Saturday, 23 March 2019 15:06

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)

 “ይቅርታ የነፍስ የሚሆነው ከበደል በላይ ኃይል ሲኖረው ነው”
                   
            “ለበጎ ነው፣ ሳይይዝ አይጣላም፣ እግዜር ምክንያት አለው” እንደምንለው፤ “The bad sometimes brings about the good” ይለናል፤ ታላቁ ሾፐን ሃወር፡፡
አንድ ምሽት ሁለት ሰዎች መሸታ ቤት ተጣሉ። አንደኛው በአካባቢው ይታወቃል፤ሌላኛው እንግዳ ቢጤ ነው፡፡ ኮማሪቷና ሌሎች ደንበኞች፣ ለሚያውቁት ሰው በማገዝ፣ እንግዳውን “አፍ አፉን” አሉት፡፡ “አንተ ነህ እሱን የምትናገር? … ማን እንደሆነ ዐውቀሃል?” እያሉ አብጠለጠሉት። ሊደበድቡትም ተጋበዙ፡፡ እንግዳው ያስቀዳውን መጠጥ ሳያጋምስ፣ ሂሳቡን ከፍሎ ውልቅ አለ፡፡ “ፈሪ? ቦቅቧቃ! ወዘተ--” እያሉ በፀያፍ ስድብ ሸኙት። … “ከጳጳሱ ቄሱ --” ሆነው ያገዙለት ሰውዬ ግን ውስጡን አልተመቸውም፡፡ እንግዳውን ተከትሎ ሄዶ፣ ይቅርታ ቢጠይቀው በወደደ ነበር፡፡ … ጥፋቱ የራሱ በመሆኑ፡፡
ይህ በሆነ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ግን እንግዳው ሰው፣ ጥርሱን እንደነከሰ በድንገት ከቤቱ ዘው አለበት፡፡
“ፈሪ እንዳልሆንኩኝ ላሳይህ ነው” በማለት መሳሪያውን መዘዘ፡፡
 እሱም አጋጣሚውን ቀድሞ ያወቀ ይመስል ሳይደናገጥ …
“ባልተዘጋጀሁበት ጊዜ መሆኑ እንጂ ምንም ችግር የለም” አለው፡፡
“እንግዲያውስ ተመልሼ እመጣለሁ” ብሎት ፊቱን አዞረ እንግዳው፡፡
በዝግታ እየተራመደ ሲሄድ፣ አንዴም እንኳ ዞር ብሎ አልተመለከተም-“Death postponed” እንደሚሉት!!
ሰውየው አንዳንድ ሰዎች ለክብራቸው የሚከፍሉትን ያውቅ ነበርና፣ ስለ ደንበኛው ባህሪና ሰፈር ለማወቅ ጊዜ አልፈጀም። በተራውም  ትጥቁን አዘጋጅቶ ብቻውን በሆነበት ሰዓት አሸምቆ ደረሰበት።
ጠበኛውም … “ሳይቀድመኝ ልቅደመው ብለህ ነው?”  
ሰውየው…  “የሞት ቀጠሮ ይዞ ቁጭ ብሎ የሚጠብቅ ማን አለ?”  
“እንግዲያውስ ትንሽ ታገሰኝ ልዘጋጅ”
“ደግ” … አለና ሰውየው በዓይነ ቁራኛ ይከተለው ጀመር፡፡ ደንበኛውም ‹የጀግና ሞት› ሊሞት ሰውነቱን ተለቃልቆ የክት ልብሱን ከለበሰ በኋላ … “ተኩስ!” ለማለት ዞር ሲል ባለብረቱ ድንገት አስነጠሰው፡፡ ደንበኛውም አፍታ በማትሞላው በዚያች ቅጽበት፣ በደመነፍስ ዘሎ ሰውየውን ገፍትሮ መሳሪያውን ነጠቀ፡፡ ፈንጠር ብሎም ምላጩን ሳበ፡፡ … ምንም የለም፡፡ እንደገና አቀባብሎ ቃታ ሳበ፡፡ … ምንም። ትንሽ ወደ ኋላ በማፈግፈግ፣ ካርታውን አውጥቶ ቢመለከት ባዶ ነው፡፡ … የጎረሰም ጥይት የለም፡፡ … ደነገጠ፡፡ … ከዚያስ?
***
 አፍሪካዊ ሚቲዮሎጂ እንደሚተርከው፡- ደቡብ አፍሪካ አካባቢ የሚኖሩ የዙሉና የማሳይ ጎሳዎች፤ በህይወት የሌሉ የአያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸው መንፈስ ወይም ነፍስ በየአካባቢያቸው ባሉ እንስሳትና ዕፅዋት ውስጥ ሰፍረው ከነሱ ጋር እንደሚኖሩ፣ በችግራቸው ጊዜም በአስማተኞቻቸው በኩል እንደሚያነጋግሯቸውና ምክር እንደሚለግሷቸው ያምኑ ነበር፡፡ እነኚሁ ጎሳዎች፤ ሞት ወደ ሰው ልጆች የመጣው በአንዲት እንስሳ ስንፍናና ንዝህላልነት እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ይኸውም፡-
እንደ ቡድሃና ኢየሱስ ታላቅ የነበረው (supreme being) አምላካቸው ‹እንኩሉንኩሉ›፤ “ሰው መሞት አለበት” የሚል መልዕክት ለእንሽላሊት፣ “ሰው ሞት አይገባውም” የሚል ደግሞ ለእስስት አስይዞ በተለያየ አቅጣጫ ወደ ሰው ልጆች ላካቸው ይባላል፡፡ እስስቷ መንገድ ላይ ስትሰናከል፣ እንሽላሊቷ መልዕክቱን በማድረሷ ሞት የሰዎች ዕጣ ሆነ ይላሉ፡፡ በነገራችን ላይ “እንኩሉንኩሉ”፣ ኢትዮጵያዊ አምላክ እንደነበር ‹ፕሬስተር ጆን› በተባለው ልብወለድ መጽሐፍ ይጠቀሳል፡፡
ወዳጄ፡- ሞት፣ ይቅርታ፣ ምህረትና ቅጣት በቀጥታም ሆነ በአግድሞሽ መገናኘታቸው አይቀርም፡፡ የኦ‘ሔንሪን ‘ሳንታ ክላውስ‘ እና የፑሽኪንን ‹ዘ ሾት› ጨምሮ ብዙ የይቅርታና የምህረት ታሪኮች ተፅፈዋል፡፡ ያልተፃፉና ያልተነገሩ ኢ-ልቦለድ ታሪኮች ግን ብዙ ናቸው፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት አንዲት አሜሪካዊት ህግ ፊት ስለቆመው የባሏ ጉዳይ ስትናገር፡- “ባለቤቴ አንዴ ሞቷል፣ በኔ በኩል ይኼ ሰውዬ እንዲታሰር አልፈልግም፡፡ ነገር ግን ልጆቼ ከአባታቸው ሲያገኙት የነበረውን ፍቅር እንዲሰጣቸው ቃል ይግባ” ስትል ተናግራ ነበር፡፡
ማህተመ ጋንዲ የሰደበውንና የተፋበትን ሰው፤ “ማንም እንዳይነካው፣ ፈጣሪ ልቦና እንዲሰጠው እፀልይለታለሁ” ማለቱ ይነገራል። ፖፕ ዮሐንስ ሦስተኛም፣ ሊገድላቸው የተኮሰውን ሰው “ይቅርታ አድርጌልሃለሁ” ብለው ባርከውታል፡፡ ገፈው፣ አዋርደው፣ በጦር ወግተው እየተሳለቁ የሰቀሉትን “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ሲል አባቱን የተማፀነው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጥያቄው፤ “አንተስ ወዳጄ፤ ለይቅርታ ዝግጁ ነህ?” የሚል ነው፡፡
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- “ምን የሚሉት ቀልድ ነው?” አለ የሰውየው ጠበኛ… ባዶውን መሳሪያ እያገላበጠ፡፡
“የመጣሁት ይቅር እንድትለኝ ነው” አለ ሰውየው፤ በኪሱ ያጨቀውን ጥይት ዘግኖ ለጠበኛው እያቀበለ። ባለጋራውም … ሲያስብ ከቆየ በኋላ …
“በኔ በኩልማ ገድዬሃለሁ፣ ምኑን ይቅር ልበልህ?” አለው …
“ይቅርታ የነፍስ የሚሆነው ከበደል በላይ ኃይል ሲኖረው ነው” አለ ሰውየው… እቅፍ እያደረገው፡፡
አንገቱን እየነካካም .. “ይልቅ እየቆረቆረኝ ከሚቀር ይኸ ጠባሳ ምን ሆነህ ነው?” ሲል ጠየቀው፤ ጠበኛውን፡፡
“ህፃን እያለሁ ከ‘ሳት ላይ ወድቄ”
“የት አገር?”
ነገረው፡፡
“እናትህ አለች?”
“እዛው እድርቁ ቦታ ነው የሞተችው”
“ወንድሞችና እህቶችስ?”
“ታላቅ ወንድሜ ነበር … መንግስት ከሰፋሪዎች ጋር ሲወስደው ትዝ ይለኛል፣ ከአደጋው በኋላ አፈላልጌ አላገኘሁትም፡፡ አለም የለም የሚለኝ ጠፋ።”
“ማ … ይባላል?”
“እገሌ”
“ብታየው ታውቀዋለህ?” …
 እንባውን አወረደው፡፡
“እ…?” ማለት ብቻ ነበር የቻለው… ታናሹ፡፡
ወዳጄ፤ “I saw it, because I looked” ያለው ማን ነበር? እ …? ሻርሎክ ሆልምስ አልከኝ? … ልክ ነህ!!
ሰላም!!!    

Read 1438 times