Saturday, 30 March 2019 13:16

እዛም ቤት እሳት አለ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የንጉሥ ሰለሞን አጫዋች ነበረ፡፡ በየቀኑ ንጉሡን የማጫወት ተግባራትን ያከናውናል፡፡ አንድ ቀን እንደተለመደው ንጉሡን እያጫወተ ሳለ መልዐከ - ሞት መጥቶ ትኩር ብሎ ሲያየው ተመለከተና በጣም ደነገጠ፡፡ ከዚያም ወደ ንጉሥ ሰለሞን ሄደ፡-
“ንጉሥ ሆይ!
እኔ እርስዎን ለማዝናናት ቀን ከሌት እየጣርኩ ሳለ፤ መልዐከ - ሞት መጥቶ ትኩር ብሎ አይቶኝ ሄደ፡፡ ንጉሥ ሆይ ያድኑኝ” አለና ተማጠናቸው፡፡
ንጉሡም፤
“አይዞህ፡፡ እኔ መልዐከ - ሞትን በፀሎት እስከማገኘው፤ ለጊዜው ራቅ ወዳለ ቦታ ወደ ህንድ እልክሃለሁ፤ ከዚያ መልዐከ - ሞትን ካነጋገርኩት በኋላ ትመለሳለህ፡፡”
“አመሰግናለሁ ንጉሥ ሆይ!” ብሎ እጅ ነስቶ ወጣ፡፡ ንጉሡ ፀሎታቸውን ተያያዙት፡፡ ከቀናት በኋላ መልዐከ ሞት ተገለጠላቸው፡፡
“መልዐክ ሆይ! ምን አድርጌ ነው አገልጋዬንና አጫዋቼን ልትወስድብኝ የመጣኸው?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
መልዐከ ሞትም፤
“አይ ገርሞኝ ነው፡፡ እኔ አምጣው የተባልኩት ከህንድ፣ እሱ እዚህ ምን ያደርጋል ብዬ ነው ትኩር ብዬ ያየሁት” አለ፡፡
*   *   *
ይህች አገራችን የአህያ ሥጋ አልጋ ሲሉት አመድ የሚባለውን ዓይነት ናት፡፡
ወይም ፀጋዬ ገ/መድህን እንደሚለን “ኢትዮጵያ ትወልዳለች እንጂ አታሳድግም! ለነገሩ አቅሙም የላትም፡፡ የሶስት ሺ ዘመን ታሪክ እንጂ የቅርብ ጊዜ የድል ትርክት የላትም፡፡ ትተረክልናለች እንጂ አልኖርንባትም፡፡ አላደግንባትም፡፡ የረባ ትምህርት አልተማርንባትም፡፡ የረባ ጤና አላገኘንባትም፡፡ ባጠቃላይ ተወለድን እንጂ አላደግንባትም፡፡ ያም ሆኖ አንጠላትም - እናታችን ናታ! ገና እንታገልላታለን! ገና እንሞትላታለን፡፡ ገና ድል እናደርግላታለን፡፡
ከድህነት አረንቋ ትወጣም ዘንድ እስከመጨረሻው እንፍረመረምላታለን፡፡ እንጮህላታለን፡፡ እንዘምርላታለን፡፡ እንሟገትላታለን፡፡ ማሰብ እስከምንችለው ጥግ ድረስ እናስብላታለን፡፡
እኛ፣
“When Rome was burning Nero was dancing”
ሮማ እንደነደደች ኔሮ እየደነሰ ነበር - የምትባል ዓይነት እናት አገር ያለን ህዝቦች አይደለንም፡፡ ብትፈርስ ከፍርስራሿ ውስጥ ህንፃ እናበቅላለን እንጂ ዳር ቆመን የምናለቅስ አንሆንም! እናውቃለን፤ ብንናገር እናልቃለን ሳይሆን፤ እናውቃለን ባንናገር እናልቃለን የምንል ነን!
የመጪውን ዘመን ምርጫ “እኔና እኔ ብቻ” ሳንል፤ መሸነፋችንንም በፀጋ ተቀብለን፣ ተጨባብጠን የምንለያይበት ያደርግልን ዘንድ ትምህርታችንን ይግለጥልን! ከሁሉም በላይ ደግሞ እዛም ቤት እሳት አለ የሚባል ልቦና ይስጠን!!

Read 10215 times