Saturday, 06 April 2019 15:46

“ሱቱኤል”ን በወፍ በረራ ቅኝት!

Written by  ይታያል እውነቱ
Rate this item
(0 votes)


                               የመጽሐፉ ርእስ- ሱቱኤል
ዘውግ - ረጅም ልቦለድ
ደራሲው - ታገል አምሳል
የገጽ ብዛት- 284
ዋጋ - 132 ብር ወይም 27 ዶላር
የኅትመት ዘመን - 2011 ዓ.ም
አከፋፋይ - ሀሁ መጻሕፍት መደብር

መጽሐፉ ሙሉ ለሙሉ ፈጠራ ነው፤ ብሶት የወለደው ፈጠራ፣ የኖርንበትንና ያለንበትን ኹነት በመገንዘብ ደራሲው ያመነጨው ፈጠራ፡፡ ልቦለድ ነው፤ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማየት የጓጓ አንድ ደራሲ የሚጽፈው ልቦለድ፡፡
መጽሐፉ የታተመው በኅዳር ወር ይሁን እንጂ ጥቂት ዓመታትን ቀድሞ የተጻፈ እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡ ለዚህ አስረጅ መጥቀስ ሳያስፈልግ የደራሲዎችን ኑሮና የኅትመት ዋጋ መናርን ብቻ ማየት ዛሬ ተጽፎ ነገ ለማሣተም አዳጋች መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ስመለከተውና አሁን በዶክተር ዐቢይ ካቢኔ አማካኝነት እየታየ ያለው የዴሞክራሲ ጭላንጭል እንዲሁም  ደራሲው ብዙ ያስተዋላቸው ነገሮች፣  የጠቆማቸው የመፍትሔ ሐሳቦች በዚህ ለውጥ ውስጥ እየታዩ መሆኑን እንታዘባለን፤ እናም የደራሲው ምናብ ትንቢታዊ ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡
"በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በሀብት መጠን፣ በሥልጣን፣ በዝና፣ በጤና፣ በትምህርት ደረጃ፣ በመሳሰሉ ጉዳዮች የተተከሉ ልዩነቶች ሥር ሰደው ሀገርን የኋሊት እየጎተቷት ነበር፡፡ እኒያ ትናንሽ የሚመስሉ ግዙፍ ደንቃራዎች ምንጫቸው ታወቀ፣ አውቆም ይሁን ሳያውቅ በሕዝቡ መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የዙፋኑን መደላደል ያጠነክር የነበረው ገዥው ፓርቲ አካሄዱ ሁሉ ታወቀ፡፡ ባለመንበሩ አካል የተሻለ መሠረት ላይ ባለመታነጹ ደራሽ ጎርፍ በሆነበት ምሥጢራዊው የምሁራን ቡድን ድንገተኛ ማዕበል የዋጣት  የበሰበሰች ታንኳ ሆኖ አረፈ፡፡

"ከአዲስ አበባ እስከዱባይና ቻይና ቆነጃጅትን በማማረጥ፣ ውስኪ በመጠጣትና የጦር መሣሪያ ሳይቀር እየነገዱ ከርስን መሙላት የስርዓቱ ዋነኛ መገለጫ ሆኖ፣ ሀገር ወደፊት ከማራመድ ይልቅ ተደራጅቶ ሀገርን መቦጥቦጥ፣ ለዘመናት ከፍላ የማትጨርሰው እዳ ውስጥ ሀገርን እየነከሩ፣ ሕዝቡን እንደተመሪ ዜጋ ሳይሆን እንደ ተራ ጥሬ እቃ ተጠቅመው እንዴት እናትርፈበት እያሉ የሚመካከሩ እርጉማን፣ እውነትም እንደበሰበሰች ታንኳ ስንጥቅጥቃቸው ወጥቶ መደበቂያ ጎሬ ውስጥ ገብተዋል፡፡”

ደራሲው በዚህ ዕይታው "ሱቱኤል" ብሎ በሰየመው ስብስብ ውስጥ ሀገራችን ተዘፍዝፋ ከኖረችበት የጸረ ዴሞክራሲና የድህነት አረንቋ እንዴት መውጣት ይቻላልን ሲመክሩ ያሳየናል፡፡ ምናልባት በኢህአዴግ መንበር ሥር ሆነው የበሰበሰውን የኢህአዴግ ስርዓትና ሰዎችን ፈንግለው ስለወጡት አዳዲስ ባለብሩህ አእምሮዎች ቀድሞ ያውቅ ነበርን? የሚለው ጥያቄ፣ እንደ አንድ አንባቢ አእምሮዬን ይይዘዋል፡፡

ሌላው በመጽሐፉ ውስጥ ያስተዋልኩት ብርቱ ቁምነገር፣ አሁን እዚህና እዚያ ችግሮች ቢፈጠሩ፣ ግጭቶች ቢጧጧፉ፣ ዘረፋ ቢበራከት፣ ሰው ማጥፋት ቢበዛ እኛ እንደለመድነው ‹በለው፣ ግደለው፣ እሠረው› ዓይነት ትእዛዝ አልሰጥ ቢል፣ ዐቢይንና አመራሩን የምናማርርበት እድል ይኖር ይሆን? ደራሲው ይሄ የሚጠበቅ ነው ይለናል፡፡ ለዚህ መልሱ በ"ሱትኤል" መጽሐፍ አስቀድሞ እንደትንቢት የተገለጠውና ከላይ በቅምሻ ያነሳሁት ሐሳብ ነው፡፡ አልሞት ባዩ የአሮጌዋ ታንኳ አንቀሳቃሽ፣ እዚህና እዚያ መንገዶችን እያማረጠ መንደፋደፉ አይቀርምና፡፡

"ሱቱኤል" እንደመጽሐፍ ሌላ የምወስድለት ቁምነገር፣ እላይ የተንጠለጠሉትን መሪዎች በመተቸት ወይም በመወረፍ አለዚያም እነሱን ብቻ ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ በዘርፍ በዘርፍ እየመረጠ፣ ዜግነትና ሀገራዊ ግዴታ ምን እንደሆነ ሊነግረን መሞከሩ ነው፡፡

"በመደበኛ የትምህርት ተቋማት በአንድና ሁለት ሙያ ስለተመረቀ፣ የምሁርነት ካባ ደርቦ የማዕረግ ስምና የክብር ወንበር ከመስጠት ባሻገር ማኅበረሰቡ በሁለንተናዊ ዕይታና አስተሳሰብ ለይቶ እንዲሾማቸው እንዲያወርዳቸውም ምሁርነት መስፈርቱ የተለየና ለሕዝብ ለሀገርና ለአካባቢ በሚያበረክተው ሚና፣ በሚያሳድረው መልካም አሻራ የሚወሰን ጽንሰ ሐሳብ ነው!”

ደራሲው  ይሄን የሚለን፣ ያለንበትን ማኅበራዊ እውነት አስተውሎ ይመስለኛል፡፡ አዎ፤ አሁን ያለንበት ዘመንና እኛ እንዲህ ነው የምንመስለው - የወያኔ የትምህርት ፖሊሲ ሲተች አብረን ነገር የምናራግብ፣ የትምህርት ፖሊሲው ችግር ፈጣሪን እንጂ ችግር ፈች ትውልድ አላፈራም እያልን የምናማ፤ ነገር ግን በዚህ ስርዓት መማራችንን አስረጅ አድርገን የተማርንበትን ሳይንስ ለትንታኔ መጠቀም ቀርቶ የተማርነውን ሳይንስ ምንነት ማብራራት ያልቻልን እኛ-ዲግሪ አለኝ እያልን አረቄ ቤት እናደምቃለን፡፡  ዳሩ ይሄ ተግባራችን እንደ ሀገር የላሸቀ መንግስታዊ ሥርዓትን እንድናይ፣ እንደሕዝብ ደግሞ አይኖሩት ኑሮን እንድንኖር ሰበብ ሆኖብናል፡፡ የተሻለው ግን፤ ምሁሩ የእውነት ምሁር መሆን፣ ሃይማኖተኛው የእውነት ሃይማኖተኛ መሆን፣ ሀገር ጠባቂው እውነተኛ  ሀገር ጠባቂ መሆን--- በጥቅሉ ከማስመሰልና ከውሸት ኑሮ መውጣትና ባለራዕይ መሆን ነው፡፡ ልክ እንደ ሱቱኤሎቹ!

"ሱቱኤል" እንደ ልብ ወለድ፣ ልብ አንጠልጣይ ታሪክ ነው፡፡ ከአሁን አሁን ምን ይፈጠር ይሆን እያልን እንድንጓጓ ያደርገናል፡፡ ትልቅ ተልዕኮን ይወጣ ዘንድ ምስጢራዊ ቡድን ተቋቁሞ፣ በዚህ ቡድን ውስጥ ያሉ አባላት ውጣ ውረዳቸውን እናያለን፤ እንኳንስና ሰይጣናዊ ፓርቲ አስወግዶ ነፍስ ያለው ፓርቲ ለመተካት ሌላም ቀለል ያለ ነገር ቢሆን፣ በዚች ሀገር ውስጥ ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆን አንባቢያን ይገምቱታል፤ ይህን የክፋትና የተንኮል ሥር በጣጥሶ ለመውጣት የሚደረገው ግብግብ በጣም ልብ አንጠልጣይ ነው፡፡ እናም መጽሐፉን አንዴ ከጀመሩት ለማቋረጥ የሚከብድ ነው፡፡ እንድታነቡት በመጋበዝ ወፍ በረራዊቅኝቴን እዚሁ ላይ አበቃለሁ፡፡


Read 1105 times