Saturday, 06 April 2019 15:44

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

"ሰው በማሰብ ሃይሉ ከሚገለጥባቸው ድርጊቶች ሌላ የተደበቀ ነፍስ የለውም"
                           
አንድ በቀቀን (ፓሮት) ነበረች አሉ… ብልህ፡፡ ያየችውንና የሰማችውን እንደ ሌሎቹ ቢጤዎቿ መደጋገሟ አያስገርምም፡፡ የሚያስገርመው በ ‹ሎጂክ› መቀለዷ ነው፡፡ ይኸ ፀባይዋ ባለቤቷን ያዝናናዋል፡፡ ለምሳሌ፡- አንድ ቀን አብረው ሲንሸራሸሩ ዝናብ ማካፋት በመጀመሩ ባለቤቷ ተበሳጭቶ … “ኤጭ! ይኸ ዝናብ… ባለጌ!” እያለ ሲያማርር ስለሰማች፣ ከብዙ ጊዜ በኋላ የንስሃ አባቱ መጥተው ቤቱን ጠበል ሲረጩ “ኤጭ! ይኸ ዝናም … ባለጌ!” በማለት አስደንግጣቸዋለች፡፡ በሌላ ጊዜም እንዲሁ ሲንሸራሸሩ ጥቁር ከረባት ያሰረ ሰው ሲገፋው “ስቱፒድ!” ብሎ ሲሳደብ ስለሰማች፣ ጥቁር ከረባት ያሰረ ሰው ስታይ “ስቱፒድ! ስቱፒድ!” እያለች ትሳደባለች፡፡ መነፅር ያደረገችን ሴት “የኔ ቆንጆ” ብሎ ሲጣራ ሰምታ፣ መነፅር ያደረገች ሴት ስትመለከት “የኔ ቆንጆ! የኔ ቆንጆ!” እያለች ትጣራለች፡፡
የወፏ ባለቤት “የተከበረና የሞላለት” የሚባል ሰው ነው … የመፍለጥ፣ የመቁረጥ አቅም ያለው፡፡ አንድ ቀን፣ አልፎ፣ አልፎ እንደሚያደርገው የከተማዋን ‹ትላልቅ› ሰዎችና ሹሞች ቤቱ ጋብዞ እያዝናናቸው ሳለ ዘግይቶ የመጣ፣ ነጭ ኮፍያ ያደረገ እንግዳ ወደ ሳሎኑ ሲገባ የተመለከተችው ፓሮት፤ “አሳይሃለሁ! ጠብቀኝ” እያለች ሰውየው ላይ መዛት ጀመረች፡፡ በአካባቢው የነበሩት ሁሉ ሳቁ፡፡ በግብዣው መሃል ሰውየው ኮፍያውን አውልቆ በኪሱ በማድረግ ወደ ፓሮቷ ሄደ፡፡ … ምንም አላለችም፡፡ ኮፍያውን መልሶ ሲያደርግ ግን እንደ ቅድሙ መዛቷን ቀጠለች፡፡ ኮፍያውን አውልቆ በኪሱ ሲያደርግ … ዝም አለች፡፡ ሰውየው ወደ እንግዳ መቀበያው ሄዶ፣ ጥቁር ኮፍያ በውሰት አደረገና ወደ ፓሮቷ ተመለሰ፡፡ ምንም አላለችም፡፡ እሱን አውልቆ ነጩን ሲያጠልቅ “አሳይሃለሁ! ጠብቀኝ!” በማለት ለፈለፈች፡፡
… እንግዳው ትንሽ ሲያስብ ከቆየ በኋላ ግብዣውን አቋርጦ ባልተለመደ ሰዓት ወደ ቢሮው በመግባት ፋይል ማገላበጥ ጀመረ፡፡ ሌሊቱ ሲጋመስ ወደ ቤቱ ቢሄድም እንቅልፍ አልወሰደውም፡፡ ስለ ፓሮቷ ሲያወጣና ሲያወርድ ነጋ፡፡ … ለምን ይሆን?
***
ወዳጄ፡- እውነትና ፍትህ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ይምሰሉ እንጂ አይለያዩም፡፡ ሁለቱም ሩቅ የምንፈልጋቸው ነገር ግን አብረውን እየኖሩ በቀላሉ የማንረዳቸው የሃሳብ ኤለመንቶች ናቸው፡፡ … “እግዜርና ተቃራኒው” እንደምንለው፡፡ በዘልማድ አስተሳሰብ በ “ቋሚነት” የምንወዳቸውና የምንጠላቸው እየመሰለን የምንታለልባቸው ሀሳቦች ጥቂት አይደሉም፡፡ በደቂቃ ልዩነት የኑሮ ማዕበል ስሜታችንን ሲያንገጫግጨው የጠላነውን ወደን፣ የወደድነውን ልንጠላ እንደምንችል እንዘነጋለን፡፡ ስሜታችን፤ከአዕምሯችን ጋር ሳይዋሃድ የሚገነፍል ሀሳብ ሲሆን አዕምሯችን ደግሞ የቀዘቀዘና የረጋ ስሜት በመሆኑ፡፡
ወዳጄ፡- መኖር ‹ማሰብ› እስከሆነ ድረስ ‹ዛሬ› የምንለው ቀን ‹ስሜት›፣ ‹ነገ› የምንለው ደግሞ ሃሳብ ሊሆን ይችላል፡፡ የሚገርመው ዛሬን ስናልፍ ነገን አለማግኘታችን ዕሙን መሆኑ ነው፡፡ እዛ ጋ የሚጠብቀን ‹ሌላው ዛሬ› ስለሆነ፡፡ ወይም ደግሞ ነገን የሚያገኘው “የዛሬ እኛነታችን” አይደለም ማለት ነው፡፡ እሱ በእንቅልፋችን ውስጥ ሟምቷል፡፡ የሚቀረው በውስጡ የተወለዱት አዲስ ሰውና አዲስ ቀን ብቻ ናቸው፡፡ እነሱ ስሜታችን ከፍና ዝቅ እያለ በሚዋዥቅበት፣ ‹ዛሬ› በምንለው የሃሳብ ሞገድ እየተናጡ ያድጋሉ፡፡ እውነት የዚህ ሞገድ መንፈስ ናት፡፡ በኑሮ ኮርቻ ላይ ተፈናጠን የምንንከራተተው የዚህን መንፈስ ትርጉም ወይም ፍቺ ለማወቅ ነው፡፡ በየቤተ እምነቱ ከሰባኪዎች አንደበት፣ ከወላጆቻችን ከራማ፣ በጓደኞቻችን ጨዋታ መሃል፣ ከምናነሳቸው መጽሃፍት ውስጥ እንፈልገዋለን … እድሜያችንን ሙሉ፡፡ ብዙዎቻችን ሳናገኘው ሳናውቀው፣ ሳንረዳው እንተላለፋለን፡፡ ምክንያቱም ውስጣችን - ሃሳባችን፣ ሃሳባችን - እውነታችን፣ እውነታችን ደግሞ ‹እኛ› መሆናችን ስላልገባን!! በዚህ አውድ፤ ዕውቀት፣ ፍትህ፣ ሰላምና ወዘተ የሚባሉ ነገሮች ከ‹Proximity sense› ጋር የተቆራኙ ይመስለኛል፡፡
“አዕምሮ የሃሳባችን ሌላው ስም ነው፣ መጀመሪያና መጨረሻ የሌላቸው፣ በየጊዜው ሲቋጠሩና ሲተረተሩ የሚኖሩ ሃሳቦች… ግንዛቤያችን፤ የማስታወስ ችሎታችን፣ ስሜታችን ሁሉ፡፡ ሰው በማሰብ ሃይሉ ከሚገለጥባቸው ድርጊቶች ሌላ የተደበቀ ነፍስ የለውም" በማለት የፃፈልን ፍራንሲስ ቤከን ነው፡፡
***
ወደ ጨዋታችን እንመለስ፡- ባለ ነጭ ኮፍያው ሰውዬ የከተማዋ የፀጥታ ሹም ነበር፡፡ ባለ ምጡቅ አዕምሮና እውነተኛ የሚባል ሰው ነው፡፡ በዚያን ቀን ሲያስብ የነበረው በድንገት ሞቶ ስለተገኘው የህግ ጠበቃ ነበር፡፡ በወንጀሉ ተጠርጥሮ የተፈረደበት ሰው እየደጋገመ ንፅህናውን ቢናገርም ሰሚ አላገኘም፡፡ በሃሰት ምስክሮችና በባለስልጣናት ተፅዕኖ የማይታመነውን ተገዶ በማመን ዕድሜ ልክ እንዲታሰር የተወሰነበት፡፡ የከተማው ሰው የሚያንሾካሹከው ግን ገዳዮቹ ሌሎች መሆናቸውን ነው፡፡ ይኸም የፀጥታ ሹሙን ለጉዳዩ እንዲጨነቅ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ሟች ነጭ ኮፊያ ማድረግ እንደሚያዘወትር፣ ከመሞቱ ሁለት ቀናት በፊት ደንበኛው ከሆነው የዛሬው ጋባዥ ቤት እንደነበረ፣ ሲወጣም የተበሳጨ ፊት እንደታየበት ቢያውቅም፣ ከጥርጣሬ ባለፈ ሰውየውን የሚያስከስስ በቂ ምክንያት ግን አላገኘም፡፡ … ዛሬ ግን መስኮት ተከፍቶለታል - ዕድሜ ለፓሮቷ!!
ወዳጄ፡- እያየን የማናስተውላቸው ወይም ልብ የማንላቸው፣ እየሰማን የማናዳምጣቸው ነገሮች ብዙ ናቸው … የቅርብ ሩቅ የሚሆኑብን፡፡ “Far in the eyes” እንደሚሉት፡፡ ነገሮችን ለማገናዘብና ወደ ትክክለኛ ድምዳሜ መድረስ የምንችለው ደግሞ አዕምሯችንን ትኩረት በማስተማርና በትክክል ማሰራት ስንችል ነው፡፡ አዕምሮን ለመገንባትና በትክክል ለማሰብ ደግሞ መጀመሪያ ከታሰረበት ነገር (የዘር ፖለቲካና ወገናዊነት ወዘተ) መፈታት አለበት፡፡ ብዙዎቻችን ሰብዓዊነት የሚያስነክሰን፣ የወፏን ያህል እንኳ ‹ሎጂካል” መሆን ያልቻልነው ለዚህ ይመስለኛል፡፡ ነገ ዛሬ ውስጥ ይወለዳል ሲባል የሚለወጠው እኛ እንጂ ቀኑ አለመሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ እዚች ጋ ‹ነገ› የምትለዋን ግጥም ልጋብዝህ፡-
ጓዙን አግተልትሎ
እኔን መስሎ ደግሞ
ይጠቃቅሰኛል
የምናፍቀው ቀን
የማላውቀው ነገ
ዛሬ ነኝ ይለኛል
ይኸው ፊቴ ቆሞ፡፡
እባክህ አትምጣ
እኔው እመጣለሁ
ደግሞ ዛሬ ብዬ
እሞኝብሃለሁ፡፡
በነገራችን ላይ “አለማሰብ በራሱ ክፉ ሃሳብ ነው (There is only one evil thought; refusal to think") ይላሉ ሊቃውንት፡፡ ትስማማለህ ወዳጄ?

ሠላም!!

Read 1131 times