Saturday, 23 March 2019 13:51

ጀግኖቼን አትንጠቁኝ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)


                                “አሉላ የሁላችንም ነው! የባንዲራችን ቀለም፣ የነፃነትና የድላችን መዝሙር!”
                                        

               ሀገራችን ኢትዮጵያ በአንድ ምሽት የተሰራች፣ በአንድ ብሔርና ወገን፣ ትድግና የተፈጠረች ሳትሆን፣ የሁሉም ያገር ልጅ ደምና አጥንት ያፀናት፣ ዋጋ የተከፈለላትና በመስዋዕትነት የተመሰረተች ነች፡፡ ስለዚህም ቴዎድሮስ ያንድነትዋ ጀማሪ፣ ባለ ህልምና መስዋዕት ቢሆኑም፣ ዮሐንስም በግራና በቀኝ የመጣውን ጠላት ተፋልመው፣ ቅጥሯን አስከብረዋል፡፡ አፋሩ አርሶ አደር ሸዋን ሊቆጣጠር የመጣውንና በሙዚንገር የተመራውን ጦር ድባቅ መትተው፣ ህልሙን ከንቱ አድርገውታል፡፡ ነገስታቱ የሀገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ ዋነኛ መሪና አስተባባሪ ቢሆኑም፣ አብረዋቸው በየግንባሩ የቆሙት የጦር መሪዎችና አዛዦች ሚናቸው ታላቅ ነበር፡፡ ለዚህ ነው ዮሐንስን ያለ አሉላ ማሰብ፣ የታሪክን ጭርታና የእውነትን ግርታ ይፈጥራል የምንለው፡፡
እንደዚሁም የአድዋን፣ የአምባላጌን ድል አውስቶ ፊታውራሪ ገበየሁን፣ ባልቻ አባነፍሶን፣ አሉላ አባነጋንና ሌሎቹን ባለሟሎች አለማስታወስ አይቻልም፡፡ ዋና ዋናዎቹን አልን እንጂ ራስ ወሌ፣ ራስ መንገሻ፣ ራስ መኮንን ወዘተን-- መጥቀስ ግድ ይላል፡፡ እነዚህ ጀግኖች በዛሬው አጠራር፣ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የወጡ ይሁኑ እንጂ ሁሉም ኢትዮጵያዊና ለኢትዮጵያ አንድነትና ክብር የቆሙ ነበሩ፡፡ ለዚህ ነው የትግራዩን-የተምቤን አንበሳ፣ ያገሩ ባለቅኔ ፀጋዬ ገብረመድህን፤ “የኔ ጀግና” በሚል መንፈስ፣ በምናብ ከጎኑ ቆሞ ለአሉላ ስንኝ የቋጠረው፡፡
ዶጋሊ
ምጽዋ አፋፍ ላይ ምጥ ጽዋ
ዶጋሊ አለት ሃሩርዋ
ከአለት ኩርፍታ ጫፍዋ
ቆመዋል ቃፊር ጠባቂዋ …
ዋ!
ምነው ብቻህን አሉላ
በንዳድ እምትቆላ!
“ቱርክ ፓሻው ኩሩ” አበሻ
ብቻህን በእሳት ፍል ዋሻ
ግንባርህን እንዳኮስተርክ፣ አቅጣጫህን ሳታላቅቅ
በዶጋሊ ጣር ብርቅርቅ
ዕጹብ ድንቅ አሉላ ዕጹብ ድንቅ፣
በዚያ በምጥ - ጽዋህ ንዳድ፣
በዚያ ባዱሊስ እሳት ጭንቅ
በእቶን ሀሩር፣ በምድር ፍም ትጥቅ
ቃፌርክን ሳታፈራርቅ
ምነው አሉላ ብቻህን፣ ብቻህን እምትጠብቅ …
እንግዲህ ጋሽ ፀጋዬ መቶ ዐመታት አልፎ፣ አሉላን በእንቶኔ ዘይቤ ውስጥ ሆኖ የሚያወራው እንዲሁ አይደለም፡፡ ዋጋ ስለከፈለለት፣ ድንበሩን በደሙ ጠብቆ፣ በህይወቱ ዋጋ ስላስከበረለት ነው፡፡ ዛሬ የሚኖርባት ሃገር ከሰማይ ዱብ ያለች ሳትሆን፣እርሱና መሰሎቹ መስዋዕት ባይሆኑ፣ከዚያ በፊት በመሳፍንት ዘመን፣ የጉልበተኞች መጫወቻ የነበረችው ብጥስጥስና አበሰኛ ሀገር ትቀጥል እንደነበር በማሰብ ነው። ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስም ሆኑ ምኒልክ አንድም በማግባባት፣ አሊያም በጦር አንድ አገርና ህዝብ ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ በዓለም ላይ የመጀመሪያዎቹ አይደሉም፡፡ የጀርመኑ ቢስማርክ፣ የጣሊያኑ ጋሪ ባልዲም ህዝባቸውን በሃይል አንድ አድርገውታል፡፡ ልዩነቱ ያንን አንድነት የምንጠቀምበት መንገድ ነው፡፡
እውነት ለመናገር የዘመን ዐውድና የህብረተሰብ ንቃተ ህሊና ደረጃዎች ለዚህ ሁሉ ወሳኝ ናቸው፡፡ አሜሪካን ከእንግሊዝ ራስዋን ነፃ አውጥታ “ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እገነባለሁ” ብላ በጀፈርሰን፣ በፍራንክሊን፣ በሀሚልተንና በዋሽንግተን ልብ ስትፀነስ፣ ዛሬ የሰለጠኑት የአውሮፓ መንግስታት ምን ዓይነት አስቀያሚና አሳፋሪ ግፍና ሥርዓት ውስጥ እንደነበሩ ማሰብ የሚያቅተን አይመስለኝም። ለዚህም ይመስለኛል ጀፈርሰን፤ ሉዊስ 6ኛን የስፔኑን ንጉስ ናፔልን “ጅል?” የሚላቸው። የፖርቱጋሏን ንግስት፣ የዴንማርኩን ንጉሥ “ደደብ!” ከማለት ያልተመለሰው ለዚህ ነበር። “እንስሳትም” ይሏቸዋል፡፡ ያን የፈጠረበት፣ በወቅቱ የነበራቸው ኋላ ቀር አገዛዝና ቀሽም የገዢዎች ሥነ ልቡና ነው፡፡
ከዚህ ጋር ስናነፃፅረው፤ ኢትዮጵያውያን ጀግኖችም ትምህርት ያልቀሰሙ፣ ስልጣኔያቸው ከዓለም ጉዞ ጋር የማይመጣጠን ቢሆንም ህይወታቸውን ሳይቀር እየሰጡ፣ አንዲት ታሪክ ያላት ሃገር አቆይተውልናል፡፡ በተለይ ደግሞ በዐድዋ ድል ያገኘነው ስነ ልቦናዊ ትሩፋት፣ ያለመሳቀቅና መሸማቀቅ እንድንኖር አድርጎናል። ይሁንና ዛሬ በተራችን በደም የተሰራችውን ሀገር ለማፍረስ የየራሳችንን ፋስና ገጀራ ይዘን፣ የደሙን ሊሾ ለመናድ እያቅራራን ነው፡፡ በሰሞኑ ማቅራራታችን በእጅጉ እየዘገነነኝና እያሸማቀቀኝ የመጣው ነገር፣ እነዚህን ብርቅ የሀገር ጀግኖች ለመናጠቅና ለመበታተን መሞከራችን ነው፡፡
ይህንን ስህተት እንድንፈጥር ያደረገን ምናልባት ስለ ቃልኪዳን ትርጉም ሳይገባን ቀርቶ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህንን ለማወቅና ለመማር ግን ከቅዱሳት መጻሕፍት በላይ ምስክር የሚሆነን የለም፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር ራሱ ከሰዎች ጋር ቃል ኪዳን በመግባት፣ ቃሉ የማይታጠፍ እንደሆነ ማሳየቱ በቂ ነው፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር አብርሃም ከተባለው ሰው ጋር ዑር በምትባል ቦታ፣ ከከላዳውያን ሀገር ሲያስመጣ አብረሃም ብቻውን የወጣው ያንን ቃል ኪዳን አምኖ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ቃል ኪዳን የማይሰበርና የማይታጠፍ ሰነድ ነውና፡፡  
አሁን ቃል ኪዳንን ያነሳሁት ለሰሞነኛ ውድቀታችን ማመላከቻ የሚሆኑ ነገሮችን ፍለጋ ነው፡፡ በፍለጋዬም የምሄደው ቀደም ሲል ወደጠቀስኳቸው የሀገሬ ጀግኖችና የጦር መሪዎች ነው፡፡ በየትኛውም አቅጣጫ፣ በየትኛውም ዘመን ስለ ሀገራቸው ህይወታቸውን የሰጡና በመስዋዕትነት ያለፉ ጀግኖች ሁሉ ቃልኪዳናቸው “ኢትዮጵያዊ” እንጂ “መንደራዊ” አልነበረም። አሉላ የተምቤን ተወላጅ፣ የትግራይ ሰው ቢሆንም የተዋጋው ግን ለክልሉ ወይም ለሰፈሩ አይደለም፡፡ “የኢትዮጵያ ድንበር ቀይ ባህር ነው!” ብሎ ነበር ግንባሩን ለጥይት የሚሰጠው፡፡ በህይወቱ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ከአድዋ ድል በኋላ ረዥም ጊዜ ባይቆይም ዕድሜውን ሁሉ የሰጠው ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ስለዚህ ማንም መጥቶ “አሉላ ትግሬ ነው፤ የኔ ነው!” ቢለኝ አልሰማውም፡፡ ምክንያቱም የእኔ  ብቻ ሳይሆን የቀጣዩ ዘመን የልጄና የልጅ ልጆቼ ሁሉ ጀግና ነውና! የየዕለት ኑሮውና ቃልኪዳኑ፣ ውርሱና ኑዛዜው ለኢትዮጵያ እንጂ ለሰፈሩ አይደለም፡፡ ስለዚህ አሁን የተፈጠራችሁ ሰፈርተኞች፤ ቀን ገለል እስከያደርጋችሁ ድረስ ጀግናዬን ልትነጥቁኝ እንደማትችሉ ልነግራችሁ እወድዳለሁ! አሉላ የአማራው፣ አሉላ የኦሮሞው፣ አሉላ የአፋሩ፣ አሉላ የጉራጌው፣ አሉላ የሁሉም ነው! የባንዲራችን ቀለም፣ የነፃነትና የድላችን መዝሙር ስንኝ ነው፡፡
በጀግንነት ውሎ አባነፍሶ የሁለት ታላላቅ ጦርነቶች ጀግና ነው፡፡ ምናልባትም በዘመኑ ከነበሩት የጦር አዛዦች ሆስፒታል በስሙ የተሰየመለት፣ ክቡርና ውድ የሀገሬ ጎበዝ ነው። ምንም እንኳ እንደ ሌሎቹ ኢትዮጵያዊ ጀግኖች፣ የኃይለሥላሴ መንግስት ጥሩ ፊት ባያሳያቸውም፣ ዳግመኛ የመጣውን የጠላት ጦር በአርበኝነት በማርበድበድ  ቆይተው ህይወታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ታዲያ ባልቻን የግሉ ሊያደርግ የሚፈልግ ወይም የሚችል ማነው? ለዚህ ፍርድ ዛሬ በየድንኳኑና በየመሸታ ቤቱ የሚወራውን ወሬ ምስክር ለማድረግ መባተት የለብንም፡፡ ወደ ኋላ ሄደን፣ ባልቻ በኖረበት ባልቻ በዞረበት፣ በአደባባይና ጓዳ፣ መዝሙሩና ህይወቱ ማን እንደነበር ሰነድ ማገላበጥ፣ ታሪክ መጠየቅ ብቻ በቂ ነው፡፡ እንደ አሉላ ሁሉ፣ ባልቻም ህይወቱና ሞቱ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ወጣትነቱን ብቻ ሳይሆነ የኋላ ህይወቱን ሳይቀር በዱር በገደል የተንከራተተው፣ ለሰፈሩና ለመንደሩ አይደለም፡፡ ለአንዲት የታፈረችና የተከበረች ኢትዮጵያ ህያውነት ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ አንዱ ታሪክ ያልገደበው፣ የአንድነት ትርጉሙና ጣዕሙ የጠፋው መጥቶ “ባልቻ የኦሮሞ ጀግና ነው!” ቢለኝ ልሰማው አልችልም … ባልቻ ያንን አልተናዘዘም፣ ያንን አላወራም። ለዚህ የሰነፍ ወሬና ቀሽም መዝሙር ነፍሱን አልሰጠም፡፡ ይልቅስ ሁላችን
“ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ!”
--- እያልን እንድንኮራበት የታሪክ አክሊል ጭኖልን አልፏል፡፡ ይህንን ማሳያ በራስ መኮንን፣ በእቴጌ ጣይቱ፣ በጌጃና በሌሎቹም ጀግኖቻችን የህይወት መስመር ልናየው እንችላለን፡፡
ድላችን የጋራ እንደሆነ ሁሉ ቁስሉም የጋራችን ነው፡፡ ህይወታችን በአንድ እንደሆነ፣ ሞታችንም በአንድ ነው፡፡ የየካቲት 12 የሰማዕታት ቀንን ስናስብ የምናነበው፣ “ኦሮሞ ሞተ፣ አማራ ሞተ፣ ትግሬ ሞተ” እያልን አይደለም፡፡ “ወገኖቻችን ሞቱ፣ መከራ ተቀበሉ” እያልን ነው፡፡
ይህንን ቀን በተመለከተ ኢትዮጵያዊው ገጣሚና ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ በስንኝ ከደረደው ጥቂት ልናይ እንችላለን፡-
የደም ቀን
አገር ተቃጠለ!
እሳተ ጎሞራ ወረደ ከሰለ፡፡
ጭስ አመድ አዋራ ሰማዩን ሸፈነው
ጥቁር ሰማይ ጥቁር!
የቀን ጨለማ ሞት በእናት ቅድስት አገር
በጀግናው ሕዝብ ላይ የጠላት ግፍ ቀንበር፡፡
ፋሽስት አስተጋባ ፋስ ተሰነዘረ
ባካፋ መዶሻ ህዝቡ ተወገረ፡፡
ድላችንም ሽንፈታችንም፣ ከፍታችንም ዝቅታችንም ባንድ ሰነድ የተጠረዘ ነው፡፡ ለአማራው ሰፈር፣ ኦሮሞና ትግሬው ሞቷል። ለትግሬው ሰፈር፣ ከአማራውና ኦሮሞው ሞቷል፡፡ ለኦሮሞው ምድር አፋሩና አማራው፣ ትግሬና ጉራጌው ሞቷል! ያንዱ ምድር፣ በሌላው ደም ተዋጅቷል፡፡ “ሰፈሬ ነው፣ መንደሬ ነው! አያገባህም!” ብትለው፣ ባያገባው ማን ለማን ይሞታል! … ባልቻ አድዋ የተዋጋው፣ ትግሬ ስለሆነ አይደለም! ገበየሁ መቀሌ የተዋጋው ሰፈሩ ስለሆነ አይደለም፤ ሀገሩ ስለሆነ እንጂ!
የዛሬውን የኛን ቀሽም ወሬ እነዚያ የምንኮራባቸው የምንጠቅሳቸው ጀግኖች ቢሰሙን የሚያፍሩብን ይመስለኛል፡፡ ያወረሱን ይህንን ስንፍና፣ እርስ በእርስ መራኮት አይደለም፡፡ ያወረሱን በአንድነት ለአንድ ሀገር፣ በጋራ መቆምን ነው፡፡ ምናልባት የታሪክ እማኞች ቢያዩም እየተደነቁ፣ የዶክተር በደሉ ዋቅጅራን ስንኞች የሚዘምሩብን ይመስለኛል፡-
አባትህ፣
ምላሱን በጥርሱ ነክሶ በግብሩ በተናገረ፣
የሀገሩን ቃልኪዳን ቃል ባህር ተሻግሮ ባስተማረ፣
የዜግነት ውግዘት ሳይነካው ሀገር ምስጢርዋ ገኖበት፣
ሰንደቅ ግርማዋ ደምቆባት፣
የኖረበትን ዘመን በግብሩ ሰንዝሮ እየለካ፣
ኋላቀር የምትለውን፣ እውን አንተን ይተካ!?
“አባቴ ይሙት” እንዳትለኝ፣ አንተን ሲወልድ ነው ሞቱ
ትጉህ ወራሽ በማጣቱ፣
ባዶ በመገደቡ፣ ጉዞው በመገታቱ፡፡
ስለዚህ አባቶች ቀና ብለው ቢያዩ የሚያፍሩበትን ስራ በመስራት ጊዜያችንን ባናባክን አትራፊ እንሆናለን፡፡ ያለበለዚያ ግን ያልተሰጠንን ኑዛዜ፣ ያልተነገረንን ትንቢት፣ ያልተሰጠንን ኪዳን ይዘን በየሰፈራችን ባንጠብ መልካም ነው፡፡ ድንኳናችንን ብናሰፋ፣ ካስማችንን ብንዘረጋ የተሻለ ውጤት ይኖረናል። ብቻ በዚያም አለ በዚህ “ጀግናዬን” ማንም ሊቀማኝ እንደማይችል ለመናገር እወዳለሁ። የኢትዮጵያን ጀግኖች፤ ቃል ኪዳናቸውና ህይወታቸው፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህ ታሪክ ላይ የምናንጠለጥለው “ትርፍ አንጀት” ከበሽታነት ያለፈ ፋይዳ የለውምና፣ ጀግኖቻችንን ለቀቅ አድርጉልን!
በጋሽ ፀጋዬ ስንኞች ልሰናበት፡-
እንዳልተዛመድን እንዳልተዋደድን፣
ፈርተን መዋደድን ጉርብትናን ናድን፣
እኛነትን ትተን እኔነት ለመድን፡፡
ፈራን
ፍቅርን ፈራን ጥላቻን ሰራን ብቸኝነት ጠራን፣
በጋራ ቤታችን አጥር ድንበር ሰራን፣-- 

Read 816 times