Saturday, 23 March 2019 14:20

ኦነግና የዐቢይ መንግስት

Written by  በአክሊሉ ገብረመድህን aklilu@qellem.com
Rate this item
(10 votes)

 በሰኔ 16ቱ ሰልፍ ለመታደም የወጣነው አምስት ወጣቶች  የሰዓሊ፥ ገጣሚ፥ የፊልም ሰሪ፥ የፎቶ ግራፈር ባለሙያዎች ስብስብ ብቻ ሳንሆን የተለያዩ “ብሄሮች” ስብጥር ነበርን። የፍቅርና የአንድነት  መንፈስ ፍርሃታችንን አስጥሎ ለሁላችንም የመጀመሪያችን የሆነውን ሰላማዊ ሰልፍ በአንድነት  ባንዲራ አስለብሶ መስቀል አደባባይ ከተመመው ህዝብ ጋር ቀላቀለን።  ይህ እጅግ ውብ የኢትዮጵያዊነት ስሜት የተንፀባረቀበት ልዩ ሰላማዊ ሰልፍ ከተካሄደበት ቀን አንስቶ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብን ጩኸት የመለሱ ብዙ አበይት ክንዋኔዎች ከግብ አድርሷል። የኢትዮ ኤርትራ ዕርቅ፥ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት፥ የመናገርና የመፃፍ ነፃነት መከበር እንዲሁም የኢኮኖሚ አውድ መረጋጋቱ አበይት ትሩፋቶቹ ናቸው። እነዚህን “በረከቶች” ጨምሮ ሌሎች መልካም ጅማሮች በለውጥ ሃይሉ ፍቃደኛነት [ችሮታ] የተገኙ እንጂ እኔም ሆንኩ አራቱ ወዳጆቼ ከጠጠር በላይ ያዋጣንባቸው የላባችን ውጤቶች አይደሉም።
የስድስት አመቱ ልጅ ታሪክ
አንድ የስድስት አመት ህፃን ልጅ ጥርሱ ይነቃነቅበትና ለእናቱ ያሳያታል። እናት መውለቂያው መድረሱን  ትረዳና ልትነቅል እጇን ስትሰድ ልጅ አላስነካም ይላል። ወንድሞቹ በእየተራ እየመጡ “ና ልንቀልልህ” ይሉት ጀመር፤ ልጅ ጥርጣሬው አላስወስን አለው። አንደኛው ወንድሙ፤ “ፈሪ ለዚች እንዲህ ትንሰፈስፋለህ” እየለ አሽሟጠጠው። ሌላኛው የራሱን የተደረበ ጥርስ እያሳየ “ነገ እንደኔ ሌላ ጥርስ ይደረብብህና የጓደኞችህ መሳለቂያ ትሆናለህ፤ ና ልንቀልልህ እያለ ለማግባባት ሞከረ፡፡ ልጅ ነገ በምኔ እበላለሁ ብሎ  የሚቀመስ አልሆነም። ሶስተኛው ከረሜላና ጣፋጮች  እንደመደለያ አቀረቦ ነገ ይበቅልልሃል ቢለው ልጁ ወይ ፍንክች አለ።
ጭራሽ ተጠቅቻለሁ ብሎ እዬዬውን አስነካው። የልጇ ጭንቀትና ፍርሃት የገባት እናት፤ ልጇን ማባበል ጀመረች፡፡ ይሄኔ ወንድሞቹ በዚህ መንገድ ያላለፉ ይመስል “ለምን አትቆጭውም!  ለምን ታሞላቅቂዋለሽ! ከአሁኑ ስርዓት መያዝ አለበት” እያሉ እናታቸውን ይወቅሷት ገቡ።
እናት ጥቂት አስባ ሌሎቹን ልጆቿን ተቆጥታ መላ ዘየድች። ክር አመጣችና እንደማትነቅልበት  ቃል ገብታ፣ የተነቃነቀችው ጥርሱ ላይ አስራ “በል ሂድና ከልጆቹ ጋር ተጫወት ብላ” ለቀቀችው።
 ልጅ ጊዜ ያለፈበት ጥርሱን ይዞ  ከጓደኞቹ ጋር ጫወታ ውስጥ ጥልቅ አለ። ጥቂት እንደ ተጫወቱ ክሯ ግራ ያጋባችው አንድ ጓደኛው ድንገት መጥቶ ክሯን ሳባት። ክሯ የልጁን ጥርስ  ነቅላ እጁ ላይ ቀረች። እንደፈራው ህመም ስቃይም ያልተሰማው ልጅ፤ ከጓደኛው ጥርሱን ከነክሩ ተቀብሎ ግዳይ እንደጣለ ጀግና ሲገሰግስ እናቱ ጋር መጣ። እናት ፈገግ ብላ፤ “እህስ?” ልጅ “ምንም አላመመኝም፤ ምን ላድርጋት ?” አለ፤ እጁ ላይ ያለውን ጥርስ ለእናቱ እያሳየ። እናት “ወፌ ወፌ የአንቺን ጥርስ ለኔ፣ የኔን ጥርስ ወደ አንቺ” በልና አርቀህ ወርውራት አለችው። ልጅ ጥርሱን እንደተባለው ወፌ ወፌ ብሎ አርቆ ወረወረ። የዚህ ጊዜ ያለፈበት ጥርስ  ጉዳይ ድጋሚ እዛች ቤት አልተነሳም።  ይህ የእናትና የልጅ ሁኔታ  አሁን ያለውን የአገራችንን  ሁኔታ ለማስረዳት የሚያገለግል ጥሩ ምሳሌ ነው።   
እናት አገራችን፥  መንግስት እናታችን
 “የመንግስት ግብ የአንድ አገር ህዝብ ድህንነቱና ደስታው ተጠብቆ እንዲኖር ማመቻቸት ነው።  መንግስት የሚያስፈልገው የገዢዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሳይሆን የህዝብን ፍላጎት ለማሟላት ነው።”
ከላይ ቶማስ ጃፈርሰን ለመንግስት የሰጠውን ትርጉም በዕለት ተዕለት የሰው ልጆች እንቅስቃሴ መሬት ወርዶ እምናየው፣ በእናትና በልጅ ግንኙነት ውስጥ ነው። ወደ እናትነት የተሸጋገርች ሴት፤ ዋንኛ ስራዋ  የልጇን ደስታና ደህንነት ማስጠበቅ ነው። ልጇን መንከባከብና ሊያጋጥሙት ከሚችሉት ማንኛውም አደጋዎች መከላከል ተፈጥሮ የቸራት [የጣለባት] የህይወት ዘመን ግቧ ነው። እኛም እንደ አገር ከዚህ የወል ምክኒያት ማምለጥ ቢያቅተን ነው አገራችንን “እናታች” እንላት የነበረው።
ሚሼል ፓፓቲክስ፤ በግለ ታሪኩ መፅሃፍ ላይ ኢትዮጵያ በ1950 ዎቹ ስለነበራት መልክ እንዲህ ብሎ ነበር፤ “ኢትዮጵያኖች በአገራቸው ኩሩና ደስተኛ ስለሆኑ በጊዜው ለኢትዮጵያ የተሰጠውን ኮታ አልተጠቀሙበትም። ነገር ግን አሜሪካ መሄድ የሚፈልጉ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች ፥ እንደ ግሪኮች፤ አርመኖች ፥ ጣልያኖች ሌሎችም በዕድሉ ለመጠቀም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የኢትዮጵያን ዜግነት በመውሰድ “ፓስፖርት” ለማግኘት በተለያየ ዘዴ ይጣጣሩ ነበር። የኢትዮጵያ ዜግነት ከተሰጣቸው በኋላ አሜሪካን ገብቶ ለመኖር ይፈቀድላቸው ስለ ነበር ነው። በጊዜው የነበሩት ኢትዮጵያዊያን ስደትን እንደ ከፍተኛ ውርደት ይቁጥሩት ንበር።”
ይህን ያነበበ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ፤ ጉዳዩ የማይቀመስ አፈታሪክ ቢሆንበት አይደንቅም። ምክኒያቱም እሱ የደረሰችው እናት ሞት ስደት አይደለም ሞት እምታስመርጥ ነበረችና።
በየጊዜው የሚነሳው የመንግስት አስተዳደር፣ ይህን የእናትነት ስምና ግብር ይዞ የልጆቿን ደስታና ደህንነት ለማስጠበቅ ሃላፊነት ይገባል። በፍቅርና በስርዓት የተንከባከበ ጊዜ ልጆቿ  መልካምና ብርቱ ይሆናሉ። በዱላና በጥላቻ የተነሳ ጊዜ ደግሞ ወሮበላና የተናቁ ፤  ቢሰሩ አክሳሪ ቢያወሩ አሳፍሪ፣ በእየሄዱበት መጡብን እንጂ መጡልን የማይባሉ ነውረኞች ይሆናሉ። በሂደት እናት [መንግስት]፤ በልጆቿ ታፍራለች፤ ልጇች እናታቸውን [አገራቸውን] ይጠላሉ።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የዐቢይ መንግስት ላለፉት አስራ ምናምን ወራቶች እንደ ወላጅ እናት [የልጇቹን ደስታና ደህንነት ለማስጠበቅ] እስረኛ ሲፈታ፣ ስደተኛ ሲያስመልስ፣ ኢኮኖሚ ሲገነባ የፖለቲካ ምህዳሩን ሲያሰፋና ጠንካራ አገራዊ ተቋማትን ለመፍጠር ሲታትር ቢቆይም፣ በቅርቡ በአዲስ አበባና በድሬድዋ የተፈጠረው ሁኔታ ግን እናትነቱን የሚያጠራጥር ተግዳሮት ከፊቱ ደቅኖበታል። በዚህ በኩል ኢትዮጵያዊነት ላይ የሚያሴር ተንኮለኛ፣ በዚያ በኩል የኦሮሞን ጥቅም የሚያሳጣ ከዳተኛ ሲሆን የተቀረው ኢትዮጵያዊ ደግሞ በጥርጣሬ እንዲመለከተው ምክኒያት ፈጥሯል።
ኦሮሚያና የስድስት አመቱ ልጅ
ጥርሴን አላስነካም ያለው የስድስት አመት ልጅ፤ ጥርሱን አላስነካም ሲል ዕውነት አለው።  ጥርሱ አካሉን ሰርስሮ የወጣ አካሉ ነው። አብሮት አድጎል። እንደ ዛሬው ሆን ብሎ አስተውሎት ባያውቅም ሲያገለግለው የነበረ የሰውነት ክፍሉ ነው። ስጋ ነጭቶበት አጥንት ግጦበታል። ወንድሞቹ የሚመክሩት ሃሳብ እንዲገባው የእናቱ አይነት ብልሃት ያስፈልጋል። ቁጣ ስድብና ሃይለኝነት ለሌላ የባሰ ጉዳት አሳልፈው ይሰጡታል እንጂ እነሱ የደረሱበት ዕውቀት ላይ ወስዶ አያስቀምጠውም። ይልቅ ወንድማችው ያለበትን የዕድሜና የአካል ሁኔታ ከግምት ማስገባት ለቤቱ ሰላም ለእናታቸውም መልካም ዜና ነው።
ይህን የስድስት አመት ህፃን ልጅ እንደ ምሳሌ  ወስደን ያየን እንደሆነ፣ ለኦሮሚያችን ጥቂት ይቀርባል። ኦነግ ደግሞ ጊዜ ያለፈበት የልጁን ጥርስ ይመስላል። እኔና  አብዛኛው መሰሎቼ  ደግሞ ወንድሞቹን ስንመስል፣ የዐቢይ መንግስት ደግሞ መከረኛውን የልጆቹን እናት ትመስላለች።
ኦነግ እንደ ልጁ ጥርስ ጊዜ ቢያልፍበትም የቆይታ ዘመኑን ለማርዘም ያለው አማራጭ ሙጥኝ ማለት ነው። የልጁ አፍ ህልውናው  እንደሆነ ያውቃልና። አርቆ እንዳይጣል ልጁን [የኦሮሞን ህዝብ] ማሳመን ብቸኛ አማራጩ ነው። ሲያሻው አካልህ [ስጋህ] ነኝ፣ እያለ ሲያሻው መብያህም መድመቂያህም [መሳቂያህም] ነኝ እየለ፣ በኦሮሞ ህዝብ የማይገፋበትን መንገድ ለማፅናት ይባክናል። እኔና መሰሎቼ ደግሞ  የልጁን የዕድሜና “የአካል”ሁኔታ ከግምት ሳያስገቡ የተለያየ ምክኒያት እየሰጡ  “ና ጥርስህን ልንቀልልህ” እንዳሉት ወንድሞቹ፤ የኦሮሞ ህዝብንና ኦነግን ቁርኝት ሳንረዳ፣ በቅፅበት አውጥቶ ይጥለው ዘንድ የተለያየ “የሞኝ” ድጋፍ ሰጥተን ስናበቃ ወደ እናታችን [ወደ መንግስት] ዞረን ለምን ታሞላቂቂዋለሽ? ለምን አትቆጪውም ? ለምን ስነስርዓት አታስይዢውም እያልን ነው።
ቢቻል በዚህ ሂደት እንዳለፈ ወንድም ልጁ [የኦሮሞ ህዝብ]  እንዳይደነብርና የኦነግ ሰለባ እንዳይሆነን የብልህ ሰው ዘዴ ማምጣት ግዴታችን ነበር። ካልሆነ ግን እናቲቱ [መንግስት] የምታመጣውን መላ ከጎኗ ሆኖ በትዕግስት መጠበቅ የብልህ መንገድ ነው። አንድም ለእናቲቱ [ለአብይ መንግስት] እኛ ልጆቿ እንደሆነው ሁሉ ልጁም  ስጋዋ ነው። ሁለትም በዚህም ሆነ በዚያ መንገድ ጥርሱ በእናት መንገድ ካልተወገደ፣ እሚጎዳው ልጃችን የሚሰቃየው ቤታችን የሚባክነው ሃብታችን መሆኑን ማገናዘብ የተለየ ዕውቀት የሚጠይቅ አይደለም። እናቲቱ ላይ ሌላ ችግር ከሌለብን በስተቀር። እነ መለስ ዜናዊ የተጓዙበት የባሮን ሮማን ፖርቻዝካ መንገድ፣ ፍፁም ለቤቷ እንደማይጠቅም ተረድታ የምትሰራ እናት ስትገኝ እንደ ልጅ ቤቱን ለማቅናት በተቻለው ሁሉ መርዳት እንጂ እንደ መደዴ ጠላት ለማፍራት መታተር፣  ህፃኑ ልጅ [የኦሮሞ ህዝብ] ወፌ ወፌ ብሎ ጥርሱን አርቆ የሚወረውርበትን ጊዜ ከማርዘም ውጪ የሚጨምረው አንድም መልካም ነገር አይኖርም።   
ዘመን ያለፈበት ጥርስ [ኦነግ] ጉዳይ
የዐቢይ መንግስት ወደ ስልጣን እንዲመጣ መንስኤ የሆነው ዋንኛ ምክኒያት የኢትዮጵያ ህዝብ በህውሃት ኢህአዴግ ላይ ያለው ጥላቻ ጫፍ መድረስ ቢሆንም ሌሎች አቀጣጣይ  ግብአቶች አልነበሩትም ማለት አይደለም። ከነዚህ ግብአቶች አንዱ  ኦነግ ነው። ለስድስት አመቱ ልጅ ማደግ ዛሬ የሚነቀለው ጥርስ አስተዋፅኦ እንደነበረው ሁሉ ኦነግም   ለለውጡ የማይካድ ሚና  አበርክቷል። ግን ለውጡ የሱን ጊዜ ያለፈበት ስሪት እንደሚያፈርስ ፍፁም አለጠረጠርም። ይህን ሳይረዳ ጊዜ ሊቀድመው ሆነ።    
በስድስት አመቱ ልጅ ጥርስና በኦነግ መካከል ያለው መመሳሰል ከተሰሩበት ሁኔታ ጋር ዝምድና  አለው።  የልጁ ጥርስ ምን ጠንካራ ቢሆን፣ ምን ቢያምር ስድስት ወይም ሰባተኛውን አመት አይዘልም፡፡  አፈጣጠሩ ዘላለማዊ ይዘት የለውምና። ኦነግም ሆነ ሌላ የጎጠኝነት ስሪት ያላቸው ነፃ የማውጣት አባዜ ስልበኞች   ምን ጉልበት ቢኖራቸው፣ ምን እንደ ጎልያድ ቢፈረጥሙ ቀናቸው ሲደርስና  በእናት ብልሃት ሲታሹ  በጠጠር መውደቅ፣ በክር መነቀል ዕጣ ፋንታቸው ነው። የእኛ የወንድሞቹ ድርሻ መሆን ያለበት በቻልነው አቅም [በፀሎት፥በዕውቀት፥በገንዘብ፥] ከእናታችን ጎን መቆም ብቻ ነው።
“ሃጢያት ያልሰራ  የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውር!”
በኢትዮጵያ ላለፉት 50ና 60 ዓመታት እየተንከባለለ መጥቶ አሁን ጨርቅ ያስጣለን የጨቋኝ ተጨቋኝ፣ የገንጣይ አስገንጣይ ድራማ፤ ከእነ ዋለልኝ ቀድሞ በእነ ባሮን ሮማን ፖርቻዝካ የተዘመረን የፋሽስት ሴራን  ነው በአንድ መንግስት በአንድ አመት ሊያውም በአንድ መዓልት እንዲጠፋ እየጠየቅን ያለነው።  እኔም ሆንኩ አራቱ ወዳጆቼ ከሰኔ 16 እስከ መጋቢት 16 በነበሩት ጊዜያት በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ የህዝብን ንቃተ ህሊና ሊያሰፋ የሚችል ጉምቱ ሃሳብ በሙያችን በማዋጣት የዐቢይን መንግስት አላገዝንም። ዐቢይን ከጎንህ ነን ያልነው ሰኔ 16 ጠዋት ሲሆን ጎንህን ጠብቅ ሳንለው የተለየነው ደግሞ ሰኔ 16 ከሰዓት ነው። ከዚህ ሁሉ የሚያስከፋው እንደ ሌላው ሁሉ እኛም ወግሮ ለመግደል ድንጋያችንን ይዘን ከአጥቂዎቹ ጋር ማሰፍሰፋችን ጭምር ነው።
“ወደ ኋላ ተመልሰን መጀመሪያችንን መቀየር አንችልም። ከዛሬ ተነስተን ግን ፍፃሜያችንን ማስተካከል እንችላለን።” አንጋፋው  የህንድ የፊልም ተዋናይ አሚት አብ ባቻን እንዳለው፤ ወደ ኋላ ተመልሰን የገንጣይ አስገንጣዮችን ውልደት ማጨናገፍ አንችልም። እንደ ልጅ ተቀብለን በምክርና በብልሃት ዱላቸውን ማስጣል ግን ቢከብድም ብቸኛ አማራጫችን ነው።  የጋራ ቤታችን የሆነችው ኢትዮጵያ፤ የህግ የበላይነትን አፅንታ ታፍራና  ተከብራ ትኖር ዘንድ መንግስታችን ተነስቶለት ለነበረው አላማ ይታመን ዘንድ ማስታወስ ማበርታትና ማገዝ የልጅነት [የዜግነት] ግዴታችን ነው።

Read 7838 times