Print this page
Sunday, 31 March 2019 00:00

የአንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ፤ ከየት ወዴት?

Written by 
Rate this item
(4 votes)


               ቃለ ምልልስ


 
                             የአንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ፤ ከየት ወዴት?

               · አዲስ አበባ የብሔርተኞች የሽኩቻ ማዕከል ሆናለች
              · ያልተገደበ ዲሞክራሲን የመሸከም ባህል የለንም

             ባለፈው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አዘጋጅነት በተካሄደው የአንድ አመት የለውጥ ጉዞ ግምገማ ላይ ሃሳባቸውን ከሰነዘሩ በርካታ ምሁራንና የፖለቲካ ተንታኞች መካከል ወጣቱ ፖለቲከኛና አክቲቪስት ዮናታን ተስፋዬ ይገኝበታል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከዮናታን ተስፋዬ ጋር ባለፈው አንድ ዓመት በተካሄደው የለውጥ ጉዞ ዙሪያ፣ በጎውንም ክፋውንም አንስተው ተወያይተዋል፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ለአንድ ዓመት በዘለቀው የለውጥ ጉዞ ሂደት ላይ የተለያዩ ሃሳቦችንና አመለካከቶችን እያንፀባረቀች ነው፡፡ ሃሳብን ማንሸራሸር አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኝ ድልድይ ነው!!

                 ለብዙዎች ተስፋ ፈንጥቆ የነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ ምን ገጠመው?
አንደኛ፤ አሁን ነገሮች ሠከን ሲሉ ሁሉም፣ ዞር ብሎ የሚመለከተው ነገር አለ፡፡ ዞር ብለው ሲመለከቱ፣ ኢህአዴጐች ሪፎርም የሚሉት ብዙዎች ለነፃነት በሚደረገው ትግል፣ አንድ ላይ የቆሙበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይብዛም ይነስም የህዝብ ሁሉ ትግል አንድ ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር በፊት የነበረው አንድነት፣ ከለውጡ በኋላ ሰዎች የቱ ጋ እንደቆሙ እየለየ የመጣ ይመስላል። በተለይ ጠ/ሚኒስትሩ ለ6 ወር ያካሄዱት ፈጣን የሪፎርም ስራ ሁሉንም ያስደሰተ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ስልጣን ላይ ሆነው ተጠቃሚ ከነበሩት በስተቀር፡፡ ስለዚህ በፊት የነበረው በትግል ሂደት የነበረ አንድነት ነው፡፡ አላማና ሃሳብ ቢለያይም፣ አፈናን ለማስወገድ ግን አንድነት ተፈጥሮ ነበር። ጠ/ሚኒስትሩ ከመጡ በኋላ ያለው 6 ወር ደግሞ አፍላ የሪፎርም ሂደት በመሆን ብዙዎችን ሲያስደስት ነበር። በሃሳብም በአላማም በፊት የማይስማሙ ሰዎች አንድ ላይ ቆመው እንድናይ አስችሎናል፡፡ ከ6 ወር በኋላ ግን የለውጡ አመራር አንዳንድ ለየት ያሉ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል ወይም ደግሞ ቸልተኛ እየሆነ መምጣቱን ያሳየበት አጋጣሚ አለ፡፡
ለምሣሌ የግንቦት 7 አመራሮች ወደ ሀገር ውስጥ ሲመለሱ፣ ደጋፊዎቻቸው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ አስፋልት ላይ እየቀቡ፣ በየመንገዱ እየሠቀሉ እየተደሰቱ ነበር። ይሄ ሲደረግ መንግስት ምንም አላለም፡፡ ነፃነት ሰጥቶ ሁሉንም ሰው በደስታ ተቀበለ፡፡ በኋላ ደግሞ የኦነግ መሪዎች እነ አቶ ዳውድ ኢብሣ ሲመጡ፣ ደጋፊዎቻቸው በተመሳሳይ መልኩ በድርጅታቸው አርማና ሰንደቅ አላማ፣ መንገዶችን መቀባት፣ አደባባዮችን ማስጌጥና ሠንደቃቸውን ለማውለብለብ ሙከራ ሲያደርጉ፣ ግጭት ተፈጠረ። “የኢትዮጵያን ባንዲራ አውርዳችሁ የእናንተን አትሰቅሉም” የሚለው በአንድ ወገን፣ “አይ እናንተ ጊዜያችሁን ጨርሳችኋል፤ የኛም ባንዲራ አለ” የሚለው በሌላ በኩል ቆሞ፣ ከፍተኛ ግጭት ነው የፈጠረው፡፡ ሰዎች የትና የት እንደቆሙ፣ የመጀመሪያው ማሳያ ይሄ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ሁሉም በአንድነት ነበር ለውጡን ሲያጣጥምና ሲደሰትበት የነበረው፡፡ ከዚያ በኋላ ቡራዩ ላይ በመንጋ ፍርድ፣ ብዙዎች አሠቃቂ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ሰብአዊ መብታቸው ተጥሷል። እንግዲህ ከዚህ የምናየው በ“ግንቦት 7” እና በ“ኦነግ” አቀባበል ላይ መንግስት ያሳየው ቸልተኝነት፣ የዚህ ሁሉ ችግር መነሻ መሆኑን ነው፡፡ ይህ የመንግስት ክፍተት፣ ሰዎች ቆም ብለው ነገሮችን እንዲያጠይቁ አድርጓል። በኋላም ከአዲስ አበባ ከንቲባ ሹመት ጋር፣ ከከተማዋ የይገባኛል ጥያቄ ጋር፣ በተለያዩ የክልል ከተሞች ከተከሰቱ ግጭቶችና መንግስት ከሚያሳየው ቸልተኝት፣ በኋላም የሠብአዊ መብት ጥሰትና ሙስና የፈፀሙ እየተመረጡ ሲታሠሩ … ለምሣሌ እነ አቶ በረከት ስምኦን ሲታሠሩ፣ ጥረት ኮርፖሬትን በማክሠር የሚል ነው፡፡ በአንፃሩ ግን እኩያ የሚሆነውና ከፍተኛ ምዝበራ የተፈፀመበት የኦሮሚያውን ዴንሾ ያከሰሩ እነ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ ባሉበት ነው የቀጠሉት። የሠብአዊ መብት ጥሰት በሚል ከትግራይ ሰዎች ሲታሠሩ፣ በ1997 ከምርጫ ጋር በተያያዘ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በሹመት ቀጠሉ፡፡ ይሄ ኢ-ፍትሐዊነትን ፈጠረ። የሰው ስሜትም ይሄን ተከትሎ የበለጠ እየዋለለ ነው የመጣው፡፡ ብዙ ልዩነቶች እየተፈጠሩ ሲመጡ፣ አጨብጭቦ ለተቀበለው የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደርም ያለው ስሜት ጥያቄ ውስጥ እየገባ እንደመጣ ነው ያየነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ተጨማሪ ማዳከሚያ የሆነው የኢህአዴግ የውስጥ ግንኙነት መቀዛቀዝ ነው፡፡ “የህወኃት የበላይነት ነበረ” የሚል ግምገማ በኦዴፓም በአዴፓም በኩል ነበረ። ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ግን አዴፓ ውስጥ ያሉ ሰዎች በአንፃሩ፣ “የስልጣን ተጋሪ አልሆንም” የሚል ቅሬታ ማቅረብ ጀመሩ።
ለተፈጠረው የለውጥ ሂደት ምስቅልቅል ተጠያቂው ማነው?
ተጠያቂው በአጠቃላይ ያለፍንበት የፖለቲካ ታሪክ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ተጠራጣሪ አድርጐ እዚህ ያደረሰን የፖለቲካ ስርአት ነው የነበረን። ላለፉት 60 አመታት የገነባነው ፖለቲካ፣ ያለመተማመን ባህልና ተጠራጣሪነትን ያጐለበተ ነው፡፡ ስለዚህ ከነበረው አፈና ስንወጣና ያ ደስታ አልፎ መረጋጋት ሲመጣ፣ ያ የጥርጣሬ ባህሪ በድጋሚ ቦታውን የያዘ ይመስለኛል። አሁን የተጠራጣሪነት ባህሪያችን ፊት ለፊት ተገልጦ እያየነው ነው፡፡ ኦዴፓ ስልጣን ላይ ሲሆን አዴፓ ወይም ሌሎች የኦሮሞ የበላይነትን ለማምጣት እየሠራ ነው የሚል ጥርጣሬ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይሄ ጥርጣሬ በተለይ በአማራ ልሂቃን ውስጥ የነገሠ ሆኗል፡፡ ስለዚህ አሁን ለውጡን ለምስቅልቅል ያደረሰው ተጠራጣሪነታችን፣ ያለፍንበት ስርአት የተወልን ጠባሳ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ግን መንግስት ራሱ ፍትህን ለማስፈን ወጥነት የጐደለው መሆኑ፣ አሁን ላለው ችግር አድርሶናል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ አሁን ያለው የፖለቲካ ሲስተም በራሱ ተፈጥሮ መታረቅ የማይችል መሆኑ ነው፡፡ አሁን ያለነው የሽግግር ወቅት ላይ ነን እንጂ ሠከን ብለን ተቀምጠን ተደራድረን፣ ችግሮችን ለመፍታት አቅም የለውም፡፡ ምክንያቱም ቀጣይ ምርጫ አለ፡፡
ይክፋም ይልማም አሁን በአመራር ያለው ፓርቲ ምርጫውን አሸንፎ ስልጣን መያዝ ይፈልጋል። በዚህች አንድ አመት ውስጥ አነዚህን ሁሉ ችግሮች ወይም ፕ/ር መረራ እንዳሉት “የሚጋጩ ህልሞች”ን አስታርቆ፣ ምርጫውን አሸንፎ ስልጣን መያዝ የሚቻል አይሆንም። አንዱን አስታርቃለሁ ብሎ ሲያስብ ሌላው ያመልጣል፡፡ ያመለጠውን ለመሰብሰብ ሲሄድ ደግሞ የተሰበሰበው ያመልጣል፤ ይሄ ነው አሁን ያለንበት ሂደት፡፡ ይሄን የፈጠረው የፖለቲካ ፍላጐቶቻችን በጣም የተራራቁ መሆናቸው ነው፡፡ አሁን ላለንበት መዋለል ያበቁን እነዚህ ሁሉ ተጠራቅመው ነው፡፡
“ኦዴፓ የህዝብን እምነት በልቷል”፣ “የኢትዮጵያውያንን ትግል ክዷል” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የአንተ ሀሳብ ምንድን ነው?
እኔ ሶስት አይነት ነገር ነው የሚታየኝ። አንደኛ ዶ/ር ዐቢይ ኦዴፓን ወክለው ነው ጠ/ሚኒስትር የሆኑት፡፡ ጠ/ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ይናገሯቸው የነበሩ ነገሮች፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሆኑ  የሚያሳዩ ነበሩ። ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አካሄድ ለዘብተኛ ነው። ፍትህን ማስፈን ላይ ለዘብተኛ አቋም ነው ያላቸው፡፡ ይሄ አካሄድ የፈጠረው የራሱ ክፍተት አለ። የዲሞክራሲ ባህልን ያላዳበረ ማህበረሰብ፣ እንዲህ ያለን ለዘብተኛ አመራር ደካማ እንደሆነ አድርጐ ነው የሚያስበው፡፡ በዚህ አይነት ስነልቦና ውስጥ ያደጉ ፖለቲከኞች፤ ዶ/ር ዐቢይን “መምራት ያልቻሉ ደካማ” አድርገው ያስባሉ። ዶ/ር ዐቢይ በአንፃሩ “አሁን ህግ እናስከብር ብለን ብናስር ተመልሰን ወደነበርንበት እንገባለን” የሚል ስጋት ያላቸው ይመስላል፡፡ በተለያዩ ንግግሮችም ያንጸባረቁት ጉዳይ ነው፡፡ የሃይል እርምጃ ልውሰድ ቢሉ ነገሩ ለእሣቸው ቀላል ነው፡፡ አሁንም የደህንነትና ፖሊስ ሃይሉ በኢህአዴግ ስር ነው ያለው፡፡ ግን እሣቸው ያንን መንገድ ባለመምረጣቸው፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ባህል ባለን ፖለቲካኞች ዘንድ እንደ ደካማ አመራር ነው ያየናቸው፡፡
ሁለተኛ ደግሞ ዶ/ር ዐቢይ በንግግሮቻቸው ስለ ኢትዮጵያ ሲናገሩ፣ ብዙዎቻችን የሠማናቸው በውስጣችን ያለችን ኢትዮጵያ ይዘን ነው እንጂ እሣቸው ስለሚያወሯት ኢትዮጵያ አይደለም፡፡ ዶ/ር ዐቢይ፣ ኢትዮጵያ ሲሉን እኛ የምናስበው በውስጣችን ያለችውን ኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያዊነትን የተለያየ የብሔር ታሪክ ያላቸው፣ በየራሳቸው ነው የሚተረጉሙት፡፡ ብዙ አይነት አተያይ ነው ያለው፡፡ ከዚህ አንፃር ዶ/ር ዐቢይ ኢትዮጵያ ሲሉ የውስጣችንን ትርጉም ነው ይዘን የምንሄደው፡፡ ለዚህ ነው አሁን በተግባር ዶ/ር ዐቢይ የሚሏትን ኢትዮጵያ ማየት ስንጀምር ግራ መጋባት ውስጥ የነባነው። ሶስተኛው ግን የስልጣን ሽሚያ ጉዳይ ነው። ዶ/ር ዐቢይ ክስ በበዛባቸው ቁጥር ውጥረት ውስጥ ይገባሉ። ለምሣሌ የኦሮሞ የበላይነትን ሊያመጡ ነው ሲባል፣ ውጥረት ውስጥ ይገባሉ። በቅርቡ እንኳ አንድ መጽሔት በአዲስ አበባ የአስተዳደር ጉዳይ ላይ ይዞት በወጣው መረጃ፣ የኦሮሞ ተሿሚዎችን ዝርዝር ብቻ ይዞ ወጥቶ፣ የኦሮሞ የበላይነት ነግሷል የሚያስብል ነገር ለመፍጠር ሞክሯል፡፡ ግን ሙሉ የአስተዳደሩ አመራርና ሠራተኞችን ዝርዝር ብንመለከት እውነታው ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይሄ አካሄድ ደግሞ ግልጽ የስልጣን ሽሚያ እንዳለ ነው የሚያሳየው፡፡ በአዴፓም ይሁን በሌላ ሃይሎች ዶ/ር ዐቢይን ደካማ አድርጐ በመሣል ወይም የኦሮሞ የበላይነት አስከባሪ አድርጎ በመፈረጅና ተጠራጣሪ የሆነውን ስነ ልቦናችንን በመጠቀም፣ ዶ/ር ዐቢይን የማዳከም አካሄድንም እናያለን። ይሄን የሚያደርጉት ሃይሎች ዋነኛ ግባቸው፣ ስልጣኑን ከዶ/ር ዐቢይ በስልት መቀበል ነው። በዚህ አካሄድ ደግሞ በራሱ ላይ ትልቁን ዱላ የሚያቀብለው ኦዴፓ ነው፡፡
በኦዴፓ እና በአዴፓ መካከል ምንድን ነው የተፈጠረው?
የስልጣን ፍላጎቶች መጋጨት ነው፡፡ ትልቁ ውጥረት ያለው ክልሎቹ ላይ ነው፡፡ ክልላቸው ላይ የሚፈጠርን የህዝብ ግፊትና ውጥረት ይዘው፣ ወደ ፌደራል ይመጣሉ፡፡ ክልላቸው ላይ ያለውን ውጥረት የሚያረግብላቸው የመሰላቸው የተለያየ የተቃረነ መግለጫ የሚሰጡትም ለዚህ ነው፡፡ ለምሳሌ ኦዴፓ ውስጥ ፅንፈኛ ብሔርተኝነትን የሚያራምዱ ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ የህዝቡን ተቀባይነት ለማግኘት የሚሄዱበት ርቀት ስሜታዊ የሚያደርጉ አጀንዳዎች በማንሳት የሚለካ ነው። በሌላ በኩል፣ ኦዴፓ የክልሉን መቀመጫ ካላገኘ፣ የፌደራል መንግስት መቀመጫንም አያገኝም፡፡ ስለዚህ ይህን ሃሳብ መግፋት አይፈልግም፡፡ ምክንያቱም የጠራ ርዕዮተ ዓለማዊ አቅጣጫ የለውም፡፡ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ድርጅት ነው፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ የሚያወጣቸው መግለጫዎች እነዚህን ውጥረቶች ለማርገብ በማሰብ ነው፡፡ የፅንፈኛ ብሔርተኞች፣ የለዘብተኛውን ሃሳብ አማክሎ መግለጫ ለማውጣት ሲታገል ነው፤ የምናየው፡፡ በተመሳሳይ አዴፓም የዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ የገባ ድርጅት ነው፡፡ የኦዴፓ ሎሌ ሆኗል የሚል ትችት ይሰነዘርበታል። ይሄ ከፍተኛ የስነ ልቦና ውጥረት ውስጥ ነው የከተተው፡፡ ይሄ በፅንፈኛ ብሔርተኞች የሚፈጠርን ጫና ለመቋቋምና ውጥረቱን ለማርገብ ነው፤ በተለይ ከማንነት ጋር በተገናኘ ከኦዴፓ ተቃራኒ የሆነ መግለጫ ለመስጠት የሚሞክረው፡፡
በዚህ ሁሉ ውስጥ ህወሓት የት ነው ያለው?
አሁንማ ህውሓት በሃገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ግን “አትድረሱብን አንደርስባችሁም” ያለ ይመስላል። በተለይ በኢዴፓ እና በኦዴፓ መካከል በተፈጠረው መቀዛቀዝ ሳቢያ ልሂቃኖቹ በሁለቱም ላይ ዱላ ሲሰነዝሩ ይታያል። ይሄ ለህውሓት ምቾት የሰጠው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አሁን ተፈላጊነትም ሊኖረኝ ይችላል ብሎ ይገምታል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ሶህዴፓ (የሶማሌ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ) በዚህ ጨዋታ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሶህዴፓ በፓርላማ ከህውሓት እኩል ማለትም 36 መቀመጫ ነው ያለው፤ ይሄ ቀላል አይደለም፡፡ አመራሩም ወደ ፌደራል ፖለቲካው የበለጠ ለመሳተፍ አዝማሚያ እያሳየ ነው፡፡ ህውሓት አሁን ከጎኑ ማድረግ የሚፈልግ ይኖራል፡፡ በቀጣይ ህውሓት ሚናው ምን ይሆናል የሚለውን ደግሞ በተግባር የምናየው ይሆናል፡፡ እስካሁን ግን ገለልተኛ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ፓርቲዎች ወደ ውህደት ሲሄዱ ግን የህውሓትን ተግባራዊ ሚና እናያለን። አሁንም ለወደፊትም ቢሆን ህውሓት ለዶ/ር ዐቢይ በጣም ፈተና የሚሆን ይመስለኛል፡፡
አሁን ባለው የብሔር ፖለቲካ መካረር “አዴፓ” እና “ኦዴፓ” በቀላሉ ውህድ ፓርቲ መሆን ይችላሉ?
ለራሳቸው ሲሉ አንድ ውህድ ፓርቲ የሚሆኑ ይመስለኛል፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ሃገሪቷን ለማስተዳደር የሁለቱ ትብብር ወሳኝ እንደሆነ ያጡታል ብዬ አላስብም። ኦዴፓ የአጋር ፓርቲዎችን ሰብስቦ ውህድ የሚፈጥር ከሆነና አዴፓ ራሱን ካገለለ ጥሩ እንደማይመጣ ያውቁታል፡፡ ውህደቱን ይፈልገዋል፤ አዴፓም በተመሳሳይ፡፡ አዴፓ በዚህ ስብስብ አልካተትም ካለ፣ ህውሓትም ተመሳሳይ አቋም ከወሰደና ሁለቱ ብቻቸውን ከተጣመሩ ለእነሱ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ ለመጣመርም በጣም ይከብዳቸዋል፡፡ ኦዴፓ እና አጋሮች ከተጣመሩ አብላጫ ወንበር ይዘው መንግስት ሆነው የመቀጠል እድል ይኖራቸዋል። አዴፓ እና ህውሓት ግን ቢጣመሩም አብላጫ ወንበር መያዝ አይችሉም። ስለዚህ ይህን ስሌት ከግምት አስገብተው፣ ሁለቱ አዴፓ እና ኦዴፓ ከመጣመር (መዋሃድ) ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ያውቃሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡
አሁን ባለንበት ሁኔታ እንዴት ነው ጤናማ ዲሞክራሲ የሚገነባው?
ይሄ ከባድ ነው፡፡ አሁን ጤናማ ዲሞክራሲን የምንገነባበት እድል የለም፡፡ አሁን መንግስት ሊያደርገው የሚችለው፣ የተገራ ‹ሊበራላይዤሽን› መተግበር ነው፡፡ ምናልባት እንደ ቱርክ ያሉ መንግስታትን በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል። በቱርኮች መንገድ ዲሞክራሲን ማስለመዱ የተሻለ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ዲሞክራሲን ልቅ ለማድረግ ቢሞከር የሚሸከም ባህል የለንም። ዲሞክራሲ ስትል ደካማ አድርጎ የሚያስብህ ሃይል ራሱ ጉልበት እያገኘ ይመጣል፡፡ ጉልበት ሲያመጣ ደግሞ ጠላት ነው የሚሆንብህ፡፡ ጠላት ሆኖ ሲመጣብህ ሳትወድ አምባገነን ትሆናለህ፡፡ ስለዚህ ሊያለማምደን በሚችል መልኩ የተቃኘ ነፃነት ነው የሚያስፈልገን እንጂ በአንድ ጊዜ ልቅ የሚሆንበት ስርአት ብዙ አያስኬድም፡፡ በሌላ በኩል፤ ዲሞክራሲ የግለሰቦችን በነፃነት የመወሰን መብት ይጠይቃል፡፡ አሁን ባለው የፖለቲካ ስርአት ግን ቡድኖች ናቸው እንጂ ግለሰቦች አይወስኑም፡፡ ህገ መንግስቱ በራሱ ለግለሰቦች ዲሞክራሲ ማነቆ ነው። ለዚህ ዲሞክራሲን መሰረት ለማስያዝ ብዙ የሚቀሩ ነገሮች አሉ። ያ ማለት ግን ዲሞክራሲ አይገባንም ማለት አይደለም፡፡ ግን ዲሞክራሲን የምንሸከምበት ሁኔታ በመጀመሪያ መፍጠር አለብን፡፡ ለምሳሌ፡- አንዱን አንዱ ሲያሸንፍ፣ ተሸናፊው መሸነፍን በፀጋ የማመን ባህል ማዳበር አለበት፡፡ ይሄ ገና አልጀመርነውም፡፡
አሁን ያለው ስርአት ይሄን ለመፍጠር ያስችላል?
አዎ በዚህ ስርአት ያንን ማምጣት ይቻላል። አንደኛ በተቻለ መጠን ተቋማትን ገለልተኛ ለማድረግ እየሞከረ ነው፡፡ ለምሳሌ ምርጫ ቦርድ፣ ጠቅላይ ፍ/ቤት የመሳሰሉትን ለመቀየር የሚደረገው ጥረት ሲታይ ተስፋ ይሰጣል። ሌሎች አፋኝ የሚባሉ ህጎችን ለማሻሻል የሚደረግ ጥረትም አለ፡፡ እነዚህን የለውጡን ኃይል ጥረቶች ስንመለከት ብዙ ተስፋ ማድረግ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ተስፋው የፀና እንዲሆን የአራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች መስተካከልና አንድ መሆን ወሳኝ ነው፡፡ ግን አሁንም ጥሩ ዕድል አለ፡፡
አክራሪ ብሔርተኝነት ሃገሪቱን ወዴት ሊወስዳት  ይችላል?
አሁን ባለው መልኩ ከቀጠለ ሃገሪቷን አደጋ ውስጥ እንደሚከታት ምንም ጥርጥር የለውም። አደጋ ውስጥ ይከታታል ስል ግን ያፈርሳታል ማለቴ አይደለም፤ ወደ ተለያየ ግጭት ነው የሚከታት። ግጭቱ ውስጥ ደግሞ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ግጭቶች በዚህ መልኩ የሚፈጠሩ ከሆነ፣ ማዕከላዊ መንግስቱን የያዙት ኃይሎች ፍፁም አምባገነናዊ ይሆናሉ። ይሄ አካሄድ ሄዶ ሄዶ ወደ ወታደራዊ ስርአት ይወስደናል የሚል ስጋት ነው ያለኝ፡፡ ግን ይሄ ከመሆኑ በፊት ራሱ ኢህአዴግ ወደ አንድ ሃገራዊ ፓርቲ ከመጣ፣ ይሄን ፅንፈኝነት ሊያረግበው ይችላል፡፡ ፅንፈኝነቱንና የስሜት ፖለቲካውን ወደ መሃል ሰብስቦ ያሰክነዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡ የኢህአዴግ ውህድ ፓርቲ መሆን አንዱ ከፅንፈኝነት የመውጫ መንገድ ይመስለኛል። ይሄ ካልሆነ ግን ሃገሪቱ አትፈርስም፤ ነገር ግን የከፋ አምባገነናዊ ወታደራዊ መንግስት ሊፈጠር እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “አዲስ አበባ የኔ ነው” … የሚል ስሜት ለምንድን ነው ያየለው?
ይሄ ስሜት በልሂቃኑ ውስጥ ካለው የመገንጠል እሣቤ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ነገ ስንገነጠል ይዘነው ልንገነጠል እንችላለን በሚልና ሲገነጠሉ ይዘውብን ይሄዳሉ ከሚለው አስተሳሰብ የመነጨ ውጥረት ነው። ይሄ እሣቤ ነው ይሄን ሁሉ ጥርጣሬ የሚፈጥረው፡፡ ነገ ለሚገነጠሉት እንዴት አዲስ አበባን እንለቃለን የሚለውም በመድረኩ አለ፡፡ ሌላው ብሔረሰቦች እንጂ የፖለቲካ ሃሳብ የስልጣን መፎካከሪያ ባለመሆኑ፣ አዲስ አበባን የስልጣን ተፎካካሪዎች እንደ መወዳደሪያ አድርገዋታል፡፡ አዲስ አበባ ነፃ ግዛት ነች፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ኢህአዴጐች እንደ ኢህአዴግ ነበር የሚወዳደሩት እንጂ ኦህዴድ እንደ ኦህዴድ፣ ብአዴን እንደ ብአዴን አልነበረም። በኮታ ነበር ስልጣን የሚከፋፈሉት። አሁን ግን ድጋፍ እያሠባሰቡ ያሉት እንደ ኢህአዴግ ሳይሆን በየራሣቸው ቆመው ነው፡፡ ይሄ በራሱ ሌላው ችግሩን አባባሽ ሁኔታ ነው፡፡ አዲስ አበባ የብሔርተኞች የሽኩቻ ማዕከል ነው የሆነችው። ግን አንዳቸውም ለከተማዋ የሚፈይዱላት ነገር የለም፡፡ ጃዋር መሐመድ በአንድ በኩል፣ እስክንድር በሌላ በኩል የቆሙበት ሁኔታ ከፖለቲካ ፍላጐት የሚመነጭ ነው፡፡ እስክንድር የሚያነሳው ጥያቄ ትክክል ነው፤ “አዲስ አበባ የአዲስ አበባውያን ነች” ይላል፡፡ አዎ ነች፡፡ ጃዋር ባለቤት ነኝ ቢል አንሠማውም፡፡ እዚህ ጋ ግን ያለው ችግር ምንድን ነው? በእስክንድርና በእስክንድር ዙሪያ የተሰባሰቡ ሃይሎች የአማራ ብሔርተኞች መሆናቸው ነው፡፡ እስክንድር ራሱ የአማራ ብሔርተኛ እንደሆነ የሚጽፋቸው ጉዳዮችን በማስረጃ መጥቀስ ይችላል፡፡
ሀገሪቱ ከገባችበት ውጥረት እንዴት ነው የምትወጣው? እስቲ ሃሳብ አዋጣ …
በመነጋገር ነው ከዚያ ችግር መውጣት የሚቻለው፡፡ ውይይት በስፋት ያስፈልገናል፡፡ አሁን ባለው ስሜት ትክክለኛ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም። ቢካሄድም አሁን ባለው ሁኔታ በምርጫ አሸናፊ የሚሆነው ብሔር እንጂ የፖለቲካ ሃሳብ አይሆንም፡፡ ብዙ ቁጥር ያለው ብሔር ያሸንፋል፡፡ አበቃ፡፡ በዚያ ደግሞ ግጭት ሊነሳ ይችላል፡፡ ይሄን ሁሉ ለማርገብ ብዙ ፖለቲካዊ ውይይቶች ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል፣ አሁን ስልጣን ላይ ያለው ሃይል አጋር ምናምን የሚለውን ትቶ፣ በመጀመሪያ ግንባር ሆኖ፣ በብዙ ነገሮች መግባባት አለበት። በመርህ ደረጃ አንድ ላይ መቆም አለባቸው። መደራደር፣ መነጋገር አለባቸው፡፡ በኋላ ወደ ውህደት መምጣት ይችላሉ፤ ከአጋሮቹ ጋር። በዚህ የእነሱ ስምምነት አንድ ውህድ ፓርቲ ከተፈጠረ፣ ትልቅ እፎይታ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ እነሱ በዚህ መልኩ ሲደራጁ አብን፣ ኦፌኮ፣ አረና የመሳሰሉት ደግሞ በተመሳሳይ ተነጋግረው ወደ ግንባር፣ ጥምረት፣ ቅንጅት መቀየር መቻል አለባቸው፡፡
አለበለዚያ ኢህአዴግ ብቻውን አንድ ሀገራዊ ፓርቲ ሲመሠርት፣ አማራ ክልል የሚያሸንፈው አብን ቢሆን ፌደራል መንግስቱ ላይ ተፅዕኖ እንኳ መፍጠር አይችልም፤ ሌላውም እንደዚያው። ፌደራል መንግስቱን የመምራት እድል አይኖረውም፡፡ ነገር ግን የስልጣን ሽኩቻው ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ኦፌኮም ተመሳሳይ ነው … ሶስተኛው ሃይል ደግሞ ግንቦት 7፣ ሠማያዊ፣ ኢዴፓ የመሳሰሉት … ወደ ውህደት ሲመጡ፣ ትልቅ ድጋፍ የሚኖራቸው ከተማ ላይ ነው፡፡


Read 6897 times
Administrator

Latest from Administrator