Saturday, 06 April 2019 15:16

ከነህመማችን አሁንም - ከበሮ ድለቃ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

ሕዝብ ነበልባሉ…
መማገድ ይወዳል የያዘውን ሁላ
ከፍየል ተጫውቶ …ካነር ተለጣፊ፣
በግ አሥብቶ ባርኮ ለተኩላ አሳላፊ፣
እፍ ብሎ ነዶ-እፍ ብሎ ጠፊ
ሕዝብ አጨብጫቢ ነው፤ ገናና ደጋፊ፡፡
ሕዝብ ማዕበሉ…
ናልኝ ብሎ ሰዳጅ መሸኘት አመሉ
ነውጠኛ ባህር ነው አመለ ቅዝምዝ፣
በነፋስ ይገፋል፣ በጉልበቱ አያዝም፣
ስትነቃ ነቅቶ፣ ስትፈዝ አይፈዝም፣
ስትሄድ ይገፋሃል፣ አብሮህ አይጓዝም፡፡
የበለው ገበየሁ ግጥም ሕዝብንና ሕዝብ በየታሪክ አጋጣሚው የፈጠራቸውን ነውጦችና ለውጦች እንድናስታውስ ቦይ ይቀድልናል፡፡ “ሠፊው ሕዝብ ታሪክ ሠሪ ነው” የሚሉት ሶሻሊስታውያን፣ ያንኑ ሠፊ ሕዝብ በጥይት እየቀነሱ፣ መዝሙራቸው ግን መልሶ ሠፊው ሕዝብ ነበር፡፡
ስታሊን ገበሬውን፤ “ኩላክ” እያለ- ሲደፋ፣ ወጣቱን በቀይ ሽብር ሰይፍ ሲተለትል፣ ትግሉ ግን ለሠፊው ሕዝብ ነፃነትና ለወዛደራዊ አምባገነንት ሥርዓት ግንባታ ነበር፡፡ ይሁንና ሠፊውም ሕዝብ ጠመንጃ ታጥቆ፣ የሚወጋው ሠፊውን ህዝብ ነው፤ ስለዚህ ነው ሕዝብ የሚያሳስተው!
የኛ ሀገሩ ደርግ ሠፊውን የኢትዮጵያን ሕዝብ በምላሱ ሲደልለውም “…አብዮትህን፣ ነፃነትህን ሊቀለብሱ የተነሱ አድሃሪያን፣ ፀረ አብዮተኞች ወዘተ” ሲለው በቁጣ “ሆ!” ብሎ ይወጣና የሚጨረግደውን ይጨረግድለታል፡፡ ከሠፊው ሕዝብ ውስጥ ቀንሶ ጠመንጃ ያስታጥቅና፣ የታጠቁት ያልታጠቁትን ያስወግዳሉ፡፡
ታዲያ መንግሥት ብቻ ሁሌ መሪ አይሆንም፤ ሕዝብም በገናና ድምፁ እየጮኸ፣ በፍቅር ዜማ እያግባባ አንዳንዴ መሪዎችን ወደተሳሳተ አቅጣጫ ይመራል፡፡ ለዚህ ደግሞ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት “ቅንጅት” የተባለውንና ታላቅ ሕዝባዊ ድጋፍ የነበረውን ፓርቲ ማስታወስ ብቻ ይበቃል፡፡ ቅንጅት በሕዝብ ማዕበል የታጀበ ፓርቲ ነበር፡፡ ይህ የቅንጅት አጃቢ ማዕበል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አሳስቷቸዋል፡፡ “ለዳቦ ወጣንበት” ያሉት ያ ሰልፍ፣ ጠቅላዩ የድጋፍ መስሎዋቸው ከመድረክ ተወርውረው እንዲወርዱ የሚያበቃ ንዝረት ፈጥሮባቸው ነበር፡፡ የዚያ ዓመቱ ማዕበል ከሠልፍ ቀን ያለፈ መሪ ሆኖም ነበር፡፡ ቅንጅት የተባለው ፓርቲ ሕዝቡን ከመምራት ይልቅ ወደ መመራት በመሄዱ የመሪዎቹ ፍፃሜ ማረሚያ ቤት ሆኖ ነበር፡፡
በመሠረቱ ሕዝብን ማዳመጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ይሁንና በሕዝብ ተወካዮች እንጂ በሕዝብ መመራት አደጋው ቀላል አይደለም፡፡ በጭብጨባ ሆዳችን ከባባ፣ በአሸወይናው ዳንስ ከቃጣን ስህተት ውስጥ መውደቅ ይመጣል፡፡
በተለይ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታና ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ የመንጋ መሪዎች ባሉበት ሀገር፣ መንግሥት የተሻለ ጥንቃቄና ብስለት - ይጠበቅብታል፡፡
ሰሞኑን የአንድ ዓመቱን ለውጥ ለማስታወስ የሚደረገውን ሽርጉድ ሳይ ብልጭ ያለብኝ ይህ የመንጋ ድምፅ፣ የአድርባዮች ጩኸት ነው፡፡ መቸም ሕዝብን ጭብጨባውን ሳይሆን ብሶቱን መስማት ይበልጥ ከአደጋ እንደሚጠብቅ፣ የሥነ አመራር ትምህርት ላላቸው መሪዎች መንገር ለቀባሪ ማርዳት ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ህዝብ ንፋስ ወደነፈሰበት ይነፍሳል፤ በተለይ በደሀ ሀገራትና ለጥቅም በሚቆሙ ሰዎች፡፡ በተለይ ደግሞ አምባገነን መሪዎች በተፈራረቁባት ምድር፣ ይህ ለምን ሆነ ማለት አይቻልም፡፡ “መሥሎ መኖር” በሚለው ጣጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቅልጥ ያለው አድርባይነት የወጣው በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን መሆኑን አንድ የሀገራችን ጋዜጣ ላይ ተፅፎ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ በንጉሡ ዘመን ስለዚሁ ችግር በብዛት የሚነገር ቢሆንም እኔም ካነበብኩት ቀን ጀምሮ አልረሳ ያለኝ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ በፃፉት ግለ ታሪክ ውስጥ ያነበብኩት የአንድ ሊስትሮ ታሪክ ነው፡፡ መጽሐፉ እንደዚህ ይላል፡-
“…ለመፈንቅለ መንግሥት ድጋፍ ስንወጣ አራት ኪሎ በር ላይ ጫማ ይጠርግ የነበረ እያጨበጨበ የሸኘን ሊስትሮ፤ ደሴ ንጉሱ ከተመለሱ በኋላ “የማላውቃችሁ መሰላችሁ፣ አንድ በአንድ ነው የማወጣችሁ” እያለ እኛን ተማሪዎቹን ማንገራገር ጀመረ፣ በቁም ነገርም ማስፈራራትም ጀመረ፡፡ እኔም በጥሞና አነጋገርኩት፣ በተሰለፍንበት ዕለት እያጨበጨበ እንደሸኘንና ይህንንም የሚያሳይ ፎቶግራፍ እንዳለ ገለጥኩለት፡፡ እኔም “መጀመሪያ የምናሳስርህ አንተን ነው” ብዬ አስፈራራሁት፤ ከዚያ በኋላ እሱም ማንገራገር አቆመ፡፡
የኛ ሀገር አድርባዮች ዐይን አውጣነት ሀሳባቸውንና ቀለማቸውን መቀየራቸው ብቻ አይደለም፤ ይባስ ብለው በአንደኝነት አራጋቢ ሆነው ስለሚቆሙ ያሳስታሉ፡፡ እኔ በታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ ካየኋቸው ሰዎች ሁሉ በምንም ጉዳይ፣ በየትኛውም ሹመትና ጥቅም አድርባይ ያልሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ብቻ ናቸው፡፡…”
ዛሬ እጃቸው እሣት እስኪተፋ የሚያጨብጭቡልን ሁሉ ነገ፣ በዚያው እጃቸው ጦር ይዘው ይነሳሉ ነው መልዕክቱ፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ ሳነሳ አንድ ትዝ የሚሉኝ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ኃላፊ ነበሩ፡፡ እኒህ ሃላፊ “የባለሥልጣኑ ምሥል ካልገባ፣ አልጫ ይሆናል” በማለት ኤዲተሮችን በቦታውም ያለቦታውም እንዲያስገቡ የሚጨቀጭቁ ነበሩ፡፡ በኋላ ግን አንድ ነገር ሆነ፡፡ ሰውየው ተቀይረው (በቅሬታም ጭምር) ወደ ሌላ ሥራ ሲዛወሩ” ኤዲተሮቹ እንደ ቀድሞው መስሏቸው ስላለፈ ሥራቸው ያስገቡትን ምሥል የቲቪው ኀላፊ በቁጣ፤ “ይህን ሰውዬ አስወጣው” ሲሉ በድንጋጤ ክው ብለው ቀሩ፡፡ እዚህ ሀገር ፖለቲካም ሆነ ሥራ እንጀራ ነው፡፡ እንጀራ ብቻ የሚያስብ ሰው ደግሞ ህሊና ይጐድለዋል፡፡ ስለዚህም የእንጀራ አሽከር ይሆናል!  
ብዙ ታሪካችን የሚያሳየን ይህንን ነው፡፡ ብዙዎቻችን በነቢብም ይሁን በገሀድ እንደምናውቀው፤ በአብዮቱ ዘመን መንግሥቱ ኃይለማርያምን ወደ ጥፋት የከተታቸው “አሥታጥቁን አታሥጨርሱን” የሚለው መንጋ ሠልፈኛ ነበር፡፡ በኋላ የያንዳንዱን ቤት እንደሚያንኳኳ አልጠበቀም ነበር፡፡ ከዚያ ቀጥሎም “አብዮት ልጇን ትበላለች” በሚል አጃቢ ዐረፍተ ነገር ቅርጠፋ ጀመረች፡፡
ስለ በዓል አከባበር ጉዳይ ሲነሳ፣ በታሪካችን አንዱ አንዱን የወቀሰበት ሰንሠለት እየቀጠለ መምጣቱን ታሪክ ያስነብበናል፡፡ ለምሳሌ ኃይለሥላሴ የወሎን ድርቅ ደብቀው የተቀናጣ ኑሮን ከመኳንንቱ ጋር ያጣጥማሉ፤ ውሻቸውን ያቀማጥላሉ፤ ለውሻቸው ሀውልት ሠርተዋል ተብሎ ተለፍፎባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ደርጉም በተራው ከፈረደበት የችግር አዙሪት አልወጣም፡፡ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ ምስረታን - “አሥረኛው የአብዮት በዓል” ብሎ ሲያከብር ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሕዝብ ተርቦ ስለነበር፣ በከፍተኛ ደረጃ ለሰላ ትችት ተጋለጠ፡፡
የዛሬ መነሻዬ የሕዝብን /የመንጋን/ አሳሳችነት ለማሳየት ቢሆንም እግረመንገዴን መንግሥትንም ለመውቀስና ለማሳሰብ ነው፡፡ ይህ ለጋ የለውጥ ጉዞ ጡት ሳይጥል እንዳይጨነግፍ!
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “አዳፍኔ” በሚለው መጽሐፋቸው ትልቅ ሰው ለማየት ያላቸውን ህልም እንዲህ ሲሉ አሥቀምጠዋል፡-
“የዛሬ ስድሳ ዓመት ግድም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ውስጥ (ነፍሱን ይማረውና) አንድ የውይይት መድረክ ነበረ፤ ተወያዮቹ ሲጨርሱ እኔ አንድ ጥያቄ አቅርቤ ነበር፤ ኬንያ ጀሞ ኬንያታ አለው፣ ታንዛኒያ ጁሊየስስ ኔሬሬ አለው፤ ኢትዮጵያ ትልቅ ሰው ለምን የላትም? ብዬ ስጠይቅ፣ በአዳራሹ ትንሽ የማጉረምረም ድምጽ ተሰማ፤ አንዱ አፈ ጮሌ ተወያይ እንደማፈር እያለ “እኛም ጃንሆይ አሉን፤” አለ፤ እኔ እንደገና ተነስቼ ጃንሆይ ሲወለዱ ትልቅ ነበሩ፤ እኔ የጠየቅሁህ በሥራው ትልቅ የሆነ ሰው ነው፤ ብዬ አብራራሁ፤ ለእኔ እስከዛሬም መልሱ ትልቅ የለንም፤ ነው፤ ኢትዮጵያ ቆማ ያስወለደቻቸው የአፍሪካ አገሮች ብዙ ታላላቅ ሰዎችን አፍርተው ለዐለም መድረክ አቅርበዋል፤ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን የተሸለሙ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ግብፅ አሉ፤ እንዲህ ያሉ ሰዎች በኢትዮጵያ ቢወለዱም አዳፍኔ እየቀጨ በሎሌነት አስቀርቷቸዋል፤…” እያሉ ይቀጥላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ትልቅ ሳትወልድ ቀርታ ሳይሆን የገዛ ወገኖቻቸው ሾተላይ ሆነውባቸው እንደጨነገፉ ይታወቃል፡፡ ከሕዝቡም እያጨበጨበ በጐን ምላስ የሚያወጣ ይበዛዋል፡፡ ለወደደው የሚሞት ህዝብ ገና አልፈጠርንም፡፡ ከላይ እንዳልኩት በጭብጨባ የሚያሳስትና ወደ ስህተት የሚጨምር ብቻ ሳይሆን “እኛም ብለን ነበር” የሚል ከሀዲ ነው፡፡
የእኛ ሀገር ሕዝብ ምሥጋናና አድናቆት መስጠት ብርቁ ነው፤ ከማድነቅ ይልቅ መተቸት ይወዳል፡፡ ያንኑ ሕዝብ ግን በተሞጋሹ ፊት ይዘኸው ከወጣህ ምርቃት አያልቅበትም፤ ውዳሴው አይጨነግፍም፤ ጭብጨባው አያባራም፡፡
ሰሞኑን ስለሚደረገው የለውጡ አንደኛ ዓመት ስናስብም፤ ዥንጉርጉር ስሜቶች እንዳሉም ማናችንም አንስተውም፡፡ ለውጡ ብዙ ድሎችን ቢያቀዳጀንም ብዙ ጣጣዎችንም አምጥቶብናል፡፡ ብዙ ሥጋቶችም እንደተጋረጡብን ለማስታወስ ሳምንት ያህል እንኳ ወደ ኋላ መሄድ አያስፈልገንም፡፡ ምክንያቱም የባልደራሱ “የጋዜጠኛ እስክንድር መግለጫ በፖሊስ ተከለከለ” ከተባለ ገና ሣምንቱ ነው፡፡ ይህ - የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ተስፋ ሥጋት ላይ እንዲወድቅ ያደርገዋል፤ የሚሉም ጥቂት አይደሉም፡፡ ከዚህ ሌላ ብዙ ተጨማሪ ችግሮች አሉብን፡፡ ለምሳሌ እኔ በቅርበት የማውቀውና በዐይኔ ያየሁት የመስቃንና ማረቆ ግጭት አሁንም እያገረሸ የሰዎችን ህይወት ይቀጥፋል፡፡ በጉዳቱም ብዙ ሀብት ወድሞ፣ ብዙ ቤተሰብ ተሰዷል፡፡ ብዙዎች ዛሬም ከሠቆቃው ጋር ተፋጥጠዋል፡፡
ሁላችንም የምናውቀው የጌዴኦው መፈናቀል አለ፡፡ የለገጣፎ ተፈናቃዮች እንባ አልደረቀም፡፡ ሰሞኑን አዳዲስ የብሔር ማፈናቀሎች ተከስተዋል፡፡ ታዲያ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ተጨባጭና ገቢራው ክዋኔ ሳይታይ፣ ህዝቡ በመፈናቀልና በስደት እንባ እየረጨ፣ የለውጡን አንደኛ ዓመት ለማሞገስ አደባባይ መውጣት ይገባል ትላላችሁ?
ይህ ለእኔ ህሊና ፈጽሞ ፍትሐዊነት የጐደለው ነው፡፡ ይህ ለውጥ የታሪካችን ምዕራፍ አንድ አንጓ ነው ብለን ብናስብ እንኳ ብዙ ቅብብል የሚጋብዝ አይደለም፡፡ ስብሰባ ሳይሆን ቀላል ያለ ታስቦ የሚውል ነገር ቢደረግ መልካም ይመስለኛል፡፡ ብዙ ግርግርና ሄቦላላ ባይረገጥ ደግ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡
ታይታ ጦሱ ብዙ ነው፡፡ የተጐዳውን /ተጐጂ ነኝ የሚለውን/ ወገን ቁስል ይቆሰቁሳል፡፡ የተዳፈነውን ስሜት ለጥላቻ ያነሳሳል፡፡ “አደረግናቸው” የምንላቸውን ያህል ያበላሸናቸውንንና ያልተሳኩልንን ነገሮች ያስረሳናል፡፡ ሰበብ ፈልገው ለሚያብጠለጥሉን ሰነፎች፣ በራችንን ከፍተን እናሳያለን፡፡
ይህ ማለት ግን ያገኘነው ለውጥ ቀላልና ዐይረቤ፣ ወይም በሀገራችንና በህዝባችን ዘንድ ምንም ፋይዳ የለውም ማለት አይደለም፡፡ ፈጽሞ ልንረሳው የማንችለው ግዙፍ የህይወት ለውጥ ያየንበት መሆኑ መቸም አይካድም፡፡ በምንም ዓይነት የሀገራችንን ሠራዊት እንደ ጠላት የምናይበትና በገዛ ገንዘባችን በተገዛ ጥይት ግንባራችን ይመታበት የነበረውን ጊዜ አንረሳውም፡፡ በመናገራችንና በመጻፋችን ምክንያት “ሽብርተኛ” ተብለን፣ ለስቃይና ግርፋት ዘብጥያ የተጣልንበትን ጭካኔ አንዘነጋውም፡፡ ለውጡ “ምን አመጣልን?” ብለን ልናቃልለውም አንችልም፤ ሕሊና ላለን ሕሊናችን አይፈቅድልንም፡፡
ግን ይህንን ግርግርና ራስ ምዘና፤ ከዚህ የተሻለ ይሆናል ብለን በምናስበው ቀጣይ ዓመት በሙሉ ደስታ ብናደርገው አይሻልም ወይ? የሚል ነው ጥያቄዬ፡፡ በሀገሪቱ ያለው በአንድ ጉንጭ እንባ፣ በሌላኛው ደግሞ ሳቅ መሆኑ ይሰቅቃል ባይ ነኝ፤ ይልቅ ዛሬ በጓዳ አክብረን የነገውን ዘንባባ ብናሣምር አይሻልም፡፡ እስቲ ወደ ሙሉዓለም ተገኘ ወርቅ መጽሐፍ ልምጣና ስንኞች ልዋስ! በዚያው ጉዳያችንን እናጣጥም፡፡
ከትናንት ዛሬ፤ መኖር ተጭኖኛል!
ድህነቴ ረግጦ፣ ቂም በቀል ገድሎኛል
ታግለናል አትበሉኝ፣ አመፅን ገድለናል!
ይልቅ …ይልቅ…ይልቅ
ከትናንትም በላይ፣ ዛሬ እኔ ሞቻለሁ
ከልጆቼ እናት ጋር፣ ጐጆ ለይቻለሁ
ካብሮ አደጌ ጋራ፣ ምርጥ ጥሩ ብዬ
ዘር ተማርጫለሁ
ዛሬ ስጋት ወርሶኝ፣ ሃሳብ ተጭኖኛል
የነገው ገዳዬን፣ መለየት ከብዶኛል
ልጄን ተሰቅቄ፣ መምከር ተስኖኛል
ይልቅ ….ይልቅ …ይልቅ
በትግል ከመጣው፣ ከዚህ ዕድገት በላይ
ለዘመን የማይሞት፣ ትግል ከቤቴ ሳይ
ሆኜ ቀርቻለሁ የሰቀቀን ሲሳይ፡፡
አሁን ይህን የለውጡን አንደኛ ዓመት መዝሙር፣ ከልክ በላይ ስናንባርቅ፣ በየቤታቸው ከላይ ያሰፈርኳቸውን ስንኞች ቀኑን ሙሉ የሚዘምሩ ይኖራሉ፡፡ ጐጆ ያጣ ሰው፣ በረንዳ የወደቀ፣ እንዴት አድርጐ በየትኛው እጁ ለለውጡ ሊያጨበጭብ ይችላል? የኔ ቢጤው እንደ ልቡ ሊጽፍ የተፈቀደለት፣ አለዚያም ከእሥር ቤት የወጣው እልልታውን ሊያቀልጠው ይችላል፡፡ ግን በቀኝ በኩል ብንስቅ፣ በግራ በኩል ያለው ቁስላችን መታማሙን አንርሳው እያልኩ ነው፡፡

Read 1117 times