Print this page
Saturday, 23 March 2019 14:40

ሲንጋፖር፣ ሆንግ ኮንግና ፓሪስ በከተሞች ዋጋ ውድነት አለምን ይመራሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 - ፊንላንድ ዘንድሮም የአለማችን እጅግ ደስተኛዋ አገር ናት ተብሏል
         - ኢትዮጵያ በደስተኛነት ከ156 የአለማችን አገራት 134ኛ ደረጃን ይዛለች


         ዘ ኢኮኖሚስት ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የ2018 የፈረንጆች አመት የአለማችን ከተሞች የዋጋ ውድነት ደረጃ ሲንጋፖር፣ ሆንግ ኮንግ እና ፓሪስ እጅግ ውድ ከተሞች በመሆን በእኩል የአንደኛ ደረጃን መያዛቸው ተዘግቧል፡፡
ዘ ኢኮኖሚስት በ133 የአለማችን ከተሞች ውስጥ የ160 አይነት ሸቀጦችን ዋጋ በማጥናት የሰራውን ግምገማ መሰረት አድርጎ ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳለው፣ ላለፉት አራት ተከታታይ አመታት በአንደኛነት ደረጃ ላይ የዘለቀችው ሲንጋፖር፣ ዘንድሮም ቀዳሚነቷን ከሆንግ ኮንግና ከፓሪስ ጋር ተጋርታለች፡፡
ዙሪክ፣ ጄኔቫ፣ ኦሳካ፣ ሴኡል፣ ኮፐንሃገን፣ ኒው ዮርክ፣ ቴል አቪቭ እና ሎሳንጀለስ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ደረጃን የያዙ የአለማችን ውድ ከተሞች ሆነዋል፡፡ የቬንዙዌላዋ ካራካስ እጅግ አነስተኛ የዋጋ ውድነት ያላት የመጀመሪያዋ የአለማችን ከተማ ናት ያለው ሪፖርቱ፣ የሶርያዋ ደማስቆና የኡዝቤኪስታኗ ታሽኬንት ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው እንደሚከተሏት አመልክቷል፡፡
በአነስተኛ የዋጋ ውድነት የካዛኪስታኗ አልማቲ፣ የህንዷ ባንጋሎር፣ የፓኪስታኗ ካራቺ፣ የናይጀሪያዋ ሌጎስ፣ የአርጀንቲናዋ ቦነስ አይረስ፣ የህንዷ ቼናይ እና ሌላኛዋ የህንድ ከተማ ኒው ዴልሂ በቅደም ተከተላቸው እስከ አስረኛ ያለውን ስፍራ ይዘዋል፡፡ ዘ ኢኮኖሚስት የከተሞችን የዋጋ ውድነት ደረጃ ለማውጣት ከተጠቀመባቸው መገምገሚያ መስፈርቶች መካከል የምግብና የመጠጥ ዋጋ፣ የመኪኖች ዋጋ፣ የህክምና አገልግሎቶች ዋጋ ይገኙበታል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ የአመቱ የአለማችን አገራት የደስተኛነት ደረጃ ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ፊንላንድ ዘንድሮም በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት መፍትሄዎች ኔትወርክ ለ7ኛ ጊዜ ይፋ ባደረገው የዘንድሮው የአለማችን አገራት የደስተኛነት ደረጃ፣ ዴንማርክ በሁለተኛነት ስትቀመጥ ኖርዌይ ትከተላለች፡፡
156 የተለያዩ የአለማችን አገራትን ባካተተው የዘንድሮው የአገራት የደስተኝነት ደረጃ ዝርዝር አይስላንድ፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ኒው ዚላንድ፣ ካናዳና ኦስትሪያ በቅደም ተከተላቸው እስከ አስረኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን ኢትዮጵያ በ134ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ በአመቱ ከአለማችን አገራት እጅግ ደስታ የራቃት አገር ደቡብ ሱዳን እንደሆነች የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ አፍጋኒስታን፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ የመን፣ ማላዊ፣ ሶርያ፣ ቦትሱዋና እና ሃይቲ በቅደም ተከተላቸው እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ተቋሙ የአለማችንን አገራት የደስተኛነት ደረጃ ለመገምገም ከተጠቀመባቸው መስፈርቶች መካከል የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ፣ አማካይ ዕድሜ፣ የህይወት ምርጫን የማድረግ ነጻነት፣ ለመንግስት ሙስና ያለው አመለካከት ወዘተ ይገኙበታል፡፡

Read 1221 times
Administrator

Latest from Administrator