Saturday, 06 April 2019 15:10

“ለውጡ የሚቀለበሰው በሴረኞች ሳይሆን የለውጥ ኃይሉ ከተሳሳተ ብቻ ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

•ሶማሊኛ ቋንቋ የሚናገር ኢትዮጵያዊ የፓርቲያችን አባል መሆን ይችላል
•ሰው ለራሱ የሚፈልገውን ነፃነት ለሌላው የመፍቀድ ባህል ቢለመድ መልካም ነው
• እንደ አገር የሃሳብ ልዩነትን ማክበርና መቻቻል ላይ መስራት ይጠበቅብናል
     (አቶ ሙስጠፌ ሙህመድ ኡመር፤ የሶማሌ ክልል ም/ፕሬዝዳንት)

እ.ኤ.አ በ1973 ዓ.ም ከክልሉ ርዕሰ ከተማ ጅግጅጋ በ175 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ደገሀቡር ዞን ነው የተወለዱት፡፡ ከ1ኛ - 8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እዛው የትውልድ ቀዬአቸው ደገሀቡር የተከታተሉ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሀረር ከተማ መድኃኒአለም ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡ በመቀጠል ያመሩት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ኢምፔሪያል ኮሌጅ በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ አግኝተዋል፡፡ የዛሬው እንግዳችን የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ም/ፕሬዝዳንትና የሶህዴፓ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ፡፡
ለ10 ዓመታት ያህል በሱማሌ ክልል በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ያገለገሉት አቶ ሙስጠፌ፤ በኢትዮጵያ ማህበራዊ ተሀድሶ ልማት ፈንድ ሶስት አመት፣ ሌላውን ጊዜ በትምህርት ቢሮ ውስጥ እስከ ምክትል ቢሮ ኃላፊነት ደረጃ ያገለገሉ ሲሆን የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዳይሬክተር ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ከዚያስ ወዴት ሄዱ? እንዴት ከለውጡ አካል ጋር ወደ አገራቸው ገብተው ይህንን ሃላፊነት ተቀበሉ? ሹመቱን ከተቀበሉ ምን ገጠማቸው? በክልሉና በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ? ወደፊትስ ምን አቅደዋል? በሚሉትና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ፣ በ10ኛው የኢሶህዴፓ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ጅግጅጋ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በጅግጅጋ ቤተ መንግስት ተገኝታ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

እርስዎ የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል አልነበሩም፤ ግን የሰብአዊ መብት ጥሰትን በመቃወም ሀሳብዎትን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሲገልፁ ነበር፡፡ የሚታወቁት፡፡ ወደ ሰብአዊ መብት ተቆርቋሪነት የገፋፋዎት ምን ነበር? እንዴትስ ከዩኤን ወጥተው ወደ አገር ተመለሱና ለዚህ ኃላፊነት በቁ? የቤተሰብዎ እንግልትና የወንድምዎም አሟሟት ከዚሁ ጋር ተያያዥ ስለሆነ ጨምረው ቢነግሩኝ …
በዋናነት በክልላችን ሲካሄድ የነበረው አፈናና ጭቆና እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ በዋናነት በዚህ አካባቢ ትጥቅ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት ስለነበሩ በጣም ብዙ ችግር ነበረ፡፡ በዚህ ክልል በጣም ብዙ ጉዳት ነው የደረሰው ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት ተሰድደዋል፡፡ ከነዚያ ውስጥ ብዙዎቹ ወደ ኬንያና ሶማልያ ነው የሄዱት፡፡ ምንም እንኳን እኔ በጥሩ ሁኔታ ላይ እየሰራሁ ብኖርም ልቤና ግንኙነቴ ከህዝቤ ጋር ስለነበረ የሚደርሰው ጭቆናና በደል እረፍት ይነሳኝ ነበር፡፡ በየቀኑ ስልክ እደውላለሁ፣ ሰዎች አገኛለሁ፣ እከሌ ታሰረ እከሌ ተገደለ፣ ይሄ ሰፈር ተቃጠለ የሚለው ነገር በጣም ይቀፈኝ ይዘገንነኝ ነበር፡፡ ያኔ ዝምባብዌ ሀራሬ ነበርኩኝ፡፡ ምንም እንኳን የምሰራበት ድርጅት አክቲቪዝም ባይፈቅድም የተለያዩ የብዕር ስሞችን በመጠቀም በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይና የተለያዩ ድረ - ገፆች ላይ መጻፍ ጀመርኩኝ፡፡ እንደ ኢትዮጵያን ሪቪው፣ ናዝሬት ዶት ኮም ላይና ሌሎችም ላይ እጽፍ ነበር፡፡ ከጽሁፎቼ አገኝ የነበረው ግብረ መልስ የጽሁፎቼ ይዘት ጥሩ እንደነበር አስገንዝቦኛል፡፡ በወቅቱ ራሴን ማሳየት አልችልም ነበር፡፡ ብዙ አንባቢያን ያላቸው በሱማልኛ ቋንቋ የሚሰሩ ዌብሳይቶች ላይም ጽሁፍ እልክ ነበር፡፡ በኋላ በክልሉ ያለው ችግር እየከፋና እየባሰ ሲመጣ፣ በራሴ ሪስክ ወስጄ በስሜ መጻፍ ጀመርኩኝ፡፡ ቀደም ሲል በአብዛኛው እጽፍ የነበረው በእንግሊዘኛ ስለነበር ለተማረው የሶማሌ ህዝብ ነበር ተደራሽ የሚሆነው፤ በኋላ ሳስበው ወደ ዋናው ጭቆናው ወደሚደርስበት ማህበረሰብ  ስለማይደርስ ህዝቡ በራሱ ቋንቋ የምጽፈውን አውቆ እንዲነቃ፣ ታግሎ ከጭቆና እንዲላቀቅ በማሰብ ፌስቡክ ላይ በሱማልኛ እጽፍ ነበር፡፡
በዚህ እንቅስቃሴዎ ነው ቤተሰብዎ ላይ ጫና መምጣት የጀመረው?
ትክክል ነው የእናንተ ልጅ ይቃወማል በሚል የቀድሞው ፕሬዝደንት አብዲ ኢሌ፤ አብረን ስላደግን በደንብ ያውቃል፡፡ በተዘዋዋሪ አባቴንና መላው ቤተሰቤን ያስጨንቅ ነበር፡፡ መንግስትን ይቃወማል ብቻ ሳይሆን ያልተባልኩት የለም፤ “ኦብነግ” ነው ተባልኩ፤ በኋላ ደግሞ የኔ አስተሳሰብ ከኦብነግ በጣም የራቀና የወጣ ሆኖ ሲገኝ “አልሸባብ” ነው፣ “አልተሀድ” ነው ማለት ጀመሩ፡፡ በዛም በኩል ደግሞ ኧረ  ሰውዬው በዛም በኩል ከነአልሸባብ ጋር ችግር አለበት አይደግፋቸውም ሲባል፣ ወደ “ግንቦት ሰባት” ነው መጡ፡፡ በየጊዜው ስም እየቀያየሩ ፎቶዬን እየለቀቁ በክልሉ ፌስ ቡክ ሲያወጡ ነበር የሚውሉት፡፡ ይሔ ነገር ሄዶ ሄዶ ነው ለወንድሜ መገደል፣ ለእህቶቼ ስደት፣ ለ70 ዓመት አዛውንት አባቴ መገረፍ ምክንያት የሆነው፡፡
አሁን ያ ሁሉ አልፎ ለውጥ ሲመጣ፣ በእልህና በቁጭት ተነሳስቼ፣ በእኛ የደረሰው ከእንግዲህ በሌላው መደገም የለበትም በሚል ነው ወደ አገር የገባሁት፡፡ ያው ከለውጥ ሀይሉ ጋር ትውውቅ ስለነበረኝ እድሎች ተመቻችተው ነው ሲታገሉ የነበሩ ሰዎች ሲመጡ የመጣሁት፡፡ ከህዝቡም ጋር ቁርኝቴ ጥሩ ስለነበር ከህዝቡ ጋር ያለኝን ጥሩ ግንኙነት ከራሴም አቅም ጋር ባገናኘው ህዝብን ማገልገል እችላለሁ ብዬ ነው የመጣሁት፡፡ የተደላደለ ኑሮዬን ጥዬ እንድመጣ ያደረገኝ ቅድም እንዳልኩሽ በኛ ላይ የደረሰው ዳግም እንዳይፈፀምና ድጋሚ የክልሉ ስልጣን የተሳሳቱ ሰዎች ላይ ቢወድቅ፣ እንደገና እከሌ ታሰረ ተገደለ ተሰደደ የሚል ዜና እዛው ቁጭ ብዬ ለሌላ ተጨማሪ አስር አመት እየሰማሁ ከምቃጠል እዛው ቦታው ላይ ሄጄ ኃላፊነት በመቀበል እንዳይፈጠር ለምን አላደርግም ብዬ ነው ውሳኔ ላይ የደረስኩት፡፡
ክልሉን በኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ እንዴት አገኙት? ምክንያም እርስዎ ረጅም ጊዜ ውጭ ነበሩ፡፡ ከሚሰሙት ነገር ጋር ሲያነጻጽሩት ችግሩ ገዝፎ አገኙት ወይስ…?
እውነት ለመናገር ከህዝቡ ጋር በቅርበት መረጃ የመለዋወጥ እድሉ ነበረኝ፡፡ በተለይ ኬኒያ በነበርኩበት ጊዜ ወደዚህ ቀረብ ብዬ ስለነበር በርካታ ነገር ነበር የምሰማው፡፡ በየቀኑ በክልሉ የሚካሄደውን ሁሉ እከታተል ነበር፡፡ ቢሆንም በአካል መጥቶ ከማየት ጋር አይወዳደርም፡፡ ያየሁት በጣም ከባድ ነው፡፡ እኔ እዚህ ስመጣ ያየሁት፣ ሰዎች የደረሰባቸውን ነገር በግል ሲነግሩኝ በጣም አሰቃቂ ነው፡፡ ለምሳሌ “ጄል ኦጋዴን” የሚባለው እስር ቤት ሄጃለሁ፤ እዛ የደረሰባቸውን ስቃይ ማየትና በወሬ 50 እና 60 ሰው ተገርፏል ሲባል መስማት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ የተገረፉ በተለይ እግሯ ተለጥጦ በብልቷ እሳት የተጨመረባትን የቀብሪደሀር ሴት ስቃይዋን ማዳመጥ ይለያል፡፡ እውነት ለመናገር በክልላችን የደረሰው በደልና ግፍ ይሄ ነው ተብሎ ተነግሮ አያልቅም፡፡ አሁን ዶክመንተሪ ለመስራት የተለያዩ መረጃዎችን እየሰበሰብን ነው፡፡ በጣም አሰቃቂና በኢትዮጵያ ውስጥ ይሄ ተፈጽሟል ብሎ ለማመን የሚከብድ ነው፡፡ እዚህ ከተማ ላይ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ቢሮ አለ፤ ሄደሽ ብታናግሪ ብዙ ነገር ታገኛለሽ፡፡ እርግጥ በሀምሌ 28ቱ ብጥብጥ ሆን ተብሎ ብዙ ዶክሜንት ተቃጥሎባቸዋል ግን አሁንም ብዙ አላቸው፡፡ በአጠቃላይ በደልና ግፉ ከሰማሁትና ከገመትኩት በላይ ነው የሆነብኝ፡፡ ሌላው ከ10 ዓመት በላይ በአገር ውስጥ አልነበርኩም፤ ነገር ግን በክልሉ ብዙ በጀት ስለፈሰሰ በክልሉ ለውጥ አያለሁ ብዬ ነበረ፡፡ ከዚህች ከተማ ውጭ ምንም ለውጥ የለም፡፡ ምንም ሰው ቢገደልና ቢሰደድም፣ ቢያንስ ክልሉ ትንሽ ለውጥ ያመጣል ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ምክንያቱም አንዳንዴ አምባገነኖች ብዙ ብር ሲያገኙ አንዳንድ ነገር መንገድም ሌላም ይሰራሉ፡፡ በክልሉ ምንም ለውጥ አላየሁም፣ አንዱ ያልጠበቅሁት ነገር ይሄ ነው፡፡
ለውጡ አንድ አመት ሆኖታል፡፡ እርስዎ ከለውጡ ትንሽ ዘግየት ብለው ነው ወደ ኃላፊነት የመጡትና ከመጡበት እስካሁን በክልሉ ምን ምን እንደተከናወኑ ቢነግሩኝ?
እኔ ወደ ሃላፊነት ከመጣሁ ገና 7 ወሬ ነው፤ እንግዲህ ገና እንደመጣን ቅድሚያ የሰጠነው የፀጥታውን ጉዳይ ነው፡፡ የመንግስት መዋቅር ፈርሶ ስለነበር ከቀበሌ እስከ ክልል ያለውን መዋቅር መስራትና በአዲስ ሀይል ማደራጀት፣ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግና የፀጥታ ዘርፉን በቁጥጥር ስር ማድረግ፣ በጎሳዎች መካከል ቀደም ሲል ሆን ተብሎ የተተከሉ ቅሬታዎች አሉ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም እንደምታየው የሚካሄደው ዘረኝነት እዚህም በጎሳ ደረጃ ተደርጓል፡፡ “ይሄ የእናንተ ቦታ ነው” በሚል ሰው ማናከስና ማጋጨት ተከስቶ ነበር፡፡ በጅጅጋም አካባቢ ሶማሌ ባልሆኑ ብሄረሰቦች ላይ ቅስቀሳ ሲደረግ ነበር፡፡ በሀምሌ 28ቱ ቀውስ ጉዳት የደረሰባቸውም ራሳቸውን አደራጅተው በነሱ በኩልም የደረሰባቸው መልሶ እንዳይመጣ በሚል አንዳንድ ግጭት ይታይ ነበር፡፡ እናም ይሄን ሁሉ ተቆጣጥሮና ሰላም አስፍኖ ማለፍ ይጠይቅ ነበር፡፡ በአሁኑ ሰአት በክልላችን በፀጥታ በኩል ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በተሻለ ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ ጅጅጋም ሆነ የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ላይ አሁን ሰላም ነው፡፡
በፖለቲካ በኩል ይሄ 10ኛው ጉባኤ ነበር የሚጠበቀው፡፡ ህዝቡም በመንግስት የተደረገው ለውጥ በፓርቲውም መደረግ አለበት የሚል ሀሳብ ነበረው፡፡ ይሄ በመዘግየቱ በህዝቡ ዘንድ አለመረጋጋትና ነገ ምን ይመጣ ይሆን የሚል ስጋት ነበር፡፡ የክልሉ መንግስት አየር ላይ የተንጠለጠለና ምንም መሰረት የሌለው አድርጎ የማየት ነገር ነበር፡፡ ይሄም ከጉባኤው በኋላ ተጠናቅቋል፡፡
በቀጣይ ዋናው ፈተና የሚጠብቀን በልማት ዙሪያ ያለው ነው፡፡ ልማቱን እንግዲህ ቀደም ብዬ የነገርኩሽን ስራዎች ቅድሚያ ሰጥተን ስንሰራ ስለነበረ ወደ ልማቱ ለመዞር ጊዜ አላገኘንም፡፡ አሁን ግን ከዛሬ ጀምሮ ወደ ልማቱ በመዞር ያለንን በጀት በአግባቡ በመጠቀም፣ ህዝቡም እንዲጠቀም እናደርጋለን፡፡
በሶማሌና በኦሮሚያ መካከል በተነሳ ግጭት በርካታ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከ3 ሚሊየን በላይ ተፈናቃይ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ከነዚህ መሀከል 650 ሺህ ያህል ተፈናቃዮች የክልላችሁ ሰዎች ናቸው፡፡ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? በሀምሌ 28ቱ ብጥብጥ ለተጎዱት የሌላ ክልል ተወላጆች የመደባችሁት 100 ሚ. ብር በምን መልኩ እየተሰራበት ነው?      
በመጀመሪያ በመፈናቀሉ በኩል ያው እንዳልሽው ብዙ የሱማሌ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ ከ600 ሺህ በላይ ናቸው፡፡ በተለይ ቆለች በሚባለው በሀረርና በጅግጅጋ መሀል ላይ በሚገኝ ቦታ ብዙ አሉ፤ የተቻለንን እርዳታ እያቀረብን ነው፡፡ መልሶ ማቋቋምና ወደ ዘላቂ ሰፈራ የሚገቡበት ነው እንጂ የቀረን እየተረዱ ነው ያሉት፡፡ መቶ ሚሊየኑ ብር የተሰጠው ደግሞ በጅግጅጋ ከተማ ውስጥ በተለይ በሀምሌ 28ቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሱማሌ ያልሆኑ ወገኖች አሉ፡፡ እርግጥ ሱማሌዎቹም ተጎድተዋል፡፡ ነገር ግን እኛ መቶ ሚሊየን ብሩን ስንመድብ አንደኛ አብዲ ኢሌ ሀምሌ 28 ቀን በጅግጅጋ የሚኖሩ ሶማሌ ባልሆኑ ወገኖች ላይ በሰራው ነገር እንደ ህዝብ አፍረናል፡፡ ለምን ካልሽኝ፣ የሱማሌ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ አብረውት የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦችን እንደ ጎረቤት በመንከባከብ አብሮ የመኖር ችግር የሌለበት ህዝብ ነው፡፡ ነገር ግን ድርጊቱ በሶማሌ ክልል መንግስት ስም የተፈፀመ በመሆኑ እጅግ አዝነናል፡፡ ማዘን ብቻ በቂ ስላልሆነ ቢያንስ በአቅማችን ሀላፊነት መውሰድ አለብን ብለን ነው በጀቱን የመደብነው፡፡
የራሳችን ክልል ሰዎች በብዛት በተፈናቀሉበት፣ ለምን እነዚህ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ይረዳሉ የሚል አስተሳሰብ መኖር የለበትም፤ ሁሉም የኛው ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ናቸው፤ ጅግጅጋ ከተማ ውስጥ ሱማሌ ክልል ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ ሶማሌ ክልል የሚለው የጂኦግራፊ ዲስክሪፕሽን ነው፡፡ እዚህ ክልል የሚኖር የማንኛውም ሰው ጉዳት ጉዳታችን ነው፡፡ ማየት ያለብን የጉዳታቸውን መጠን እንጂ ይሄ ሶማሌ ነው ያኛው አይደለም የሚል አመለካከት ስህተት ነው፡፡ ሌላው የሶማሌ ተፈናቃዮች አንዴ ተፈናቅለው ጉዳት ደርሶባቸው አንድ ቦታተሰብስበው በክልሉ መንግስት እየተረዱ ነው፡፡ ሌላው በሶማሌ ማህበረሰብ ባህል መደጋገፍ  የተለመደና የቆየ ባህል በመሆኑ ተፈናቃዮቹ ከወገኖቻቸውም ድጋፍ እየተጠቀሙ ነው፡፡ ሱማሌ ያልሆኑት የሌላ ብሔር ተወላጅ የከተማችን ነዋሪች ግን ሙሉ በሙሉ ነው ኑሯቸው የጠፋው፡፡ መደብራቸው ተቃጥሎ ንብረታቸው ወድሞ ነው ያሉት መንግስትም አይረዳቸውም በቅርብ ሆኖ የሚረዳቸው ሌላም አካል የለም፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ ሰጠናቸው፡፡ የእምነት ተቋማትን መልሶ ስለመገንባት ላነሳሽው ጥያቄ ከተሰጠው መቶ ሚሊዮን 10 ሚሊዮኑ ለቤተ እምነቶቹ ግንባታ የሚውል ነው፡፡
በኦሮሚያና በሱማሌ ግጭት ኦሮሚያ የነበሩት ሶማሌዎች ወደ ሶማሌ፣ ሶማሌ ውስጥ የነበሩትም ወደ ኦሮሚያ ሄደዋል፡፡ በዶ/ር አብይና በአገር ሽማግሌዎች እርቅ ወርዷል፡፡ ነገር ግን ተፈናቃዮቹ የሁለቱም ክልሎች ወደየቀድሞ መኖሪያቸው እስካልተመለሱ ድረስ እውነተኛ እርቅ የለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎስ ምን ይላሉ?
በመጀመሪያ በኦሮሞ ህዝብና በሶማሌ ህዝብ መካከል የተፈጠረ ጠብም ሆነ ግጭት የለም፡፡ አልነበረምም፡፡ ባለፉት 3 አመታት የታየው የፖለቲካ ሴረኞች ሆን ብለው በተለይም የሱማሌ ክልልን አመራርና ልዩ ሀይልን በመጠቀም የኦሮሞን ትግል ለማኮላሸት ሆን ብለው ያደረጉት ወረራ ነበር፡፡ ይሄን ስናገር ማንንም ለማስደሰት ሳይሆን ሀቅ ስለሆነ ነው፡፡ ስትራቴጂ ተይዞ እዚህ ያለው አመራር ታጥቆ ኦሮሚያን በመረበሽ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ወደ ምስራቅ አዙሮ ትኩረት ለማስቀየስ የተደረገ ሴራ ነው፡፡ አጀማመሩ ይሄ ነው እንጂ ሁለቱ ህዝቦች ተጣልተው የጀመሩት አይደለም፡፡ እንደ ህዝብ ሁለቱ ህዝቦች ወዳጅ እንጂ እንደ ጠላትነት የሚተያዩ አይደሉም፡፡ የተፈናቀሉት ግን ስለተጎዱ የድሮውን መልካም ነገር ሳይሆን የደረሰባቸውን ችግር ነው የሚያስታውሱት፤ ቅያሜም ጥላቻም ሊኖር ይችላል፡፡ ሶማሌውም - ኦሮሞ፣ ኦሮሞውም - ሱማሌ አፈናቀለኝ ሊል ይችላል፡፡ ይሄ ቢሰማቸውም አይፈረድባቸውም፡፡ ስህተቱ ያፈናቀለኝ ግለሰብ ሳይሆን ብሔር ነው ብሎ ከፍ አድርጎ ማሰቡ ላይ ነው፡፡ አሁን ዋናው መፍትሄ ሶማሌ የነበሩት ኦሮሞዎች እዚህ ይምጡ ወይም ኦሮሚያ የነበሩት ሶማሌዎች ወደዛ ይሂዱ አይደለም፡፡ ፈቃደኝነታቸው መታወቅ አለበት፤ አልሄድም ካሉ ምን ይደረጋል፤ ያ ሁሉ የደረሰብኝ ቦታ ተመልሼ  አልሄድም ሊሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ተመልሼ እሄዳለሁ የሚሉ ሲገኙ ከመንግስት ጋር ተነጋግረን እንቀበላለን፡፡ በአጠቃላይ ፈቃደኝነታቸው ነው የሚወስነው ለማለት ነው፡፡ በወቅቱ ኦሮሚያ ክልል አቅም ነበረው፤ አመራሩም ጥሩ ስለነበር ተፈናቃዮቹን ቦታ በማስያዝ በኩል ጥሩ ሰርቷል፡፡ እኛ ጋ ግን አመራሮቹ አልረዷቸውም፤ የተሰጠውም እርዳታ በሙስና ተበልቶባቸዋል፡፡ ከፌደራል መንግስት ለፈተናቃዮች እኩል የተሰጠው ገንዘብ የኦሮሚያው ቤት ሰርቶበታል፡፡  የእኛ ክልል በሙስና ተበልቷል፡፡ መዋቅሩም ፈረሰ ስለዚህ በጣም ተጋላጭ ናቸው፡፡ አሁን ጊዜ አግኝተናል ያንን ቁጭት ወገኖቻችንን መልሰን በማቋቋም እንወጣዋለን፡፡
ከኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር “ኦብነግ” ጋር አሁን ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል? የእነሱ ወታደሮችስ በምን ሁኔታ ነው የሚገኙት?
እኛ እንግዲህ እነሱም ተስማምተው መጥተዋል፡፡ እርግጥ አንድ የሚጨቆን ህዝብ ባለበት አካባቢ ነጻ ለመውጣት ከሚደረጉ ትግሎች አንዱ አማራጭ የትጥቅ ትግል ነው፤ ስለዚህ ትግላችሁ ትክክል አልነበረም ለማለት አልችልም፡፡ የህዝባችን ኑሮ እንዲህ መሆኑን አንቀበልም ብለው ነው ትጥቅ ያነሱት፡፡ ነገር ግን በዓላማ ደረጃ የሱማሌ ክልል ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆነው ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር  እጅ ለእጅ ተያይዞ መብቱን ፍትሃዊ በሆነች ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያስከብር የሚል አላማ ነው ክልሉን እየመራ ያለው ፓርቲ የሚያራምደው፡፡ እነሱም የምንፈልገውን አላማ የምናራምደው በሰላማዊ መንገድ ነው ብለው እስከተስማሙ ድረስ እዚህ መጥተው ስራቸውን መቀጠል ይችላሉ፡፡ የተለየ ግንኙነት የለንም፤ ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ በየጊዜው እንገናኛለን ስለ አጠቃላይ የክልሉ ችግር ያነሳሉ ሆኖም በፖለቲካ ደረጃ ከታየ እንደ ተፎካካሪ ነው የምናያቸው፡፡ አንዳንዴ የምንስማማቸው ነገሮች ካሉ አብረን እንሰራለን፤ በሚለያየን ነገር ላይ ተለያይተን ህብረተሰቡ የእኛን አላማ እንዲቀበል ተግተን ነው መስራት ያለብን፡፡ ሌላው በአጠቃላይ የእነሱ ወታደሮች ገብተው ክልሉ ተረክቧቸዋል፡፡ የቀረው መልሶ ማቋቋም ነው፡፡ በሌሎች ክልሎች ላይ እንደተፈጠረው እዚህ ገብተው ምንም የፈጠሩት ረብሻ የለም፡፡ አሁንም ቢሆን ስምምነታችንን አክብረው፣ በነጻነት ተንቀሳቅሰው፣ ተመዝግበው የፖለቲካ ፓርቲ ሆነው ዓላማቸውን እንዲያራምዱ ምቹ ሁኔታ እየፈጠርንላቸው እንገኛለን፡፡
አሁን ላይ በአዲስ አበባ ህብረ ብሔር ፓርቲዎችም ብሄር ተኮር ፓርቲዎችም ሆነ ንቅናቄዎችና ስብስቦች በመዋሃድ ወደ አንድነት እየመጡ ነው፡፡ ከኦብነግ ጋር የእንዋሃድ ጥያቄ ቢመጣላችሁ ትቀበላላችሁ?
የሚያዋህደው አላማ ነው አይደለም? ስለዚህ የእኛ አላማ ሁለት መሰረታዊ ነጥቦች አሉት፡፡ አንደኛ፤ የሱማሌ ህዝብ እንደ ህዝብ አንድ ሆኖ መምጣት አለበት እንጂ በጎሳ መከፋፈል የለበትም የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው፤ የሱማሌ ህዝብ የመገንጠል አጀንዳን አይቀበልም፤ አይጠቅመውም፤ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር አብሮ መስራትና መኖር ነው የሚፈልገው፡፡ ፓርቲያችን በዚህ ነው የሚያምነው፤ መስመሩም ይሄው ነው፡፡ በዚህ መስመር ከመጡ ምንም የሚያግድ ነገር የለም በነዚህ አጀንዳዎች ላይ የመርህ ልዩነት ካለ ግን የመዋሃዱ እድል ሰፊ አይደለም፡፡
10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የስያሜ ለውጥ ከማድረግ ጀምሮ እርስዎንም የፓርቲው ም/ሊቀመንበር አድርጎ መርጦ ብዙ ውሳኔዎች ተላልፈውበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በመዝጊያው ላይ ተገኝተው በተለይ የሶማሌን ህዝብ እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚያስቆጥረው ስያሜ በመቀየሩ የተሰማቸውን ደስታም ገልፀው ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈ እስኪ ምን ምን አንኳር ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች አሳለፋችሁ?
የድርጅቱ መስመር ቀድሞም የአፈጻጸም እንጂ ሌላ ችግር አልነበረበትም፡፡ ያው ከጊዜ ብዛት መሻሻል የነበረበት ነገር ነው የተሻሻለው፡፡ የተጻፈው ነገር ብዙ ችግር አልነበረውም፤ ሌላው በጣም ሊፈርስ የደረሰ ድርጅት ነበር፤ አሁን በአዲስና በተማሩ በክልሉ በስነ-ምግባር የተመሰገኑ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የሚያደርጉ እንዲሁም የሶማሌን ህዝብ አጀንዳ በብሄራዊ ደረጃ ማንፀባረቅ በሚችሉ ምሁራን መዋቀሩ ዋናውና ትልቁ ነገር ነው፡፡ ሌላው በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት ሱማሌ የሆነም ሆነ ያልሆነ በፓርቲው አላማ የሚያምንና የክልሉን ቋንቋ የሚችል ከሆነ ሶማሌ አለመሆኑና ብሄሩ የፓርቲ አባል ከመሆንና በፖለቲካው ከመሳተፍ እንደማያግደው ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ መስፈርቶቹን እስካሟላ ድረስ “እንዲህ ብሄር ነህ፤ ከዚህኛው ብሄር ነህ” ተብሎ በር አይዘጋበትም፡፡ ይሄ አግላይነትንና ዘረኝነትን ያስቀራል፡፡ በዚህ የማያምን ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊባል አይችልም፡፡ የብሄርተኝነት የጥላቻና የአግላይነት አስተሳሰብ የሱማሌ ህዝብ አስተሳሰብም አይደለም፤ እኛም እንደ አመራር ይገልጸናል ብለን አናስብም፡፡
አሁን በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ያዩታል፡፡ እዚህም እዚያም በሚነሱ ግጭቶች መፈናቅሎችና አለመረጋጋቶች ለውጡ ሊቀለበስ ይችላል ብለው የሚሰጉ አሉ፡፡ እርስዎ ይሄ ጉዳይ ያሰጋዎታል?
በበኩሌ ለውጡን ለመቀልበስ የሚሰሩ አካላት እንዳሉ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ለውጡ የሚቀለበሰው በእነሱ አቅም ሳይሆን በለውጥ ሀይሉ ስህተት ከተሰራ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በለውጥ ሀይሉ ስህተት ካልተፈጠረ፣ ለውጡ የያዘውን መስመር ይዞ ከቀጠለ፣ ለእኔ ተስፋ ነው የሚታየኝ፡፡ አንድን ለውጥ የያሳካውና የሚያራምደው ሀሳቡ ነው፡፡ ሀሳቡ ወቅቱን የጠበቀና ከጊዜው ጋር ይሄዳል ወይ? “ትክክለኛ ሀሳብ በትክክለኛ ጊዜ” እንደ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጊዜው የሚጠይቃቸው መሻሻል ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እንደነዚህ አይነት የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል ሀሳብ ማፍለቅ ከቻልን፣ አገሪቱ ትልቅ ደረጃ ላይ ትደርሳለች ብዬ አምናለሁ፡፡
በክልላችሁ አንዱ የውጥረት መነሻ የሆነው የነዳጅ ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ጅቡቲም መስመር እየተዘረጋለት እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ የኔ ጎሳ ከነዳጁ ብዙ መጠቀም አለበት የሚል አካልም እንዳለ ይነገራል፡፡ ፌደራል መንግስትም በአንድ በኩል አለ፣ የቻይና ኩባንያም በዚሁ ነዳጅ ላይ አለ፡፡ ይህን ጉዳይ በምን መልኩ ነው የምትመሩት?
ልክ ነው የውጥረት መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ በየትኛውም አለም እንደዚህ አይነት ሁከቶች ሲፈልቁ የውጥረት መነሻ ይሆናሉ፡፡ በእኛ ክልል ደረጃ ስንመለከት በፌደራል ደረጃ ያለ ቀመር አለ፡፡ በተለይ ነዳጅን በተመለከተ ቀመሮች አሉ፡፡ ከክልሉ ጋር ውይይቶች ይካሄዳሉ፡፡ እኛ በዛን ጊዜ የሶማሌ ህዝብን ጥቅም ያስጠብቃል የሌላውንም ኢትዮጵያዊ ጥቅም አይጎዳም የምንለውን ምክረ ሀሳብ (ፕሮፖዛል) ይዘን ነው የምንቀርበው፡፡ ከዚያ በፊት ግን ተጠቃሚ መሆን አለብን የሚል እምነት አለን፡፡ በየትኛውም አለም በአንድ አካባቢ የሆነ ሀብት ሲወጣ ትሩፋቱ ለሁሉም ዜጋ መድረሱ እንዳለ ሆኖ፣ ነገር ግን የአካባቢ የጤና ጉዳትም ስለሚያደርስ አካባቢው መጠቀም አለበት የሚል ሀሳብ አለን፡፡
በተለይ ይሄ አካባቢ ከሌላው በጣም ወደ ኋላ የቀረና በድጎማ የሚተዳደር ስለሆነ አካባቢው ተጠቃሚ መሆን አለበት የሚለውን ያጎላዋል፡፡ ፌደራል መንግስት የሚያደርገው ድጎማ ቆሞ አካባቢው ራሱን ይችላል ማለት ነው፡፡ አሁን ባለው የህግ ማዕቀፍ ውስጥ የኛ ክልል 50 በመቶ፣ ፌደራል መንግስት 50 በመቶ ያገኛል ይላል፡፡ ወደ ጅቡቲ ያለው የመስመር ዝርጋታ ተጀምሯል፡፡ መቼ እንደሚጠናቀቅ ለጊዜው አላወቅኩም፡፡ በመጨረሻ የማስተላልፈው መልዕክት፤ በአገራችን በአሁኑ ወቅት የመናገር ነጻነት ስላለ ሁሉም ነጻ ሆኖ መናገር ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነጻ ሆኖ እንዲናገር እንጂ ሌላው ሰው ነጻ ሆኖ እንዲናገር አይፈልግም፤ ሰው ለራሱ የሚፈልገውን ነጻነት ለሌላው የመፍቀድ ባህል ቢለመድ መልካም ነው፡፡ አሁን ላይ በአንዳንድ የፖለቲካ ጥያቄዎች ዙሪያ ልዩነቶች አሉ፡፡ የሁሉም ግንዛቤና እይታ እኩል አይደለም፡፡ አንዳንዶች “እኔ ያልኩት ብቻ ነው ትክክል፤ እኔ ያልኩት ካልሆነ በሀይል ሌላውን መጫን አለብኝ የሚለው አመለካከት መቅረት አለበት፤ መቻቻል ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው ከሌላው የተለየ ሀሳብ አሰበ ማለት ወንጀል ፈፀመ ማለት አይደለም፡፡ እንደ አገር የሀሳብ ልዩነትን ማክበርና መቻቻል ላይ መስራት ይጠበቅብናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተረፈ ጋዜጣችሁ በጣም ጥሩ ጋዜጣ ነው፡፡ በርቱ እላለሁ፡፡


Read 2594 times