Saturday, 30 March 2019 13:34

“የወደፊቱን ተመልካች ፓርቲ ነው የመሠረትነው”

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ፓርቲ ማቋቋም እንደ ነውር መታየት የለበትም

        የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ድግሪያቸውን ያገኙት በምጣኔ ሀብት ነው፡፡ በምጣኔ ሀብት ባለሙያነትና ተመራማሪነት በበርካታ ሀገር በቀል መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ሠርተዋል፡፡ ባለፉት 8 አመታትም ኑሮአቸውን በውጭ ሀገር አድርገው፣ የሀገሪቱን የፖለቲካና ምጣኔ ሃብት ሁኔታ ሲከታተሉ መቆየታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ከወዳጆቻቸው ጋር የፖለቲካ ድርጅት ለማቋቋም ካቀዱ 10 አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ያኔ የተፀነሰው ሃሳብ በኢትዮጵያ ባለፈው 1 አመት ውስጥ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ዛሬ ተወልዷል ይላሉ - ዶ/ር ዐብዱል ቃድር አደም፡፡ አዲሱ ፓርቲያቸው ነፃነትና እኩልነትን በዋናነት ያቀነቅናል፡፡ ስያሜውም “ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ” ነው፡፡ ፓርቲውን ከመሠረቱት አንዱ የሆኑትና በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ዶ/ር አብዱል በፓርቲው አላማ፣ ግብና በፖለቲካ ፕሮግራሙ እንዲሁም በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር እንደሚከተለው ቆይታ አድርገዋል፡፡


              “ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ” እንዴት ተወጠነ?
የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ብሆንም፣ እኔ በግሌ ከድሮ ጀምሮ የፖለቲካ ፍላጐት ነበረኝ፡፡ ብዙ ጊዜዬንም በሀገራችን የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አተኩሬ እንቀሳቀስ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል ጊዜ በሀገራችን የነበረው ሁኔታ ለእውነተኛ ፖለቲካ ትግል የሚመች አልነበረም፡፡ ስለዚህ ዝም ብሎ እጅን አጣጥፎ ከመቀመጥ ብዬ በሲቪክ ማህበራት በኩል እንቅስቃሴ አደርግ ነበር፡፡ በተለይ አርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ በአገልግሎትና ማህበረሰብን በማንቃት ስራዎች ስሳተፍ ቆይቻለሁ፡፡ ያን ማድረጌ የሀገሪቷ አቅጣጫ ወዴት ነው መሄድ ያለበት? ያለንን አቅም ምን ላይ ነው ማዋል ያለብን? የሚለውን ከጓደኞቼ ጋር ሆነን ስናጠና ቆይተናል፡፡ ውጪ ትምህርት ላይ እያለሁም ከበርካታ ኢትዮጵያውያን ጋር በዚህ ባለራዕይ ፓርቲ ምስረታ ላይ  ለረጅም ጊዜያት፣ ውይይትና ምክክር ስናደርግ ቆይተናል፡፡
ርዕዮተ አላማችሁ ምንድን ነው? የሀገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ፍላጐትስ ያማከለ ነው ትላላችሁ?
በመጀመሪያ ደረጃ አሁን በሀገሪቷ ውስጥ በግልጽ የሚታይ ለውጥ አለ፡፡ በአስተሳሰብም በተግባርም ለውጥ አለ፡፡ ይሄን እኔም ባልደረቦቼም ገምግመን ተረድተናል፡፡ ምርጫ ቦርድ ኃላፊነት ሠራተኞችም ጥሩ ድጋፍ ነበር ሲያደርጉልን የነበረው እኛ ፓርቲውን ለመመስረት ከተንቀሳቀስንበት ያለፉት 5 ዓመት ውስጥ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎችናት ባለሙያዎች ከፍተኛ ድገፍ ነው ያደረጉልን፡፡ በተለያዩ ውይይቶች ላይ ስንሳተፍ ቆይተናል። በቅርብ ጊዜ በተዘጋጀወ የቃል ኪዳን ሰነድ ላይም ፈርመናል፡፡ ገና ሳንመሠረት እንድንፈርም ምርጫ ቦርድ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጐልናል። እኛ የተጀመረ የለውጥ በር ውስጥ ገብተን፣ ማስፋት አለብን የሚል አላማ ነው፣ ያለን፡፡ ስንቋቋም ሁለት ዋነኛ ጉዳዮች መነሻ አድርገን ነው፡፡ አንደኛ የኢኮኖሚ ችግር ነው፡፡ ሀገራችን በጣም ድሃ ከሚባሉት ሀገሮች ውስጥ ናት፡፡ ሁለተኛው ጊዜያዊ ችግሮች ናቸው፤ ሠላምና መረጋጋት ጠፍቷል፡፡
በቀጣይ ምን ሊሆን እንደሚችል አናውቅም። ስለዚህ ይሄን ሁኔታ ለአጋጣሚ ወይም ለእድል ከመተው እኛ የምንችለውን ያህል ተሳትፈንበት ማስተካከል አለብን ከሚል ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ በሀገራችን ብዙ ያልተሞከሩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አካሄዶች አሉ እነዚያን አውጥቶ ለህዝባችን አዲስ ነገር ለማበርከት ነው፡፡
ርዕዮተ አለማችንም ከዚህ ተነስቶ የተቀረፀው ነው፡፡ ለዘብተኛ ሊበራል አስተሳሰብ ነው፡፡ ለዘብተኛ ሊበራሊዝምን የመረጥነው ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ይጣጣማል በሚል ነው። ጭልጥ ያለ ሊበራሊዝም አይጠቅመንም። ከሶሻል ዲሞክራሲም በጐ የሆነውን እንወስዳለን። መሀል ላይ ያለውን አስተሳሰብ ነው ይዞን የምንራመደው፡፡
ትግላችንም ሙሉ ለሙሉ ርዕዮተ አለምን መሠረት ያደረገ ነው የሚሆነው፡፡ የራሳችንን የኢኮኖሚ ፕሮግራምም ቀርፀናል፡፡ ማህበራዊ ጉዳዮችን በተመለከተም በዋናነት ባህላችንን መነሻ የሚያደርግ ይሆናል እንጂ ከአውሮፓ ሊበራሊዝም የሚቀዳ አይሆንም፡፡ ለዚህ ነው ለዘብተኛ ሊበራሊዝምን አማራጫችን ያደረግነው፡፡ በነገራችን ላይ ከሊበራሊዝም ብቻ ሳይሆን ከሶሻል ዲሞክራቶች ጠቃሚ ነገር ሲኖር እንወስዳለን፡፡ ርዕዮት አለማችን የማይለወጥ የማይቀየር ነው ብለን አናስቀምጥም፡፡
“ነፃነት እኩልነት” የሚለውን ስያሜ ስትመርጡ ምንን ታሳቢ በማድረግ ነው?
የፓርቲ ስያሜ ለማውጣት ብዙ ተጨንቀንበታል። ተግባራችንን በትክክል ሊገልጽ እንደሚገባ ስንነጋገር ነበር፡፡ አኛ በፖለቲካ ትግላችን አማካዩን ፍለጋ ላይ ነው የምናተኩረው፡፡ ኦሮሞነትን አማራነትን፣ ጉራጌነትን፣ ሲዳማነትን የማያኮስስ፣ ኢትዮጵያዊነትን የማያኮስስ፣ ሁለቱንም በእኩል የሚመለከት የፖለቲካ አካሄድ ነው የመረጥነው።
ስለዚህ ነፃነት ስንል፣ ሁሉን አቀፍ ነፃነት፡- የመደራጀት፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ ሠርቶ የመበልፀግ የመሳሰሉትን ማንሳት እንችላለን። እኩልነት ስንል በህዝቦች፣ በፆታ፣ በብሔር … ማንም ከማንም የማይበልጥ እንዲሆን ነው። ነፃነትና እኩልነት ሁለቱም የወቅቱ የፖለቲካ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሁለት አንኳር ጉዳዮች ማሳካት እንደተቀመጠው፤ ሀገሪቱን በሚገባ አስተማማኝ አድርጐ ያሻግራታል የሚል ጽኑ እምነት ነው ያለን። በሀገሪቱ የብዙ ችግሮች መነሻ፣ የእኩልነት ጉዳይ ነው፡፡ ኤርትራን ያሳጣን ስንመራመር ብንውል መጨረሻው የእኩልነት ጥያቄ ሆኖ እናገኘዋለን። አሁንም ያለው የብሔር የግዛት ይገባኛል ጥያቄ መነሻው የእኩልነት ጉዳይ ነው፡፡
ፓርቲያችሁ ምን አይነት አባላትን ነው ያሰባሰበው?
ሁሉም መስራች አባላት ከዚህ ቀደም ቀጥተኛ የፓርቲ ፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው አዳዲሶች ናቸው፡፡ በመተዳደሪያ ደንባችን እንደተቀመጠው፤ በምስረታ ጉባኤያችን 50 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተመርጠዋል፡፡ ከእነዚያ 50 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል 11 የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ተመርጠዋል። ሁሉም እኔን ጨምሮ ለፓርቲ ፖለቲካ አዲስ ነን፤ ግን እንዳልኩት ለረጅም አመታት ዝግጅት በማድረግ ሂደት ውስጥ ሠፋፊ ልምዶችን ለመቅሰም ሞክረናል፡፡ ፓርቲያችን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች መጥፎና እና ነገሮች ለይቶ ጠቃሚውን እየሰወደ ነው ወደፊት የሚጓዘው። ፓርቲው ተቋማዊ እንዲሆን ነው እየሠራን ያለነው፡፡
የሀገሪቱን ወቅታዊ ፖለቲካ እንደ ፓርቲ እንዴት ነው የምትረዱት?
ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ለውጥ አለ፡፡ ሠፊ የፖለቲካ ምህዳር አለ፡፡ አስቸኳይ ሁኔታዎች አሉ። መንግስት ጠንካራ ድጋፍ እያደረገልን ነው። ተግዳሮት ሊሆን የሚችለው በሀገሪቱ ያለው የፀጥታ መደፍረስ ካልሆነ በስተቀር፣ ጥያቄ ውስጥ የማይገባ አስቸኳይ ሁኔታ፣ አሁን በሀገሪቱ አለ፡፡ እርግጥ ነው የሽግግሩ ጊዜ በጣም ማጠር አለበት፤ በተራዘመ ቁጥር ብዙ ችግር ነው የሚፈጥረው። ግጭቶችና አለመግባባትን በአንድ ጊዜ ማስቆም ከባድ እንደሆነ ይታወቃል። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ከመተቸት ይልቅ አማራጭ ሃሳቦችን ማቅረቡ የተሻለ ይሆናል፡፡ የኛ ፓርቲ በፖለቲካ ትግሉም ከመተቸት ይልቅ አማራጭ ሃሳቦችን በማቅረብ ላይ ያተኩራል። አሁን ጥሩ የሽግግር ጊዜ ላይ ነን፤ በዚያው ልክ የታዩ ክፍተቶች አሉ፡፡ እነዚህን በአማራጭ ሃሳቦችና ምክሮች ማቃናት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው ከመረረ ትችት ወጥተን፣ መንገድና አቅጣጫ ማመላከት አለብን የምንለው፡፡
ለውጡ ወዴት ሊያመራ ይችላል? ተገማች ሁኔታዎች ይኖራሉ?
አሁን ብዙዎቻችን ያለን አስተሳሰብ ጥናት ላይ ያተኮረ አይደለም፡፡ ያለው አካሄድ ብሔር ላይ መሠረት ያደረገው በአንድ ጐራ፣ የዜግነት ፖለቲካ የሚባለው ደግሞ በሌላ ጐራ ነው። ብሔር ላይ የተመሠረተው ሀገሪቱ ወደ አሃዳዊነት እንዳትሄድ ነው የሚታገለው፡፡ በእነዚህ ሁለት አካሄዶች መሃል አማካይ ካለ፣ ጥሩ የለውጥ አካሄድ ይኖረናል፡፡ አሁን እንዲህ ያሉ አስተሳሰቦች እንዲበራከቱ ነው እኛም የምንሠራው፡፡
በፌደራሊዝሙና በብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ጉዳይ አቋማችሁ ምንድን ነው?
እኛ በምንም መመዘኛ የመገንጠል ጥያቄን አንደግፍም፡፡ ፌደራሊዝሙ ግን ከአለም ተሞክሮም አንፃር የተጠና መሆን አለበት። ፌደራሊዝም ጠንካራ ስርአት መፍጠር የሚያስችል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲተገበር ግን አንድን ብሔር ከሌላው ጋር እንዲጠራጠር፣ እንዲጋጭ በሚያደርግ የከፋፍለህ ግዛው አይነት ነው፡፡ ይሄ ለአገዛዝ እንዲመች የተደረገ ነው፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ፌደራሊዝም እንዴት ይምጣ የሚለው ምክክር ሊደረግበት ይገባል፡፡
የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሚያ፣ የሌላውም ህዝብ በቋንቋው መናገር፣ ባህሉን የሚያሳድግበት መንገድ ተፈጥሮ እውነተኛው ፌደራሊዝም መተግበር አለበት ነው አቋማችን። የመንግስት ስልቱ ፕሬዚዳንታዊ ነው፡፡ ጽንፍ የሄደ ብሔርተኝነትንም ሆነ ጽንፍ የተረገጠ የአንድነት ንቅናቄን ወደ አማካይ ማምጣትን ታሣቢ አድርገን ነው የምንንቀሳቀሰው። ሁሉም ቦታ ኖሮት፣ ሳይከፋ፣ ሀገሩን እንዲወድ የሚያደርግን ስርአት ነው እውን ማድረግ ያለብን፡፡ እኛ እንደ ፓርቲ፣ እንድንፈጠር ያደረገን ይሄ ነው፡፡
አንድነቱንም ብዝሃነቱንም በእኩል ደረጃ እንፈልገዋለን፡፡ ይህ እውን እንዲሆንም እንታገላለን። መሀከለኛ ፖለቲካን ማለማመድ አለብን፡፡ ብሔር እና አንድነት የሚሉት፣ ሁለቱም ጋ ጥሩ ነገር አለ፡፡ ከሁለቱም የሚወሰድ አማካይ ነገር ደግሞ የበለጠ ለሀገራችን ፈውስ ይሆናል፡፡
“ፓርቲዎች ተሰባሰቡ” እየባበለ … እናንተ ተጨማሪ ፓርቲ መፍጠራችሁ ትችት አያስነሳም?
በመርህ ደረጃ መሠባሰብ አብሮ መስራት ተገቢ ነው፡፡ ይሄ መሆን ያለበት ግን ራሱን በቻለ ሂደት ነው፡፡ ሲሮጡ የታጠቁት አካሄድ፣ ህዝባችንን ያሰለቸ ነው፡፡ መንግስት “ተሰብሰቡና ልርዳችሁ” ስላለም መሠብሰብ አያስፈልልም። መንግስት ገንዘብ ይሠጠኛል ብሎ መሰብሰብ የትም አያደርስም። ሌሎች ሀገሮችም እኮ በርካታ ፓርቲ ነው፤ ያላቸው። ለምሣሌ አሜሪካ ሁላችንም የምናውቀው ሪፐብሊካኖችንና ዲሞክራቶችን ነው ነገር ግን ከ90 በላይ ፓርቲዎች ናቸው ያሉት፡፡ በሌላውም ሀገር እንደዚያው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደገሞ ብዙሃነት አገር ስለሆነች በርካቶች በፈለጉት መንገድ ቢደራጁ የሚደንቅ መሆን የለበትም፡፡ በሌላ በኩል ባለፉት 27 አመታት ዝም በለው ለቁጥር ማሟላት የውሸት ፓርቲዎች ጭምር ሲቋቋሙ ነበር፡፡ አሁን ግን እውነተኛ ፓርቲዎችን ማቋቋም የሚቻልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ዋናው ፓርቲዎች ይዘውት የሚነሱት ሃሳብ ነው፡፡ ሃሳብ በመድረኩ ቀርቦ አሸናፊ የሆነው ነጥሮ ይወጣል። ስለዚህ ሰዎች አሁንም በፈለጉት መንገድ ይደራጁ በኋላ ብዙሃኑ የተቀበሉት ሃሳብ ገዥ ይሆናል። ሌላው በወንፊት እየተንገዋለለ ወደ ኋላ ይቀራል፡፡ ይከስማል፡፡ እኛ ሀገር ገና ብዙ አይነት አደረጃጀቶች መፈጠር አለባቸው፡፡ አሜሪካ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የሲቪክ ተቋማት አሉ፡፡ በኛ ሀገር ግን በመቶዎች ናቸው፡፡
አዲስ ፓርቲ ከመመስረት ለምን ሃሳባችሁን ከሚገራ የተቋቋመ ድርጅት ጋር አትጣመሩም ነበር ነው ጥያቄው?
ይሄ ተገቢ ጥያቄ አይደለም፡፡ አዲስ ሃሳብ አለን የምንል ሰዎች ለምን? አንደራጅም፡፡ ለምን ሃሳባችንን ሌሎች ይቀበላሉ አይቀበሉም ማለት አስፈለገ? ፓርቲ ማቋቋም እዚህ ሀገር ላይ እንደ ነውር መታየት የለበትም፡፡ የተቋቋመው ፓርቲ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ? የሚለው ነው መጠየቅ ያለበት፡፡ ያመጣው ሃሳብ ገዥ ከሆነ መደገፍ ይቻላል፡፡ ካልሆነ መተው፡፡ ይሄ ነው ተፈጥሮአዊ ሂደቱ፡፡ እውነተኛ አላማ ያለው፣ በህዝብ የተመረጡ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ሌላው በራሱ ጊዜ ይከስማል፡፡ አብሮ የመስራት ቅንጅት፣ ግንባር፣ ውህደት ግን በሂደት የሚመጣ  ነው እንጂ በአንድ ሰሞን ሆያ ሆዬ የሚሆን አይደለም፡፡ ተሰብሰቡ ስለተባለ መሰብሰብ መርህ አልባነት ነው፡፡
ፓርቲያችሁ ኢትዮጵያውያን እንዴት ነው የሚረዳት? ለሀገሪቱ ያላችሁ አላማስ ምንድን ነው?
ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ነች፡፡ የነፃነት ምድር ነች፡፡ በሌላ መልኩ ስናይ ደግሞ ደሃ ነን። እኛ ትልቅና ገናና ሀገር እንድትሆን እንፈልጋለን፡፡ እርጥ ነው እስከ ዛሬ በታሪካችን አልተስማማንም፡፡ ሁላችንንም ያግባባ ጀግና የለንም፡፡ ከዚህ አንፃር ጥሩ ታሪኮችን እንቀበል መጥፎ ታሪኮችን እንማርባቸው የሚል አቋም ነው ያለን፡፡ ባለፈ ታሪክ መቆዘም አይገባም የሚል ጽኑ እምነት አለን፡፡
ስለዚህ “እኛ አፄ እገሌ በድሎናል” ከሚል ወጥተን፣ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ምንድን ነች? ከ25 አመት በኋላ ምን ትሁን የሚለው ላይ እናተኩራለን። የወደፊቱን ተመልካች ፓርቲ ነው የመሠረትነው። ከ25 አመት በኋላ ከአፍሪካ ስንተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ነው የምንገነባው? ስንት ሰው ከድህነት እናወጣለን? የሚለው ላይ ነው ትኩረታችን፡፡ ያለፈ በደልን እየቆጠሩ መቆዘም የትም አያሻግረንም። ሩዋንዳ በዚህ ጥሩ ምሣሌ ነች፡፡ ሁቱም ቱትሲ የተጨፈጨፉት በቅርቡ ነው ግን ከዚያ ቁዘማ ወጥተው ዛሬ ታሪኩን እንደ መማሪያ እንጂ እንደ መበቀያ አያዩም። የወደፊታቸውን አሻግረው ነው የሚያዩት፡፡ ከብሶትና ቁዘማ ወጥተዋል፡፡ እኛም እንደዚህ ነው የምናስበው፡፡   


Read 1993 times