Saturday, 30 March 2019 13:19

“አርበኞች ግንቦት 7” በባህርዳር የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ነፍጥ ይዘው የወጡ ለህግ እንዲቀርቡ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)


               በባህርዳር በጦር መሳሪያ በመታገዝ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፉ አካላት በአስቸኳይ ለህግ እንዲቀርቡ “አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ” ያሳሰበ ሲሆን ድርጊቱ በዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው ብሏል፡፡
ንቅናቄው ባለፈው እሁድ መጋቢት 15 ሊያካሂደው የነበረው የአዳራሽ ስብሰባን በሚቃወም ሰልፍ ላይ የጦር መሳሪያ ታጥቀው በተቃውሞ የተሳተፉ አካላትን ያነሳሱና ድርጊቱን የደገፉ በሙሉ በአፋጣኝ ለህግ እንዲቀርቡ ባወጣው መግለጫው ጠይቋል፡፡
“የዲሞክራሲ ስርአት ምስረታ ጥረታችን በአመፀኞችና በዕብሪተኞች ድርጊት አይገታም” ያለው ንቅናቄው፤ በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ውስጥ የሚታየው ሁኔታ በምንም ዓይነት መንገድ ነፍጥ አንግቦ ህገ ወጥ አመፅን አማራጭ ለማድረግ የሚያስገድድ አይደለም” ብሏል፡፡
ንቅናቄው በባህርዳር  ያዘጋጀው ህዝባዊ ስብሰባ እንዳይካሄድና ህዝብ ሀሳቡን በነፃ እንዳይገልፅ መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች የወሰዱት ፈፅሞ ፀረ ሰላም የሆነ እርምጃ ሀገርን ለማረጋጋትና ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያለፈ ነው ብሏል  - በመግለጫው፡፡ ድርጊቱም በአንድ አካል ላይ የተቃጣ ጥቃት ብቻ ሳይሆን ለዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ በሚታገሉ ኃይሎች ሁሉ ላይ ነው ብሏል፡፡  
የፌደራልና የክልል መንግስታት፣ ሀገራዊ ፓርቲዎችና ዜጎች የታየውን በነፍጥ የተደገፈ የአደባባይ እንቅስቃሴ ገና በጥሬው ማስቆምና ድርጊቱን ማውገዝ ይገባቸዋል ያለው ንቅናቄው፤ ድርጊቱን የፈፀሙና እንዲፈፀም ያገዙ ግለሰቦች ለህግ እንዲቀርቡ የሚደረገውን ጥረት ሁሉም እንዲያግዝ ጥሪ አቅርቧል፡፡
አጥፊዎቹ በህግ እስኪጠየቁ ድረስ ጉዳዩን በቸልታ አንመለከተውም ያለው ንቅናቄው፤ መንግስትም አጥፊዎችን ለህግ አቅርቦ ህግና ስርአት እንዲያስከብርና ውጤቱን ለህዝብ እንዲያሳውቅ ጠይቋል፡፡

Read 7565 times