Saturday, 30 March 2019 14:01

ጥቂት ዕብዶች እንዳያሳብዱን!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ለመስዋዕት - ሻማ
ለውበት …አበባ
ለጀግኖች ….አንበሳ
ከመምሰል በቀር አዲስ ቃል ብርቅ ሆነ፤
አዲስ ያለው ሁሉ እየተኮነነ፣
ሻማው ከጨለማ ላይቀልጥ ተዳልቦ፣
አበባና ውበት በብር ተቸብችቦ፣
አንበሳው በጅቦች ጉልበቱ ተሰልቦ…
(እናት ፍቅር ሐገር፣ አሌክስ አብረሃም)
ጣጣችን  የማያልቅ፣ ታሪካችን እንባ ያጨቀየው፣ ደማችን ፍሬ አልባ እየሆነ ሺህ ዓመታት መኳተንና መበተን ዕጣችን ቢሆንም፣ ተያይዘን ለመውጣት ግን ውስጣችን ያደገው ሥነ ልቡናዊ ቁስል ሰንሰለት የሆነብን ይመስላል፡፡
ሰሞኑን እንደዋዛ ያገኘሁት አንድ ወዳጄ በቁዘማ ካወራኝ ብጀምር ደስ ይለኛል፡፡ ነገሩ ውስጤ ተቀምጦ እንደ እሣት ይለበልበኛል፡፡ ዐይኖቹ ውስጥ ይንቀለቀሉ የነበሩት የተስፋ ሻማዎች ቀልጠው፣ ዐመድ የታቀፉት ኳሶች ያስነበቡኝ፣ ጦርነትና ግጭት ገዳይ መሆናቸውን ነው፡፡ በሚኖርበት አካባቢ ጓደኞቹ ለሁለት ተከፍለዋል፡፡ አማቾቹ ተለያይተዋል፡፡ አጐቶቹ ጐራ ለይተዋል፡፡ ከዚህ በላይ እርግማን የለም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት ከተነሣባቸው አካባቢዎች በአንዱ የመንግሥት ሠራተኛ ሆኖ አውቀዋለሁ፡፡ አስተሳሰቡም በሰል ያለ ነው። መጻሕፍት የሚያገላብጥ ስለሆነ ሲያወራም የሚደመጥ፣ ሲስቅና ሲያለቅስም እውነት ያለው ነው፡፡ አሁን ሥራውን ከሚሠራበት አካባቢ በዘውግ ግጭት ለቅቆ፣ ወደ ራሱ ዘውግ በመሸሽ ኑሮውን ጀምሯል፡፡ በግጭቱ ከሁለቱም ወገን የሞቱትን፣ ሀብታቸው የተቃጠለውንና የተዘረፈውን እያሰበ በእጅጉ ይቆዝማል፡፡
ዋናው አሳዛኝ ነገር ይህ ነው፡፡ ግጭቱ ደም እስኪያመጣ ለምን ይጠበቃል? የሠላሙ ዘንባባ በደም እስኪጨቀይ መንግሥት ለምን ዝም ይላል? ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ ችግሩን የክልሉ መሪዎች ያውቃሉ፡፡ ግን መፍትሔ አልሰጡትም፤ ሕዝቡን አላወያዩም፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ዳኛ ሲያጣ ወደ መገዳደል ገባ፡፡ ችግሩም ጦዘ የሀገርና የሕዝብ ሀብት አፈር ጋጠ፡፡ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ተሰነካከሉ። በሚያሳዝን ሁኔታ የተዋለዱና አብረው የኖሩ ሰዎች ጐራዴ ተማዘዙ፣ ቁርሾ ከመሩ፤ ለትውልድ ቂም አስቀመጡ፡፡
እንግዲህ የዚህ ዓይነት ትዕይንቶችን ስንሰማ ይህ የመጀመሪያችን አይደለም፡፡ ይልቅስ የየሳምንቱ ወሬ ስለሆነ ለመድነው፡፡ አሁን መፈናቀል ብርቅ አይሆንብንም፤ መገዳደል ሱስ እየሆነብን ነው። የሚመከር፣ የሚቃና ሰው ጠፍቶ ሁሉም እሳቱ ላይ ቤንዚን ይረጫል፡፡ በዶክተር ዐቢይ የሚመራው የለውጥ መንግሥትም ጉዞውን የጀመረው እሾሁን ሳይነቅል ስለነበር ዛሬም አንካሳነቱን ቀጥሏል፡፡ በአንድ ዐመት ውስጥ በርካታ አስደናቂና አነቃቂ ተግባራትን ያከናወነው መንግሥት፤ በትይዩው አሳዛኝና አሸማቃቂ አሣፋሪ ድርጊቶችም ያስመዘገበው በከፊል ከዚህ ጋር በተያያዘ ይመስለኛል፡፡
ገና ከጅማሬው በአደባባይ ላይ ቦንብ አፈንድቶ ጠቅላዩን ለመግደል ከመሞከር ጀምሮ፣ ሠራዊት ቤተ መንግሥት ድረስ በመላክ፣ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እስከማድረግ ተደረሰ፡፡ ይህም ሲሆን ዶክተሩ ተፈጥሯዊ ልስላሴያቸውን በቁጣ ቅኝት ቀይረው፣ ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን መውሰድ አልቻሉም። ይልቁንም በፍቅር፣ በንግግርና በሰለጠነ መንገድ ሕዝቡንና ተቃዋሚዎችን ለሀገር በአንድ ልብ እንዲሠሩ መምከርና ሄድ ሲልም መውቀስ ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ ለሃያ ሰባት ዓመታት ሥር ሰድዶ የቆየው ሕወሓት መራሹ መንግሥት ቅሪቶች፣ እግር በእግር እየተከተሉ የለውጡን እሳት ለማጥፋት፣ ውሃ ማፍሰስና ፀብ በተፈጠረባቸው ቦታዎች፣ እሳቱ ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ ቀጠሉ። እናም ብዙ ግጭት ስደትና መፈናቀል ዓለምን በሚያስደንቅ ሁኔታ ተከሰተ፡፡ ይህም በራሱ የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት ቅርጥፍ አድርጐ በላ፡፡ ሰውየው በአንድ በኩል ችግሩን ለማረጋጋት ላይ ታች ሲሉ፣ በሌላ በኩል የተረከቡትን ባዶ ካዝና ሳንቲም ለማጉረስ በሀገራቱ ተንከራተቱ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ ከየአቅጣጫው የሚሰነዘሩትን ሽሙጦችና ዘለፋዎች ላለመስማት ጆሮ ዳባ ብለው ነው፡፡
በአንድ ወገን ለውጡ በእኛ መስዋዕትነት የተገኘ ነው ብለው የሚያምኑና የጫጉላ ቤት ይመስል “እስቲ እዩት የደሙን ሸማ” መዝሙር የሚዘምሩ፣ መጪውን ዘመን ሳይሆን ደጅ ላይ ያለውን ጥሪት ለመቀራመት የጐመዡ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ሲጮሁባቸው በሌላ በኩል ደግሞ ሃያ ሰባቱን ዐመታት በስደት፣ በግድያ፣ በዘር ማምከን ግፍ ተሠርቶብናል፣ ስለዚህ “ኢትዮጵያዊነት የሚለው መዝሙር ለእኛ ከሙሾ የተለየ ጣዕም አይሰጠንም” ያሉ ሰዎች በቡድን ተደራጅተው፣ ሀገሪቷን ሲንጡት እነሆ እስከ ዛሬ ዘልቀናል፡፡
ከዚህ ባለፈ ደግሞ “የክልል ጥያቄ አለን” የሚሉና አንዳንዴም በሰላማዊ ሠልፍ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሚያሥፈራ ጩኸትና መፈክር አካባቢያቸውን ሲያስበረግጉ፣ በሌላ በኩል፣ “የማንን ሀብት ማን ይዞ ይገነጠላል?” በሚል ውዝግብ የቦነነው አቧራ ዛሬም የሀገሪቱን የፖለቲካ ጉዞ አፍኖ ህዝቡን እያስነጠሰው ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎችን ሁሉ ያነጋገረና መግለጫ እስከመስጠት ያደረሰ ነው። በዚህ ሁሉ ውስጥ የለውጡ ፊታውራሪዎች የነበሩት ለማ መገርሣና ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን የተረዳላቸው የለም፡፡
በአንድ በኩል ለዐመታት ሲታገሉለት የነበረውና ለሃላፊነትም ያበቃቸው ሕዝብ ጥያቄ በጦዘ ዜማ ሲዘመርና የቁጣ መብረቅ ሲተፋ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በታሪክ አጋጣሚ የተቀበሉት ሀገራዊት ሃላፊነትና የህዝብ ጥያቄ እረፍት እየነሳቸው በእጅጉ መራራ በሆነ ምጥ ውስጥ ሊያልፉ ግድ ሆነ፡፡ እኛ ሁላችን ግን በየራሳችን ወገን እንዲቆሙልን ስንጎትታቸው መሀል ለመሆን፣ ሚዛን ለመጠበቅ ያዩት መከራ ቀላል የሚባል፣ ወይም ከምጥ የሚተናነስ አልነበረም።
አቶ ለማም ይሁኑ ዶ/ር ዐቢይ ቀጣዩና የመጨረሻ ግባቸው፣ ኢትዮጵያን ወደ ጥንቱ ክብሯ መመለስ መሆኑን ደጋግመው በአደባባይ በመናገራቸው፣ የሀገሩ ታላቅነት ጉጉት ያለው ሕዝብ በሙሉ ልብ እንደተከተላቸው እናስታውሳለን፡፡ ይሁንና በየጊዜው በሚፈጠሩ አጣብቂኞች ውስጥ በተነሱ ግጭቶች ህዝቡ እምነቱን እያጣና “እየተካድን ነው” ወደሚል መላምት ሄደ፡፡ መላምቱን የሚቀበሉት ሰዎች መነሻ የለገጣፎ ቤቶች መፍረስ፣ የሰዎች መፈናቀል፣ ስለጉዳዩ መግለጫ የሚሰጡት ባለስልጣናት የንግግር ድምፀትና የቃላት ምርጫ ጉዳይ ነበር። ከዚያም በኋላ በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባና በሌላ መሰል ጉዳዮች የሰጠው መግለጫ፣ ሕዝቡ በመሪዎቹ ላይ የነበረውን አመኔታ ነጠቀው፡፡
የዚህ መግለጫና ጊዜውን ያልጠበቀው ህገ ወጥ ቤቶችን የማፍረስ ስራ፣ “የረቀቀና በስልት የተሞላ የሌሎች ፓርቲዎች እጅ አለበት” የሚሉ ወገኖች ምናልባት፣ ለረጅም ዓመታት ለሥልጣን ሲባትት የነበረው ኦነግ፣ በተፈጠረለት የግርግር አጋጣሚ ኦዴፓ ውስጥ ገብቶ የዚህ ዓይነት የጥፋት ሥራዎችን ያስፈጽም ይሆናል ወደሚል ጥርጣሬ አመሩ፡፡ ሌሎች ደግሞ የነአቶ ለማ መገርሳ የአሁን አካሄድ አውሎ ንፋስና ወጀቡን በተለያዩ ዘዴዎች አሳልፈው፣ የሀገሪቱን ዋነኛ ሥራ ሊሠሩ ይሆናል፤ በማለት የራሳቸውን ግምት እየሰጡ አለፉ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ አንዴ የተፈጠረውንና የጀርመንና የሩሲያን ግጭትና እርቅ እንዳስታውስ አደረገኝ። ዘመኑ የሌኒንና የቦልሺክ ዘመን ነበር። የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት (ሩሲያ) በጦርነት በመዳከሟ በርካታ መሬቶቿ በጀርመናውያን ተይዘው ነበር። በተለይ ደግሞ የበርካታ ማዕድናት ምንጭ የነበረችው ዩክሬን በጠላት ተይዛ ስለነበር ሁኔታው ከባድ ነበር፡፡ በሌኒን የሚመራው ፓርቲ ሁለት ነገር መምረጥ ተገደደ፡፡ ዩክሬንን ሰጥቶ ከጀርመን ጋር መደራደርና መታረቅ! አለዚያም ጦርነቱን መቀጠል፡፡ ይሁንና ሁለተኛው ምርጫ የሚያስኬድ አልነበረም። ምክንያቱም ሠራዊቱ ጦርነት ሰልችቶታል፡፡ ብዙ ነገሮች ተዳክመዋል፡፡
ስለዚህ ሌኒን ባለው ሁኔታ መታረቅና ጦርነቱ መቆም አለበት ሲል ጓዶቹ አልዋጥላቸው አለ። ሌኒን ግን በመከራ አሳመናቸው፡፡ ያ ብልሃት የተሞላ ውሳኔ ሀገሪቷን ውርደትም ከጥፋትም ያዳነ ነበር። ዩክሬንና ሌሎቹ መሬቶች ያለ ጦርነት በእጃቸው የገባው ጀርመን በጦርነት ስትዋከብ ስለበር ጥቅሙ ብዙ ነበር ዛሬም የአቶ ለማ መግለጫዎች ከጀርባቸው ምን እንደበርና እንዴት ከቀጣዩ ጥፋት እንዳዳኑን የምናውቀው ምናልባት ዘግይቶ ይሆናል። በተለይ እኛንና የሀገሪቱን ሁለመና ሊውጡ በተነሱ ጽንፈኞች መከበባቸውን በማሰብ ትንሽ የማርያም መንገድ ልንተውላቸው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ቸኩለን “ካዱን ሸነገሉን” ማለት ከጥርጣሬ ያለፈና፣ ከግጭት በስተቀር የሚያመጣው ፋይዳ ስለሌለ፣ ነገሮችን ሰከን ብሎ ማሰብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡
ለምሳሌ በኮየ ፈጬ ኮንዶሚኒየም የተነሳ ጃዋርና ሠልፈኞቹ “ኮንዶሚኒየም ወይም ሞት” ባሉበት ጊዜ በኦሮሚያ ክልል የተጀመሩ ሠልፎች ቢቀጥሉ ኖሮ፣ አክራሪ ብሔርተኞች ዕድሉን ተጠቅመው፣ ኦሮሚያንና መላ ሀገሪቱን ቢያመሳቅሉስ ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ የለማ መገርሳ መግለጫ ከሌኒን የጀርመን እርቅ ጋር አይመሳሰልም።
ይሁንና እኛ መቶ ሚሊየን ዕብዶች ሆነን፣ ለየጐጣችን በቆምንበትና መደማመጥ ባቆምንበት ሁኔታ እነዚህ ሰዎች ለምንጮኸው ስፍራውን ቢተውልን፣ ቀጣዩ ጉዳይ ምን ሊሆን እንደሚችል አስበናል? አሁን ከብሔር ወጥተን፣ አማራውን ኦሮሞውን ሳይቀር በሠፈር ለመበታተን፣ የሚሰሩ የማህበራዊ ሚዲያ ክፍተቶች እንዳሉስ መገንዘብ የሚገባ አይመስላችሁም፡፡ ከዚህ ባለፈ የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር፣ ዋቄ ፈታን፣ ከኦርቶዶክስና ፕሮቴስታንት ጋር ለማጋጨት የተጀመረው ዘመቻስ ግብ የት የሚያደርሰን ይመስላችኋል? ይህ ጊዜ ለሀገራችን በጣም ከባድ የፈተናና የምጥ ጊዜ ነው፡፡ ይሁንና ጽንሱ እንዳይነግፍ በጋራ ከሠራን ጤነኛ ልጅ መውለድ አይቀሬ ነው፡፡
ይህ የአንድ ዓመት የለውጡ ጉዞ ሂደትና አሁን ያለንበት ሁኔታ ነው፡፡ ትኩስ የሆነው የአዲስ አበባ/ፊንፊኔ ጉዳይ ግን እኛን ብቻ ሳይሆን የዶክተር ዐቢይን መንግሥትም ጥያቄ ውስጥ የሚከትት ነው፡፡
አዲስ አበባ ላይ በቅርቡ በተነሱት አለመግባባቶች እንደምናየው ከሆነ፣ የአንድ ብሔር መድልዎ አለ እየተባለ ነው፡፡ ለምሳሌ ሠራተኛ ቅጥር ላይና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ህዝቡ ለተሰማው ቅሬታ መንግሥት ምላሽ መስጠትና ነገሩ አሁንም እየተደረገ ከሆነ ማስቆም ሲገባው “ለምን ትጠይቃለህ?” ብሎ መቆጣት ትክክለኛ ነው ብዬ አላስብም፡፡ “ዶክተር ዐቢይ ተሳስተዋል” ብዬ የምልበት ቦታም ይህ ነው። ጋዜጠኛ እስክንድርን ከገሰፁ፣ ለምን አዲስ አበባ ላይ የሚሠራውን የመድልዎ ሥራስ በይፋ አይኮንኑም? ይህ አካሄድ ፍትህን ወደማዛባት የሚወስድ ይመስለኛል፡፡ እውነት ለመናገር ጋዜጠኛ እስክንድር አሁን በመታሠሩ የሚያገኘው ስምና ዝና የለም፡፡ እስክንድር በብዙ ነገሩ ኑሮ የሞላለት፣ ከዚያም ባለፈ እጅግ ጭካኔ የተሞላበት መከራ በነበረበት እሥር ቤት ዘጠኝ ዓመታትን ያሳለፈና በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኘ ነው፡፡
እንደኔ እንደኔ ዶክተር ዐቢይ አደባባይ ላይ ይህን ከሚናገሩ ይልቅ እርሱንና መሠሎቹን ሰብስበው ቢያናግሩ ለሚያስቧት ኢትዮጵያ ጥሩና ቀላል መንገድ ይሆንላቸው ነበር፡፡ አለበለዚያ ንትርኩ እየቀጠለ ወደማንወጣው አደጋ ውስጥ የምንገባ ይመስለኛል፡፡
ከሁላችን ይልቅ ሃላፊነቱን የተሸከመው መንግሥት፣ ነገሮችን ከማባባስና በችግር ላይ ችግር ከመጨመር ይልቅ ችግር ቅነሳ መልመድ አለበት። ለምሳሌ የአዲስ አበባ ችግሮች ተጧጡፈው ሳለ በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶችን ማፍረስ ምን የሚሉት ጠማማነት ነው? እውን ኢንጂነር ታከለ ይህን ነገር ሳያውቁት ቀርተው ነው? ካወቁትስ የሚያመጣው መዘዝ፣ በምሬት ላይ ምሬት አያመጣም?
እውነት ለመናገር አሁን በሚታየው ሁኔታ ከቀጠልን ሀገራችን ትፈርሳለች፤ ስትፈርስ ደግሞ በሚዘገንን ሁኔታ እኛም እንፈርሳለን፡፡ በታሪካችን ውስጥ ታይቶ ወደማይታወቅ እልቂት እንገባለን፡፡ ካልተጠነቀቅንና ከእልህና ጥላቻ ካልወጣን፣ ከዚህ የሚታደገን ደግሞ ምንም የለም፡፡
በተለይ አሁን መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው በእግዚአብሔር አደባባይ የሚቆሙ ሰዎች ዋና ዋና ዘረኞችና የጥላቻ ወንጌል ሰባኪዎች በሆኑበት ጊዜ ፀብን ማርገብ ቀላል አይሆንም፡፡ ዛሬ በጥላቻ የተሞሉ ጽንፈኛ ወጣቶችን የፈጠርን ሁሉ የምንፈርደው በነርሱ ላይ ሳይሆን በራሳችን ላይ ነው፡፡
ቃላት እየሰነጠቅን ወደ ዝቅጠት ባንወግድ ዝቅ ባንል፣ ለኛም ለሀገራችንም ክብር ነበር። ለማንኛውም በአንድ ዓመቱ የለውጥ ጉዞ በትዕግስት የመራችሁን እኛም ፍቅራችንን ገልጠን የተቀበልናችሁ መሪዎቻችን ማስተዋል ይብዛላችሁ! ከጥቂት ዕብዶች ጋር እንዳታብዱ! ተጠንቀቁ፡፡ አንበሶቻችንን የከበባችሁ ጅቦች በዚሁ አትቀጥሉም፡፡    

Read 1428 times