Saturday, 30 March 2019 13:57

ሥነ - ጥበብ የማን ናት?

Written by  በሚፍታ ዘለቀ (የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)
Rate this item
(1 Vote)

 “መገላልጦች” ስለ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ-ሥላሴ ሐውልት በአፍሪቃ ሕብረት
                             
                (ክፍል ሁለት)
የግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሃውልት በአፍሪቃ ሕብረት ቅጽር ውስጥ መቆሙን ተከትሎ ከሁለት ሳምንት በፊት በዚሁ ጋዜጣ የጀመርኩትን ጽሁፍ የምቀጥለው ሃውልቱን በማቆም ታሪክ ብንመለከታቸው ጠቃሚ የሚመስሉኝን ነጥቦች በመዘርዘር ነው፡፡ እንዲህ አይነት ከፍ ያለ ሥነ-ጥበባዊ፣ ሃገራዊና አህጉራዊ ፋይዳ ያለውን ሃውልት የማቆም ሃላፊነትና ተልዕኮ የወሰደ ፕሮጀክት ለማንቀሳቀስ ግቡን እንዲመታ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው ለመጓዝ የሚያስችለው የጽንሰ-ሃሳብ ማስታወሻና የውል ስምምነት እንዲኖረው ግድ ይላል፡፡ የፕሮጀክቱን መነሻ፣ አካሄድና አፈጻጸም፤ የሃውልቱን ባህሪ ለማግኘትና ለመወሰን የሚያስችሉ ጥናቶችና ዳራቸው፤ ሃውልቱ የሚቀረጽባቸው ፍልስፍናዊና ቴክኒካል መሰረቶች ከነ አመክንዮአቸው፤ የባለሞያዎች ስብስብና የስራ ድርሻቸው፤ የሚጠበቀው ውጤት፤ የፕሮጀክቱ ጊዜ ገደብና በጀት እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች እነዚህ ሁለት ሰነዶች ከሞላ ጎደል ማካተት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሃገራችን አውድ በተለይ ሰፊውን ሕዝብ ሊነኩና የባለቤትነት ጥያቄ የሚያስነሱ የሥነ-ጥበብ ፕሮጀክቶች የሚሹት መደላድል ከዚህም የጠለቀና የረቀቀ መሆን እንደሚገባ ከሚያስገነዝቡን ታሪካዊ ክስተቶች መሃከል በአፍሪቃ ሕብረት የቆመው የግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሃውልት ነው፡፡ እንዲህ አይነት መሰረቶችን ተንተርሶ ለመነጋገር የሚያስችል እድል ቢኖር በሃውልቱ ዙሪያ የተፈጠሩ ትርምሶች ሊቀሩ ባይችሉም ስርዓት ባለው መንገድ ለመነጋገርና ለመማማር ይውሉ ነበር፡፡
ሃውልቱን የመቀበልም ሆነ ያለመቀበል ውሳኔ እንደየተመልካቹ የሚወሰን መሆኑ ግልጽ ቢሆንም ከደቂቅ እስከ ልሂቅ ሃውልቱ ያሟላቸው አልያም ያጎደላቸው ሥነ-ጥበባዊና ሌሎች እሴቶች ስለመኖራቸው ሁሉም እንደአቅሙና እንደአተያዩ ፍርድ የመስጠት፤ የሚፈጠሩበትንና ጥያቄዎች የመጠየቅና መልስ ለማፈላለግ መሞከር፤ ተጠያቂ የሚሆነውም መልስ ለማቅረብ ዝግጁ መሆን፤ ይመለከተኛል የሚለውም ‘ከጋን ውስጥ መብራትነት’ በመውጣትና የብርሃን ጉዞ እንድንጓዝ በሚያስችል የውይይት፣ የክርክርና የመማማር መድረክ ላይ ማስገኘትና የሃገራችን ሥነ-ጥበብ ባለቤት እንዳላት ለማስገንዘብ የሚያስችል እድል መፍጠር የዚህ ሃውልት መገለጥ የከሰተው አንድ ጥሩ እድል ነው፡፡
ጥያቄ ከተነሳባቸው ነጥቦች መሃከል ሃውልቱ አጼውን መምሰል አለመምሰሉ ዋንኛው ነው። ምላሻችን አዎንታዊ አልያም አሉታዊ ቢሆን ልናነሳ የሚገባን ቀጣይ ጥያቄ ለምን እንደሆነ ለመረዳት የሚያስችል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የዚህ ምላሽ ደግሞ የሃውልቱ ዋና ቀራጺ፣ የቡድን አባላቱ፣ ፕሮጀክቱን በሃላፊነት የመራው ተቋም እንዲሁም አሰሪው አካል የተስማሙበት ሃውልቱ የሚቀረጽባቸው ፍልስፍናዊና ቴክኒካል መሰረቶች ጋር ይወስደናል፡፡ ለምሳሌ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በሃውልቱ የተወከሉበት ገጽታ፣ እድሜ፣ አለባበስ፣ የአገዛዘፋቸው ልክ፤ ሃውልቱ የሰው ምስል ቢሆንም የሚሰራበት የሥነ-ውበት ዘዬ (aesthetical style) እና ዘውግ ለምሳሌ እውነታዊ (Realistic)፣ እውነታዊነት(Realism)፣ ዘመናዊ(Modern) ወይም ቅይጥ .... ወዘተ እንዲሆን የሚወሰነውና ስምምነት ላይ የሚደረሰው ሃውልቱ የሚቀረጽበትን ፍልስፍናዊና ቴክኒካል መሰረቶች በመንተራስ ነው፡፡ ይህን በማምጣት ሂደት ዝርዝር ውሳኔዎችን የመወሰን ነጻነት የሚሰጠው በአብዛኛው ለሃውልቱ ዋና ቀራጺ ሲሆን ይህን ነጻነት ተቀዳጅቶ በመስራትና ሰርቶ ባመጣው ውጤት ላይ መወያየትና እኛ ምናብ ውስጥ ባለው የአጼው ምስል (ስንት አይነት የአጼው ምስል ሊኖር እንደሚችል አስቡት) ላይ መወያየት ሁለት የተለያዩ አቅጣጫዎች ናቸው፡፡
የቀደመውን ብንመለከት፤ የሃውልቱ ዋና ቀራጺ በቀለ መኮንን(ተባባሪ ፕሮፌሰር) እና ቡድኑ ይህን ሙያዊ ነጻነት ማግኘት አለማግኘቱን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እንደው መላ ብንመታ፤ በቀለ መኮንን ማንኛውም የሙያ አጋሩ ሊክደው ከማይችለው የቀራጺነት ችሎታው ባሻገር ያካበተው ልምድ፣ ተሰሚነትና ዝና እንዲሁም ፕሮጀክቱን ያስጠለለው የሃገራችን ሥነ-ጥበብ መፍለቂያ ከሆነው የአ.አ.ዩ. አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ከፍታ አንጻር የሃውልቱ ዋና ቀራጺ በቀለ መኮንን(ተባባሪ ፕሮፌሰር) እና ቡድኑ ይህን ሙያዊ ነጻነት አሳልፎ ይሰጣል ተብሎ አይገመትም፡፡ የአሰሪዎቹ የአፍሪቃ ሕብረትም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲሁም የንጉሳዊ ቤተሰቦች ተወካዮች ሥነ-ጥበብን የመረዳትና የሚሰራውን ሃውልት የመተቸት አልያም የመቀበል ውሳኔ ይህን ሙያዊ ነጻነት ከመንፈግና ከመቸር ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነው የሚሆነው፡፡ ይህም ማለት የሃውልቱን የአሰራር ሂደት እየመዘኑ አልያም በሌሎች ባለሙያዎች እያስመዘኑ ይበል፣ ይቀጥል፣ ሸጋ ነው በማለት፤ ሳይሆንም የለም፣ ይህ ይስተካከል፣ ይህ እንዲህ መሆን አይገባውም በማለት ሃውልቱ በሚቀረጽበት ሂደት ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተው ሊሆን ይችላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የዋና ቀራጺውን፣ የቡድኑ እንዲሁም የተቋሙን ሙያዊ ነጻነት በማክበርና በመቀበል የበኩላቸውን አስተዋጾ አድርገው የመጨረሻውን ውጤት በጸጋ ተቀብለው ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለቱም ቢሆኑ ገንቢና ተገቢ ናቸው፡፡ የትኛው እንደሆነ አልታወቀም እንጂ፡፡ በተመሳሳይም የዋና ቀራጺው፣ የቡድኑ እንዲሁም የተቋሙ ሙያዊ ነጻነት ተጠብቆ አልያም ከአሰሪው ጋር በመወያየት የተከወነ ሊሆንም ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ መሆን አለመሆናቸው ነገሮችን በጠራ መንገድ ለመወያየት፣ ጥበበኛውን ለመረዳት፣ የሥነ-ጥበብን ባለቤት ለማወቅ፣ ሃውልቱ የተሰራበትን አካሄድና በሂደቱ የሚገለጡ ጉዳዮችን ለመረዳት መንገድ ከመጥረግ አንጻር ሊነሱ የሚችሉ ነጥቦችን ለማንሳት እንዲረዱን በማስቻላቸው ነው ትንሽ ልሄድባቸው የፈለግኩት፡፡ .... እና..... ሃውልቱ አጼውን ይመስላል?
 አጼው በሃውልቱ እንዴት ሊመሰሉ ይገባል? የሚለው ጥያቄ ሃውልቱ አጼውን ይመስላል? ከሚለው የሚቀድም ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሃውልቱ የሚቀረጸው አጼውን መሰረት በማድረግ በመሆኑ ነው፡፡ ሃውልቱ አጼውን ይመስላል ወይ? በሚለው ጥያቄ ብንጀምር በቀዳሚነት መፈተሽ የሚገባን እንዲመስል የተፈለገውን ወይም የተመረጠውን ምስል(ፎቶ) በማጣራትና በማግኘት ከሃውልቱ ጋር ማመሳሰል ይሆናል፡፡ በመቀጠልም ሃውልቱ እንዲሰራ የተመረጠውና ስምምነት ላይ የተደረሰበት የሥነ-ውበት ዘዬ (aesthetical style) እና ዘውግ ለምሳሌ እውነታዊ (Realistic) ከሆነ የዚህ ምርጫ መገለጫና የምርጫው ውሳኔ ያረፈበትን ምስል (ፎቶ) ከቆመውን ሃውልት ጋር በማመሳከር መፍረድ ያስችላል፡፡ ከዚህ አኳያ እያንዳንዷ ምስሉ(ፎቶው) ያለች ጥቃቅን ነገር ለምሳሌ አይን አፍንጫ ጢምና ደምስር ሳይቀር እያመሳከሩ የሃውልቱ አጼውን የመምሰል ያለመምሰል ጉዳይ በተጨባጭ መነጋገር ይቻላል። ሆኖም እውነታዊ (Realistic) የሆነ ምስል (ፎቶ) በውጤትነት እንዲመጣ የሚጠበቅ አውድ በሌለበት የመምሰል ያለመምሰል ጥያቄ ውድቅ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው ይህን ወይም ሌላኛውን ምስል(ፎቶ) ይመስላል አይመስልም እንጂ አጼውን ይመስላል አይመስልም አይሆንም፡፡ በእርግጥ በአፍሪቃ ሕብረት ቅጽር ውስጥ የቆመው የግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሃውልት ሲሰራ የተመረጠው ምስል(ፎቶ) ግርማዊነታቸው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ጋር በመሰረቱበት ታሪካዊ ቀን ከተነሱት ፎቶግራፍ የተወሰደ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ምስል(ፎቶ) የተመረጠ መሆኑ ብቻ የቆመውን ሃውልት ከዚህ ምስል(ፎቶ) ጋር በማመሳከር ለትችትና ለወቀሳ መነሳት ተገቢ ይሆናል? እንደ እኔ እምነት ሃውልቱ እውነታን (Realism’ን) መሰረት በማድረግ የሃውልቱ ዋና ቀራጺ እና ቡድኑ የወሰኗቸው ውሳኔዎች እንዳሉ የመመልከት ትዕግስት ቢኖረን ወደ ፍርድ ከመሄድ በፊት ሌሎች ጉዳዮችን እንድንመለከት እድል የምናገኝ ይመስለኛል፡፡
የሃውልቱ ዋና ቀራጺ በቀለ መኮንን(ተባባሪ ፕሮፌሰር) እና ቡድኑ ሆን ብለው (deliberately) የወሰኗቸው ከሚመስሉኝ ነጥቦች አንደኛው ከተመረጠው የፎቶግራፍ ምስል በተለየ ሃውልቱ ላይ የሚታየው የአጼው የእይታ አቅጣጫና የራስ ቅል ዝንባሌ ነው፡፡ በተመረጠው ምስል (ፎቶ) ላይ ግርማዊነታቸው ቀና ብለው ሩቅ የሚመለከቱ ሲሆን በሃውልቱ ግን ወደ ማቀርቀር ያዘነበለ የቅርብ-ርቀት ላይ የተተከለ ዕይታ ነው ያላቸው። ይህ የአጼውን የራስ ቅል ዝንባሌ የመቀየር ውሳኔ በአንድ በኩል የዋና ቀራጺውን የፈጠራ ነጻነት፤ በሌላ በኩል አጼው በአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ የተጫወቱትን የሸምጋይነት፣ ግራ ቀኙን የማዳመጥ፣ ስክነትና ጽኑነታቸውን ለማሳየት የታሰበ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ሆነም አልሆነም ግን ይህ የዋና ቀራጺውና የቡድኑ የውጥን (deliberate) ውሳኔ ለመሆኑ ከተመረጠው የፎቶግራፍ ምስል የተለየ መሆኑ ብቻ በቂ ነው። ይህ ቁንጽል ዕይታ ሃውልቱን ካየሁባቸው ፎቶግራፎች መሃከል በብዙዎቹ ያስተዋልኩትና የዋና ቀራጺውና የቡድኑ የውጥን ውሳኔ ላይ ሚዛናዊ አስተያየት ለመስጠት የሚያስችለኝ በመሆኑ አነሳሁት እንጂ በሃውልቱ ላይ የሚነሱ ሌሎች ነጥቦችን በሙሉ ሚዛን ከማስደፋት አንጻር አለመሆኑን ልብ ይሏል። ከፎቶግራፎች በዘለለም ሃውልቱን በዓይን የመመልከት እድል ቢገጥም ሃውልቱን የመቅረጽ ሂደት ጥቃቅን ዝርዝሮችን ከማስመሰል ይልቅ ይህን መሰል የአጼውን ባህሪያት ለማምጣት የተለፉ ልፋቶችንና ሙከራዎችን መዳሰስ እንደሚቻል አምናለሁ፡፡
እንደ አብዛኛው ሕዝበ-ተመልካች ሃውልቱን የተመለከትኩባቸው ፎቶግራፎች የፈጠሯቸው የሚመስሉም ሆኑ ሃውልቱ ራሱ ያስተጋባቸው ሊሆኑ የሚችሉ የሃውልቱ ገጾችን በማንሳት ወደ መደምደሚያዬ እሄዳለሁ፡፡ በዚህም ሃውልቱ የአጼውን መልክና ምስል በዝርዝር ከማስቀመጥና ከማስመሰል ይልቅ ለአጠቃላይ ገጽታና ባሕሪያቸው የተጨነቀ መሆኑ ከቆመው ሃውልት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሆኖም የአጼው ልዩ የእጅ ምልክት በወትሮ ከሚታወቀው የሰውነታቸው እኩሌታ (symmetrical) አቀማመጥ በሚጣረስ መልኩ ወደ ግራ ፈቀቅ ብሎ መታየቱ፤ አጼው ካላቸው ቁመት በተለየ ረዥም የሚመስለው ይህ የቆመው ሃውልት፣ የሁለቱም ክንዶቻቸው ላይ ያለው የኮታቸው እጥፋቶች ሃውልቱ ላይ የተመጣጥኖ (propotion) ጥያቄ ማስነሳቱ፤ እንዲሁም የአንገታቸው እርዝማኔ ከሸሚዛቸውና ከኮታቸው ኮሌታ ጋር ሲታይ ገጽታቸው ላይ የፈጠረው ቅሬታ ሃውልቱ የአጼውን አጠቃላይ ገጽታና ባሕርይ ከመወከል አንጻርም ቢሆን በሰፊው ልንነጋገርባቸው ከምንችልባቸው ነጥቦች መሃከል ይገኙበታል፡፡ በነዚህና በሌሎች ነጥቦች ዙሪያ ሙያዊ በሆነ መልኩ በመነጋገር በተለይ በሃገራችን አውድ የሥነ-ጥበብ ባለቤት ሙያተኛው እንደሆነ በሚያስገነዝብ መንገድ እንዲሁም ሰፊውን ማህበረሰብ ግንዛቤ በሚያስጨብጥ መልኩ ውይይት መቀጠል ያሻል፡፡ በዚህም የሥነ-ጥበብ ሃቲት በመፍጠር የሃገራችን ሥነ-ጥበብ ወንዝ እንዲሻገር ማድረግ ይቻላል፡፡
ይህን በማድረግ ሂደትም በተለይ ይህን የሃውልቱን መቆም የታሪክ አጋጣሚ በመጠቀም ሥነ-ጥበባዊ መረዳቶች እንዲዳብሩ በማስቻል ሃውልቱ በሚሰራበት ወቅት የነበሩ ሂደቶችን ሊያሳዩ የሚችሉ የፎቶግራፍም ይሁን የቪድዮ ሰነዶች፣ ሃውልቱ አሁን ያለበትን ቅርጽ ሊይዝ የቻለባቸው ሂደቶችን እንዲሁም በአፍሪቃ ሕብረት ቅጽር የተተከለው የመጨረሻው ውጤት በተቻለ ዝርዝር በባለሙያ ፎቶግራፈሮችና የፊልም ባለሙያዎች በማዘጋጀት ሰፊ የውይይት መድረክ ማሰናዳት የሃውልቱ ዋና ቀራጺ የበቀለ መኮንን(ተባባሪ ፕሮፌሰር) እና ቡድኑ እንዲሁም የአ.አ.ዩ. አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ሙያዊና ሞራላዊ ቀሪ የቤት ስራ ይመስለኛል፡፡ ይህም ለሥነ-ጥበባችንና ሌሎች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች በሃገራችን እንዲበራከቱ በማስቻል በኩል ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚፈጥር ሙሉ እምነቴ ነው፡፡
የብቻዬ ጥግ፡- የሃውልቱ ዋና ቀራጺ በቀለ መኮንን በአ.አ.ዩ. አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ሃውልት እንደ ምርምር ውጤት ተቆጥሮ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያስገኝለት ይሆን? ይህ እውን ከሆነ በሃገራችን የሥነ-ጥበብና በአ.አ.ዩ. ታሪክ የመጀመሪያው ሠዓሊ እንደሚሆን ያውቃሉ? ይህ መሆን ከቻለ ለሥነ-ጥበባችን ምን አይነት እድል ያመጣ ይሆን? በእርግጥ የሃገራችን ሥነ-ጥበብ ችግር የባለ ሙሉ ፕሮፌሰር ሠዓሊ ያለመኖሩ ባይሆንም የብቻዬ ጥግ ላይ ስሆን ከማስባቸው ሃሳቦች ውስጥ በቀለ መኮንን(ተባባሪ ፕሮፌሰር) በኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ፣ በት/ቤቱና በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ውስጥ ያለው ምታሬ (breadth) ነውና በሌላ ጽሁፍ አሊያም ቃለ-ምልልስ እንደምመጣ እየተመኘሁ ቸር እንሰንብት እላለሁ፡፡  

Read 959 times