April 2019 12:24

“ያዋከቡት ነገር…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 --”አይ ፖለቲካ! እንደው እኮ አፋችሁን ሞልታችሁ እንዲህ ስትናገሩ ግርም ይለኛል፡፡ ስለ የትኛው ፖለቲካ ነው የምታወራው! ንገረኛ… እዚህ ሀገር ፖለቲካ የሚባል ነገር አለ እንዴ! ፖለቲካ ፓርቲ ነን የሚሉ ጉዶች በየቀበሌው ስለተፈለፈሉ፣ ፖለቲካ አለ ማለት ነው እንዴ!---”
                 
               እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው… ነገርዬው ሁሉ ደንገርገር አላለባችሁም! የምር እኮ…የሆነ ግራ የተጋባ ነገር ነው፡፡ ማን ምን እንደሆነ፣ ማን ምን እንደሚያስብ፣ ማን ሲፋቅ ምን እንደሚሆን፣ ማን የትኛውን ገመድ እንደሚጎትት… ግራ የተጋባንበት ዘመን ላይ ነን፡፡
ስሙኝማ… ጨዋታም አይደል … በኮንስፒሬሲ ቲየሪ ወይም የሴራ ፖለቲካ በሚባለው ነገር አሜሪካኖችን የሚያህላቸው የለም፡፡ ጨረቃ ላይ ሰው ከመውጣቱ እስከ ኬኔዲ ግድያ፣ እስከ ትረምፕ ምርጫ ማጭበርበር….ብቻ በሁሉም ነገር የሴራ ፖለቲካ ወሬ በሽ፣ በሽ ነው፡፡ ታዲያላችሁ…አሁን፣ አሁን እኛም ዘንድ የሴራ ፖለቲካ ወሬ እንደ ጉድ እየተፈለፈለ ነው፡፡ እናላችሁ… እየሆኑ ባሉ ነገሮችና ሊሆኑ ሲገባቸው ባልሆኑ ነገሮች ግራ ሲገባን፣ “በሀበሻ ምድር አንዲህ አይነት እብደት መቼም ሊፈጠር አይችልም፣” ስንለው የነበረው ነገር ሁሉ በከፋ መልኩ ብቅ፣ ብቅ ሲል… በቅን ልቦና ነገሮችን ሊያስረዳን የሚችል ሲጠፋ፣ የሴራ ፖለቲካ ወሬ ቢበዛ ምን ያስገርማል!    
ጠያቂ፡ — ጌታዬ ጤና ይስጥልኝ…
ተጠያቂ፡ — ጤና ይስጥልኝ…
ጠያቂ፡— ከ… ቴሌቪዥን ነው የመጣሁት፡፡ ስለ ሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ አንዳንድ ነገር ልጠይቅዎት ፈልጌ ነበር፡፡
ተጠያቂ፡— አይ ፖለቲካ! እንደው እኮ አፋችሁን ሞልታችሁ እንዲህ ስትናገሩ ግርም ይለኛል፡፡ ስለ የትኛው ፖለቲካ ነው የምታወራው! ንገረኛ…እዚህ ሀገር ፖለቲካ የሚባል ነገር አለ እንዴ! ፖለቲካ ፓርቲ ነን የሚሉ ጉዶች በየቀበሌው ስለተፈለፈሉ፣ ፖለቲካ  አለ ማለት ነው እንዴ!
ጠያቂ፡— ምነው ጌታዬ፣ ቆጣ፣ ቆጣ አሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መብዛቱን አልወደዱትም እንዴ?
ተጠያቂ፡— ውደድድ ነው ያደረግሁት እንጂ!” (የምጸት ሳቅ) ትገርሙኛላችሁ፡፡ ለመሆኑ ስቱዲዮ ቁጭ ብላችሁ ፖለቲካ፣ ትርኪምርኪ ከማለት ውጪ ህዝቡ ምን አይነት ኑሮ እየኖረ እንደሆነ አይታችሁት ታውቃላችሁ?
ጠያቂ፡— እኮ ኑሮ መክበዱ ከፖለቲካው ጋር የተያያዘ አይመስልዎትም?
ተጠያቂ፡— ወይ ጣጣ! እኔ እኮ የምለው… የዘንድሮ ጋዜጠኞች እናንተ የምትፈልጉትን ብቻ እንድንናገር የምትፈልጓቸውን ቃላቶች በአፍ በአፋችን ልታጎርሱን ምንም አይቀራችሁም፡፡
ጠያቂ፡— ይቅርታ፣ አሁን ያሉኝን ቢያብራራልኝ:: ምክንያቱም እኛ ዋና ፍላጎታችን የህዘቡን አሰተያየት ለማሰማት ነው፡፡
ተጠያቂ፡— እናንተው አብራሩልኝ እንጂ፣ ለሁላችንም አብራሩልን እንጂ! የቴሌቪዥን ጣቢያውን ሁሉ የቤተሰብ ጉባኤ አስመስላችሁት…እናንተ አብራሩልን እንጂ!  
ጠያቂ፡—  እኔ ልልዎት የፈለግሁት ብዙ ችግሮች እየተከሰቱ ያሉት ፖለቲካው የተረጋጋ ስላልሆነ አይመስልዎትም?
ተጠያቂ፡— እኮ… በዋነኛነት እያመሳችሁት ያላችሁት እናንተ አይደላችሁም እንዴ!
ጠያቂ፡— በምሳሌ ሊያስረዱኝ ይችላሉ…
ተጠያቂ፡— የሆነ ያልሆነውን እያቀረባችሁ ሰዉ ውስጥ መርዝ እየዘራችሁ ያላችሁት እናንተ አይደላችሁም እንዴ! ታስራ ኖራ እንደተለቀቀች ጥጃ፣ አገር ጠበበን የምትሉት እናንተ አይደላችሁም እንዴ! አናግረኛ!
እናማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ነገሮች ተርመስመስ ብለዋል፡፡ ደግ፣ ደጉን ማሰብ አሪፍ ቢሆንም….አለ አይደል…ደግ ደጉን እንዳናስብ የሚያደናቃቅፉን ነገሮች እየበዙ ግራ የተጋባንበት ዘመን ነው፡፡ ነገራችን የጸጉራማው ውሻ ታሪክ እንዳይሆን፣ ግራ ብንጋባና ብንሰጋ አይገረምም፡፡
ጠያቂ፡— ወንድሜ ከ… ቴሌቪዥን ነው የመጣሁት፡፡ አንዳንድ ጥያቄዎችን ልጠይቅህ ፈልጌ ነበር፡፡
ተጠያቂ፡— አባውት ኋት!
ጠያቂ፡— አንተ እዚህ ቦሌ አካባቢ ነው ያገኘሁህ፡፡ ዘመናዊ ወጣት እንደመሆንህ ስለ ሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ፣ አንተና ጓደኞችህ ምን እንደምታስቡ ለማወቅ ነው፡፡
ተጠያቂ፡— ኦ ማይ ጋድ! ፖለቲከስ! አይ ዶንት ኬር አባውት ፖለቲክስ! ስማ…ይሄን ስኒከር የስተርዴይ ስንት እንደከፈልኩበት ታውቃለህ…  ሲክስ ታውዘንድ! ስድስት ሺህ ብር!  ቱ ሄል ዊዝ ፖለቲክስ!
ጠያቂ፡— ግን እኮ የዋጋው ነገር ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ አይመስለልህም? ፖለቲካው ቢስተካከል እኮ ስኒከሩን እዚሁ በኩዋሊቲ እየሠራን፣ ኤክስፖርት ማደረግ ሁሉ እንችል ነበር፡፡
(ከት ብሎ ይስቃል)  ዩ ጋይስ የማደንቃችሁ ለምን እንደሆነ ልንገረህ?
ጠያቂ፡— ብሰማው ደስ ይለኛል፡፡
ተጠያቂ፡— በፋንታሲ መኖር ትችላላችሁ፣፣ አይ ሚን ኢት…የራሳችሁን ዓለም ፈጥራችሁ፣ ዩ ዶንት ኢት ኢነፍ፣  ዩ ዶንት ድሪንክ ኢነፍ ግን እዛ ትደሰታላችሁ:: አይ ሪሊ አድማየር ዩ ፒፕል!
ጠያቂ፡— አመሰግናለሁ… ግን አሁንም ስለፖለቲከ የተየቅሁህን አለመለስክልኝም፡፡
ተጠያቂ፡— ዩ ሀቭ ኖ ኩዌሽን… ማን! ፖለቲካ በሌለበት እንዴት ነው ስለ ፖለቲካ የምነግርህ፡፡ ቴክ ኢት ኢዚ!
ታዲያላችሁ…ግራ ተጋብተንም ነገሮች እንዴት እዚህ ደረጃ ደረሱ እንላለን፡፡ ዛሬ እንዲህ አይነት ነገሮች ከተከሰቱ ነገና ከነገ ወዲያ ነገሮች ከድጡ ወደ ማጡ ላለመንሸራተታቸው ምን ማረጋገጫ አለን እንላለን፡፡ ሌሎች ሃሳቦቻቸውን እንዲገልጹ እድል መሰጠት ሲገባን እኛ ብቻ ካልተሰማን፣ የእኛ ብቻ ትክከለኛ፣ ወይም “እኛን ትሰማላችሁ፣ አለበለዛ ፓሲፊክና አትላንቲከ ውቅያኖሶችን ወደኩሬነት እንለውጣቸዋለን፣” አይነት ደረት ማስፋት ሲበዛ ግራ ቢገባ ምን ይገርማል!
 ጠያቂ፡— እማማ፣ እንደምን አደሩ…
ተጠያቂ፡— እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
ጠያቂ፡— እማማ… እንደው ስለ ሀገራችን አንዳንድ ነገር ልጠይቅዎት ፈልጌ ነበር…
ተጠያቂ፡— ስለምኑ ልጄ? ስለምኑ ነው የምትጠይቀኝ?
ጠያቂ፡— ማለቴ…ስለሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ እንዲነግሩኝ ፈልጌ ነው፡፡
ተጠያቂ፡— አይ ልጄ…እንዲህ አይነት ነገር እኔ ምኑን አውቄ! እናንተ ስትሉ እሰማለሁ እንጂ እኔ ምኑን አውቄ!
ጠያቂ፡— እማማ…ስለ ለውጡ ምን ያስባሉ?
ተጠያቂ፡— ልጄ እኔን ለውጥ አጠገብ ማን አስጠግቶኝ! ስማኝ፣ እኛን ማን አስጠግቶን፣ ማንስ ሰምቶን!
ጠያቂ፡— እማማ… ከአነጋገርዎ የተናደዱ ይመስላል…
ተጠያቂ፡— ብናደድስ ምን እንዳላመጣ! እኮ ንገረኛ…ብናደድ ጨጓሬዬን ከመላጥ በስተቀር የትኛውን ድንጋይ እንዳልፈነቅል ነው! የእኔ ልጅ… እንደው አትክልት ተራ፣ እህል በረንዳ ሄደህ ታውቃለህ?
ጠያቂ፡— እ…እማማ፣ እውነቱን ለመናገር ሄጄ አላውቅም፡፡
ተጠያቂ፡— ሂድና እየው ልጄ፣ ለአንተም ይጠቅምሀል፣ ሂድና እየው፡፡ ደግሞ ሀኪም ቤት ሂድና፣ ደግሞ ወረዳ ሂድና… ደግሞ ሸማቾች ሂድና… ያኔ የእኛ ሆድ ምን እንደሚመስል ታውቀዋለህ::  ልጄ… የእኛ ፖለቲካ ይኸው ነው... ችግር ብቻ!
አንድ ነገር በተተነፈሰ ቁጥር፣ አማራጭ ሀሳብ በቀረበ ቁጥር… “ኒኦ ሊበራል፣” “የድሮ ናፋቂ”  ምናምን እየተባለ ዝም ጭጭ ማሰኘት እንደ ስትራቴጂ ነገር ይመስል ነበር፡፡ (ኮሚክ እኮ ነው…የሀያ ዓመቱ ወጣት ሁሉ እኮ ‘የአጼዎቹ ዘመን’ የሚባለውን በመናፈቅ ይከሰስ ነበር፡፡) አሁን፣ አሁን ደግሞ “ለውጡን የማይፈልጉ…” ምናምን አይነት አባባል መግባት በሚገባው ስፍራ ብቻ ሳይሆን መስመር እያለፈም መገኘት የሌለበት ስፍራ ብቅ ማለት ጀምሯል፡፡ ‘አይፈልጉም፣’ የሚባሉትን፣ ‘አደናቃፊዎች’ የሚባሉትን… አለ አይደል… ‘ማስፈራሪያ ዱላ’ በሚመስሉ ቅጽሎች ሳይሆን፣ ሀሳቦቻቸውን በመሞገት ቢሆን አሪፍ ነው፡፡
ብቻ…ብቻ…ብቻ…ቀኙም፣ ግራውም… “ያዋከቡት ነገር…” እየሆነብን ግራ ተጋብተናል፡፡
ግራ ከመጋባት የምንወጣበትን ዘመን ያፍጥንልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2104 times