Saturday, 23 March 2019 14:05

የአውሮፕላን አደጋ፣ ሁሌም በረዥም ሀዘን፣ በረዥም ውዝግብና ፈተና የታጀበ ነው።

Written by  ዮሃነስ ሰ
Rate this item
(2 votes)


            1. “የሞተ ተጎዳ” ይባላል። እውነት ነው። ሕይወት ምትክ የላት! “737 ማክስ” አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ መራራ ነው።
• የሟች ሚስት ወይም ባል፣ ወላጆች ወይም ልጆች፣ ወዳጆችና ቤተሰቦች፣... ሃዘናቸው ከመክበዱ መርዘሙ! ብርታት እንዲያገኙ ከመመኘት በቀር ምን ይባላል?
         2. ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ አደጋው በቀላሉ የማይገላገለው ትልቅ ፈተና ይሆንበታል - ለወራት ብቻ ሳይሆን ለዓመትና ከዚያም በላይ በቀላሉ የማይለቅ መከራ ነው!
• በየዓመቱ፣ በአየር መንገዶች ላይ የደረሰ አደጋ በሪፖርቶች እየተዘጋጀ ሲሰራጭ፣ ከሰሞኑ የተከሰው አደጋና የጠፋው ሕይወት፣ ተደጋግሞ በቁጥር እየተጠቀሰ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ስም ጋር አብሮ ይዘረዘራል። የአደጋው መንስኤ ምንም ሆነ ምን፣ ይህንን ፈተና አያስቀርለትም!
      3. የአውሮፕላን አደጋው፣ ለቦይንግ ኩባንያ፣ ከፈተናም በላይ ሕልውናውን የሚያናጋ፣ ዋና ገበያውን የሚንድ አደጋ ሆኖበታል።
• ባለፉት ሀያ ዓመታት ከተሰሩት 10ሺ ቦይንግ አውሮፕላኖች መካከል 700ዎቹ፣ ስኬታማ የ737 ሞዴል ናቸው። ይህንን ታሪክ ለመድገም የተሰራው አዲሱ “737 ማክስ” ነው፣ አደጋ ላይ የወደቀው።
               
         “737 ማክስ” ለሚቀጥሉት አስር አመታት፣ የቦይንግ አለኝታ ይሆናል ተብሎ ነበር። አሁን፣ ያ ሁሉ የቦይንግ እቅድ እየተፍረከረከ ነው። ቢያንስ፣ የ”737 ማክስ” ምርት ለበርካታ ወራት ይስተጓጎላል። ከአደጋው ወዲህ በየአገሩ ያለአገልግሎት ለቆሙ ከ200 በላይ አውሮፕላኖች፣ የኪሳራ ማካካሻ ካሳ ይክፈለን የሚል ጥያቄም እየቀረበበት ነው።
ከነአካቴው፣ የአውሮፕላኑ ዲዛይንስ ትክክል ነው ወይ የሚሉ ምርመራዎችም ተጀምረውበታል። ይሄ ትልቁ ፈተና ነው። በእርግጥም፣ የምርመራው ውጤት ምንም ሆነ ምን፣ የአውሮፕላኑ ዲዛይን በተለይ ከኢንጂኑ ትልቅነት ጋር ተያይዞ የበረራ ደልዳላነት (ስታብሊቲ) ላይ የሚያስከትለው ችግር፣ ዋነኛው የቦይንግ ውጋት ይሆናል። ይህም ብቻ አይደለም።
የወንጀል የምርመራ መዝገብ በአሜሪካ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት ውስጥ ተከፍቶበታል - ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው። ነገሩ እንደ ዋዛ የሚታለፍ ጉዳይ አይሆንም - ለቦይንግ።
ከሁሉም በላይ ግን፣ ቀስ በቀስ እየተመዘዙ ከሚመጡት መዘዞች በፊት፣ ራሱ የአውሮፕላን አደጋው ነው ትልቁ ጉዳት። ማንም ሊተካው የማይችል ነውና፣ በአውሮፕላን አደጋ የ157 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ነው ቀዳሚው አሳዛኝ ጉዳይ። የሟች ወዳጆችና ቤተሰቦች፣ ሚስትና ባል፣ ወላጆችና ልጆች፣.... በአደጋው እጅግ ውድና ተመልሶ የማይገኝ ሰው ተለይቷቸው፣.... ከአጠገባቸው ያጡትን ማንም ሊጋራላቸው አይችልምና፣ ሀዘናቸውንም ለማንም የሚያካፍሉት አይደለምና፣ ከባድ የልብ ስብራት ነው። እስከ ቀብር ድረስ፣ ለበርካታ ቀናት ብቻ ሳይሆን ለወራት መጠበቅ ደግሞ፣ ሃዘናቸውን ከባድም ረዥምም ያደርገዋል።
እንዲበረቱ ከመመኘት በቀር ምን ማለት ይቻላል?
በአደጋው ዙሪያ፣ እያንዳንዱ እለትና ሳምንት፣ አዳዲስ መረጃዎችን ብቻ ሳይሆን፣ እየተከለሱ የሚዘጋጁ የተለያዩ ነባር መረጃዎችንም እንደሚያመጣ አትጠራጠሩ። የአውሮፕላን አደጋ እንደዚህ ነው።
የአደጋ ምርመራውም፣ በየእለቱ የተጨበጡ መረጃዎችን ብቻ ሳይሆን፣ የመረጃ ጭላንጭሎችንና ግምቶችን ጭምር እያስከተለ፣ ሳምንታትንና ወራትን ይፈጃል። ከዓመት በኋላ የመጨረሻው የምርመራ ሪፖርት እስኪዘጋጅ ድረስ፣ በየመሃሉ፣.... “የምርመራ ሂደት ገለፃ”፣... “ጊዜያዊ ሪፖርት”፣.... “የዋና ሪፖርት ዝግጅት”.... እየተባለ፣.... በየጊዜው ከሚፈጠር አለመግባባትና ወቀሳ፣ ሽኩቻና ውዝግብ ጋር፣ በሚዲያ ሲወራና ሲዘገብ ይከርማል።
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ እለት እንኳ፣ የአውሮፕላኑ “ብላክ ቦክስ” (የበረራ መረጃዎችን እየቀረፀ የሚሰንድ እና የፓይለቶችን ሁኔታ እየተከታተለ ድምፅ የሚቀርፅ ብርቱካናማ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ) በቁፋሮ ከተገኘ በኋላ የውዝግብ ስሜትን ፈጥሯል። ሁለቱ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች፣ ለምርመራ ወደ አሜሪካ ሳይሆን ወደ ፈረንሳይ አገር እንደተላኩ የተዘገበው፣ በውዝግብ ታጅቦ ነው። “Ethiopia snubs FAA, sends ‘black boxes’ from crashed Boeing 737 Max to France” ይላል ሐሙስ ማታ በብሉምበርግ የተሰራጨው ዜና።
የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ፣ ለአሜሪካ ፌደራል አቪየሽን ኤጀንሲ (FAA) ላይ ቅሬታውን ያሳየበት ውሳኔ እንደሆነ የብሉምበርግ ዘገባ ያትታል። የመረጃና የድምፅ መሳሪያዎቹን ወስደው ለመመርመር የFAA ባለሙያዎች ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ የኢትዮጵያ መንግስት ግን፣ መሳሪያዎቹን ወደ ፈረንሳይ የምርመራ ማዕከል ለመላክ መርጧል።
በያዝነው ሳምንት ሐሙስ እለት ሲሰራጭ የዋለው ዜና ደግሞ፣ የአውሮፕላኑ ዋና ፓይለት ላይ ያተኮረ ነው። ቀደም ሲል በቦይንግ 737 አውሮፕላን ላይ ስልጠና ወስዶ በዋና አብራሪነት ሲሰራ የቆየው ፓይለት፣ አዲሱን 737 Max ለማብረር፣ “በሲሙሌተር” ስልጠና አልወሰደም የሚል ዜና በኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እና በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቧል። አዲስና ትልቅ ዜና ይመስላል፤ ግን አይደለም።
ኒው ዮርክ ታይምስ ከሳምንት በፊት የዘገበውን ሌላ ዜና ስትመለከቱ ትፈርዳላችሁ። ከዚያ በፊት ግን፣ ቫይስ ኒውስ ከ10 ቀን በፊት የዘገበውን ዜና ተመልከቱ።
አሜሪካን ኤርላይንስ እና ሳውዝዌስት አየርላይንስ፣ በርካታ 737 Max አውሮፕላኖችን በመግዛት የሚጠቀሱ ናቸው። አሜሪካን ኤርላይንስ 24፣ ሳውዝዌስት ደግሞ 34 አውሮፕላኖች አሏቸው - 737 ማክስ። ነገር ግን፣ ሁለቱም አየርመንገዶች ለ737 Max፣ የፓይለት መለማመጃ ሲሙሌተር የላቸው።
የአሜሪካን ኤርላይንስ ፓይለቶች ማህበር ቃል አቀባይ ካፕቴን ዴኒስ ታዠር፣ አውሮፕላኑን ለማብረር የሲሙሌተር ልምምድ አያስፈልግም የሚል መመሪያ መኖሩ አሳዛኝ ነው ብሏል። ቀደም ሲል፣ 737-800 የተሰኘው ተመሳሳይ አውሮፕላን ላይ አብራሪ የነበሩ ፓይለቶች፣ “በ56 ደቂቃ የቪዲዮ ስልጠና” ብቻ አዲሱን አውሮፕላን ማበረር ይጀምራሉ ብሏል የፓይለቶቹ ቃል አቀባይ።
ሁለቱ አየርመንገዶች፣ እጅግ ግዙፍ ኩባንያዎች ከመሆናቸው የተነሳ፣ ከኢትዮጵያ አየርመንገድ፣ እጥፍ ድርብ ይበልጣሉ። ሳውዝዌስት ለብቻው፣ 750 አውሮፕላኖች አሉት - ከቦይንግ የተገዙ።
እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ አምስት እና አስር አውሮፕላኖችን አይገዙም። ሁለት ሦስት መቶ ለመግዛት የቅድሚያ ትዕዛዝ የሚያስመዘግቡና በዚህም ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ የሚያገኙ አውራ አየር መንገዶች ናቸው። 737 Max ገና በትኩሱ ለምርቃት ሲበቃ፣ የመጀመሪያውን አውሮፕላን የተረከበው ሳውዝዌስት ነው። እስካሁንም ሁለቱ አየር መንገዶች፣ የአዲሱ ሞዴል 58 አውሮፕላኖችን ተረክበው እየሰሩ ነበር።
ነገር ግን ለአዳዲሶቹ አውሮፕላኖች (ለ737 Max) የፓይለት መለማመጃ ሲውሌተር የላቸውም ብለዋል የሁለቱ አየርመንገዶች ፓይለቶች። በቃ፣ እንደ ሌሎች አየር መንገዶች፣.... በቦይንግ የበረራና የስልጠና መመሪያ መሰረት፣ ቀደም ሲል 737-800 የተሰኙትን አውሮፕላኖች የማብረር ፈቃድ የነበራቸው ፓይለቶች፣ በአጭር ተጨማሪ ስልጠና ነው፣ አዲሱን አውሮፕላን ማብረር የጀመሩት።
ይሄ መጋቢት 3 እና ከዚያ በኋላ ሲዘግብ የሰነበተ ጉዳይ ነው።
እንዲያም ሆኖ፣ ከአስር ቀን በኋላ በዚህ ሳምንት ከትናንት በስቲያ፣ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ፣ አንዳች አዲስ እና ልዩ ግኝት የተገለጠለት ይመስል፣ ኢትዮጵያዊው ፓይለት፣ በሲሙሌተር አልተለማመደም የሚል ዜና ሲሰራ፣ እንደ ጉድ ነው የተራገበው።
ሮይተርስን ጨምሮ በርካታ ሚዲያዎች ዜናውን እየተቀባበሉ አሰራጭተውታል።
አስገራሚው ነገር፣ ራሱ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ፣ ባለፈው ሳምንት ባወጣው ዜና፣ አሜሪካ ውስጥ አንድም አየር መንገድ የ737-MAX ሲሙሌተር እንደሌለው ገልፆ ነበር። አሜሪካ ውስጥ አንድ ሲሙሌተር አለ። እሱም የቦይንግ ኩባንያ ብቻ እንደሆነ ኳርትዝ ከ10 ቀን በፊት ዘግቧል።
እንዲያውም፣ አሜሪካን ኤርላይንስ፣ ገና የሚቀጥለው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ ነው ሲሙሌተር የሚደርስለት። ዩናይትድ ኤርላይንስም ከዓመት በኋላ፣ ለአዲሱ ሞዴል አውሮፕላን፣ ሲሙሌተር ለመትከል እየጠበቀ እንደሆነ ዘግቧል - ራሱ ኒውዮርክ ታይምስ - ባለፈው ቅዳሜ። በአጭሩ፣ በአሜሪካ ውስጥ ለ737 Max የሚሆን የበረራ መለማመጃ ሲሙሌተር ያለው አየር መንገድ የለም።
ፓይለቶች አውሮፕላኖቹን ሁለት ሺ ጊዜ እና ከዚያ በላይ ሲያበርሩ የነበሩት፣ በሲሙሌተር ተለማምደው አይደለም። ይሄ ለ10 ቀናት ሲዘገብ የቆየና በይፋ የሚታወቅ ነገር ነው።
ታዲያ ከትናንት በስቲያ፣ እንደ አዲስ ግኝት እና እነደ ልዩ መረጃ፣ ኢትዮጵያዊው ፓይለት በሲሙሌተር አልተለማመደብ ብሎ መዘገብ ምን አመጣው?
አዎ ዘገባው ያሳዝናል። ነገር ግን፣ ዘገባውንና ሚዲያዎቹን ማማረርና መውቀስ፣ ወይም ይባስ ብሎ፣ “የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለመጉዳት ታስቦ የተዘገበ ነው”፣ “ሴራ ነው” በሚል ስሜት መብከንከንም ብዙም ጥቅም የለውም።
አዎ፣ እንዲህ አይነት ዘገባዎች፣ ለኢትዮትያ አየር መንገድ ከባድ ፈተና ናቸው። ግን ሁሌም፣ የአውሮፕላን አደጋ፣ ከአሳዛኝነቱ በተጨማሪ፣ በየጊዜው ሀዘንን መላልሶ እያጫረ ለሳምንታት ብቻ ሳይሆን ለወራትም የማይደርቅ ህመም፣ ለረዥም ጊዜ ለቅቆ የማይለቅ ፈተና ነው።
ለአየር መንገድ ብቻ ሳይሆን ለቦይንግም ጭምር ነው ፈተናው። ፈተናውማ፣ ቦይንግ ላይ ብሷል።
የኢትዮጵያ መንግስት፣ የአውሮፕላን አደጋው፣ የማሌዢያ ላየን ኤርላይንስ ላይ ከደረሰው አደጋ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ በይፋ መግለጫ ሲሰጥ፣ ትልልቆቹ የዓለም ሚዲያዎች ዘግበውታል። ትርጉሙ ረቂቅ፣ መልዕክቱ ድብቅ አይደለም። “አንድ አይነት አውሮፕላኖች በተመሳሳይ ሁኔታ አደጋ ከገጠማቸው፣ አውሮፕላኑ ላይ ችግር ቢኖርበት ነው” የሚል መልዕክት የያዘ እንዲህ አይነት ዜና በየሚዲያው ሲዘገብ፣ ለቦይንግ ፋታ የማይሰጥ ህመም ነው።
737 አውሮፕላኖች፣ የቦይንግ እንጀራ ናቸው። ሌሎች ስኬታማ አውሮፕላኖችም አምርቷል፤ እያመረተም ነው። ከ707 ጀምረ እስከ 787 እስከዛሬ፣ በጥራትና በስኬት ከ19500 በላይ አውሮፕላኖችን ሰርቶ ሸጧል።
ነገር ግን፣ ከእነዚህ አውሮፕላኖች መካከል፣ 10500 ያህሉ ሞዴላቸው 737 ነው። በየጊዜው እያሻሻለ፣ በ4 ዙር ደግሞ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እያሳደገ፣ ለ50 ዓመታት በስኬት እንዲራመድ አስተማማኝ አለኝታ ሆነውለታል - የ737 ምርቶቹ።
737 Max ደግሞ ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት፣ ዋና ገበያው እንዲሆኑለት ነበር የቦይንግ እቅድ። በዚህ አመት አዲሱ 737 Max ሞዴል ላይ በማተኮር፣ በወር 57 አውሮፕላኖችን እየፈበረከ ነበር - ቦይንግ። በዓመት 680 ማለት ነው።
በዚህ መሀል፣ ሁለት አውሮፕላኖች ላይ አደጋ ሲደርስ፣ አደጋዎቹ ተመሳሳይ እንደሆኑ ሲገለጽ፣ “አውሮፕላኖቹ ላይ አንዳች ችግር ቢኖርባቸው ነው” የሚል መልዕክት ያዘሉ ዘገባዎች ሲሰራጩ፣ ለቦይንግ እጅግ ትልቅ ፈተና ነው። ከመሀል እስከ ዳር፣ ምሰሶና ማገሩን ሁሉ የሚያናጋ ፈተና1
የቦይንግም ሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈተና፤ “በምርመራው ውጤት ነፃ እወጣለሁ” የሚል ተስፋ የለውም። ለምን ቢባል፣ አንደኛ ነገር የአውሮፕላን አደጋ፣ መዘዘኛ ነው። የምርመራው ውጤት ምንም ሆነ ምን፣ ወለል ያለ ግልጽ ድምዳሜ ተገኝቶ የምርመራ መዝገቡ ቢዘጋ እንኳ፣ በሌሎች በርካታ አመታዊ መዝገቦች ውስጥ፣ የማይፋቅ ጥቁር ነጥብ ሆኖ መዘርዘሩ አይቀሬ ነው።
ሁለተኛ ነገር፣ የአደጋው አይነት፣ በበርካታ ገጽታዎች የሚከበብ፣ በብዙ ቅርንጫፎች የሚመነዘር፣.... ምርመራውም የዘወትር አሠራሮችን የሚፈትሽና የቆዩ መዛግብትነትም እየቆፈረ የሚያገላብጥ ስለሆነ፣ የምርመራው ውጤት ቅልብጭ ያለ ነጠላ ፍርድ አይሆንም።
“የአደጋው ዋና መንስኤ እንዲህ ነው” የሚል ድምዳሜ ከምርመራው ይገኛል ብሎ መጠበቅ ያላዋቂ ጥበቃ ነው። ምን ምን እንደተከሰተ፣ ከተፈጠሩት እክሎችና ችግሮች ጋር አንድ በአንድ ሊዘረዝር ይችላል።
ለአደጋው ያጋለጡና መንገድ የከፈቱ ጉዳዮች፣ መነሻዎችና ሰበቦች፣ አባባሽና ተደራቢ ችግሮች፣.... እንዲህ ብዙ ነገሮችንም የሚጠቃቅስ የምርመራ ሪፖርት፣ ቅልብጭ ያለ ድምዳሜ አይኖረውም።
ከመነሻውም፣ ምርመራው የፖሊስ ምርመራ አይደለም። ለወደፊት አደጋዎችን ለመከላከል የሚያግዝ የቴክኒክ ምርመራ ነው። እናም በምርመራው ውጤት ከጉዳት ነፃ እወጣለሁ የሚል ተስፋ የለም። የኢትዮጵየ አየር መንገድ ፈተና፤ ከበርካታ ሳምንታት በኋላ ትንሽ የመርገብ፣ ከዓመት በኋላም የመረጋጋት እድል አለው - እፎይ የሚያስብል ባይሆንም።
የቦይንግ ፈተና ግን ረዥም ነው። አውሮፕላኑ ላይ የተነሳው ጥያቄ፣ እንጀራው ላይ የተነሳ ጥያቄ ነውና - የምርመራው ውጤት ምንም ይሁን ምን።
በአጭሩ፣ “ተጠያቂው ያኛው ነው”፤ ወይም “ይሄኛው ነው” የምትል የምርመራ ድምዳሜ ወይም ውሳኔ ለመስማት አትጠብቁ። ከሰማችሁም፣ አንድ የውዝግብ መነሻ እንጂ የመጨረሻ ድምዳሜ እንደሰማችሁ አትቁጠሩት።

Read 1265 times