Sunday, 07 April 2019 00:00

ከአፋርና ከትግራይ ብንማርስ?

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(3 votes)


               የታሪክ ምሁራን እንደ ቀልድ፣ እንደ ዋዛ ደጋግመው የሚናገሯት አባባል አለች፡፡ እንዲህ ይላሉ፡- “የትናንት ፖለቲካ የዛሬ ታሪክ ነው፡፡ የዛሬ  ፖለቲካ ደግሞ ነገ ታሪክ ይሆናል” ይላሉ፡፡ በዚህ ድንቅ አባባል መሰረት፤ ዛሬ በሀገራችን እየተከናወነ ያለን ፖለቲካ በትኩሱ ከትበን ካላስቀመጥነው የነገ ታሪካችን ጉድለቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ መጠርጠር ብልህነት ነው፡፡ ዛሬ ብዕሬን ያነሳሁት በዚህ ታሪካዊ ወቅት እየተፈጸሙ ካሉ ጉዳዮች ውስጥ አንዷን አንስቼ ሃሳብ ለማካፈል በማሰብ ነው፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከሰማናቸውና በዚህም ወቅት ደጋግመን እየሰማናቸው ካሉ ጉዳዮች አንዱ ለዘመናት አብረው የኖሩ፣ ክፉና ደጉን አብረው ያሳለፉ፣ በጋብቻና በልዩ ልዩ ማህበራዊ ትስስሮች ተቆራኝተው ዘመናትን ያስቆጠሩ ማህበረሰቦች ድንገት ከመሬት ተነስተው “አንተ መጤ፣ ሰፋሪ ነህና ውጣልኝ” የማለታቸው እርግማን፣ የህዝብ መፈናቀል ነው፡፡
በዚህም መሰረት በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰ ግጭት ይህን ያህል ሺህ ህዝብ ተፈናቀለ፣ በጌዲኦና በጉጂ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ይህን ያህል ሺህ ህዝብ ለርሃብ ተጋለጠ፣… የሚለው ዜና የመገናኛ ብዙሃን መክፈቻ ከሆነ ዋል አደር እያለ ነው፡፡ “ከክልሌ፣ ከዞኔ፣ ከወረዳዬ፣… ውጣልኝ” ተባለ የሚለው ዜና፣ ማህበራዊ ሚዲያውን ማጨናነቁ የእለት ተእለት ክስተት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
የውጣልኝ ዘመቻው መቼ ተጀመረ? ምክንያቱ ምንድነው? የዚህ ዘመቻ አቀንቃኞች በዋናነት እነማን ናቸው? ለምን? ማን ማንን ነው ውጣልኝ እያለ ያለው? እውነት ህዝብ ህዝብን “የዓይንህ ቀለም አላማረኝም” ብሎ እያፈናቀለና ውጣልኝ ብሎ እያባረረ ነው?... የሚሉት ጥያቄዎች በጥናት ምላሽ ቢያገኙ ወደፊት የሚመጡ ትውልዶች ከስህተታችን ይማሩበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡
እስከ አሁን ባለው “የውጡልኝ ዘመቻ” ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ ውጣ መባሉን ያልሰማነው በሁለት ክልሎች ብቻ ነው፡፡ እነዚህም ሁለት ክልሎች ትግራይና አፋር ናቸው፡፡ የመጠን መለያየት ካልሆነ በስተቀር በሌሎች ክልሎች ችግሩ ተንጸባርቋል፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በደቡብና በቤንሻንጉል ክልሎች የነበረው የውጡልኝ ግፊት መጠኑ የሰፋ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በዚህ የውጡልኝ ግፊት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተፈናቅሎ የእለት ደራሽ እርዳታ ጠያቂ መሆኑ ይነገራል፡፡
በአፋርና በትግራይ ክልል “ውጡልኝ” የሚለው አስነዋሪ እርምጃ ያልተወሰደ መሆኑ የሚያስደስት ነው፡፡ እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው መሰረታዊ ጥያቄ፣ በእነዚህ ሁለት ክልሎችስ ጥያቄው ለምን አልተነሳም? የሚል ነው፡፡ በርካታ ምክንቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡አንድ ጋዜጠኛ ወዳጄ “የትግራይየፖለቲካማኅበረሰብኢትዮጵያውስጥበተሻለደረጃየሚናበብማህበረሰብ ነው፡፡ ለድጋፍምለተቃውሞምአይቸኩልም፡፡ ሰከንማለትይችላል፡፡ በመላሀገሪቱ ‘የተደምረናል’ሰልፎችሲቀጣጠሉትግራይበአርምሞ ነበር ያሳለፈቺው፡፡ የሚናበብናየሰከነማኅበረሰብስለተፈጠረይመስለኛል ውጡልኝ የሚል የማፈናቀል እርምጃ ሊወሰድ ያልቻለው፡፡ ወደድንምጠላንምይህንንመቀበልአለብን” ብሎ ፌስቡክ ገጹ ላይ ጽፎ አንብቤአለሁ፡፡
በርግጥም በትግራይ እንደ መሀል አገር ለውጥ መጣ ብሎ መጯጯህ የለም፡፡ ድልቂያና ዳንኪራ የለም፡፡ በስሜት መሳከር የለም፡፡ ከለውጡ በፊት በትግራይ ሊፈነዳ የደረሰ የህዝብ ቁጣ ነበር፡፡ ለውጡ በመሀል ሀገር ፈንድቶ ከፌዴራል የስልጣን ማማ ላይ የወረዱት ዋና ዋናዎቹ የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን ተሰባስበው ወደ ትግራይ በመሄድ የበሰበሰውን የክልሉን አመራር በተወሰነ ደረጃ ሲቀይሩት ሊፈነዳ ደርሶ የነበረው የህዝብ ቁጣ ረገብ አለ፡፡ “እነዚህ ሰዎች ወደዚህ የመጡት እስከ ዛሬ የበደሉንን ሊክሱ ነው” የሚል መንፈስም በህዝቡ ላይ ያደረ ይመስላል፡፡ የህዝቡ ጩኸት ረገብ ያለበት አንዱ ምክንያት ይሄ ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት የህወሓት የአንድ ለአምስት ጥርነፋ ዛሬም በክልሉ አለመፈራረሱ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ አመራሩ ህዝቡን “ተከበሃል፣ ካለ እኔ ማንም ሊደርስልህ አይችልም…” እያለ በማስፈራራቱ እንደሆነ ጭምጭምታዎች ይሰማሉ፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በትግራይ የታየው የህዝቡ መንፈስ የሚደነቅ ነው!
በዶ/ር ዐቢይ የመንግስት አስተዳደር ደስተኛ ያልሆኑት የትግራይ አክቲቪስቶችበበኩላቸው፤ በሶሻል ሚዲያ የሚጽፉት ጠቅላይ ሚኒስትርዐቢይላይትኩረት አድርገው ነው፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩየበቀሉበትንማኅበረሰብ ሲሳደቡ አይታዩም፡፡ (ባለፉት ዓመታት ህወሓት መራሹን ኢህአዴግ ሲታገሉ የነበሩ የመሀል አገር አክቲቪስቶች ግን አቶ መለስንም፣ ወይም ሌሎች የትግራይ ፖለቲከኞችንም፣ ህወሓትንም፣ ትግራይንም፣ የትግራይን ህዝብም ጭምር አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያዊ ስነ-ምግባር ባፈነገጠ መልኩ ይተቹ፣ ይሳደቡ ነበር፡፡)
ይህየትግራይ ክልል ዜጎች አካሄድ ከስክነት፣ስትራቴጂክ“ጠላትን”ለይቶ ከማወቅናፖለቲካንበአግባቡ ከመረዳትየመነጨ እስተውሎት ይመስለኛል፡፡ በዚህ የሽግግርና የግርግር ወቅት እንዲህ ያለው ብስለት የተሞላበት አካሄድ አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡ ሌሎችም በአርኣያነት ቢከተሉት መልካም ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ ከትግራይ አክቲቪስቶች ያስተዋልኩት ጉድለት ቢኖር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወይም ሌላ የፖለቲካ ባላንጣ ነው የሚሉትን ሰው በሚተቹበት ወቅት የተለያዩጸያፍ ቃላትንና ቅጽል ስሞችን ጨማምረው ማንጓጠጣቸውና መዝለፋቸው ነው፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ተገቢስላልሆነ ሊታረም ይገባል፡፡ ሳይሳደቡ ሃሳብን በመጻፍ መከራከር ወይም መተቸት የስልጡኖች መንገድ መሆኑን ልብ ሊሉትያስፈልጋል፡፡
“ዳጉ” በሚሉት ባህላዊ የመረጃ መቀባበያ ዘዴ የሚታወቁት አፋሮችም ቢሆኑ በክልሉ ውስጥ አብረዋቸው ለዘመናት የኖሩ ማህበረሰቦችን “ውጡ” ሲሉ አልታዩም፣ አልተሰሙም፡፡ በዚህም ምክንያት በአፋር የተፈናቀለ ማህበረሰብ የለም፡፡ ይህም ሁኔታ የአፋሮችን የተረጋጋ አመለካከትና ጨዋነት የሚያሳይ ተግባር ነው፡፡በኔ ግምት “የውጡልኝ ዘመቻው” ገፊ ምክንያት የመንጋነት አስተሳሰብና አካሄድ  ይመስለኛል፡፡ ሰዎች በራሳቸው አስተሳሰብ ውስጥ ከሆኑ ተረጋግተው ማሰብ ይችላሉ፡፡ ተረጋግቶ የሚያስብ ሰው ደግሞ በአእምሮው አስቦ ሚዛኑን የጠበቀ ተግባር ከመፈጸም ውጪ ወደ ጥፋትና የጉልበት እርምጃ አይሄድም፡፡ ቢሄድም የጥፋቱ መጠን ከመንጋው ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ነው፡፡
በመሰረቱየሀገራችን ፖለቲካ ተገማች አይደለም፡፡ አይሆንም የተባለው ይሆናል፤ ይሆናል የተባለው አይሆንም፡፡ በዚህም ምክንያት በእነዚህ ሁለት ክልሎች ነገ ከነገ ወዲያ ይህ አይፈጸምም ብሎ ለመደምደም የሚያስችል ዋስትና የለም፡፡ ምክንያቱም አፋር ክልል አጎራባች ከሆኑት ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከትግራይና ከሶማሌ ክልል ማህበረሰቦች ጋር ያልተቋረጡ የድንበር ላይ ውዝግቦችና ከግጦሽ መሬት ጋር የተያያዙ ግጭቶች አሉት፡፡ የትግራይ ክልልም ከአማራና ከአፋር ክልሎች ጋር የመሬት ይገባኛል ውዝግቦችና ግጭቶች ነበሩት፣ ዛሬም እልባት አላገኙም፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ምክንያት ነገ ከነገ ወዲያ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን የእነዚህ ክልሎች የአስተዳደር አካላትና ማህበረሰቦች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
ለኦሮሚያ የፖለቲካ ልሂቃን አንድ መልእክት አለኝ፡፡ “ፖለቲካ” ለሚለው ጽንሰ ሃሳብ ከተሰጡት ትርጉሞች ውስጥ “የህዝብን ችግሮች በቅደም ተከተል (priority) በማስቀመጥ የሚሰጥ ውሳኔ ነው” የሚለው ይገኝበታል፡፡ ችግሮች ሁሉ ተመሳሳይ ባህሪ የላቸውም፡፡ አንዳንዶቹ ችግሮች ጊዜና ፋታ ይሰጣሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የህልውና ጉዳይ ይሆናሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ጊዜ ካለፈ በኋላ መፍትሄ ቢያገኙ ትርጉም አይኖራቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት ከፖለቲከኞች የሚጠበቀው አንዱና ዋነኛው ነገር ችግሮችን በቅደም ተከተል አስቀምጦ፤ ካለው ሀብት፣ ውጫዊና ውስጣዊ ሁኔታ፣ ውሳኔው ከሚያስገኘው ጥቅም አኳያ ብቻ ሳይሆን በዚያ ውሳኔ ምክንያት በሌሎች ላይ ሊደርስ የሚችልን የጉዳት መጠን ግምት ውስጥ በማስገባት ሚዛናዊና ተጨባጭ ሁኔታውን ያገናዘበ (pragmatic) ውሳኔ መስጠት ነው፡፡
ከዚህ የፖለቲካ መርህና የአሰራር ስርዓት አኳያ በተለይ የኦሮሚያ ፖለቲከኞች ከትግራይና ከአፋር ትምህርት መውሰድ ይገባቸዋል፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ያነሱትን እሰጥ አገባ ቆም ብለው ሊመረምሩት ይገባል፡፡ ይህ አጀንዳ በዚህ ወቅት እንዲነሳ ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል? የሚለውን የቅደም ተከተል (priority) ጉዳይ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡በሌላ በኩል፤ኦሮሚያ የመሬት ችግር የሌለበት ሰፊ ክልል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሲሆን ሲሆን እንደ ቨርጂኒያ እና እንደ ሜሪላንድ (ለአሜሪካ ዋና ከተማ ለዋሺንግተን ዲሲ መሬት ቆርሰው እንደሰጡት) ለአዲስ አበባ መስፋፊያ የሚሆን መሬት በሊዝ ወይም በነፃ ለ“ፊንፊኔ” መስጠት የሚያስችል አቅም አለው፤ ክልሉ፡፡ የአዲስ አበባ መሬት ነዳጅ ዘይት ወይም ወርቅ ወይም ሌላ የማዕድን ሀብት የተገኘበት ይመስል ጎምቱዎቹ ፖለቲከኞች ጭምር ወቅታዊ ባልሆነ አጀንዳ ስማቸው መነሳቱ ያሳዝናል፡፡ ይህንን አጀንዳ በህገ መንግስቱ መሰረት ቀስ ብሎ ማየት ይቻላልና ረጋ ብለው ቢያጤኑት መልካም ነው፡፡
በአጀንዳ ቅደም ተከተል (priority) መፋለስ ምክንያት በአዲስ አበባ ጉዳይ ሲነታረኩ ዛሬ በኦሮሚያ ያለው የልማት ጉዳይ፣ የኢንቨስትመንት ጉዳይ፣ የፀጥታና ሰላም ጉዳይ አረም የተጫነበት መሆኑ ይስተዋላል፡፡ ትናንት አደባባይ ወጥቶ ሲጮህ የነበረ ቄሮ፤ ስራ እንደሚፈልግ ረስተው አሁንም “… ኬኛ፣ …ኬኛ” የሚል መፈክር አስይዘውበየአደባባዩ ያንከራትቱታል፡፡ እንዲህ ያለውን አካሄድለአብሮነታችን አይበጀንምና ነገ ዛሬ ሳይሉ ጋብ ቢያደርጉት ተገቢ ነው ብዬ  አስባለሁ፡፡
የተሸከምነውለሦስትሺህ ዘመንየተጠራቀመኮተትአላላውሰንስላለነውወደፊት መራመድአቅቶንየምንነታረከው፣በየወንዙ የምንማማለውና የምንጋደለው፡፡አሜሪካኖችየተባበረችአሜሪካንን በፌዴሬሽን ካቋቋሙበኋላያደረጉትነገርእውነተኛታሪካቸውንመጻፍና ለዚያእውቅናመስጠትነበር፡፡ እኛ ይህንን እንዳናደርግ ያገደን ነገር ይኖር ይሆን? ወይስ በስሜት መሳከራችንና መደማመጥ አለመቻላችን ጋረደን? ለማንኛውም ግርዶሹ እስኪገፈፍ የትግራይንና የአፋርን ተሞክሮ ተግባራዊ ብናደርገው መልካም ነው፡፡
*******
    ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው፡-ahayder2000@gmail.


Read 754 times