Print this page
Saturday, 06 April 2019 15:19

“ኢ/ር ታከለ ኡማ የመጡበትን ህጋዊነት እናከብራለን” - ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(14 votes)



በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አስተባባሪነት የተቋቋመው የአዲስ አበባ ባለአደራ ም/ቤት መጋቢት 25 ቀን 2011 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙሃን በሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ከተነሱ ዋነኛ ርዕሰ ጉዳዮች የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ በመግለጫው ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሚዲያ አካላት የተገኙ ሲሆን አምስት ጋዜጠኞች ብቻ ጥያቄዎችን ለመድረኩ ሰንዝረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሠላም ገረመው እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች፡፡  


የፕሬስ ሴክረቴርያቱ ጋዜጣዊ መግለጫውን የከለከልነው ለእስክንድር ደህንነት ነው ብለዋል፡፡ ምንድነው የተፈጠረው?
ከመጀመሪያው ስነሳ ያለፈውን ቅዳሜ መግለጫ አስመልክተን ማክሰኞ ዕለት ከፍለን ደረሰኝ ተቀብለን፣ ቅዳሜ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ  ለህዝብ ተናግረናል፤ በማህበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳ አድርገናል፡፡ አርብ እለት ስድስት ሰአት ላይ ስልክ ይደወላል፤ ከራስ ሆቴል ስራ አስኪያጅ፡፡ እሳቸው እንዳሉን ከሆነ፤ የቂርቆስ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋናው ኮማንደርና ምክትል መጥተው ጋዜጣዊ መግለጫው እንዳይደረግ እንደከለከሏቸው ነገሩን፡፡
ይሄንን ሲሉን “አገሪቱ በለውጥ ድባብ ውስጥ ሆና ይህ ሊከሰት አይችልም፤ ተረጋጉ” ነው ያልናቸው፡፡ እንደውም “ተረጋጉ ለሚመለከተው አካል አሳውቀን ስልክ ይደውሉላችኋል ነው ያልናቸው፡፡ በነጋታውም ጋዜጣዊ መግለጫው ይሰጣል ብለን ነው ነግረናቸው የወጣነው ወዲያው የጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የቅርብ አማካሪ ጋር ደውለን የተደረገውን ክልከላ አሳውቀናቸዋል፡፡
እሳቸውም የሰጡን ምላሽ ልክ እኛ እንደገመትነው “ይሄማ ሊሆን አይችልም፤ ጋዜጣዊ መግለጫ አይከለከልም ስለዚህ ተረጋጉ፤ እኔ ሁሉንም አስተካክዬ በነጋታው መግለጫውን ትሠጣላችሁ” የሚል ምላሽ ሰጡን፡፡ እንዳሉትም ከግማሽ ሰዓት በኋላ መልሰው ደወሉልንና ከንቲባው ጽ/ቤት እንዳነጋገሩ ገልፀውልን፤ ካቢኔ ውስጥ ያሉ አንድ የቢሮ ሃላፊን ስልክ ቁጥር ሰጡን፡፡ ለእነሱ ደውሉላቸው ተባልን፡፡ በተባልነው መሠረት ስንደውል እሳቸውም “ጋዜጣዊ መግለጫ አይከለከልም” አሉን፡፡ አሁን የእነዚህን ሰዎች ማንነት መግለጽ አንፈልግም፤ አላልንም ብለው የሚክዱ ከሆነ ግን ድምፃቸውንም ቀድተናል ማሰማት እንችላለን፡፡ እሳቸውም “ምንም አታስቡ” ብለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነርን ስልክ ሰጡን፤ “ለእሳቸው ደውሉና ንገሯቸው፤ ጋዜጣዊ መግለጫውን ታደርጋላችሁ፤” አሉን፡፡ በተሰጠን ስልክ ለም/ኮሚሽነር በተደጋጋሚ ስንደውል አያነሱም፡፡ አላነሳም ሲሉን የጽሑፍ መልዕክት ላክንላቸው፡፡ የሆነውን ገልፀን ላክንላቸው፤ መልስ ግን አልሠጡንም፡፡ እኛም የጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤትና የከንቲባው ቢሮ መግለጫውን መስጠት ትችላላችሁ ባሉን መሠረት ቦታው ላይ ቅዳሜ ዕለት በሰአቱ ሄደን ነበር፡፡ ከእኔ ቀድሞ ቦታው ላይ የደረሰው ስንታየሁ ነበር አይደለም፤ ወደ አዳራሹ ሊገባ በር ላይ ሊያሳልፋት አልቻሉም፡፡ እኔ ደርሼ ፖሊሱን ሳነጋግረው፤ እሱ ምንም ማድረግ እንደማይችል፤ ትዕዛዝ እንደተቀበለ ጥያቄ ካለን፤ ለገሀር የሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ማመልከት እንደምችል ሲነግሩን፣ ወደ ለገሃር ጣቢያ ሄድን፡፡ እዛም ያነጋገርናቸው ሃላፊዎች ትዕዛዙ የመጣው ካዛንቺስ ከሚገኘው ፖሊስ መምሪያ መሆኑን ተነገረን፡፡ ወደ ቦታው ስንደርስ ሃላፊዎቹ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ከቢሯቸው ወጥተው ነበር፡፡ ተመልሰን ወደ ራስ ሆቴል ስንሄድ ኮማንደር ያሲንን አገኘናቸው (ቂርቆስ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ) መግለጫ ለመስጠት እንደመጣን ስንነግራቸውና ከጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት እና ከከንቲባ ቢሮ ፍቃድ በቃል እንደተሰጠን ብንገልጽላቸውም ትዕዛዝ እንደተሰጣቸውና ወደ ውስጥ መግባት እንደማንችል ነው የገለፁልን፡፡ ይሄንን ጥሪ ተቀብለው የመጡ የሚዲያ አካላት ስለነበሩ ለእነሱ እንኳን እንግለጽ ስንል ተከልክለናል፡፡ “ጋዜጣዊ መግለጫ ማድረግ አልቻልንም ለማለት እንኳን ተከልክለናል” ለምን እንደሆነ ባላውቅም ቦታውን ለቀን እንድንሄድ ተደርጓል፡፡ ያን ቀን ምሽት ከእኛ ደህንነት ጋር በተያያዘ ምክንያት ጋዜጣዊ መግለጫው መሰረዙ ተገልጿል፡፡ እኛም ጥያቄ ያለን እዚህ ጋ ነው ለምሳሌ ዛሬ ያደረግነው ጋዜጣዊ መግለጫ የፖሊስ ጥበቃ ያለውም ፍፁም ሠላማዊ ነው ከሁለትና ከሶስት ቀን በፊት በአካል ላይ ጉዳትና ዛቻ የሚያደርስ አካል ካለ እንዴት አሁን በሠላም ጋዜጣዊ መግለጫ ማድረግ ቻልን?
አቶ ንጉሱ ጥላሁን የጠ/ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክረቴርያት፤ መግለጫውን በጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ማድረግ እንደምትችሉ ተናግረዋል፡፡ ይሄ ለፖለቲካዊ ፍጆታ የዋለ ነው ወይስ ጠይቀዋቸዋል?
ጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት መግለጫ ለመስጠት ለምን እምቢ አላችሁ ለተባለው፣ እኛ ከህዝቡ ጋር ነው ያለነው፡፡ የህዝብ ድምጽ ነው ያለን፡፡ ቤተ መንግስት አንገባም፡፡ ቤታችንም ከቤተ መንግስት ውጪ ነው፡፡ ወደ ቤተመንግስት ከገባን የህዝብን ጥያቄ ይዘን ነው መግባት የምንፈልገው፡፡ ወደፊትም ቢሆን በመንግስታዊ ተቋም ውስጥ ሆነን ጋዜጣዊ መግለጫ አንሰጥም፤ የህዝብ ነን ህዝቡ ውስጥ ሆነን ነው መግለጫ የምንሰጠው፡፡
ባለአደራ ህጋዊ አይደለም የሚል ቅሬታ ሲነሳ ይሠማል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም “ባለአደራ የሚል ጨዋታ መቅረት አለበት፤ ካልሆነ ወደ ጦርነት እንገባለን” ብለዋል፡፡ በዚህ ላይ ምን ትላላችሁ?
ጦርነት ውስጥ እንገባለን ያሉትን በተመለከተ እኛ ባልደራስ ላይ በነበረን ስብሰባ ህዝቡ ቃልኪዳን አስገብቶናል፡፡ የገባነው ቃል ኪዳንም እንቅስቃሴያችን ሙሉ በሙሉ ህጋዊና ሠላም መሆን አለበት ተብሎ ነው፡፡ ከዚህ ቃል ኪዳን መውጣት አንችልም፡፡ ይህንን ቃል ኪዳን አፈረስን ማለት ህዝቡን ከዳን ማለት ነው፡፡
ጦርነት ቢከፈትብን ምላሻችን ጦርነት አይደለም፤ ያው ሠላማዊነት ነው የሚሆነው፤ ዱላ ለሚያነሳብን ምላሻችን ዱላ አይደለም… ገጀራ ላነሱብን ምላሻችን ገጀራ ማንሳት አይደለም፤ ለሁሉም ያለው ቅድመ ሁኔታ ሠላማዊነትና ህጋዊነት ነው፡፡ ህጋዊነት ሦስት መግለጫዎች አሉት፡- ሞራላዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ህጋዊነት ነው፡፡ የፖለቲካና የሞራል ህጋዊነት ነው፡፡ የፖለቲካና የሞራል ህጋዊነትን በሚመለከት ሁለቱም አለን፡፡ በባልደራስ የተሰበሰበው ህዝብ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ በአደባባይ ውክልና ሲሰጠን የሞራልና የፖለቲካ ህጋዊነት ተላብሰናል፡፡
በዚህች ከተማ ላይ በዚህ ደረጃ አሁን የህዝብ ውክልና ያለው ማንም የለም፡፡ ም/ቤቱን ይጨምራል፤ ከንቲባውን ይጨምራል፡፡ እኛ ነን ያለን፡፡ ከሰባት ሚሊዮን ህዝብ መካከል በአስር ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ መወከል ብዙ አይደሉም በሚለው እንስማማለን፤ ግን በአንድም በሁለቱም ሰው ህዝብ ተሰባስቦ በፍቃደኝነት ውክልናውን የሰጠን ለእኛ ነው፡፡
አስተዳደራዊ ህጋዊነት አያስፈልግም እያልን አይደለም ያስፈልጋል፡፡ በማህበራት ማደራጃ ለመመዝገብ አዲሱ አዋጅ ታትሞ ተግባር ላይ እስኪውል እየጠበቅን ነው፡፡
ባልደራስ የመጣው ህዝብ የአዲስ አበባን ህዝብ ይወክላል ብላችሁ ታምናላችሁ?
ባልደራስ የመጣው ህዝብ ናሙና ነው፤ ድርጅታዊ ስራ ሰርተናል፡፡ ከሁሉም ክ/ከተማ እንዲመጡ ትልቅ ስራ ነው የሠራነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብም በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ጥቅም ይገባኛል እንደማይል እናውቃለን፡፡ ኢ/ር ታከለ ስለ ኦሮሞ ህዝብ የተናገሩት ነገር አለ፤ “ኦሮሞ የእኔ የሚለው ነገር የለም የእኛ እንጂ” ብለዋል፡፡ ይሄ መንፈስ ነው በኦሮሞ ህዝብ ላይ ያለው፤ ይሄንን ማን ተክሎት እንደሄደ እናውቃለን፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ “መታወቂያ በህጋዊ መንገድ ነው የተሰጠው” ብለዋል፡፡ እናንተ ደግሞ በህገወጥ መንገድ በሺዎች የሚቆጠሩ መታወቂያዎች ተሰጥቷል ብላችኋል፡፡ ማንን ነው ማመን ያለብን?
መታወቂያን በተመለከተ ጠ/ሚኒስትሩ የተናገሩትን እኔም ሰምቻለሁ፡፡ ግን እሳቸው መስተዳድር አካባቢ ጠይቀው ነው መልስ የሰጡት፡፡ ይሄንን መግለጫ ለመስማት ጊዜ ላይኖራቸው ይችላል፤ ነገር ግን የሚችሉ ከሆነ ማስረጃ አለን፡፡ መታወቂያውን ስትሰጥ የነበረችው ሰናይት ታደሰ ናት፡፡ ሰናይትንና መታወቂያ አልተሰጠም ያሉትን ፊት ለፊት ያገናኙዋቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እምናገኛቸው ከሆነ ሰናይትን ይዘናት ነው የምንሄደው፡፡
የአዲስ አበባ መስተዳድርም “ህጋዊ ነኝ በአዋጅ ነው የተመረጥኩት” የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡ የእናንተን ባለ አደራ የሚለውን ለመሸንቆጥ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ምን ትላላችሁ?
በአዋጅ መሠረት የአዲስ አበባ ም/ቤት አስተዳደራዊ ህጋዊነት አለው፤ እሱን አልጠየቅንም፡፡ መስተዳድር አልባ ትሁን አላልንም፡፡ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ መስተዳድር መኖር አለበት፡፡ እስከሚቀጥለው ምርጫ መኖር አለበት ምክንያቱም የተመረጠበትን ዘመን ጨርሷል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ለመወያየት በሬ ክፍት ነው ብለዋል፡፡ ጥያቄያችሁን ይዛችሁ ለምን ውይይት አላደረጋችሁም?
ጠ/ሚኒስትሩ በራቸው ክፍት መሆኑን እኛም እንፈልገዋለን፡፡ የሚሻለውም በውይይት መፍታት ነው፡፡ እነ ኢ/ር ታከለ አንዱን መስፈርት ብቻ ነው የሚያሟሉት፤ የአስተዳደር ህጋዊነትን ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካና የሞራላዊ ህጋዊነት የላቸውም፤ ውክልናም የላቸውም፡፡
በሚቀጥለው ምርጫ እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ የመመረጥ እድሉ በጣም አናሳ ነው፡፡ ይሄንን ሊረዱት ይችላሉ፡፡ በይፋ ወጥተው ልዩ ጥቅም የሚለውን አንቀበልም ካላሉ በስተቀር፡፡ የመጡበትን ህጋዊነት ግን አከብራለሁ፡፡

Read 5778 times