Print this page
Saturday, 30 March 2019 13:36

የዶ/ር ዐቢይ 365 ቀናትና ፈተናዎቹ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

 ኢሕአዴግ በሕግ የሚመራና የሚተዳደር ድርጅት አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሲሞቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትራቸው የነበሩትን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ በሾመበት መንገድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ባልተጠበቀ ጊዜ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ሲለቁ፣ ምክትላቸውን አቶ ደመቀ መኮንንን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ አልሾማቸውም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ለስድስት ዓመት ይዘውት የቆዩትን “የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን” የለቀቁት ወደው ነው ብዬ አላምንም፡፡ ተጨንቀው እንጂ፡፡ ተገድደው ደግሞ አይደለም። “ለስድስት ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትር ወንበር ተቀምጫለሁ፡፡ ሥልጣኑ በእኔ እጅ አለ ወይ? በእኔ ስም የሚፈፀሙ ወንጀሎችን እያየሁ እስከ መቾ ዝም ብዬ እቀመጣለሁ? አጋዚ ክፍለ ጦርን ማስቆም የማልችል ሰው እዚህ ወንበር ላይ ምን አስቀመጠኝ? አይበቃኝም?” ብለው እራሳቸውን ደጋግመው ጠይቀው፣ ሥልጣን መልቀቅን ለራሳቸው መልስ አድርገው እንደሰጡ አምናለሁ፡፡ አቶ ኃይለማርያም በገቡት ቃል መሠረት በሥልጣን ላይ የነበሩበትን ጊዜ እንዴት እንዳሳለፉት ነግረውን ቢሆን ኖሮ፣ እንደ ጥላ ይከተሏቸው የነበሩት እነ አቶ ጌታቸው ረዳ በእሳቸው ላይ የነበራቸውን ተፅዕኖ ለመረዳት ያገለግለን ነበር፡፡ ምናልባትም እንደ ሜቴክ እግዚኦ! ብለን እንድንጮህ ያደርገን ነበር፡፡
ያልተጠበቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣን መልቀቅ፣ ያልተጠበቁትን ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር አመጣ። ያልተጠበቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያልተጠበቀ ነገር አመጡ፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ በሚብጠለጠልበት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትና መተባበር በማይፈለግበት ዘመን፣ ፀረ - አንድነት በተሰበከበት የተወካዮች ምክር ቤት ስለ ኢትዮጵያዊያን አንድነት አስፈላጊነት ተናገሩ። “ትናንት በአድዋና በካራማራ አጥንታቸውን ከስክው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆዩአት አገር አለችን፡፡ እኛ እድለኞች ነን አማራው በካራ ማራና ትግራዋይ በመተማ፣ ኦሮሞው በአድዋ ተራሮች ላይ ስለ ሀገሩ ደረቱን ሰጥቷል፡፡ ሶማሌው፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ቤንሻንጉሉ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌውና፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ሐድያው ሌሎቹም ኢትዮጵያውያን ከእኔ በፊት ብለው ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ አገር - ኢትዮጵያ እንሆናለን” በማለትም በየጊዜው በጋራ ለነፃነት የተከፈለውን መስዋዕትነት አስታውሰው መስክረዋል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፤ ብዙዎቻችን ውለታቸው ያለብን ቢሆንም አክብሮቱን ሰጠናቸው፡፡ የማናውቃቸውን እናቶቻችንን እንድናከብር የሚያደርግም ነገር ተናገሩ፡፡ ከሰባት ዓመታቸው ጀምሮ ከፍ ያለ ደረጃ እንደሚደርሱ ይተነብዩ የነበሩትን እናታቸውን አስታውሰው፤ “ዛሬ በሕይወት በአጠገቤ ባትኖርም፣ ወደ እናቴ ምስጋናዬ በአፀደ ነፍስ ይደርሳት ዘንድ በክብር ላመሰግናት እወዳለሁ፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያውያን እናቶች በልጆቻቸው የነገ ራዕይ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው በመገንዘብ ነገ ለሚያጭዱት መልካም ፍሬ፣ ዛሬ ላይ የሚዘሩት ዘር ዋና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለሚከፍሉት መስዋእትነት ያለኝን በምንም የማይተካ አድናቆትና ምስጋና በብዙ ክብር፣ በብዙ ፍቅር አቀርባለሁ” አሉ፡፡
እነዚህና እዚህ ላይ ያልዘረዘርኳቸው፣ በዚያ ንግግራቸው የገለጧቸው ሀሳቦች ከምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ ያስገኘላቸውና በተደጋጋሚ ጭብጨባ የተገለጠላቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኔን ጨምሮ እጅግ በጣም በሚበዙ ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥም እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡
አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቀመናብርት ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እርምጃ እንደሚወሰድ አስታወቁ፡፡ እነ አቶ ጌታቸው አምባዬ ይቅርታውን ጠምዝዘው ልዩ ልዩ መስፈርት አወጡለት፡፡ የዐቢይ ወደ ስልጣን መምጣት የእነ አቶ ጌታቸውን ሴራ በጣጣሰው። ብዙ እስረኞች በተከታታይ ተፈቱ። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን መደራደሪያ አድርገው እንዳስፈቷቸው በአደባባይ መሰከሩ፡፡ እነ አቶ በቀለ ገርባ፣ እነ ጀነራል አሳምነው ጽጌ፣ ከእነ አቶ መላኩ ፈንታም ተፈቱ፡፤
የዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት ታላቅ የምስራች የሆነው ደግሞ በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝብ መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲፈጠር ይጥሩ ለነበሩ ወገኖች ነው። ውል በውልነቱ ይከበር ከተባለ ምንጊዜም መፈፀሙ የማይቀረውን የኢትዮጵያና የኤርትራ  ስምምነት ወደ ጎን በመተው፤ እሳቸው ወደ ኤርትራ፣ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ጉብኝት አደረጉ፡፡ ይህም በዓለም ፊት እንዲከበሩ አደረጋቸው፡፡
የታመመውን በመጠየቅ፣ የታሰሩትን በማስፈታትና ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ዶ/ር ዐቢይ የፈፀሙት ተግባር፤ ከሚደነቁላቸው ሥራቸው ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡  
ኢትዮጵያ የነበረባትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለልም ከአገር አገር መንከራተታቸው እውነት ነው፡፡ ለፍተው አለመቅረታቸውም እግዚአብሔር ከእርሳቸው ጋር ነው የሚያሰኝም ነው፡፡ “እኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረታችንን እያቃለልን ነው፤ ዶላር ዩሮ የያዛችሁ ሰዎች ታቅፋችሁት እንዳትቀሩ” በሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ማሳሰቢያ ገንዘቡ ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገባ መንግሥታቸው ያደረገው ጥረትም ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ከጊዜያዊ መፍትሔነት አላለፈም፤ ጥቁር ገበያውም ተመልሶ ጣራ እየረገጠ ነው፡፡
በ2008 ዓ.ም መጨረሻና በ2009 በቀጠለው የሕዝብ አመጽ፣ በየቦታው የወደሙት ፋብሪካዎች የትራንስፖርትና የልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ተቋሟት የፈጠሩት ሥራ አጥ እንዳለ ሆኖ፣ መንግሥትንም በእዳና በኪሣራ ውስጥ መክተቱ ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ከለውጥ በፊት የጀመረውና ከለውጡ በኋላም በብዛት በየአካባቢው የተከሰተው ግጭት፣ የዜጐች መፈናቀል ችግርን አባባሰው፡፡
እዚህ ችግር ላይ የወደቁት አርሶ አደሮች በመሆናቸው የተነሳ ማሳቸው ጦም ማደሩ፣ እነሱና ቤተሰባቸውም እርዳታ ጠባቂ መሆን ሲታይ ደግሞ የመፍትሔ ያለህ ብሎ ለመጮህ ያስገድዳል፡፡ እሳቸው ወደ ሥልጣን ሲመጡ በሰባት መቶ ሺህ አካባቢ የነበረው ተፈናቃይ ዛሬ ከሁለት ሚሊዮን በላይ መሆኑን ስናይ፣ ከሀዘናችን ብዛት አንገታችንን እንድንደፋ እንገደዳለን፡፡
ዶክተር ዐቢይ “ልጅ እያሱን” የሆኑባቸው የመጀመሪያ ሶስት ወራት፣ የሀገር ውስጡን ፖለቲካ መለወጥ የሚያስችሉ ጊዜዎች እንደነበሩ አምናለሁ፡፡ ያ ጊዜ በቀላሉ ለማሻሻል የሚችለውን የሕገ መንግሥቱን ክፍል ጨምሮ ኢሕአዴግ በ1997 አገር አቀፍ ምርጫ አኩርፎ ተቀናቃኞችን ለማጥቃት ያዘጋጃቸውን አዋጆች ሁሉ መለወጥ ያስችል እንደነበር ከልብ አምናለሁ፡፡ ሕገ መንግሥቱና እነዚያ አሳሪ ሕጐች አሁን በዶክተር ዐቢይ መንግሥት አንገት ላይ የተንጠለጠሉ ድንጋዮች ሆነው ወገቡን እያጐበጡት ነው፡፡
“ከእነጐረቤቴ አማን አድርገኝ” የእኔም የአገር ምድሩም ፀሎት ነው፡፡ ዶክተር ገቢይ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት፣ ጅቡቲንና ኤርትራን ለማቀራረብ አልፎም በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል የተሻለ ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ ያደረጉትን ጥረት በጣም አደንቃለሁ፡፡ ከዚህ ጐን ደግሞ ዝንጀሮ “መጀመሪያ የመቀመጫዬን” ያለችው ለአፍታም ቢሆን አይዘነጋኝም፡፡ አስራ ስምንት ባንኮችን የዘረፈውና እራሱን በገንዘብ እያጠናከረ ያለው የኦነጉ ሼኔ፣ ምሥራቅ ወለጋ ላይ አለመረጋጋት ከመፍጠሩም በላይ በውጪም ሆነ በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተሰሚነት ለማግኘት ሲል ሰሞኑን በኢትዮጵያዊያንና በአንድ የውጭ አገር ሰው ላይ ግድያ ፈጽሟል። ነገሩ በዝምታ የታለፈም እየመሰለ ነው ለምን? ይኸ ችግርስ ነገ የት ላይ ይቆማል? አብዝቶ መንግሥት ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
“የታፈነ ቤት ሲከፈት የሚሰነፍጥ ሽታ ሊፈጥር ይችላል” የሚሉት ዶክተር ዐቢይ የሚሰነፍጠው ሽታ መቆራቆስ መፈራረስ እንዳያመጣ ምን ያህል እያሰቡና እየተጠነቀቁ ናቸው? ጥያቄዬ ነው፡፡ በተለይ በትግራይና በአማራ ክልል መካከል፣ በየትም አገር በየትኛውም ዘመን በማንኛውም መንግሥት፣ የዚያ መንግሥት መቀመጫ ከተማ፣ ከተማው የሚገኝበት አካባቢ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በዚያ መንግሥት ግዛት ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎች ሁሉ የመጨረሻው ጠረፍ መንደር ሳይቀር ዋና ከተሞች ነው፡፡ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጐንደር በየዘመኑ የነበረው መንግሥትና ሕዝብ ዋና ከተሞች ነበሩ፡፡ አዲስ አበባም እንዲያ ናት። ሕገ መንግሥቱም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው፡፡ “የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም” ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ለምን አላማ እንደገባ የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ያጣዋል ብዬ አላስብም በዚህ ጉዳይ ግልጽና ቁርጥ ያለ አቋም ያለ መውሰድ፣ ይባስ ብሎ ግልጽነት የማይታይበት ኮሚቴ ማቋቋም፣ በቡሃ ላይ ቆረቆር አይሆንም ወይ ብሎ የዶክተር ዐቢይን መንግሥት መጠየቅ ይገባል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ እያዘናጉን ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፣ ጊዜ ልንሰጣቸው ይገባል የሚሉም ሰዎች አሉ፡፡ ለእኔ ደግሞ የሚታየኝ መልካም ጊዜዎችን እያሳለፉ፣ እራሳቸውን ፈተና ውስጥ የሚከቱ ሰው ሆነው ነው፤ የኢሕአዴግ መዋቅር እንዳለ መቀመጠል ለዶክተር ዐቢይ አንገታቸው ላይ የታሠረ ቀንበር ሆኖ እየታየኝ ነው፡፡ አንድ ካላሉት እሱ አስቀድሞ አንድ ሊላቸው እንደሚነሳ መገመት ነብይ አያሰኝም፡፡ እሱ ሌላ አደጋ ነው፡፡
“በታሪካችን በተለያዩ አጋጣሚዎች አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የመጀመር እድሎችን አግኝተን ብዙዎችን በወጉ ሳንጠቀምባቸው አምልጠውናል” ሲሉ ለምክር ቤቱ ያደረጉትን ንግግር ይዤ፣ እኔም አሁን እጠይቃለሁ፤ መልካም ሥራቸውን ሊያጐድፉ መንገዳቸውን እየዘጉ ያሉትን  ቅንቅኖች መግታት ይችላሉ ወይ? ካልቻሉ፣ የሚከተለው አያሳስባቸውም ወይ? እላለሁ፡፡ ሰላሙን ያምጣልን!!

Read 1711 times