Saturday, 06 April 2019 14:56

ከሀረር ማረሚያ ቤት ታራሚ ጠፋ ተባለ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(2 votes)

   በማታለል ወንጀል ተከሰው ሰባት አመት ከ6 ወር የተፈረደባቸው አቶ ጌታሁን መንግስቴ የተባሉ የህግ ታራሚ፣ ከሀረር ማረሚያ ቤት ጠፍተዋል መባሉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ግለሰቡ አዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መታየታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በማታለል ወንጀል ተከሰው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ አራዳ ምድብ ችሎት ነሐሴ 2 ቀን 2010 ዓ.ም በሠጠው ውሳኔ በሦስት የክስ መዝገብ ሦስት አመት፣ በድምሩ  ስድስት አመትና ስድስት ሺህ ብር ይፈረድባቸዋል፡፡
በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በመዝገብ ቁጥር  132809 በተከሰሱት በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል ወንጀል አንድ አመት ከ6 ወር የእስር  ውሳኔ ይሠጣል፡፡
ግለሰቡ የተጣለባቸውን ቅጣት ለመፈፀም ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የገቡ ቢሆንም፣ ታራሚዎች ለቤተሰቦቻቸው ቅርብ ለመሆን በሚያመለክቱት የመብት ጥያቄ መሠረት አንድ ሶስተኛው የቅጣት ጊዜን ማጠናቀቅ ሲገባቸው፣ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ስድስት ወር ከታሠሩ በኋላ በየካቲት ወር በጠየቁት የዝውውር ፈቃድ መሠረት፣ ወደ ሀረር ማረሚያ ቤት ዝውውር እንደተደረገላቸው የገለፁልን ምንጮች፤ ሀረር ማረሚያ ቤት ከገቡ ከሁለት ቀን በኋላ ከማረሚያ ቤቱ በመውጣት አዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መታየታቸው ግርምት ፈጥሮብናል ብለዋል፡፡
አቶ ጌታሁን ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ሲሆን፤ ዝውውር የተደረገላቸው ደግሞ ሀረር መሆኑን የገለፁት ምንጮች፤ ይሄ የአሠራር ክፍተትን ያሳያል ብለዋል፡፡
የሀረር ማረሚያ ቤት የመረጃ ክፍል ዶ/ር ዋሴ ካሳ ስለ ጉዳዩ ጠይቀናቸው በሰጡን ምላሽ፤ ጉዳዩን ለማጣራት በወቅቱ ጥበቃ ላይ የነበሩት ፖሊሶች ላይ ምርመራ እያደረጉ መሆኑን ገልፀው፤ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ለፌደራል ፖሊስ የትብብር ድጋፍ መጠየቃቸውን ገልፀዋል፡፡  

Read 1521 times