Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 02 June 2012 08:43

የህፃናቱ ጥቃት ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ወንጀሎች ህግፊት አይቀርቡም

. በህፃናት ጥቃት የሚቋረጡ ክሶች ይበዛሉ....

. “ጉዳችን እንዳይወጣ” በሚል ብዙ ጥቃቶች ተሸፋፍነው ይቀራሉ

. ጥቃት ፈጣሚወዎች ቤተሰብና ዘመድ ናቸው...

.  የህፃናት ጥቃት

ከወላጆች ይልቅ ጎረቤቶች ለፖሊስ ያመለክታሉ

የዛሬ ዓመት ገደማ የ3 ዓመቷ ህፃን ሚጡ ከወላጆችዋ ቤት ወደ አያቶችዋ ቤት ተወሰደች፡፡ እናቷ ወደ አረብ አገር በመሄዷና አባቷ ጠዋት ወጥቶ ማታ የሚገባ ስለነበር ነው፡፡ የዛሬ አራት ወር ግን ያልተጠበቀ ነገር አጋጠመ፡፡ ህፃኗ በወንድ አያትዋ ተደፈረች፡፡ ሚጡ በወቅቱ ሆስፒታል ተወስዳ ህክምና ብታገኝም ጥቃቱን ለህግ ያመለከተላት ማንም የለም፡፡ ቤተሰቡ ወደ ፍ/ቤት ያልሄደው ጉዳችን አደባባይ ይወጣል በሚል ፍራቻ ነበር፡፡

የህክምና ምርመራ ውጤቱ ህፃኑዋ ቁስለት እንዳላት ያሳያል የምትለው የሚጡ ሴት አያት ጐረቤት ናት፤ ይህን ለፖሊስ ጣቢያ ስታመለክት ማስረጃ እንድታቀርብ መጠየቋንና የመክሰስ መብት ያላቸው አሳዳጊዎቹ ናቸው እንደተባለች ተናግራለች፡፡ ከሚጡ ሴት አያት ጋር መነጋገሯን የምትናገረው እቺው ጐረቤት፤ ሴትየዋ የተፈፀመባት ጥቃት ቀላል እንደሆነና ለክፉ እንደማይሰጣት ገልፀውልኛል ብላለች፡፡ ሴት አያቷ  ህፃኗን ከሰው ማገናኘት አይፈልጉም፤ ታወራለች ብለው ስለሚፈሩ ብላለች - ጐረቤትየዋ፡፡ ዛሬም ህፃኗ ከአያቶቿ ጋር እንደምትኖር ታውቋል፡፡

አራት ኪሎ ባልቻ አባነፍሶ ሠፈር አካባቢ የሚኖረው አንድ አባት ደግሞ በ5 ዓመት ህፃን ልጁ ላይ የደረሰባትን ጥቃት ነግሮናል፡፡ ከቀድሞ ሚስቱ ከተለያየ አራት ዓመት እንደሆነው የሚናገረው ይህ አባወራ፤ ሌላ ሚስት ማግባቱንና ሁለት ልጆችም መውለዱን ይገልፃል፡፡ ከቀድሞ ባለቤቱ የወለዳት ሴት ልጁ አሁን አምስት አመቷ ሲሆን፤ ህፃኗ የ6 ወር ልጅ ሳለች ነበር ከእናቷ የተለየችው፡፡ ለአምስት አመት ብቻውን እንዳሳደጋትና የቀድሞ ባለቤቱ ልጄን ማየት እፈልጋለሁ ብላ በቀበሌው ሴቶች ጉዳይ በኩል ጠይቃ እንደተፈቀደላት ይናገራል፡፡ ከኬጂ ተማሪ የሆነችው ህፃን አርብ አርብ ከት/ቤት ስትወጣ ወላጅ እናቷ ጋር ሄዳ ታድርና ሠኞ ወደ አባቷ ቤት ትመለሳለች፡፡ ህፃኗ በጥምቀት ጊዜ እናቷ ጋር ደርሳ ስትመጣ የተለየ ባህሪ ማሳየቷን የተናገረው አባት፤ ባለቤቱ የህፃኗን ገላ ስታጥባት የሆነችውን ጠየቀቻት፡፡  የቀድሞ ባለቤቴ ከሌላ የወለደችው ወንድ ልጇ ጥቃት እንደፈፀመባት ነገረቻትና ሆስፒታል ወሰድኳት ይላል፡፡ “የካቲት 12 ሆስፒታል ወስጃት ስትመረመር የመድፈር ሙከራ እንደተደረገባት ገለፁልኝ፤ ሆኖም የእናቷ አጐት እዛ ዶ/ር በመሆኑ ማስረጃ ሊሰጡኝ አልቻሉም” ብሏል - አባት፡፡

ጥቃት የፈፀመባት ወንድሟ ከተናገርሽ እገድልሻለሁ እንዳላት ልጁ እንደነገረችው የሚገልፀው አባት፤ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ቃሏን እንደሰጠችና ለህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርም ማመልከቱን ይናገራል፡፡ ልጁን በግል ክሊኒክ አስመርምሮ ጥቃቱን የሚገልጽ ማስረጃ መያዙንም የገለፀው የህፃንዋ አባት፤ ጥቃት ያደረሰው ልጅ ግን እስካሁን ጥያቄ እንኳን አልቀረበበትም ይላል፡፡

“የወረዳው ፖሊስ የምታወራው የውሸት ፈጠራ ነውና፤ ሁለተኛ ስለዚህ ጉዳይ እንዳታወራ” ብሎኛል የሚለው አባት፤ “ልጄ አሁንም ስትሸና እንባዋ ይፈሳል፤ ሲጨልም አትወድም ትባንናለች፡፡ ልጆቼን ለማሳደግ ብዬ ቤቴ ተቀምጬ የፍትህ ያለ እላለሁ” ብሏል፡፡

ሦስት ልጆችን የወለደችው ከሦስት አባት ነው፤ የቀድሞ ባለቤቷ እራሱን አጥፍቶ ሲሞት ሁለተኛው  በመኪና አደጋ ህይወቱ አልፏል፡፡ አንድ ልጅ የወለደችበት የአሁኑ ባሏ በአንድ ጭፈራ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ ይሠራል ሙሉ በሙሉ በእሱ ወጪ የሚተዳደሩት እነዚህ ቤተሰቦች በአንድ ክፍል ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡

አንድ ጊዜ እናት ለቅሶ ገጥሟት ወደ ክ/ሀገር ትሄዳለች - የመጨረሻ ልጇን ይዛ ሁለተኛ ልጇን ደግሞ ጐረቤት ጋ እንድታድር አድርጋ፡፡ እቤት የቀሩት የመጀመሪያ ወንድ ልጇና ባለቤቷ ነበሩ፡፡ ማታ ሲተኙ እንጀራ አባቱ መደብ እንዳይቆረቁረኝ አብረን እንተኛ ሲል እሺ ብሎት አብረው እንደተኛ ይናገራል፡፡ ከዛም እንዳይሞቅህ ሱሪህን አውልቅ ይለዋል፡፡ ከእንቅልፉ የባነነው እንጀራ አባቱ በመቀመጫው በኩል ሲደፍረው ነው፡፡ “ታዳጊው ከሰው ተገልሏል፤ ማንንም አያናግርም፤ በቀን ሁለት ጊዜ ያስመልሳል፤ የመጨረሻዋን እህቱን አይወዳትም፤ ሁሌም ይወረውራታል”፡፡ ብላለች እናት፡፡ የሚያስተዳድራት ባሏ ስለሆነ የወንድ ልጇን መደፈር ወደ ህግ ለመውሰድ እንዳልቻለች የገለፀችው እናት፤ ባሏ ሁለተኛዋን ልጇንም ሳይደፍራት እንደማይቀር ትናገራለች፡፡ “ልጄ ሁሌም ስወጣ አብሬሽ ልሂድ ትለኛለች፡፡ አብራው መቀመጥ አትፈልግም፡፡ ያደረገውን ብነግርሽ ትሞችብኛለች ትለኛለች” ብላለች፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ በሷ በኩል ሳይሆን በጐረቤቶቿ በኩል ወደፍርድ ቤት እንዲሄድ እንደምትፈልግ የምትናገረው እናት፤ ምክንያቱም ገቢ የለኝም ብላለች፡፡ አሁንም ከባለቤቷ ጋር ነው የምትኖረው፡፡

ፍርድ ቤት ያገኘናቸው ወ/ሮ ዳግም የ11 አመት ልጇቸውን የደፈረባቸው የጓደኛቸው ልጅ ሲሆን ከጓደኛቸው ጋር ባላቸው ቅርበት  ቤተሰብ እንደሆኑና ለመክሰስ እንደሚቸግራቸው ይናገራሉ፡፡ “ልጁ ገና የ16 አመት ልጅ በመሆኑ ነገ ይማራል ብዬ ትቸዋለሁ” ይላሉ፡፡ ጓደኛቸው የ10ሺህ ብር ካሳ ስለሰጧቸውም ጉዳዩን እርግፍ አድርገው ትተውታል፡፡ ዛሬ ፍ/ቤት ብቆም ክብሬን ነው የማዋርደው፤ አንዴ የፈሰሰ ውሃ አይመለስም፤ ድርጊቱ ለጉዳት አሳልፎ አልሰጠውም የሚሉት ወ/ሮዋ፤ ቢከሱ የጐረቤት መጠቋቆሚያ እሆናለሁ ብለው እንደሚፈሩ ገልፀዋል፡፡

ወ/ሮ ሌሊሴ ተርፋሳ በፍ/ሚኒስቴር የልደታ ፍ/ጽ/ቤት ም/ሃላፊ ሲሆኑ እንዲህ አይነት ጉዳዮች በየቀኑ ይገጥመናል ይላሉ፡፡ ማህበረሰቡ ወንጀለኛ ከማስቀጣት ይልቅ ከጐረቤቴ እቀያየማለሁ፤ ሰው ያገለኛል የሚል ስሜት እንዳለው ገልፀው፤ በዚህ ምክንያት ድርጊቱ የተፈፀመባቸው ህፃናት ከሆኑ “ሌላ ሰው ነው” እንዲሉ፤ ለአቅመ ሔዋን ወይም አዳም የደረሰ ከሆነ ደግሞ “ፈቅጄ ነው የተደረገው” ብለው እንዲመሰክሩ በማድረግና ምስክሮችን በማጥፋት ለወንጀለኛ ከለላ ይሰጣሉ ብለዋል፡፡ ም/ሃላፊዋ በአንድ ወቅት የገጠማቸውን ሲያስታውሱ፤ አንዴት ልጅ ተደፈርኩ ብላ ክስ ታቀርባለች፡፡ ሆኖም ድርጊቱን የፈፀመባት የጐረቤት ልጅ በመሆኑ እናቷ ስማቸው እንዳይጠፋ በሚል “ድርጊቱ በሀይል አልተፈፀመብኝም፤ ፈልጌ ነው በይ” ብለዋት እሷም በማለቷ ክሱ መቋረጡን ጠቁመው፤ ከሚከሰሱት በበለጠ የሚቋረጡ ክሶች እንደሚበዙ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻ ሃላፊዋ በሰጡት ማሳሰቢያ “ስሜ፣ ክብሬ፣ ድጋፌ እያሉ ወንጀለኛን መሸሸግ በራሱ ወንጀል ነው” ብለዋል፡፡

 

 

Read 19579 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 11:02