Saturday, 30 March 2019 13:44

“ኦሮሚያ የአዲስ አበባ ጐረቤት እንጂ ባለቤት አይደለችም”

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(5 votes)

 ቃለ ምልልስ




                                 “ኦሮሚያ የአዲስ አበባ ጐረቤት እንጂ ባለቤት አይደለችም”


             ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ በእጅጉ እያወዛገበ ይገኛል፡፡ የኦሮሞ አክራሪ ብሔርተኛ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ብቻ ሳይሆኑ የኦሮሚያ ክልልን የሚመራው ኦዴፓ በድፍረት ሲያቀነቅነው ነበር፡፡ የአማራ ክልልን የሚመራው አዴፓም አልቀረለትም፡፡ ከአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ውዝግብ ጋር ተያይዞ በቅርቡ በባልደራስ የመዲናዋን ነዋሪዎች ስብሰባ የጠራው ጋዜጠኛና አክቲቪስት እስክንድር ነጋ፤ “የአዲስ አበባ ባለአደራ ም/ቤት”
ማቋቋሙ ይታወቃል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ የባለአደራ ም/ቤት የሚባለው “አገር ስለሚያፈርስ ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ ነው” ብለዋል፡፡ “የባለ አደራ ም/ቤት” ሰብሳቢው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጠን አጭር ቃለ ምልልስ አድርገንለታል፡፡ እነሆ፡-


             ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፣ ሰሞኑን  በአዲስ አበባ ጉዳ ይ ላይ ሲናገሩ “ባለአደራ ማቋቋም ጨዋታ ነው” ብለዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አለህ?
ጠ/ሚኒስትሩ ብዙ ነገሮች ተናግረዋል፤ አንዱ ባለአደራ ማቋቋምን በተመለከተ ነው። ባለአደራ በየቦታው ተቋቁሞ የኢትዮጵያ አንድነትን አደጋ ውስጥ ይጥላል ያሉትን ነገር እኛም እንቀበለዋለን፤ ምክንያቱም የእኛም እንቅስቃሴ ገዢ ሃሳብ ስለሆነ። እኛ በሁለት ነገሮች አንደራደርም እንላለን፤ አንዱ የኢትዮጵያ አንድነት ነው፡፡ ይሄም ማለት የኢትዮጵያ አንድነትን የሚያናጉ ማናቸውንም አይነት እንቅስቃሴዎች አናደርግም፡፡ ጥያቄያችን ውስጥ የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ የሚል ሃሳብ ስላለ የጠ/ሚኒስትሩን ንግግር እንቀበለዋለን፡፡
ባለአደራ እየተባለ በየቦታው ሲቋቋም፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ስጋት መሆን የለበትም ማለታቸውን እንቀበላለን ስንል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ የተመረጠ መንግስት የለም ተብሎ፣ በየቦታው ባለአደራ የሚቋቋም ከሆነ፣ በየቦታው ትናንሽ መንግስት ተቋቁሞ የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል ማለት ነው፡፡ አሁን የአዲስ አበባ ባለ አደራ ተቋቁሟል፤ ነገ ደግሞ የኦሮሚያ፣ ከነገ ወዲያ የአማራ፣ የትግራይ --- እየተባለ ሁሉም ተነስቶ በየቦታው ባለአደራ የሚያቋቁም ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች በሚል እሳቤ ነው የተናገሩት፡፡ ይሄ ደግሞ እሳቸውን ያሳሰባቸውን ያህል እኛንም ያሳስበናል፡፡ እኛ ገዢ ሃሳባችን ሁለት ናቸው፤ አንዱ የኢትዮጵያ አንድነት የሚል ነው፤ ሁለተኛው ሠላምና  ዲሞክራሲ ማስፈን ነው፡፡ እሳቸው እንዳሉት፣ ባለ አደራ ብለን ያመጣነው ነገር፣ የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ፣ በደንብ ከስር መሠረቱ እንድናስብበት ያደርገናል ለማለት ነው የፈለግሁት፡፡ የምንቀጥለው ባለ አደራነቱ፣ የኢትዮጵያን አንድነት የማይነካ መሆኑን ስናረጋግጥ ብቻ ነው፡፡ አሁን በጉዳዩ ላይ እየተወያየንበት ነው፡፡ ንግግራቸው እራሳችንን እንድንመረምር ያደርገናል፡፡ መርምረን እንደተባለው ከሆነ ደግሞ  ማሻሻያዎችን እናደርጋለን፡፡
ባለ አደራነቱን ለማቋቋም ስትነሱ  መሰል ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አላሰባችሁም?
ስንመሰርተው መርምረን ነው፤ ነገር ግን ጠ/ሚኒስትሩ የአገሪቱ መሪ በመሆናቸው ጥያቄ አንስተውበታል፤ ስለዚህ አንድ ጊዜ መርምረነዋል ብለን አንተወውም፤ በድጋሚ የእሳቸውን ማሳሰቢያ ይዘን እየመረመርን ነው፡፡
“ባለአደራ” ማለት ምን ማለት ነው?
እሱን አሁን መመለስ አልችልም፤ መግለጫ እንሰጣለን፤ በዚያን ወቅት እንመልሰዋለን። ህገ ወጥ መታወቂያ፣ የብሔር ስብጥር --- በቀድሞዎቹም ይደረግ ነበር፡፡ ህገ ወጥ መታወቂያ መታደሉ፣ባልተመረጠ መንግስት ሰፈራ መካሄዱ የኢትዮጵያን ሠላምና አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው የሚሆነው፡፡ አቶ ለማ መገርሳ  መድረክ ላይ ቁጭ ብለው፣ በአደባባይ ስለ ሠፈራ ተናግረዋል፡፡ እንደ ክልል መንግስት ሲናገሩ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የብሔር ስብጥር የኦሮሞ ድርሻ አነስተኛ ነው፤ ስለዚህ የኦሮሞን ህዝብ ከገጠር አውጥተን ወደ ከተማ እናሠፍራለን” ብለዋል፡፡ ይሄንን ለመተግበር ከሱማሌ የተፈናቀሉ የኦሮሚያ ተወላጆችን አዲስ አበባ እያሰፈሩ ነው፡፡ ይሄ የኢትዮጵያ አደጋና ስጋት አለመሆኑን የማረጋገጥና የመከታተል ሃላፊነት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። በዛው ልክ የእኛንም እንቅስቃሴ የመከታተልና የማረጋገጥ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ከራሳቸው ቤተ መንግስትና ፓርላማ  የሚወጡ ፖሊሲዎች፣ የኢትዮጵያን አንድነትና ሠላም የማያውኩ መሆናቸውንም ማረጋገጥ  አለባቸው፡፡ በመንግስትም ሆነ ከመንግስት ውጪ ያሉት ወገኖች ኃላፊነት የመውሰድ ግዴታ አለባቸው፡፡ እኛ ለኢ/ር ታከለ ኡማና ለአቶ ለማ መገርሳ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በኦሮሚያ ያሉት መስተዳደር፣ በህዝብ ያልተመረጡ በመሆናቸው፣ (በተለይ የአዲስ አበባው ጊዜው ያለቀ ነው)፤ ህዝቡ የመረጠው መንግስት እስኪመጣ ፖሊሲው ተግባራዊ ሆኖ ሊቀጥል አይገባም፡፡ እስከዚያው ድረስ የመንግስትን የእለት ተእለት ስራ እየሠራችሁ፣ ህግና ዲሞክራሲን እያስከበራችሁ  ጠብቁ ነው  ያልነው፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ የእኛን ጉድለት ከነገሩን በኋላ የጠየቅናቸው ጥያቄዎች ላይም ምላሽ መስጠት ነበረባቸው፡፡ በእኛ ጉድለት ላይ ብቻ ማተኮራቸው ተገቢ አይደለም፤ ህዝቡን አክብረው የህዝቡን ጥያቄ መመለስ አለባቸው፤ “ትክክል ናችሁ እስከ ሚቀጥለው ምርጫ ጠብቁ” ወይም ደግሞ “ትክክል አይደላችሁም” ማለት ነበረባቸው፡፡ ዋናውን ጉዳይ ትተው በሁለተኛ ጉዳይ ላይ ማተኮራቸው ተገቢ አይደለም፡፡
በምርጫ ተወዳድራችሁ አዲስ አበባን የማስተዳደር አላማ አላችሁ?
ፍላጐት የለንም፤ ጥያቄያችን ፖለቲካዊ ነው፤ ግባችንም ፖለቲካዊ ነው፡፡ ማንም በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አለው የሚል እንዳይመረጥ ማድረግ ነው ግባችን፤ እኛ ግን ምረጡን ብለን አንቀርብም፡፡
ከህዝብ ጥያቄ ቢቀርብላችሁስ?
እኔ በግሌ ይህንን ህዝብ ለማስተዳደር ብቃት የለኝም፤ ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ከምክር ቤቱ ለቀው በምርጫ ሊሳተፉ ይችላል፤ ም/ቤቱን ወክሎ ግን ምርጫ መሳተፍ አይቻልም፡፡
አዲስ አበባ የማናት?
አዲስ አበባ በቀዳሚነት የኢትዮጵያ ነች፤ በሁለተኛ ደረጃ የነዋሪዎቿ ነች፤ እዛ ጋ ያበቃል፤ ካስፈለገ ጐረቤቷ ኦሮሚያ ናት ግን ጐረቤቷ ብቻ ናት እንጂ ባለቤት አይደለችም፡፡ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ዙሪያ  ስላለች ብቻ የኦሮሚያ ናት ማለት አይቻልም፤ የሀረር ጐረቤት ኦሮሚያ ናት፤ሀረር ግን የኦሮሚያ አይደለችም። አዲስ አበባን ከነቀምት ወይም ከመቀሌ ጋር አናመሳስላትም፡፡
ባለፈው እሁድ ልታደርጉት የነበረው ስብሰባ ለምን ቀረ?
በፀጥታ ችግር ነው፤ እኛ የምንጠራው ህዝብ በሠላም ወጥቶ በሠላም እንዲመለስ እንፈልጋለን። አንዳንድ ጥርጣሬዎች ነበሩን፤ በተሳሳተ አመለካከት ሊመጡ ያሰቡ ወንድሞቻችን ነበሩ፤ የእነሱንም ሠላም ለመጠበቅ ከማሰብ ነው ስብሰባውን በመጨረሻ ሰአት የሰረዝነው፤ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ስለሆንን፡፡
ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂው ማነው?
የባለፈው 27 አመታት ከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ተንደባሎ የመጣ ችግር ነው፡፡ ይሄ የሚጠራው በሀይል ሳይሆን በሠላማዊ ድርድር ብቻ ነው። ከዚያ በላይ ደግሞ በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንፈታዋለን። በዚህ መንገድ ነው ዴሞክራሲ መፍጠር የምንችለው።

Read 3985 times Last modified on Saturday, 30 March 2019 14:55