Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 02 June 2012 08:45

“የመንግስትን ፖሊሲ መፈተሽ የኢትዮጵያውያን ሥራ ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ወይዘሮ ሊስሎር ሳይረስ፣ ወደዚህ አገር ከመጡ ሁለት ዓመት ባይሞላቸውም የተለያዩ የኢትዮጵያን ክፍሎች ጎብኝተዋል፡፡ አምባሳደሯ ስለ ሁለቱ ሀገራት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ግንኙነቶች ሲናገሩ፤ በሰብአዊ መብት ጉዳይ ዙሪያ አስተያየት ተጠይቀዋል፡፡ ከ7 ሚ. በላይ ሰዎች ራሳቸውን እንዲችሉ ያደርጋል ተብሎ የተጀመረው የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ውጤታማነት አጠያያቂ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር፤ ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ቀውስ ያደረሰው ተፅእኖ ላይም ተናግረዋል፡፡ የጀርመን የኢኮኖሚ ጥንካሬ ከምን የመነጨ እንደሆነ የገለፁት አምባሳደር ሊስሎር፣ የጀርመን ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ በብዛት አለመምጣታቸውን በተመለከተም ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኞች መልካሙ ተክሌ እና መንግስቱ አበበ ጋር አጭር

ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡

የፀረ-ሽብርተኝነት ህጉ እና የሚዲያ ሕጉ ያሳስቡናል

በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያና የጀርመን የንግድ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ወደ ጀርመን የምናስገባውን የኢትዮጵያ ምርት መ160 ሚ.ዩሮ ወደ 240 ሚ.ዩሮ  ጨምሯል፡፡ ጀርመን ዋነኛ የኢትዮጵያ ቡና ተቀባይ (ኢምፓርተር) ነች፡፡ ከኢትዮጵያ የቡና ምርት 30% ያህሉ ወደ ጀርመን ነው የሚላከው፡፡ ከጀርመን ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው ምርት ግን ተዳክሟል!! 140 ሚሊዮን ዩሮ የነበረው ወደ 120 ሚ.ዩሮ ቀንሷል፡፡ ከጀርመን የሚላከው ምርት የቀነሰው ኢትዮጵያ ኢምፓርት የሚደረጉ ምርቶችን በአገር ውስጥ የመተካት ፖሊሲ በመከተሏ ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ወደ ጀርመን የምትልከው ምርት በጎ አቅጣጫ ይዟል፡፡ አሁንም  በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት የማስፋት ዕድልና አማራጮች አሉ፡፡

በሰብዓዊ እርዳታስ በኩል?

ባለፈው ዓመት ድርቅ ሲከሰት ጀርመን ለሰብአዊ ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ ሰጥታለች፡፡ በሁለቱ መንግስታት መካከል በተደረገ ስምምነት መሠረት፣ ለሶስት ዓመት 102 ሚሊየን ዩሮ ተሰጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በጀርመን የትብብር ሚኒስቴር በከፊል ፋይናንስ የሚደረጉ መንግስታዊ ያልሆኑ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ለምሣሌ በጀርመን ግብርና ሚኒስቴር የሚደገፍ የግብርና ቁሳቁስና የእርሻ ሜካናይዜሽን ተቋማት እና የሥልጠና ማዕከሎች አሉ፡፡ የዘር ማሻሻያ ፕሮጀክቶች ላይም ይሰራል፡፡ በሦስትዮሽ ትብብር ማለትም በኢትዮጵያ፣ በጀርመን የአካባቢ ሚኒስቴር እና በእስራኤል መንግስት የሚካሄድ የመስኖ ፕሮጀክትም አለ፡፡

በሀይል አቅርቦት ላይም እርዳታ ትሰጣላችሁ፡፡ ነገር ግን በአነስተኛ ዋጋ ከሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ብዙ ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን አታደርጉም፡፡ ከዚያ ይልቅ፤ ብዙ ሰዎችን ለማይጠቅም የፀሐይ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ከፍተኛ ገንዘብ ታወጣላችሁ፡፡ የምትሰሩዋቸው ፕሮጀክቶች ምን ይመስላሉ?

ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ባለፈው ዓመት የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል ጀርመን የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች፡፡ በጂአይዜድ ለሚንቀሳቀስ ድርቅ መቋቋሚያ ፕሮጀክት ስድስት ሚሊየን ዩሮ ረድታለች፡፡ በትግራይ የተገነባው ግድብ የድርቅ መቋቋሚያ ፕሮጀክቱ አካል ነው፡፡ የኃይል አቅርቦትን በተመለከተ የመንግስቶቻችን ትብብር በሁለት ቦታዎች ላይ ያተኩራል፡፡ አንዱ ዘላቂ የመሬት አያያዝ ነው፡፡ ሌላው ትምህርት፣ ሥራ እና ገበያ መር ትምህርት ነው፡፡ አንተ የጠቀስከው፤ ያልከው በጂአይ ዜድ የሚንቀሳቀስ ተጨማሪ የኃይል አቅርቦት ፕሮግራም ነው፡፡ ጂአይዜድ ኢኮ ይባላል፡፡ ጂአይዜድ በታዳሽ ሃይል ዙርያ ይሰራል፡፡ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል የበለፀገ አቅም አላት፡፡ ውሃ ብትል የፀሃይ ኃይል፣ ንፋስ ወይም ደስ ያለህን በል፡፡ ጂአይዜድ ኤኮም በዚህ ዙርያ ሲሰራ ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይና አየርላንድ ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ ሲሆኑ ጂአይዜድ ደግሞ የፕሮጀክቶቹ ዋነኛ አስፈፃሚው ነው፡፡ የትኩረት አቅጣጫዎቹ ሁለት ናቸው፤ አሉ፡፡ አንደኛው ማይክሮ ሃይድሮ ፓወር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የፀሃይ ኃይል ነው፡፡ የፀኃይ ሃይል ማመንጫ ለምሳሌ ለሕክምና ማዕከላት ይቋቋማል፡፡ ባለፈው ዓመት ደቡብ ክልልን ስንጎበኝ በፀሃይ ኃይል የሚሰሩ መሣርያዎች ያሉት የጤና ማዕከል አይተናል፡፡ ይህም የኤሌክትሪክ አቅርቦቱን አስተማማኝ ያደርግለታል፡፡ ይህ ያልተማከለ አካባቢያዊ የኃይል አቅርቦት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደሞም፤  ማይክሮ ሃይድሮ ፓወር አለ፡፡ ኢትዮጵያ ከጥቁር አባይ እና ከአዋሽ በሚመነጨው ውሃ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ትናንሽ ወንዞች ላይም እምቅ የውሃ ሃብት አላት፡፡ እነዚህ ሁሉ ላልተማከለ የሀይል አቅርቦት ሊውሉ ይችላሉ፡፡ ባለፈው የካቲት ከኖርዌይ እና ከደች አምባሳደሮች ጋር ሆነን፤ ሁለት ማይክሮ ሃይድሮ ፓወር ማመንጫዎች በገጠር መርቀናል፡  የኤሌክትሪክ ሀይሉ ለትምህርት ቤቶች፣ ለሕዝባዊ ሕንፃዎችና ለሌሎች የየእለት ፍላጎቶች ይውላል፡፡ በማታ ብርሃን ማግኘት ከተቻለ ልጆች ያጠናሉ፡፡ ሕዝቡም ማንበብ ይችላል፡፡ ለዚህ የሚያስፈልጉ ጀነሬተሮች ሐዋሳ በሚገኘው ሰላም በተባለ ኩባንያ የተመረቱ ናቸው፡፡ ጂአይዜድ ታዳሽ ሃይል ማመንጨት ላይ ሰርቷል፡፡

ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውሱ፤ ጀርመን ለኢትዮጵያ የምታደርገው ድጋፍ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው?

ጀርመንን በተመለከተ ተፅእኖ አላሳደረም፡ በተቃራኒው ባለፈው ዓመት ትብብሩ ጨምሯል፡፡ ቢያንስ በአራት ወይም በስድስት ሚሊየን ዩሮ ጨምሯል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረንን ግንኙነት የሚያግዙ ሌሎች ተቋማትም አሉ፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያ የሚደረገው ድጋፍ ጨመረ እንጂ አልቀነሰም፡፡

በአውሮፓ ሕብረትና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት አማካይነት ጀርመን ለኢትዮጵያ የምትሰጠው እርዳታስ?

ጀርመን ከአውሮፓ ሕብረት በጀት ውስጥ 20 በመቶውን ትሸፍናለች፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ፤ በአውሮፓ ሕብረት ድጋፍ የሚከናወኑ ሥራዎችን ስታዩ ሃያ በመቶው ገንዘብ የጀርመን ድርሻ ይሆናል ማለት ነው፡፡

እርዳታ ስትሰጡ በፕሮጀክት ወይም በዘርፍ እየከፋፈላችሁ ሳይሆን፤ ገንዘቡን በጥሬው እንድትሰጡት መንግስት ይፈልጋል፡፡ ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ የጀርመን መንግስት ምን ይላል?

ባሁኑ ጊዜ የቀጥታ የበጀት ድጋፍ፤ ትኩረታችን አይደለም፡፡ ከዘርፎች ጋር የተያያዘ እርዳታ እናደርጋለን፡፡ በእርግጥ ጀርመን ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት፤ “መሠረታዊ አገልግሎት ጥበቃ” (Basic services protection) በተሰኘው ፕሮግራም ቀጥተኛ ድጋፍ ትሰጣለች፡፡ በመሠረታዊ አገልግሎት ጥበቃ እርዳታ ስንሰጥ፤ ዋናው ነገር ገንዘቡ በትክክል ስራ ላይ መዋሉን የሚያረጋግጥ የተጠያቂነት ሠንሠለት መኖሩ ነው፡፡ በኛ የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ፕሮግራሞች ላይ፤ በሲቪል ማህበረሰብ ጭምር መንግስት በተጠያቂነት እንዲሰራ ማድረግ ነው፡፡ ይህም በደንብ እየተሠራበት ነው፡፡ ገንዘቡ የት እንደሚሄድ፣ የተጠያቂነት መንገዱ ምን እንደሆነ በሲቪል ማህበረሰቡ ጭምር ይታወቃል፡፡ ስለዚህ፤ በመርህ ደረጃ የበጀት እርዳታ መስጠት አያስቸግረንም፡፡ ግን የተወሠኑ ነገሮች መሟላት አለባቸው፡፡ እስከዚያው  ከዘርፎች ጋር መሥራታችን ጥሩ ነው፡፡

በምታደርጉት ድጋፍ ቅድሚያ የምትሰጡት ለየትኛው ዘርፍ ነው?

ለትምህርት ቅድሚያ እንሰጣለን፡፡ ግን የምንሰጠው ገንዘብ ለየትኛው ትምህርት ቤት ነው የሚውለው፣ ለየትኛው ስራ ነው የሚሉት ጥያቄዎችም አሉብን፡፡  ባለፈው ዓመት በደቡብ ክልል አንድ ትምህርት ቤት አይተናል፡፡ የትምህርት ቤቱ በጀት ግልፅ እንዲሆን ስለተደረገ፣ ከገንዘቡ ውስጥ ለቁሳቁስ ምን ያህል፣ ለመምህራን ደመወዝ ምን ያህል እንደወጣ ታውቋል፡፡ ይህን የወላጅ ኮሚቴም አይቷል፡፡

ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም የተጀመረው ችግረኛ ገበሬዎች ራሳቸውን እንዲችሉ ያደርጋል ተብሎ ነው፡፡ ነገር ግን ፕሮግራሙ ከተጀመረ ሰባት አመት ቢያስቆጥርም፤ አሁንም ሰባት ሚሊዬን ገደማ ተረጂዎች አሉ፡፡ ፕሮግራሙ ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል? ውጤታማ የመሆን ተስፋስ አለው?

የሴፍቲኔት ፕሮግራም አደገኛ ድርቅን ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ ሕዝቦች እንዳይርባቸው በማድረጉ ረገድ ተሳክቶለታል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም በረሃብ አይሞትም፡፡ በእርግጠኝነት በምግብ ራስን ለመቻል ያበቃል ወይ ስንል ግን፤ ያጠያይቃል፡፡

እስካሁን መንግስት እዚህ ግብ ላይ አልደረሰም፡፡ አስቸጋሪ እንደሆነም አስባለሁ፡፡ ሰዎች ከሴፍቲኔት ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ ብታደርግ እንኳ፤ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ ሌሎች እርዳታ ፈላጊዎች ይመጣሉ፡፡ ይህም ሴፍቲኔት እንዳይሳካ ፈተና ሆኖ ይጋረጣል፡፡ በእርግጥ ጀርመን በቀጥታ የሴፍቲኔት ፕሮግራምን ፋይናንስ አታደርግም፡፡

ሶስት የጀርመን የተራድኦ ተቋማት ተዋህደው የአሁኑን ጂአይዜድ መመስረቱ ለምን አስፈለገ?  ምን ጥቅም አስገኝቷል?

የጀርመንና እንግሊዝ የተራድኦ ተቋማትን አነፃፅር፡፡ የእንግሊዝ ዲኤፍአይዲ ብቻ ነው ያለው፡፡ የጀርመን ግን ልዩ የራሳቸው ሥራ ያላቸው ብዙ ድርጅቶች አሉ፡፡ ስራችንን የበለጠ ውጤታማና ጠንካራ ለማድረግ ማዋሀዱ አስፈልጓል፡፡ ሥራዎቹ ያው ናቸው፡፡ የሦስቱ ድርጅቶች ውህደት የዛሬ አንድ አመት ተጀምሯል፡፡ ድርጅቶቹን በቅጡ ለማዋሀድ ግን ተጨማሪ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ድርጅቶቹ ይሰሯቸው የነበሩ ሥራዎች ግን አሁንም አሉ፡፡

ጀርመንን ጨምሮ የአውሮፓ መንግስታት ሰብዓዊ መብትን አስመልክቶ በየጊዜው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውይይት እንደምታደርጉ ይነገራል፡፡ የፖለቲካ ውይይት ለማካሄድም ቋሚ ውል ተፈርሟል፡፡ ግን ያን ያህልም ብታደርጉም ውጤታማ አለመሆናችሁ ሚናችሁን አያሳንሰውም?

ይኼ አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የእድገት አጀንዳ በመሳሰሉ ጉዳዮች መሻሻል አሳይታለች፡፡ በሌሎች ዘርፎች ደግሞ የማሽቆልቆል አዝማሚያ ሊኖር ይችላል፡፡ የተወሠኑ ሕጎች ለምሣሌ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ እና የሚድያ ሕጉ ሥራ ላይ መዋላቸው ያሳስበናል፡፡ ከመንግስት ጋር በየጊዜው እየተነጋገርንበትም ነው፡፡ በውይይታችን ግልፅ ነን፡፡

ግን ደግሞ ይህች አገር ሉዓላዊት አገር ነች፡፡ ስለዚህ አገሩን እንዴት ማስተዳደር እንዳለበት  የሚያውቀው መንግስት ነው፡፡ ሆኖም ጉዳዮቹን  በተለያየ ደረጃ ለመዳሰሳችን እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ፡፡ የፍርድ ሂደቶችን በንቃት እንከታተላለን፡፡ በፍርድ ቤቶች ቋሚ ታዛቢ አለን፡፡ በአውሮፓ ሕብረት የሥራ ክፍፍል ስላለ ሁሉንም ጉዳዮች አንከታተልም፡፡ ለኛ በጣም አስፈላጊው ሕጎች እንዴት እንደተተገበሩ ማየትና የሚያሳስቡንን  ጉዳዮች ሁሉ መግለፃችን ነው፡፡

በዓለም ላይ በተከሰተው ዓለምአቀፋዊ የኢኮኖሚ ቀውስ ጀርመን ከሌሎች የአውሮፓ አገራት ቀድማ ማገገም የቻለችበች ምስጢር ምንድነው ?

ጀርመን በ1990ዎቹ ከተዋሃደች በኋላ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ገጥሟት ነበር፡፡ በ2000 ዎቹ ዓ.ም በቻንስለር ጌርሃርድ ሽሩደር በሚመራው ጥምር መንግስት፤ አገሪቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን ወሰደች፡፡ ሕጐችን አወጣች፡፡ በመንግስት የሚከናወኑ ሥራዎችና ድጐማዎች ላይ ቅነሳ ተደረገ፡፡ ለጊዜው ብዙ ሰዎች ተጎድተዋል፣ የማሻሻያ እርምጃው ቀላል አልነበረም፡፡ ሆኖም ኢኮኖሚያችን ተፎካካሪ እንዲሆን አደረግነው፡፡ እናም በ2008 አለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ ሲከሰት የጀርመን ኢኮኖሚ በተሻለ አቋም ላይ ነበር፡፡ ይኼ አንድ ነገር ነው፡፡

ቀደም ብለን ባደረግነው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ የመንግስት የበጀት ዲሲፕሊን እንዲጠናከር አድርገናል፡፡ ሌላው ደግሞ በጣም ጥሩ የኢኮኖሚ መሠረት አለን፡፡ የጀርመን ኢኮኖሚ መሠረት፤ ትናንሽ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው፡፡ ኢኮኖሚያችን ኤክስፖርት ተኮር  ነው፡፡ ብቅ ብቅ በሚሉ አዳዲስ ዘርፎችና ገበያዎች ላይ ተፎካካሪ እየሆንክ ዘመናዊ ኢኮኖሚ የምትገነባ ከሆነ ፈተናዎችን መቋቋም ትችላለህ፡፡ ይሄም ነው ከቀውሱ ቶሎ እንድንወጣ ያስቻለን፡፡ ትልልቆቹ የጀርመን ፓርቲዎች አብረው መስራታቸውም አስተዋፅኦ አበርክቶአል፡፡ ውስጣዊ የፖለቲካ ትግል የለም፡፡ በ2008 ግዙፍ ጥምር መንግስት ነበረን፤ ትልልቆቹ ወግ አጥባቂ እና ሶሻል ዲሞክራት ፓርቲዎች ተባብረዋል፡፡ የኢኮኖሚ ቀውሱን ለመቋቋም በሀገር ውስጥ ትልቅ ሀገራዊ መግባባት ተፈጥሯል፡፡

ብዙ የጀርመን ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ላይ አይታዩም?

እያንዳንዱ ኢንቨስተር ለራሱ ይወሥናል፡፡ ጥቅም፣ ተስፋ እና ጉዳቱን አስልቶ እዚህ እና እዚያ ኢንቨስት ላድርግ ይላል፡፡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም እንዳላት ምንም ጥርጥር የለም፡፡ ግን እስካሁን በለውጥ ሂደት ላይ ነች፡፡ የተለያዩ ሕጎችና ደንቦች አሁንም እየወጡ ነው፡፡ አንዳንዴ ከቀን ወደ ቀን የሚለዋወጡ ይመስላል፡፡ ሕዝቡ አይነገረውም፤ለዚያም ዝግጁ አይደለም፡፡

ኢንቨስተሩ መብቱን እንዴት እንደሚያስከብር እርግጠኛ መሆን ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ በትራንስፎርሜሽን ሂደት ላይ ነች፡፡ መሻሻል አለ፡፡ ሆኖም ይኼ ለጀርመን ኢንቨስተሮች  በቂ አይደለም፡፡

ብዙ ኢንቨስተሮች እንዲመጡ የሚያስችል አይደለም፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት መካከለኛ መጠን ያላቸው ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ኩባንያዎች ደግሞ የስጋት ትንተና አስፈላጊ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የኢንቨስትመንት ጥበቃ ስምምነት ቢኖረንም በቂ ስላልሆነ፤ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር ነገሮች ወደፊት እንዲራመዱ እየጣርን ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን፤ ኢትዮጵያም ግዙፍ አቅም አላት፡፡ የተወሠኑ ማበረታቻዎች አሉ፡፡ ይሄ ግን የሳንቲሙ አንድ ገፅታ ብቻ ነው፡፡ ሌላው የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡ ለመሻሻል አሁንም መንገዱን መጓዝ ያስፈልጋል፡፡

የመንግስትን ፖሊሲዎች እንዴት ያዩዋቸዋል?

እንደ ውጭ ሀገር አምባሳደርነቴ ይኼን መመለሥ በጣም ይከብደኛል፡፡ የመንግስት ፖሊሲን መፈተሽ የኢትዮጵያውያን ሥራ ነው፡፡ መንግስት ፖሊሲ የሚያዘጋጀው ለኛ ሳይሆን ለራሱ ሕዝብ ነው፡፡

ባለፈው እሁድ ቼልሲና ባየር ሙኒክ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ለመውሰድ  ሲፋለሙ ቻንስለር አንጌላ ሜርኮል የቡድን ስምንት ስብሰባን አቋርጠው ጨዋታውን ሲመለከቱ በቲቪ ታይተዋል፡፡

በዚህ ላይ አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ ሕይወትን ከማጣጣም ባለፈ ብዙ ከባድ ሥራ ይሰራሉ፡፡ እኔ የቻንስለሬ ባህርይ ላይ አስተያየት መስጠት አልችልም፡፡ ደግሞም ያንን ጨዋታ  አላየሁትም፤ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ነበርኩ፤ እዚያ ቴሌቪዥን የለም፡፡

በፓርኩ ስንት ዋሊያዎች ተመለከቱ?

ብዙ አይቻለሁ፡፡ አንዳንዶቹን በቅርበት፣ሌሎቹን በርቀት፡፡ አካባቢው በጣም የበለፀገ ነው፡፡ የዓለም ቅርስ መሆን የሚችል አካባቢም ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ባለሥልጣን ይሄን ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡ አንድ ቀሪ ሥራ ግን አለ፡፡ በፓርኩ የሰፈሩ ነዋሪዎችን በሌላ ቦታ ማስፈር ያስፈልጋል፡፡ እንደገባን ሕዝቡ ለመልቀቅ ፈቃደኛ ነው፡፡ ምክንያቱም መሬቱ ምርታማነቱን አጥቷል፡፡ መንግስትም መልሶ ሊያሰፍራቸው ፈቃደኛ ነው፡፡ የካሳና የአማራጭ ሕይወት ጉዳይ ነው፡፡

ክብርት አምባሳደር፤ የመጨረሻ አስተያየት ቢሰጡን…

እም… የሕዝብ ቁጥር እድገት በኢትዮጵያ አሳሳቢ ነው፡፡ ሀገሪቱ በጣም አጓጊ አላማ አላት፡፡ የኢኮኖሚ እድገትዋን ለማሳካትም ትጥራለች፡፡ ነገር ግን ሁሉም ስኬቶች፤ በከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እድገት ፈተና ሊጋረጥባቸው ይችላል፡፡ መፍትሄ መፈለግ አለበት፡፡

 

 

Read 2292 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 11:13