Saturday, 06 April 2019 15:53

የሳዑዲው የነዳጅ ኩባንያ በአለማችን ከፍተኛውን ትርፍ አግኝቷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የአለማችን የሙዚቃ ሽያጭ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል


           ሳኡዲ አራማኮ የተባለው የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ኩባንያ በ2018 የፈረንጆች አመት በአለማችን ከፍተኛውን ትርፍ ያገኘ ቀዳሚው የንግድ ኩባንያ መሆኑን የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ፤ ኩባንያው በአመቱ 111.1 ቢሊዮን ዶላር ማትረፉን አመልክቷል፡፡
የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ንብረት የሆነው ሳኡዲ አራማኮ በአመቱ በአማካይ 10.3 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ማምረቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ አጠቃላይ አመታዊ ገቢውም 355.9 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ገልጧል፡፡
ሞዲ ኢንቬስተርስ ሰርቪስስ የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ባወጣው በ2018 ከፍተኛ ትርፍ ያስመዘገቡ የአለማችን ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ የሁለተኛነት ደረጃን የያዘው አፕል ሲሆን፣ ኩባንያው በአመቱ 59.5 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱ ተነግሯል፡፡በአመቱ 39.9 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ያስመዘገበው የደቡብ ኮርያው የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ ሳምሰንግ የሶስተኛነት ደረጃን የያዘ ሲሆን፣ ጄፒ ሞርጋን በ32.5 ቢሊዮን ዶላር፣ አልፋቤት በ30.7 ቢሊዮን ዶላር አራተኛና አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የአመቱ የአለማችን የሙዚቃ ሽያጭ ባለፉት አስር አመታት እጅግ ከፍተኛው ሆኖ ክብረ ወሰን ማስመዝገቡን የዘገበው ቢቢሲ፣ በአለማቀፍ ደረጃ 19 ቢሊዮን ዶላር ያህል ሽያጭ መከናወኑን አመልክቷል፡፡በአመቱ በአለማችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በድረ-ገጽ የቀጥታ ሽያጭ፣ በሶፍት ኮፒና በአልበም የተከናወነው ሽያጭ በ9.7 በመቶ ያህል ዕድገት ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው፤ 3.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘው የግሬተስት ሾውማን አልበም በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን አመልክቷል፡፡

Read 1383 times