Print this page
Saturday, 02 June 2012 08:46

“ጥቁር ሰው”፤ ጠይም ቢሆን ጀግንነቱ ይጠፋል?

Written by  አለሙ ከበደ
Rate this item
(3 votes)

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ “ቴዲአፍሮ - የዘመኑ ጥቁር ሰው” በሚል ርእስ የቀረበው ፅሁፍ፣ “አጓጉል ውዳሴ” የበዛበት ቢሆንም፤ ፀሃፊው መመስገን አለባቸው። ከግርግር እንድንወጣ አግዘውናል። በአልበሙ ውስጥ የምናደምጠው “ሆይሆይታ” ያነሰ ይመስል፤ ሌሎች ግርግሮች ተጨምረውበት ስለ አልበሙ እንዳንወያይ ፋታ ነስተውን ቆይተዋል። አልበሙ የወጣ ሰሞን፣ የቴዲአፍሮና የአምለሰት የጋብቻ ወሬ ሰሞነኛ ትኩሳት እንደሆነብን ታስታውሳላችሁ። እንደ ፊልም “soundtrack” ዘፈኖቹን ወደ “background” ተገፍተን፤ የቀለበትና የሰርግ ትረካዎችን ስንሰማ ሰነበትን። ይሄኛው ግርግር ከሁለት ሳምንት በኋላ ድምፁ ሲጠፋ ደግሞ፤ የቴዲና የአሳታሚው ውዝግብ ዋነኛ ወሬ ሆኖ መጣብን። ደግነቱ፤ ስለ አልበሙና ስለ ዘፈኖቹ እንዳንነጋገር ወዲህና ወዲህ የሚያጣድፉን ግርግሮች፣ እለት በእለት እየተፈጠሩ እስከ ወዲያኛው ሊዘልቁ አይችሉም። ለማንኛውም ግን፣ ሌላ የትረካ ወይም የውዝግብ ትኩሳት ሳይፈጠር፤ ጊዜውም ሳያልፍበት ቶሎ ስለዘፈኖቹ ተወያይተን ብንጨርስ ይሻላል። ለዚህም ነው፤ ባለፈው ሳምንት የቴዲአፍሮን አልበም በማወደስ አስተያየት ያቀረቡልን ፀሃፊ መመስገን የሚኖርባቸው።

 

 

በእርግጥ፤ የፀሃፊው አስተያየት በሁለት ወይም በሶስት የዘፈን ግጥሞች ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ፣ ጥንካሬ ይጎድለዋል። ዜማዎቹንና የሙዚቃ ቅንብሮቹን፣ አዘፋፈኑንና ድምፁን፣ እንዲሁም ሌሎች የአልበሙን ገፅታዎች በሙሉ የግድ  መዳሰስ ነበረባቸው እያልኩ አይደለም። እንደ አስፈላጊነቱ፣ አንዱ ገፅታ ላይ ወይም አንድ ግጥም ላይ ብቻ በማተኮር ማድነቅና መተቸት ስህተት አይሆንም።

ነገር ግን፤ ከአንድ ወይም ከሁለት ግጥሞች ብቻ በመነሳት፤ ሁሉንም ግጥሞች ማድነቅ ስህተት ነው። ከዚህም አልፎ፤ ሙሉ አልበሙ ( ከነዜማውና ከነቅንብሩ፣ ከነቅላፄውና ከነአቀራረቡ) ድንቅ ስራ እንደሆነ ማስመሰል ደግሞ፣ ትልቅ ስህተት ይሆናል። ፀሃፊው ይህንን ትልቅ ስህተት ፈፅመዋል።

“...ነገ ከነገ ወዲያ ሲሰሙት፣ እየሻተ እየጐመራ፣ ውስጥን በሀሴት እየኮረኮረ የሚሄድ”... በማለት ፀሃፊው አልበሙን ሲያደንቁ፤ እንደ ማሳያ ያቀረቡልን መረጃ ከሁለት ዘፈኖች... ማለቴ ከሁለት ግጥሞች የተቀነጨቡ ስንኞችን ነው። ለማሳያነት የቀረቡት ስንኞች ያን ያህልም ድንቅ የሚባሉ አለመሆናቸው ደግሞ የፀሃፊውን ስህተት ያጎሉታል።

እንግዲህ፤ ፀሃፊውን ወይም ግጥሞቹን እንዲህ ለመተቸት፤ እኔም በቂ ማሳያ ማቅረብ እንደሚጠበቅብኝ አውቃለሁ። እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት ነገር አለ። በርካታዎቹ ግጥሞች፤ እጅግ ደካማ መሆናቸውን በማረጋገጫ ለማሳየት ቻልኩ ማለት፤ አልበሙ ቀሽም ነው ማለት አይደለም።

ሆይሆይታ እና ድንክ ዜማዎች

የአልበሙ ጥበባዊ ዋጋ የሚመዘነው፤ በግጥሞቹ ብቻ መሆን የለበትም። ዜማዎቹንና አዘፋፈኑን፤ የሙዚቃ መሳሪያውንና ቅንብሩን ጨምሮ፤ በርካታ ገፅታዎችን ማገናዘብ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ሆይሆይታ የበዛበት አዘፋፈን የአልበሙ አንድ ድክመት እንደሆነ መጥቀስ ይቻላል። “ጥቁር ሰው” የሚለውን ዘፈን ስሙት፤ ከመግቢያው ዜማ ቀጥሎ ጩኸቱን ያቀልጠዋል - “ኢ ኡ... ኢ ኡ” እያለ። “ባሻው” የሚለው ዘፈንም፣ ማርሽ በሚመስል ሙዚቃ እንደጀመረ፣ ጮቤ የሚያስረግጥ “ሃ ሃ ሃ ሃ” የሚል ጩኸት ይከተለዋል - ስለ ኑሮ አለመቃናት እየዘፈነ። “ስቴድ”፣ “ደስ የሚል ስቃይ” እና ሌሎች በርካታ ዘፈኖቹም ከአላስፈላጊ ሆይሆይታ አልተረፉም።

ሌላኛው የአልበሙ ድህመት፤ የ”መዝሙር” ወይም የዘፈን ማሳረጊያ የሚመስሉ ድንክ ዜማዎችን ማብዛቱ ነው። ደህና በሚመስል ዜማ የሚጀምረው “ጥቁር ሰው”፤ በዚያው አቅጣጫ እያደገ ከመሄድ ይልቅ፤ በአጭሩ ተቀጭቶ የዋይታ ዜማ ውስጥ ይዘፈቃል - በድንክ የአስለቃሽ ዜማ።  “ጨዋታሽ” የሚለው ዘፈን ላይ ሳይቀር ድንክ የዜማ ስንዝሮዎች አሉ - “ተይ አታስጨንቂው - ልቤን/ ሲከፋሽ አይወድም .... ካልነገርሽን ቁርጡን - ዛሬ/ከጎንሽ አልሄድም” እያለ የሚያዜመው እንዴት እንደሆነ አድምጡ።በርካታ ዘፈኖች፤ ከግጥሞቻቸው መልእክትና መንፈስ ጋር የማይጣጣም ዜማና አቀራረብ መያዛቸውም፤ የአልበሙ ድክመት ነው። እንግዲህ፤ ብዙዎች እንደሚሉት ከሆነ “ጥቁር ሰው” የሚለው ዘፈን፣ ጀግንነትንና ድልን ለመግለፅ የታሰበ ዘፈን ነው። ዜማውና አቀራረቡስ? “ድል ቀናኝ ሳልል ዋይ” እያለ ጀግንነትን እንዲገልፅ የታሰበው ዘፈን፤ በዋይታ ዜማና በሆይሆይታ ነው የቀረበው። ትካዜንና የኑሮ መከራን የሚጠቃቅስ ግጥም የያዘው “ባሻው”ስ እንዴት ተዘፈነ? ሞቅ ባለ ሙዚቃ ያስጨፍራል። “የውበት ፀሃይ ወጥቶልሻል” የሚልና ተመሳሳይ የአድናቆት ስንኞችን የያዘው “ጸባየ ሰናይ” የተሰኘው ዘፈን ደግሞ፤ ከትካዜ ስሜት ጋር የተጎራበተ ዜማ ይዟል።

በነገራችን ላይ “ጸባየ ሰናይ” የሚለው ዘፈን፤ የአረጋኸኝ ወራሽን ዘፈን እንዳስታውስ አድርጎኛል - “ነፋስ ገብቶ ከመሃላችን...” ምናምን ከሚለው ዘፈን ጋር ተመሳሰለብኝ። ግጥሞቹና ዜማዎቹ፤ የቀለም ወይም የድምፅ ምጣኔያቸው ቢለያይም፤ ተቀራራቢነት አላቸው። በተመሳሳይ ሁኔታ፤ “ስለ ፍቅር” የሚለው የቴዲ ዘፈን፤ ከሚካኤል በላይነት አልበም ዘጠነኛው ዘፈን ጋር ቅርርብ እንዳለው ተሰምቶኛል። አዎ፤ የቀለም (የድምፅ) ምጣኔያቸው ላይ ልዩነት አለ። ነገር ግን፤ የቴዲ ዘፈን ላይ፤ “እንደሚወድ ካቅሙ በላይ... አየሁ እኔስ ባንቺ ስቃይ” ብሎ ሲየዜም አድምጡና፤ ሚካኤል በላይነህ “ስቄ እሸኝሻለሁ” ብሎ ሲዘፍን ስሙት።

“ሀይል” የምትለው ቁራጭ ዘፈንስ፤ “ፅጌረዳ አበባ”፤ “አስታውሳለሁ፤ መች እረሳለሁ” ከሚሉ የድሮ ዘፈኖች ጋር አትቀራረብም? የዜማ ተቀራራቢነት የሚፈጠረው፤ በመኮራረጅ ላይሆን ይችላል። ሰርፀ ፍሬሰንበት ለፎርቹን በሰጠው ቃለምልልስ እንደጠቆመው፤ የአገራችን ሙዚቃ የፈጠራ አቅሙ ስለተሟጠጠ ሊሆን ይችላል።  የአገራችን ጥንታዊ ቅኝቶች ከዚህ በላይ አዲስ የዜማ ፈጠራዎችን ለማስተናገድ አቅም ከሌላቸው... አስቸጋሪ ነው።የሆነ ሆኖ፤ ስለ አልበም ድክመትም ሆነ ጥንካሬ ለመናገር፤ በርካታ የዘፈን ገፅታዎችን መዳሰስ እንደሚያስፈልግ ለማሳየት ነው ምሳሌዎችን የጠቃቀስኩት። ስለ ሰው የጤንነት ጉድለት ስናወራ፤ “አተኮሰውና አስመለሰው፤ ቆሰለና አነከሰ፤ አበጠና ጎበጠ” እንል የለ? ልክ እንደዚያው የተለያዩ ገፅታዎችን በማካተት፤ ስለ ዘፈን ጤንነትና ህመም መናገር ይቻላል። ግን ደግሞ የጤና ባለሙያዎች፤ በግልፅ የሚታዩትንና ሌሎች የጤንነት ነገሮችን ከነመንስኤያቸው በጥልቀት መርምረው ይናገራሉ። የሙዚቃ ባለሙያዎችም እንዲሁ በጥልቀትና በስፋት የመመዘን ብቃታቸውን ተጠቅመው ትንታኔ ሲጨምሩበት፤ ውይይቱ የበለጠ የተሟላ ይሆናል።

በዚህም ተባለ በዚያ፤ አንድ የማያጠራጥር ነገር ቢኖር፤ ግጥሞችን ብቻ በማየት  አልበሙን በጥቅሉ መመዘን (ማድነቅና መተቸት) ስህተት መሆኑ ነው። ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን ያካፈሉን ፀሃፊ፤ ይህን ስህተት መፈፀማቸውን ለማሳየት የቻልኩ ይመስለኛል። ግን... ለመሆኑ... ፀሃፊው እንደሚሉት፤ ግጥሞቹን ብቻ ብናይስ፤ ... ያን ያህል የሚደነቁ ናቸው?

ስቴድ - በህፃናት አፍ ይጣፍጣል?

ቴዲአፍሮ፤ የግጥም ዝንባሌና ችሎታ እንዳለው አምናለሁ። የዘፈኖቹን ግጥሞች በሙሉ የፃፈው ራሱ ቴዲአፍሮ እንደሆነ፣ በአልበሙ የሰፈረው ፅሁፍ ይመሰክራል። የግጥም ዝንባሌው አያጠራጥርም። ነገር ግን፤ የግጥም ችሎታውን የሚመሰክር ግጥም ከአልበሙ ውስጥ ለማቅረብ አስቸጋሪ ነው። “ደህና ናቸው” የሚባሉት ግጥሞች እንኳ፤ ያን ያህልም ድንቅ አይደሉም - በያዙት መልእክትም ሆነ በአገላለፅ ብቃት።

ሁለት ጥያቄዎችን በማቅረብ ግጥሞቹን ለመመዘን እንሞክር። ግጥሞቹ፤ የነጠረ ጠንካራ የሃሳብና የስሜት መልእክት ይዘዋል? ግጥሞቹ፤ የቃላት አጠቃቀማቸው ሲታይ ምጥንና ምርጥ አገላለፅ ይዘዋል?

“ቀሽም” ሆነው ያገኘኋቸውንና “ደህና ናቸው” የምላቸውን፣ አንድ ሁሉቱን በመጥቀስ ብጀምር ጥሩ ይመስለኛል። ለምሳሌ፤ “ጨዋታሽ” ከቀሽሞቹ መካከል አንዱ ነው። “ኦ አፍሪካ” በሚለው ዘፈን ላይ የምናየው አይነት ችግር፤ “ጨዋታሽ” ላይ ተትረፍርፎ እናገኘዋለን - የተዝረከረከና የደበዘዘ እንጂ ነጥሮና ጎልቶ የሚታይ መልእክት የለውም። ከዚህም በተጨማሪ፤ “ስቴድ” በሚለው ግጥም ውስጥ እንደምናየው ሁሉ፤ “ጨዋታሽ” የሚለው ግጥምም፤ በቃላት አጠቃቀምና በአገላለፅ ድክመት ሳቢያ ሽባ ሆኗል።

እስቲ አራተኛውን ዘፈን በማስቀደም፤ ግጥሙን እንመልከት። “ስቴድ” ይላል ርእሱ - “ስትሄድ” ለማለት ነው። ያፈቀራትና ያመናት ሴት ተለይታው ጥላው ስትሄድ፤ “ዋ እኔ፤ ዋ እኔ” ይላል። “ለስንት ያሰብኩት ፍቅር በጅምሩ ሲቀር” ... በማለትም ቁጭቱን ይተነፍሳል። “በጅምር ሲቀር” ተብሎ የተገለፀው ነገር፤ ፍቅር ሳይሆን አንዳች ፕሮጀክት ቢመስልም፤ የግጥሙ መልእክት ግልፅ ነው። በቃ፤ በአጭሩ የተቀጨ የፍቅር ችግኝ፤ በድንገተኛ መለያየት ሳቢያ የተሰበረ የአፍቃሪ ልብ... ይታያችሁ። እንደ “መርዶ ... ዋ እኔ”ን ያሰኛል የሚል መልእክት የያዘ ግጥም ነው። ጥሩ።

አሁን ደግሞ፤ ግጥሙ ውስጥ እንደ አዝማች ተደጋግመው እንዲደመጡ የተደረጉትን ስንኞች አስተውሉ።

ስቴድ ሆዴ ባባ

ተናነቀኝ፣ ተናነቀኝ እምባ

ሆዴ ባባ? ተናነቀኝ እምባ? እንደመርዶ የከበደ ነው የተባለው ነገር፤ ሆድ ከማባባት ያላለፈ ተራ ነገር ነው እንዴ?

ልሰናበታት ብዬ ሳወጋት ቀርቤ

ይጨነቅ ጀመር የሚወዳት ልቤ

ምናልባት፤ ፍቅረኛው ለወር ወይም ለሁለት ወር ያህል ጊዜ፣ ለስራ ጉዳይ ወደ ሌላ አገር ልትሄድ ብትዘጋጅ፤ እሺ። ያኔ ሲሸኛትና ሲሰናበት... “ሆዴ ባባ፤ ተናነቀኝ እንባ” ቢል አይገርምም። እንደምትመለስ ቢያውቅ እንኳ፤ ለአጭር ጊዜ መለያየትም ሆድን ይባባል። ማልቀስ እንደሌለበት ቢያውቅም እንባ ይተናነቀዋል። “እናቱ ወደ ገበያ የሄደችበት” እንደሚባለው አይነት ነው - ያባባል። ለዚህም ይሆናል፤ በርካታ ህፃናት ዘፈኑን የሚወዱት፤ “ተናነቀኝ፤ ተናነቀኝ” እያሉ ያዜሙታል። “ዋ እኔ”ን የሚያሰኝ የመለያየት “መርዶ”ን ለመግለፅ የተፃፈው ግጥም፤ እንዲህ በቃላት አመራረጥና በአገላለፅ ድክመት ሳቢያ፤ የህፃናት “አፍ መፍቻ” ሆኖ ቀረ።

እንግዲህ አስቡት። ነጥሮ የወጣ ግልፅ የሃሳብና የስሜት መልእክት የያዘ ግጥም፤ በአገላለፅ ድክመት የተነሳ ብቻ ደረጃው ወደ ታች ይወርዳል። ደብዛዛ መልእክት ላይ የአገላለፅ ድክመት ሲጨመርበት ደግሞ፤ ምን ያህል እንደሚበለሻሽ ይታያችሁ። በ”ማንነት”፤ በ”አህጉራዊነት” ዙሪያ፣ ነጥሮ ያልወጣ መልእክት የያዘውን ግጥም በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል - “ኦ አፍሪካ” ይላል ርእሱ። “ኦ” የሚለው ድምፅ፤ በእንግሊዝኛ ለአድናቆት ወይም ለጥሪ የሚጠቀሙበትን አባባል ለመወከል የገባ ይሁን አይሁን በእርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል።

አፍሪካዊነቴ ዜግነቴና ማንነቴ ነው፤ “ማንነት አይለወጥም” ይላል ግጥሙ። “ዜግነት” ሲል፤ የፓስፖርት ጉዳይ ከሆነ አያስኬድም። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ዜግነታቸውን እየለወጡ መሆናቸው፤ ሁላችንም የምናውቀው እውነታ ነው። “ዜግነት” ሲባል፤ “ጥቁር” መሆንን የሚያመለክት ከሆነስ? በእርግጥም፤ የቆዳ ቀለም ላይ የተመሰረተ ማንነትና ዜግነት ያን ያህል ላይለወጥ ይችላል። ነገር ግን፤ ሰዎች ማንነታቸውን በቆዳቸው ቀለም የሚመዝኑ ከሆነ፤ አሳዛኝ የዘረኝነት ስሜት ውስጥ ገብተው ይቀራሉ። ጤናማ አስተሳሰብ ከዚህ ይለያል። የቆዳ ቀለሙ፤ ነጭም ሆነ ጥቁር፤ ጠይምም ይሁን ቢጫ፤ ለማንኛውም ሰው ትልቁ ነገር የስብእና “ማንነት” ነው።

መጥፎ ወይም መልካም ባህርይ፤ ክፉ ወይም ጥሩ ተግባር፤ ስልጡን ወይም ኋላቀር ስብእና... ይሄ ነው ትርጉም ያለው የስብእና ማንነት። የስብእና ማንነት፤ በዘር አይወረስም፤ በአገርና በአህጉር ተወላጅነት አይታደልም። የጥረት ውጤት ነው። በጥረት ይሻሻላል ወይም በስንፍና ይበላሻል። በአጭሩ ሊለወጥ የሚችል ነው - የስብእና “ማንነት”። ይህንን እውነታ፤ ኦ አፍሪካ በሚለው ግጥም ውስጥ ልታገኙት ትችላላችሁ። ከሰው ቀድሜ ብነቃም፤ ዛሬ በአባይ ዙሪያ ውሃ ጠምቶኝ ተኝቻለሁ የሚል መልእክት ይዟል። የጥንቶቹ ኢትዮጵያዊያን በጥረታቸው ስልጡን ማንነትን ቢጎናፀፉ እንኳ፤ በውርስ ወይም በትውልድ ሃረግ ስለማይተላለፍ፤ የዛሬ ኢትዮጵያውያን የሚያንቀላፋ ኋላቀርነትን የተሸከሙ ይችላሉ። ማንነት ይለወጣል ማለት ነው።

ግጥሙ ጎልቶ የወጣ ግልፅ መልእክት የለውም ያልኩት፣ በዚህ ምክንያት ነው። ግጥሙ፤ በአንድ በኩል “ማንነት አይለወጥም” ይላል፤ በሌላ በኩል ማንነት እንደሚለወጥ ያሳያል - “ስልጡን ንቃት” ጠፍቶ፤ በቦታው “የሚያንቀላፋ ኋላቀርነት” እንደተተካ በመጥቀስ። ደብዛዛው መልእክት ላይ የአገላለፅ ድክመት ሲጨመርበት ደግሞ ግጥሙ ይበልጥ ተበላሽቷል። እንዲህ ይላል፡

ይህ ዜግነቴን ሳፈላልገው ኖሬ... እግሬ ሲዞር ባቋራጩ

“ሳፈላልገው ኖሬ” የሚለው ሐረግ፤ “እግሬ ሲዞር” የሚል ሐረግ ሲጨመርበት መልእክቱን እንደሚያጠናክረው አይካድም። “ባቋራጩ” የሚል ቃል ሲደነጎርባቸውስ? መልእክቱን ያፈርሰዋል። አቋራጭ የሚያስፈልገው መዞርን ለማስቀረት አይደል? ሲዞር የሚውል ከሆነማ፣ አቋራጩን ስቶታል ማለት ነው።

ነገር ግን “ባቋራጩ” የሚለው ቃል፤ የግጥሙን መልእክት የማያጠናክር ቢሆንም፤ ግጥሙ ውስጥ የገባው ያለምክንያት አይመስለኝም። “ቤት ለመምታት” ያገለግላል። ምን ዋጋ አለው? ምት በማይጠብቅና ቤት በማይመታ የቃላት አጠቃቀም መልእክት ለማስተላለፍ የሚሞክር ግጥም ቀሽም እንደሚሆን ሁሉ፤ መልእክትን በሚያፈርሱ ቃላት “ቤት ለመምታት” መሯሯጥም ቀሽምነት ነው።

ይህ ዜግነቴን ሳፈላልገው ኖሬ... እግሬ ሲዞር ባቋራጩ

ለካ ቤቴ እኔ አፍሪካ ነው... ደሜ ካባይ ላይ ነው ምንጩ

ኦ አፍሪካዬ.... ኦ አፍሪካ እማማ

“አፍሪካ” የሚለው ግጥም በአጠቃላይ ሲታይ፤ በመልእክትም በአገላለፅም የደከመ ግጥም ነው። ለነገሩ፤ “እማማ አፍሪካ” ይቅርና፤ “እምዬ ኢትዮጵያ” የሚል የተለመደ መዝሙርም ለብዙዎች ትርጉም አጥቷል። “እማማ ኢትዮጵያ”ን እየዘመሩ ለኑሯቸውና ጠብ የሚል ነገር ያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፤ ኑሮን ፍለጋ እየተሰደዱ ነው። “እምዬ አፍሪካ” እያልን ተጨማሪ ጊዜ ማባከን፤ ለማንም የሚበጅ አይመስለኝም።

የተምታታ መልእክት፤ የተንዛዛ አገላለፅ

“ጨዋታሽ” የሚለው የዘፈን ግጥም፤ ከሁሉም የባሰ ሳይሆን አይቀርም። በተምታታ ሃሳብና በተንዛዛ አገላለፅ ሳቢያ የተዝረከረከ ግጥም ሆኗል ብንል አይበዛበትም። ያፈቀራት ሴት፣ ድንገት ነገረኛ ትሁንበት አትሁንበት ባይታወቅም። ነገር ግን፤ ጨዋታዋ እንዳላማረው ተናግሮ ሲያበቃ፤ ፊትዋ ጭር እንዳለበት ማውራቱ ለሰሚ ግራ ነው። ከዚያም “ምናልባት አስቤ ይሆናል” እያለ ነገር ያራዝማል። ከፍቷት እንዳይሆን አስቦ የተጨነቀ ሰው፤ እንግዳ አመልሽን ችዬ አልቀመጥም ብሎ ማማረሩስ ምን ይሉታል? ለማንኛውም፤ ታሪኩ ባጭሩ ይህን ይመስላል፡

ጨዋታዋ አነጋገርዋ አልጣመውም፤ አለወትሮው ፊቷ ጭር ብሏል፤ ከፍቷት እንዳይሆን አሰበ? እንዴት የሌለባትን አመል ይቻል? ... ይሄው ነው ባጭሩ። እነዚህ ሃሳቦች በግጥም ሲገለፁ፤ እጥር ምጥን ተደርገው እንዲቀርቡ ብንጠብቅ አይፈረድብንም። ግጥሙ ላይ እንዴት እንደተንዛዙ ተመልከቱ።

ጨዋታሽ አልጥም አለኝ አነጋገርሽ

ከወትሮው ተለየብኝ ምነው ጭር አለ ፊትሽ

ምናልባት አስቤ ይሆናል ከፍቷት ይሆን ብዬ

ታዲያ እንዴት የሌለሽን አመል ዝም ልበል ችዬ

ሶስተኛው ስንኝን አንብቡት። “ምናልባት አስቤ ይሆናል፤ ከፍቷት ይሆን ብዬ” ... እንዲህ ተንዛዝቶም ግልፅ መልእክት አልያዘም። “ከፍቷት ይሆን?” ብሎ ማሰቡንና አለማሰቡን እርግጠኛ አይደለም ማለት ነው? ሌላ ስንኝ ስናነብ ደግሞ፤ ለካ ከማሰብ አልፎ፤ “ከፍቷታል” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። በዚያ ላይ፤ አነጋገርሽ አልጣመኝም ሲል የነበረው ሰውዬ፤ “አልናገርም” ብላ ያስቸገረችው ይመስል፤ “ቁርጡን ካልነገርሽኝ” ብሎ ይወተውታል።

ተይ አታስጨንቂው ልቤን ሲከፋሽ አይወድም

ካልነገርሽን ቁርጡን ዛሬ ከጎንሽ አልሄድም

በአጠቃላይ፤ “ጨዋታሽ” የሚለው ዘፈን፤ የአልበሙ የመጨረሻ ዘፈን እንዲሆን መደረጉ ተገቢ ነው። አስረኛ ቁጥር ላይ የተቀመጠው “ፊዮሪና”ም ትክክለኛ ቦታውን አግኝቷል - “ካብ ዳህላክ” ከሚለው ዘፈን የተለየ ሃሳብ ይዞ የመጣ አይመስለኝምና። አይ፤ ሁለቱ ዘፈኖች ምንም ተመሳሳይነት የላቸውም የሚል ሰው ካለ ግን፤ ይሁንለት ብዬ ባልፈው ይሻላል። በነገራችን ላይ፤ “ፊዮሪ” በጣልያንኛ፤ “አበባ” እንደማለት ነው። “ፊዮሪና” ሲሆን፤ እንደ “ሲኞሪና” ወይዘሪት የሚል ስሜት ይኖረው ይሆናል። ያው፤ ከጣልያን ቅኝ ግዛት ጋር የመጣ ስያሜ ነው - ፊዮሪና። ከዚሁ ጋር አያይዘን፤ ወደ “ጥቁር ሰው” እንሸጋገር።

 

“ጥቁሩ ሰው”፤ ጠይም ቢሆን ኖሮስ?

“ጥቁር ሰው” የሚለው ግጥም ደህና ነው የምልበት ምክንያት፤ በተወሰነ ደረጃ ጥርት ያለ የሃሳብና የስሜት መልእክት ስለያዘ ብቻ አይደለም። የቃላት አጠቃቀሙና አገላለፁም ደህና ነው። የሌለ “ሰምና ወርቅ” ወይም አንድምታ ለማውጣት ሳንንቀዠቀዥ ግጥሙን ካየነው፤ በአድዋው ጦርነት የውጊያ ጀግንነትን እንደሚገልፅ አያከራክርም። የግጥሙ መልእክት እዚህ ድረስ ነጥሮና ጎልቶ ወጥቷል።

በአገላለፅ በኩልም፤ በደፈናው “አቤት ጀግንነት”፤ “ጉድ የሚያሰኝ ጀብድ”፤ “እናንተን የመሰለ ጀግና የትም አይገኝ”... ምናምን እያለ ተድበስቦ አይቀርም፤ ጀግንነትን ለማሳየት ይሞክራል እንጂ። “መድፉን ጣለው ተኩሶ”፤ “ሰልፉን በጦር አሰመረው”፤ “ሳንጃ ጎራዴው ቀላ” የሚሉት አገላለፆች በምሳሌነት ይጠቀሳሉ። በመልእክትና በአገላለፅ ረገድ ግጥሙ ደህና ቢሆንም፤ ትልቅ ጉድለት አለበት። የአድዋው ጀግንነት ከ”ጥቁር ሰው” ጋር በየትኛው ሃሳብና አገላለፅ አማካኝነት እንደሚገናኝ ግልፅ አይደለም። የያኔው ዘመን ኢትዮጵያውያን ከጣልያን ጦር ጋር የተዋጉት፤ “ወራሪ መጣብን” በሚል እንጂ፤ “ነጮች መጡብን” በሚል ብቻ አይደለም። ከሱዳን ወይም ከሶማሊያ በኩል፤ ጥቁር የቆዳቸው ቀለም ያላቸው ወራሪዎች ቢመጡ፤ ኢትዮጵያውያን እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡማ።

ጠይም ይሁን ቢጫ፤ ነጭ ይሁን ጥቁር፤ ለወረራ የሚመጣባቸውን ጦር መዋጋታቸው ክብር አለው - ለነፃነት ሲባል የተፈፀመ ነዋ፤ ነፃነትን ከማፍቀር የሚመነጭ ጀግንነት ነዋ። ጥቁር ከመሆን የመነጨ አይደለም። ማንኛውንም ወረራ ለመከላከል ከመዋጋት ይልቅ፤ የቆዳ ቀለም እየለየ የሚዋጋ ከሆነ ግን፤ ነገርዬው ከነፃነት ፍቅር የመነጨ ጀግንነት ሳይሆን ከዘር ጥላቻ የመነጨ እብደት ይሆናል - አሳፋሪ ዘረኝነት ልትሉት ትችላላችሁ። ታዲያ፤ የአድዋውን ጦርነት የምናደንቀው፤ ከነፃነት ፍቅር የመነጨ ጀግንነት ስለተፈፀመበት ነው? ወይስ፤ ጥቁሮች ነጮችን ስላሸነፉ? “ጥቁር ሰው” የሚለው ግጥም ላይ የሚታየው ትልቁ ጉድለት፤ ከእነዚህ ጥያቄዎች ጋር የተያያዘ ነው። አብዛኞቹ የግጥሙ ስንኞች ከግጥሙ ርእስ ጋር ብዙም ሳይተሳሰሩ የቀሩትም በዚሁ ምክንያት ይመስለኛል።በተመሳሳይ ሁኔታ፤ የዘጠነኛው ዘፈን ግጥም ውስጥም፤ ርእስና ይዘት ተራርቀዋል። የግጥሙ ርእስ “ጸባየ ሰናይ” የሚል ቢሆንም፤ ግጥሙ ውስጥ የጸባይ ነገር ተረስቷል ማለት ይቻላል። በእርግጥ በጸባይ ላይ ያተኮሩ ሁለት ስንኞች በግጥሙ ውስጥ ተካተዋል፤ ግን በደካማ አገላለፅ ሳቢያ መክነዋል።

ያንስብሻል የኔ መልካም ያመል ሙዳይ

ሰው አለ ወይ ውብ እንዳንቺ ጸባየ ሰናይ

ስለ አድዋው ጀግንነት ሲፅፍ በደፈናው “ማን አለ እንደነሱ ጀግና” እያለ ጊዜ አላባከነም። ከ”መድፍ”፣ ከ”ጎራዴ”፣ ከ”ጦር” ጋር በተጨባጭ አያይዞ ጀግንነትን ለማሳየት ሞክሮ የለ? እዚህ ላይ ግን፤ “እንዳቺ ማን አለ ጸባየ ሰናይ” በማለት ጉዳዩን ከመደጋገም አልፎ፤ መልካም ጸባይን ለማሳየት የምትችል አንዲት ስንኝ አላስገባም። በርካታ ስንኞች ደግሞ፤ ከግጥሙ ርእስ ውጭ የአካል ቁንጅናን ለመግለፅ የሚሞክሩ ናቸው። ለነገሩማ፤ የዘፈኑ የመጀመሪያ ስንኞች ስለህልም የሚያወሩ ናቸው። ለምን እንዳስፈለጉ አላውቅም። ስንኞቹ ባይሰረዙ እንኳ፤ በስምንተኛ ቁጥር ላይ ወደ ተቀመጠውና “ህልም አይደገምም” ወደሚለው ግጥም ቢሸጋሸጉ ይሻል ነበር - ድግግሞሽን ለማስቀረት ይጠቅማል።

 

 

 

Read 6624 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 08:54