Saturday, 06 April 2019 15:09

የለውጡ ጉዞና ለቀጣዩ ሂደት አንዳንድ ሃሳቦች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)


-እውቀት ስሜታዊነትን ካላሸነፈ፣ ጥበብን ካልያዘ፣ አገር ያፈርሳል
-በስመ ህጋዊነት የሚወሰድ አቅል ያጣ ድርጊት  ለውጡን ይጐዳል
-በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን አጀንዳ አድርጐ ማቅረብ ጤናማ አይደለም
-የመንግስት ኃላፊዎች እርስ በርስ መናበብ አለባቸው

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይና በለውጥ አመራሩ የለውጥ እንቅስቃሴ ተስፋ ከሰነቁ አንጋፋ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የቀድሞ የ"ቅንጅት"፣ ኋላም የ “አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ” አደራጅና አመራር የነበሩት አቶ አስራት ጣሴ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ራሳቸውን አግልለው የሃገሪቱን ፖለቲካዊ ሂደት እየተከታተሉ የሚገኙት አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ አስራት፤ ባለፈው አንድ አመት በነበረው የለውጥ ሂደትና ፈተናዎቹ፣ በቀጣይ መንግስት አተኩሮ ሊሰራባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ትንታኔያቸውንና ሃሳባቸውን አጋርተውታል፡፡ እነሆ፡-
የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን የ1 ዓመት የፖለቲካ አመራርና የለውጥ ሂደት እንዴት ይገመግሙታል?
የለውጥ ሂደቱ ፈታኝ ነበር፡፡ አሁንም ነው፡፡ የለውጥ ሂደቱ በተስፋና በፈተና የታጀበ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የለውጥ ሁሉ ሂደት አካል እንጂ ሊያስደነግጠን ሊያስገርመንም የሚገባ አይደለም፡፡ የቅርብ ጊዜው የ27 ዓመት የአምባገነን ስርአት፣ የከፋ የሰብአዊና የዲሞክራሲ መብቶች ረገጣ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የህግ የበላይነት መጥፋት፣ የግዙፍ ሙስና መስፈንን ተከትሎ የመጣ የለውጥ ሂደት በመሆኑ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጎታል፡፡ የለውጥ ሂደቱ በሞትና ሽረት ትግል አንፃር ሊታይ ይችላል፡፡ በነፍስ ውጪ፣ ነፍስ ግቢ መመሰልም ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አሮጌው ክፉውና ሰይጣናዊው ስርአት አልሞትም ሲል፣ ተስፋ አድርጎ የመጣው ለውጥ ደግሞ አድጋለሁ እመነደጋለሁ ብሎ ቆርጦ ሲመጣ፣ ሂደቱ በከፋ ፈተናና ውጣ ውረድ የታጀበ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው፡፡ አንድ የሰማሁት ቀልድ ይሄን አመለካከት የሚደግፍ ስለሚመስለኝ ልናገረው፡፡ በዓለም ላይ ካሉ ሰይጣኖች በሶሪያ  በየመንና በሊቢያ ከነበሩት መካከል የተወሰኑት በእነዚህ ሃገራት የነበራቸውን ስራ ያጠናቀቁ ስለመሰላቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነው የለውጡን ሂደት የበለጠ ፈታኝ ያደረገው የሚል ነው፡፡ ቀልዱ ለኔም የሚስማማኝ ነው፡፡ በህይወት ዘመኔ በእውነቱ፣ መልካምና በጎ ለውጥ ይሄን ያህል ክፉና ሰይጣናዊ ምላሽ ያጋጥመዋል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ ለካ የኢትዮጵያ ህዝብ ጭቆናንና ምዝበራን፣ አምባገነንነትን፣ ኢ-ፍትሃዊነትን፣ ኢ-ሰብአዊነትን፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊነትን ሳያውቀው ወይም አውቆ በደንብ ተለማምዶታል ወይም ወዶታል ማለት ይቻላል፡፡
እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፣ ልማዳዊ አስተሳሰብ፣ ስነ አመክንዮም የሚያስተምረን፤ ሰውን ያህል ክቡር የሆነ ፍጡር፤ ከነፃነት ያህል ክብር ይልቅ ባርነትን፣ ከመልካምነት ይልቅ ክፋትን፣ ከጤንነት ይልቅ በሽታን፣ ከብልፅግና ይልቅ ድህነትን፣ ከአትራፊነት ይልቅ ኪሳራን ይመርጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እየሆነ ያለው ግን ይሄን ስለሚመስል የለውጡ ሂደት ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ይህም ሆኖ በመጨረሻ በጎነት ክፋትን፣ ሀገራዊ አንድነት ሃገራዊ መከፋፈልን፣ ሰብአዊነት ኢትዮጵያዊነትና ዜግነት፣ አክራሪ ብሄርተኝነትና ጎሰኝነትን ያሸንፋል ብዬ በፅኑ አምናለሁ፡፡ አሁን ያለንበትም ሆነ የወደፊቱ ሂደት ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡ ይሄን ግን በወርቅ ወይም በብር ሰሃን ላይ አስቀምጦ የሚሰጠን የለም፡፡ በኛው ያላሰለሰ ጠንካራ ትግል፣ በመነጋገር በመወያየት ፍላጎት፣ ከአንድ ወገን አሸናፊነት የሁሉንም አሸናፊነትን ከመሻት፣ ሰጥቶ የመቀበል ባህሪን ስንለማመድ ስናዳብር ነው ወደ እውነታው የምንጠጋው፡፡
በአሁኑ ወቅት ሰፊ የመጠራጠርና ያለመተማመን ሁኔታዎች የተፈጠሩ ይመስላሉ፡፡ እነዚህ መጠራጠሮችና አለመተማመኖች ከምን የመነጩ ናቸው?
በሰው ልጆች ሰብዕና ውስጥ አንዱ ሌላውን መጠራጠሩ አዲስ አይደለም፡፡ መተማመን ይከብዳል፤ መጠራጠር ይቀላል፡፡ የታሪክ ትርክት ራሱ ሁለት ገፅታ አለው፡፡ አንዱ ትርክት ሰዎች ከታሪክ ብዙ ነገር ይማራሉ ሲል፣ ሌላኛው ትርክት ደግሞ ታሪክ የሚያስተምረን ቢኖርም፣ ሰዎች ከታሪክ እንደማይማሩ ነው ይላል፡፡ ስለዚህ ታሪክ ብዙ አስተምሮን ቢሆን ኖሮ፣ ለምን ሰዎች በሌላው ላይ የታየውን ችግር፣ በተደጋጋሚ በታሪክ የታዩ ስህተቶችን ይፈፅማሉ? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ መቼም ይሁን የትም ቦታ፣ ከጨቋኞች አምባገነኖች ጋር የሚደረገው ፍልሚያ እልህ አስጨራሽ ነው፡፡ በዓለም ላይ አንዱን ጌታ በሌላ ጌታ፣ አንዱን ጨቋኝ በሌላ ጨቋኝ ለመተካት የሚደረግ ትግል የለም፡፡ የጨቋኞች ቆንጆ የለም፡፡ የጨቋኞች መልካም የለም፡፡ ትግል የሚደረገው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጭቆናን አሽቀንጥሮ ለመጣልና ዘላለማዊ ነፃነትን፣ እኩልነትንና ፍትህን ለማስፈን ነው፡፡ አንድን ብሔር በሌሎች ላይ የማንገስ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች አሉ ብዬ ለማሰብ እቸገራለሁ፡፡ ካሉ ግን ይሄ አስተሳሰብና አካሄድ ትናንትም አልሰራም፤ ዛሬም ነገም አይሰራም፡፡ ይሄን የሚያስቡ የሚሞክሩ ካሉ ደግሞ ሌሎቻችን ትግልን “ሀ” ብለን እንድንጀምር ያደርጋሉ እንጂ አላማቸው አይሳካላቸውም፡፡ ሌላኛውን ትግል ሀ ብለን ስንጀምር በሁሉም ወገን የሚከፈለው እዳ፣ የሚያስከፍለን የሰብአዊ ውድመትና ጥሪት ከፍተኛ ዋጋ ያለው ይሆናል እንጂ የአናሳ ህዝቦችን መብት በመጣስ ወይም በመደፍጠጥ የብዙ ህዝቦችን መብት ማስከበር አይቻልም፡፡ የአናሳ ህዝቦችን መብት መጣስ ማለት የብዙኃንን መብት መጣስንም ያስከትላል፡፡ አናሳዎች ሲደመሩ ደግሞ የብዙኃንን ድምፅ መብለጥ እንደሚችሉ ብዙም የሂሳብ እውቀት አይጠይቅም፡፡ ወርቃማው መርህ መሆን ያለበት አንዱ ለሁሉም፣ ሁሉም ለአንዱ ይስራ ይቁም የሚለው ነው፡፡ በእኔ እምነት ሰው መሆን ራሱ አንድ ሊያደርገን ይችላል፡፡ እኛ ደግሞ ታድለን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊም ነን፡፡
በአሁኑ ወቅት የለውጥ ኃይሎች በመልካም ሁኔታ ኢትዮጵያዊነትን እያስተማሩ እያቀነቀኑ ስለሆነ እኔ ብዙም አልጨምርበትም፡፡ ከጠ/ሚኒስትሩ አባባል በመጥቀስ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” ብለዋልና እነዚህን መሰረታዊ ሃሳቦች አሳድገን፣ እንደ ህዝብ ትልቅ መሆን አለብን፡፡ በመጠራጠር በመወሻሸት፣ በመካካድ የምንጓዝበት መንገድ ሁላችንንም ያከስረናል እንጂ ማንም ከዚህ ሊያተርፍ አይችልም፡፡
እንዴት ነው ከመጠራጠርና አለመተማመን ስሜት መውጣት የሚቻለው?
በመሰረቱ ብሔርተኝነትን ስናስብ፣ እኔ ከዚህ ብሔር ነኝ ብሎ መግለፅ ክፋት የለውም፡፡ ችግርም አይደለም፡፡ ችግሩ ብሔርተኝት በዚህ ላይ ያለማብቃቱ ነው፡፡ በዓለም ታሪክም እንደታየው፤ ብሔርተኝነት “ካንተ ብሔር የኔ ብሔር ይበልጣል” የሚለውን ያስከትላል፡፡ “የኔን ብሔር መብት የማስጠበቅ ኃላፊነት አለብኝ” እየተባለም ይቀጥላል፡፡ እነዚህ ሃሳቦች በአክራሪ ብሔርተኞች ሲቀነቀኑ ደግሞ ወደ ፋሺስዝም ነው የሚሄደው፡፡ ፅንፈኛ ብሔርተኝነትን ነው የሚያስከትለው፡፡ ጥፋትና ውድመት ነው መጨረሻው፡፡ ሰው መሆናችን፣ ኢትዮጵያዊ መሆናችን፣ ቀጥሎም ዜግነታችንን አስቀድመን፣ አንዱ ለአንደኛው መቆም ስንችል ነው ችግራችንን የምንሻገረው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለችግሮች ሁሉ መፍትሄ ባይሆንም አብዛኞቹን ችግሮቻችንን ይፈታልናል፡፡ በመሆኑም ሃቀኛና ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባት፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ፣ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ወደ ስልጣን ማምጣት፣ በዜግነት ላይ የተመሰረተ ሃገራዊ አንድነትንና መግባባትን መፍጠር ችግሮቻችን ማሸነፊያ መንገዶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን የማቅለጫ ማሰሮ (A melting pot) ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ማሰሮ ውስጥ ህዝቦች ይቀልጣሉ፡፡ ይሄ በየትኛውም ዓለም የተሰራ ነው፡፡ ሁላችንም አንድ ማሰሮ ውስጥ ቀልጠን ነው የተሰራነው፡፡ እከሌ የነጠረ የዚህ ብሔር ነው፣ እከሌ የነጠረ የዚህ ዘር ነው ማለት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ የማቅለጫ ማሰሮ ነች፡፡ ሁላችንም ቀልጠንባታል፡፡ ለብዙ ዓመታት ሁላችንም ቀልጠንባታል፡፡ ይሄን ፖለቲከኞች ለማየት አልፈለጉም እንጂ ኢትዮጵያ ባለፉት ብዙ አመታት የብሔሮች ማቅለጫ ማሰሮ ሆና ኖራለች፡፡ አንዱ ብሔር ከሌላው ጋር በጋብቻ፣ በጉዲፈቻ ተሳስሯል፡፡ የምንከተላቸው እምነቶች በብሔር ማንነት ልክ የተወሰኑ አይደሉም፡፡ የስጋ ዘመዳሞች ሳይቀር የተለያየ እምነት ነው ሲከተሉ የምናየው፡፡ አንድነታችን ከልዩነታችን ይበልጣል፡፡ እኛ ግን ክፋታችን በዝቶ ልዩነታችንን እያጎላ፣ አንድነታችንን እያጠፋን ነው፡፡ በቅን መንፈስ ከታየ ልዩነታችን ውበታችን እንጂ ችግራችን ሆኖ አያውቅም፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በብዙ ንግግሮቻቸው ስለ ኢትዮጵያ ሲናገሩ  ይደመጣል፡፡ እሳቸው የሚጠቅሷትን ኢትዮጵያ እርስዎ እንዴት ነው የሚረዱት?
ስለ ኢትዮጵያ ሲገለፅ በኔ አዕምሮ ውስጥ አንዲት ኢትዮጵያ ነው ያለችው፡፡ በውስጧ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦችን ያዘለች ሃገር ነች፤ ስለ እሷ ኢትዮጵያ ነው ጠ/ሚኒስትሩም አቶ ለማም የሚናገሩት፡፡ ከዚህ በፊት በህውሓት/ኢህአዴግ ዘመን ስለ ኢትዮጵያ ሲነገር ብዙ ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን እነሱ የሚያሳዩኝ ኢትዮጵያና እኔ የማውቃት ኢትዮጵያ ሁለት የተለያዩ ነበሩ፡፡ አሁን ግን በዶ/ር ዐቢይም፣ በአቶ ለማም፣ በእነ አቶ ገዱም በሌሎች የለውጥ ኃይሎች የምትነገረውን ኢትዮጵያ ስሰማ፣ እኔ የሚታየኝ የሁላችንንም የጋራ ኢትዮጵያን ነው የሚመስለኝ፡፡ የጋራዋ ኢትዮጵያ ነች እነሱ የሚያነሷት፡፡ ህዝቦቿ በእኩልነት፣ በአብሮነት የሚኖሩባት፣ ሰዎች በማንነታቸው አድልኦ የማይደረግባቸው ሃገር እንድትሆን፣ ሰዎች መመዘኛቸው ብሔርና ከማን መጡ? የማን ዘር ናቸው? ምን ሃይማኖት ይከተላሉ? የሚለው ሳይሆን በእውቀት በችሎታ ላይ የተመሰረተ መመዘኛ የሚጠበቅባቸው ኢትዮጵያን ነው የሚነግሩን፡፡ እነሱ የሚናገሯት ኢትዮጵያ፣ እኔም የማስባት ኢትዮጵያ ናት፡፡ በኔ ኢትዮጵያና በእነሱ ኢትዮጵያ መሃል ልዩነት አላይም፡፡ በህውሓት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያና በኔና በጓደኞቼ ኢትዮጵያ መሃል ግን ሁለት ኢትዮጵያ ነበር የምናየው፡፡
ለውጡ እንዴት አስተማማኝ መሰረት ይዞ መቀጠል ይችላል?
በሁሉም መስክ ህዝብን የማሳተፍ ባህል መቀጠል አለበት፡፡ ህዝብን በተለያየ መንገድ ለለውጡ መቀስቀስ መቀጠል አለበት፡፡ ለውጡ ተቋማዊ እንዲሆን ማድረግ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ለውጡን ከውስጥ ቦርቧሪዎችና አደናቃፊዎች መከላከል፣ ከክፉና ጠላት አብዛኛው ከውስጥ ስለሆነ ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ለውጡን እያንዳንዱ ዜጋ መከታተል አለበት፡፡ የመልካም አስተዋፅኦ ትንሽ የለውም፡፡ ሁሉም በጎ ሃሳብ ቢያዋጣ ውጤቱ ያማረ ይሆናል፡፡ የህዝብን መፈናቀል ማስቆም፣ የተፈናቀሉትን መልሶ የማቋቋም ስራዎች በቅደም ተከተል መከናወን አለበት፡፡ አፈናቃዮች፣ ህገ ወጥ ድርጊት ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች በሞቀ ቤታቸው ተቀምጠው ሌሎች ሲፈናቀሉ ማየት እንደ ዜጋ ያቆስላል፤ እንደ ሰው ያማል፡፡ ልብ ይሰብራል፤ አንዳንድ ጊዜ ሰው መሆንንም ያስጠላል፡፡ ህገ ወጥ የሆነን ሁሉ ህጋዊ ለማድረግ የ24 ሰዓትና የ1 ወር ሩጫ ለኔ ተገቢ አይደለም፡፡ በህዝብና በመንግስት መሃል ቅራኔ እንዲፈጠር በስመ ህጋዊነት የሚወሰድ ድንብርብሩ የወጣ ውሳኔና አቅል ያጣ ድርጊት ለውጡን ይጎዳል፡፡ ከተፈናቃዮቹም በላይ ሃገርንና ታላቁን የለውጥ ተስፋ ነው የሚጐዳው፡፡ የሃገርን ህልውና ነው ፈተና ውስጥ የሚከተው፡፡
ቀጣይ የለውጥ ፈተናዎች ምንድን ናቸው?
አንዱ በብሔር የመደራጀት ጉዳይ ነው፡፡ የፓርቲዎች በብሔር መደራጀት አሁንም ለሃገሪቱ አንድ ፈተና ሆኖ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ለዚህ መፍትሄው ፓርቲዎች በአላማ በአስተሳሰብ፣ በሃሳብ ልዕልና ላይ ቢሰባሰቡ ይሄ አስጊ ሁኔታ ሊቀረፍ ይችላል፡፡ አሁን በተጨባጭ እያየን እንዳለነው፣ ይሄ ጉዳይ ፅንፍ ወጥቶ፣ እከሌ በኔ ቦታ መጥቶ ህዝብ አያደራጅም አይቀሰቅስም እየተባለ ነው፡፡ በአንድ ሃገር እየኖርን አይደለም ማለት ነው? ስለዚህ ይሄን በብሔር የመደራጀት ፈተና መወጣት ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት በብሔር የመደራጀት ነገር አስፈላጊ የነበረበት ጊዜ ኖሮ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ግን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ በብሔር መደራጀትን የሚሻ አይደለም፡፡ አሁን የዲሞክራሲያዊ ስርአት እየገነባን፣ አንድ ሰው አንድ ድምፅ እያልን፣ ነፃና ፍትሃዊ ተቋማት ተቋቁመው ህዝብ የመረጠው መንግስት ወደ ስልጣን ይመጣል በሚባልበት ጊዜ በሃሳብ ዙሪያ መደራጀት ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ ኢህአዴግም ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ ይመጣል ብለዋል፤ ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ ከኢህአዴግ በተጨማሪ ለአጋሮችና ለተቃዋሚዎችም በሩ ክፍት ነው ተብሏል፡፡ ይሄ መንገድ ችግር ያሻግራል፡፡ ወደ ውህደት ሲኬድ ብሔርተኝነትና ማዶ ለማዶ መተያየቱ ያበቃል፤ ይከስማል፡፡ ከዚህ ፈተና በዚህ መንገድ ከወጣን፣ ትልቁን የሃገሪቱን ፈተናና ችግር እንሻገራለን ብዬ አምናለሁ፡፡
ከዚህ በኋላ መንግስት በምን ላይ አተኩሮ እንዲሰራ ይመክራሉ?
ህዝባዊ ውይይቶች መጠናከር አለባቸው፡፡ የመግባቢያ ፎረም፡- ዜጎች ተነጋግረው የሚግባቡበት መድረክ ባላሰለሰ መንገድ መቀጠል አለበት፡፡ በሌላ በኩል መንግስት የሚሰራውን ነገር በቅደም ተከተል ማስቀመጥ አለበት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሊቆዩ የሚችሉ የቤት ስራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ጉዳይ፡፡ አዲስ አበባን አጀንዳ አድርጎ በዚህ ወቅት በአጉሊ መነፅር ማቅረብ ጤናማ አይደለም፡፡ ባሉብን የሰላምና የመረጋጋት ችግሮቻችን ላይ እንዳናተኩር አጀንዳ አስቀያሽ ድርጊት ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት እንደ መንግስት፣ ህዝብም እንደ ህዝብ እነዚህ ጉዳዮች ሊቆዩ ይችላሉ ማለት አለባቸው፡፡ አንዳንድ መፍትሄዎች በራሳቸው ጊዜ ይመጣሉ፡፡ አጀንዳዎችን ያለ ቦታቸው፣ ያለ ሰአታቸው ማራገብ አይገባም፡፡ ሌላው የመንግስት ኃላፊዎች እርስ በእርስ መናበብ አለባቸው፡፡ አንድ መግለጫ ከወዲያ ጫፍ፣ ሌላኛው ከወዲህ ጫፍ ይወጣል፡፡ ሁለቱም የተለያዩ ናቸው፡፡ መናበብ የለም፡፡
ይሄ አንዱ የችግር ማበራከቺያ ስልት ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን አንዱ ሌላውን የጠበቀ፣ የጋራ ፀባይን የሚያንፀባርቅ ነው መሆን ያለበት፡፡ አንዱ ሌላው ያለውን ለማዳን እንደገና ቀዶ መስፋት ውስጥ እየተገባ፣ ጉልበት ማባከን አያስፈልግም፡፡ በዚህ ረገድ መንግስትና የመንግስት ኃላፊዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ፕሬሱም ቢሆን ኃላፊነት በተሰማው መንገድ መሄድ አለበት፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑም ወቅቱን በጥንቃቄ ማየት አለባቸው፡፡ አንድን ነገር ካላወቅን ተሽቀዳድመን መናገርም ለህዝብ መግለፅም ተገቢ አይደለም፡፡ ስለምንናገረው ነገር ጊዜና ወቅት ማገናዘብ አለብን፡፡ ያወቁትን ሁሉ የትም አይለቀቅም፡፡ ኃላፊነት ይሰማን፣ መቆጣጠር የማንችለውን ሃሳብ ማዘግየት ማሳደር መልመድ አለብን፡፡ መንግስትን ሂስ ማድረግ፣ መንቀፍና መጣላት ይሄን ያህልም ጀግና አያደርግም፡፡ ለማጣላት ጊዜ አያልቅብንም፡፡ ስሜታዊነት ነው የጎዳን፡፡ እውቀት ስሜታዊነትን ካላሸነፈ፣ ጥበብን ካልያዘ ሃገር ያፈርሳል፡፡ ህዝብ ይበትናል፡፡ ስለዚህ ስለምንናገረው ነገር፣ ስለምንሰራው ነገር ጥንቃቄ ያስፈልገናል፡፡ ትልቁን ስዕል ኢትዮጵያን እያየን ነው መስራት ያለብን፤ ቅርንጫፉን ሳይሆን ግንዱን እያየን፣ ለግንዱ መኖር ከሰራን፣ ቅርንጫፎቹን ማለምለም ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡  

Read 890 times