Saturday, 23 March 2019 13:13

ቃለ ምልልስ የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት ምን ገጠመው?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

• የክልል ሚዲያዎች የፈራረሰችውን የሶቪየትን መንገድ እየተከተሉ ነው
         • መንግስት ለጥያቄዎች በመርህ ላይ የተመሰረተ ምላሽ መስጠት አለበት
         • ኢህአዴግ የርዕዮተ አለም ቀውስ ውስጥ መግባቱን መረዳት አለበት
         • አሁን ብሔርተኝነት የመጨረሻው አስከፊ ጫፍ ላይ ይገኛል

         በሀገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ትንታኔዎችን በመስጠት የሚታወቁትና የለውጥ አመራሩ ስልጣን በተቆናጠጠ ማግስት “የማስጠንቀቂያ ደወል” በሚል ርዕስ ባወጡት ወቅታዊ የፖለቲካ መጽሐፍ ሳቢያ አነጋጋሪ የሆኑት የኪነ-ህንጻ ባለሙያው ሚካኤል ሽፈራው፤ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየገጠመው ባለው ተግዳሮትና አጣብቂኝ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ የገነነው አክራሪ ብሔርተኝነት በደቀነው አደጋና መንግስት ሊወስዳቸው በሚገባቸው
የማስተካከያ እርምጃዎች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡

           ብዙዎች ተስፋ ያደረጉበትን ለውጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጠራጠር ጀምረዋል፤ ለመሆኑ አንድ ዓመት ገደማ ያስቆጠረው የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስት ምን አገኘው?
የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ምን አገኘው? የሚለው ጥያቄ የሚያመላክተኝ፣ ጥሩ መጥቶ አሁን ምን ሆነ? የሚል አንደምታውን ነው። እኔ ግን ገና ከመነሻውም ትንሽ የተዛባ አነሳስ ስለነበረው ነው የሚል አተያይ ነው ያለኝ፡፡ በመጽሐፌም ያነሳሁት ሃሳብ፣ ከተለያዩ የአለም ተሞክሮና አቅጣጫዎች አንፃር ያሉ ሃቆችን ነው፡፡ እንደምናስታውሰው እነ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን የመጡ ጊዜ በሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ተቃርኖዎችና ልዩነቶች ጨርሶ የጠፉ ይመስል ነበር፡፡ አንድ ፈላስፋ በጨለማ ሁሉም ላሞች ጥቁር ናቸው ይላል፤ ሲነጋ ነው የላሞች መልክ የሚለየው፡፡ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ይሄን የሚመስል ነበር። ግልፅነት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ልዩነቶቹ በሙሉ የጠፉ ይመስል ነበር፡፡ ስለዚህ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት መንገድ በመጀመሪያ የሳተው የሚመስለኝ፣ከኢህአዴግ ውስጥ የመጣ ለውጥ ፈላጊ ሃይል እንደመሆኑ መጠን፣ በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩትን ችግሮች ግልጽ አድርጐ ለይቶ ባለመነሳቱ ነው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ እና በኢትዮጵያም ያሉ ችግሮች እነዚህ ናቸው፤ መሄድ የምንፈልገው በዚህ አቅጣጫ ነው፤ የምናከናውናቸው ተግባራት ይሄን ይመስላሉ በሚል ፍኖተ ካርታ ያለው፣ በሚገባ መነሻና መድረሻውን የተነተነ፣ ግልጽ ያደረገ የለውጥ ሃይል አልነበረም፡፡ ወቅታዊ የሆኑ አጀንዳዎችን በእሣት ማጥፋት መልኩ በመመለስ ላይ ነው ያተኮረው እንጂ ግልጽ አቅጣጫ አላስቀመጠም ነበር፡፡ ሌላው አንድ የፖለቲካ ሃይል ግልጽ መርህ ያስፈልገዋል፡፡ ርዕዮተ አለም ያስፈልገዋል። የቀድሞ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ አለም ቀውስ ውስጥ ገብቷል፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በአጭሩ ሲገለጽ፣ መሠረታዊ ቁምነገሩ፣ ብሔር አቀፍ ፌደራሊዝም ነው፡፡ አሁን ቀውስ ውስጥ የገባው ይሄ ብሔር አቀፍ ፌደራሊዝም ነው፡፡ ይሄ ቀውስ ውስጥ የገባው ብሔር አቀፍ ፌደራሊዝም ምንድን ነው ችግሩ? ብሔር አቀፍ ፌደራሊዝም አይሠራም? የሚሠራ ከሆነ ለምንድን ነው የታለመለትን አላማ ያልመታው? ብሔር ብሔረሰቦች ተግባብተው አንድ ኢትዮጵያን መፍጠር ያልቻሉት ለምንድን ነው? --- ብለው እንደ ኢህአዴግ መገምገም አልቻሉም፡፡ እነሱ ፕሮግራሙ ላይ ምንም ችግር የለም፤ የአፈፃፀም ነው ይላሉ፡፡ አፈፃፀሙም ቢሆን፣ እነ እገሌ ስለያዙት ነው፣ እነ እገሌ ሲይዙት የተሻለ ነው የሚል  እንጂ መርሁ ላይ ያለውን ችግር ለማየት በፍፁም አልሞከሩም፡፡ ያንኑ ቀውስ ውስጥ የገባ መርህ ነው በሌሎች አስፈፃሚ ሃይሎች ለማስፈፀም እየተሞከረ ያለው፡፡
እንደኔ ከሆነ፣ የብሔር ፌደራሊዝሙ ራሱ ችግሮች የነበሩበት ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ አያስፈልግም አይባል እንጂ ህክምናና ሪፎርም ይፈልግ ነበር፡፡ ለምሣሌ ባለፉት 27 አመታት፣ በዚህ የፌደራሊዝም አወቃቀር ተበድለናል የሚሉ ምሬት ያረገዙ በርካታ ሃይሎች አሉ። የእነዚህ ሃይሎች ጥያቄ እንዴት ነው የሚመለሰው? ለምሣሌ የጅግጅጋ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ ጅግጅጋ ላይ ቤተ ክርስቲያን መቃጠልና መጤ የተደረጉ ወገኖች አሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ወገኖች በየቦታው አሉ፡፡ አላማ እየተደረጉ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ ብሔር አቀፍ ፌደራሊዝሙ፣ እንደ መርህ ከፌደራሊዝሙ የተወለደው ህገ መንግስት ደግሞ እንደ ህገ መንግስት አፈፃፀሙ ጭምር ላይ የነበረ ችግርን አይቶ ከመፍታት ይልቅ፣ ብሔርተኛ ሃይል በሌላ ብሔርተኛ ሃይል መተካት ነው የተደረገው፡፡
ያለፈው ጊዜ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ መርህ፣ ህግጋትን መመርመር የቻለ ለውጥ ነበር መነሳት የነረበረበት፡፡ የለውጥ አካሄዱ እዚህ ላይ ከማተኮር ይልቅ ብአዴን እና ኦህዴድን አቅፎ፣ ህወኃትን እንደ ጠላት ቆጥሮ፣ እንዲመሽግ አድርጓል፡፡ ይሄ  ለውጡ በራሱ ላይ የፈጠረው ሌላ ወጥመድ ነው፡፡ ለውጡ በህወኃት የለውጥ ፈላጊ ሃይሎች ውስጥ ተቀባይነት እንዲኖረው መስራት ነበረባቸው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ፣ በዚህ አካሄድ ፓርቲያቸውን አንድ ማድረግ ቢችሉ ነበር አጣብቂኝ ውስጥ ከመግባት የሚድኑት። ፓርቲውን በአስተሳሰብ አንድ አድርገውት ቢሆን ኖሮ፣ በውስጡ ከሚደረግ ክርክርና ሃሳብ ጥሩ ጥሩ ፖሊሲዎችና ህግጋት ማውጣት ይችሉ ነበር፡፡ ለውጡ ወዴት ይሄዳል? ምንን ያካትታል? የሚለውን ማጥራት የሚቻለው በዚያ መንገድ ነበር፡፡ አሁን የሆነው የኢህአዴግ እውናዊ ባልሆነ መንገድ መፍረስ ነው፡፡  አሁን የፈረሰ ፓርቲ የሚመራው ሀገር ሆኗል። የመጀመሪያው የዶ/ር ዐቢይ ሪፎርም ሊሆን ይገባል ብዬ “በማስጠንቀቂያ ደወል” መጽሐፌ ያስቀመጥኩት፣ ፓርቲውን ሪፎርም ማድረግ ነው፡፡ የፓርቲውን አስተሳሰብ አደረጃጀትና አፈፃፀም ላይ ነበር  የመጀመሪያው የለውጥ አብዮት መፈፀም የነበረበት፡፡ ኢትዮጵያን የሚመራት ፓርቲ መጀመሪያ ራሱ በሃሳብ ውህድ መሆን ነበረበት፡፡ በመጀመሪያ ኢህአዴግ ራሱ ታድሶ፣ ሃገሪቱን መምራት ቢችል ኖሮ፣ አሁን ያለው  መከፋፈልና መበታተን እጅግ በሚያስፈራ ደረጃ አይመጣም ነበር ብዬ ነው የማምነው፡፡
አሁን ግን ዶ/ር ዐቢይ ኢህአዴግን ይመሩታል እንላለን እንጂ በተግባር እየመሩት አይደለም። እያንዳንዳቸው የኢህአዴግን ግንባር የፈጠሩ ድርጅቶች በየራሳቸው መንገድ እየሄዱ ናቸው፡፡ በዚህም የፓርቲው ህልውና የልባስ ነው እንጂ ውስጣዊ የመርህ፣ የአስተሳሰብ አንድነት ጠፍቷል፡፡ ይሄ አሁን የዐቢይ መንግስት የገጠመው ትልቁ ፈተና መነሻ ነው፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግ ተቃውሞ በርቶበት ስለነበረ መፍረሱ እንደ ምስራች ቢወሰድም፣ ለኔ ግን ሁኔታው አስፈርቶኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም የፈረሰ ፓርቲ፣ ብሔር አቀፍ ፌደራሊዝም ላይ ያለችን ሀገር እንዴት እንደሚመራ አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚያ ላይ  የተደራጀ፤ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የተረዳ
ሌላ ሃይል አለመኖሩ፣ ያለውም መናዱ ለኔ እጅግ አስፈሪ የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን የምናያቸውን አስፈሪ የሀገር መናድ ምልክቶች እያሳየን ያለው ይሄው ሁኔታ ነው፡፡ የአስተሳሰብ አንድነት የሌለው የፖለቲካ ሃይል፣ እንደኛ አይነት ባህሪ ያለውን ሀገር መርቶ አንድ ሊያደርግ አይችልም።
ጠ/ሚኒስትሩ አንድ ውህድ ፓርቲ በፍጥነት እንደሚፈጠር መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ይሄ ለችግሩ መፍትሄ ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ?
ውህድ ፓርቲ ከማድረግ በፊት ጠንካራ ግንባር መፍጠር ይቀድማል፡፡ የተጠናከረ ግንባር ሲኖር ነው ውህድ መሆን የሚቻለው፡፡ እየፈረሰ ያለ ግንባር ወደ ውህደት ይሄዳል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ይመስለኛል፤ የማይፈልጉትን ጥሎ በፊት ተቃዋሚ ከነበሩ ሃይሎች ጋር በመሄድ፣ አንድ ሁሉን አቀፍ ኢትዮጵያዊ ፓርቲ እንደ አዲስ እንፈጥራለን ካልተባለ በስተቀር። ይሄም ቢሆን በራሱ ችግር አለው፡፡ መሄድ በኛ ሀገር ፖለቲካ ቀላል አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ከአመሠራረቱም የብሔርተኛ ድርጅቶች ግንባር ስለሆነ፣ ህገ መንግስቱም ይሄን ስለሆነ የሚያውጀው፣ አሁን አንድ ውህድ ፓርቲ ለመፍጠር አስቸጋሪ የሚሆን ይመሰለኛል፡፡
በእርስዎ አመለካከት ከለውጡ የተገኙ ትሩፋቶች ምንድን ናቸው?
በፓርቲው በራሱ ውስጥ ለውጥ እፈልጋለሁ የሚለው ሃይል፣ እንቁላሉን ሰብሮ ሲወጣ፣ ከፍተኛ ለውጥ የታየው ሃሳብን በነፃነት በመግለጽ በኩል ነው፡፡ በተለይ በሚዲያ ነፃነት። ነገር ግን  አሁን የሚዲያ ነፃነትን ፖለቲካው ራሱ ገድቦታል ብዬ ነው የማምነው፡፡ ለምሣሌ የመንግስት ሚዲያዎች ሣይቀሩ፣ የክልልና ብሔር አቀፍ ሚዲያዎች እየሆኑ ነው፡፡ የአማራ ክልል ቴሌቪዥንና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ በፊት የሚሠማው ተመሳሳይ የመንግስት አቋም ነበር፤ አሁን ግን እያንዳንዱ ክልል የየራሱን ክልል መንግስት አቋም የሚያስተጋባበት ሆኗል፡፡ ይህ በመሆኑ እያንዳንዱ የክልል ሚዲያ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት፣ ከሠላም ይልቅ ግጭት እያቀነቀነ ነው፡፡ በሶቪየት ህብረትም ያኔ የሆነው እንዲሁ  ነው፡፡ ሶቪየት ህብረትን ያፈረሱት የክልል ቴሌቪዥን ሚዲያዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ የክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ የየራሱን ክልል ብሶትና እሮሮ ነበር የሚያስተጋባው። በፌደራል መንግስቱ ላይ ያለውን ምሬት ነበር የሚገልፁት፡፡ ማዕከላዊ መንግስቱን በወቅቱ ኮሚኒስት መንግስት ነበር የሚመራው፡፡ ስለዚህ “ጠላታችን ኮሚኒስት ፓርቲው ነው፤ ላለፉት 70 አመታት ይሄን በደል እየፈፀመብን ነበር የቆየው” እየተባለ እያንዳንዱ ክልል ለየራሱ ህዝብ ብሶትና ምሬትን ያስተጋባ ነበር፡፡ በኛም ሃገር አሁን ያለው ሁኔታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሶቪየት ህብረትን ለማፍረስና 15 ሀገር እንድትሆን መንገዱን የደለደለው ይሄ የሚዲያዎች አካሄድ ነበር፡፡ ሶቪየት ህብረት ስትፈርስ፣ 15 ሀገራት በራሣቸው መቆም ችለዋል፡፡ በኛ ሀገር ግን ይሄ መሆን የሚችል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም  አሁን ያሉት ክልሎች ራሳቸውን ችለው፣ እንደ ሃገር መቆም የሚችሉበት በቂ ኢኮኖሚ፣ በቂ የፖለቲካ መዋቅር እንዲሁም በቂ መሰረተ ልማት የላቸውም፡፡ ነገር ግን የክልል ሚዲያዎች የሶቪየትን መንገድ እየተከተሉ ነው፡፡
ሌላው ደግሞ የአክቲቪስቶች ሚዲያ ነው፡፡ ዛሬ ማንኛውም ሰው ሚዲያ ሊኖረው ይችላል። የሚዲያ መመሪያ የለንም፡፡ አክቲቪስቶች ነን የሚሉ ሁሉ ይሄን በመጠቀም፣ የየራሳቸውን ሃሳብና አመለካከት በማዕከላዊ መንግስቱ ላይ ለመጫን እየሞከሩ ነው፡፡ ቀጥሎ ያለው የመንግስት ሚዲያ ነው፡፡ የመንግስት ሚዲያው ከቀድሞው የተለየ አይደለም፤ የሁሉንም ቡድን አስተያየት የሚያስተናግድ ሆኖ አልተገኘም። አሁንም ቢሆን ከመንግስት ጎን የተሰለፉ ሆኗል። የመንግስት ወገንን የፖለቲካ አቋም ብቻ ነው የሚያስተጋባው፡፡ የገደል ማሚቱ ሆኗል፡፡ ሌላው ቀርቶ ቀድሞ የሚዲያው ባለቤት የነበሩ የህወሓት ሃይሎች ሳይቀሩ ከሚዲያ ማዕዱ ተገፍተዋል፡፡ የሚሉት ሳይኖራቸው ቀርቶ ሳይሆን ያለው ሚዲያ  ከእያንዳንዱ ወገን ተፅዕኖ ነፃ ያልወጣ ነው፡፡ ለምሳሌ በብሄርተኞች ሚዲያ ላይ ቀርቦ የአንድነትን ድምፅ ማስተጋባት አይቻልም፤ በዚያው ልክ በአንድነት አቀንቃኞች ሚዲያ ላይ ቀርቦ ስለ ብሄርተኝነት ሃሳብ በሰፊው ለመወያየት አይቻልም፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን በየሚዲያው የሚታየው መፈራረጅ ነው እንጂ በትክክል ችግራችን የቱ ጋ ነው ብሎ በጋራ ችግሩን የመፈለግ ሂደት የለም፡፡ ሁልጊዜ ማጠንጠኛው እኛን ማን ነው የተቃወመው? የሚል ነው፡፡ ጥፋትን የመመርመር ስራ የለም፡፡ ለውጡም የሚጓዝበት ሀዲድ በዚህ መሃል ነው።
ወደ ሶቪየት ህብረት አይነት መበታተን ልንሄድ እንችላለን ብለው ይሰጋሉ?
ሁኔታዎቹ የሚያመለክቱት የሶቪየትን አቅጣጫ ይዘን እየተጓዝን እንደሆነ ነው። ነገር ግን አካሄዳችን በሶቪየት አይነት መንገድ ይደመደማል ወይ ከሆነ ጥያቄው፣ አሁን ያንን ማወቅ አይቻልም፡፡ የኛ የታሪክ አመጣጥ ከምክንያታዊነት ይልቅ ተአምራዊነት ስለሚያመዝንበት፣ በምክንያታዊነት ወደዚህ ነው እየሄድን ያለነው ለማለት አስቸጋሪ ነው፤ ነገር ግን የክልል መንግስታት ፀንተው መቆም እያቃታቸውም፣ እርስ በእርሳቸው እየተወነጃጀሉ ነው፡፡ ማዕከላዊው መንግስት፣ የክልል መንግስታትን መዳኘትና በአንድ አቅጣጫ መምራት እየተሳነው ነው፡፡
በማስረጃ ሊያስደግፉት  ይችላሉ?
ለምሳሌ በአማራና በትግራይ መካከል ያለውን አለመግባባት፣ ህገ መንግስታዊም ሆነ ፖለቲካዊ በሆነ መርህ መነሻነት ችግሩን ለመፍታት፣ የፌደራል መንግስቱ ሲንቀሳቀስ አይታይም። እንደ ሽማግሌ ሊሸመግላቸው ይሞክራል፤ እሱ ሲያቅተው ካህናትና ሽማግሌዎች ይገቡበታል። ሁለቱም አምባ ለአምባ እየተያዩ፣ ለጦርነት ዝግጅት እያደረጉ ባሉበት፣ ምንም ማድረግ ያልቻለ መንግስት ነው፡፡ ይሄ የተናጋ መንግስት ባህሪን ነው የሚያሳየው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ እየተቸገሩ ያለው የሚመስለኝ፣ ለውጡን በመርህ አለመምራታቸው ነው፡፡ ምን ማለት እንዳለባቸውና ምን ማለት እንደሌለባቸው የሚመራቸው መርህ ያላቸው አይመስለኝም። ስለዚህ ከሁሉም ወገን የሚመጣባቸውን ተቃውሞዎች በማሰብ ግልፅ አቋማቸውን ሳያሳውቁ፣ ጊዜ መግዛትን እንደ አማራጭ የሚጠቀሙ ይመስላል፡፡
ወደ ብሔርተኛ አክራሪነት እና አለመተማመን ተገብቷል የሚሉ አሉ የእርሶ አተያይ ምንድን ነው?
ብሄር ድሮም በኢትዮጵያ ውስጥ ነበር፤ነገር ግን ባለፉት 27 ዓመታት ብሔረሰባዊ ማንነት ሲከበርም ሃሳቡን ይዘው የተነሱትና በጫካ ሲታገሉለት የነበሩ ሃይሎችም፣ ዛሬ የተፈጠረው ይፈጠራል ብለው አስበው አይመስለኝም፡፡ የብሄራዊ ማንነት ከተከበረ፣ እያንዳንዱ ራሱን በራሱ ካስተዳደረ፣ እያንዳንዱ የየራሱን ክልል አንጡራ ሃብት መጠቀም ከጀመረ በጋራ በሰላም እንኖራለን፤ የእድገት መንገድ ይከፈታል--  ነው ህልማቸው የነበረው፡፡ ግን በውጤቱ የጠበቁት አልሆነም፡፡ ውጤቱ የሆነው፣ ብሄርተኛነት ሲያከብሩት ይረግባል ከሚለው ይልቅ ሲያከብሩት እየገነነ ይሄዳል የሚለው ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት፣ የየብሄረሰቡ ምሁራንና ልሂቃን ተፈጠሩ፡፡ የየራሳቸውን ክልልና ህዝብ ብቻ ማስተዳደር የሚፈልጉ ሃይሎች ተፈጠሩ። ባለፉት 27 ዓመታት በመጣንበት መንገድ፣ አሁን እያንዳንዱ ጎሳ የየራሱ ልሂቅ አለው፡፡ የየራሱን ጎሳ ፖለቲካ እመራለሁ የሚል እምነት ያለው ልሂቅ ተፈጥሯል፡፡ አሁን ልዩነቶቹን በጣም የሚያራግባቸው ይኸው አዲስ የተፈጠረው ልሂቅ ነው፡፡ ብሔርተኝነት ባለፉት ዓመታት ከሚገባው በላይ ትርጉም ተሠጥቶታል። የራሱ የክልል ህገ መንግስት አለው፤ አለፍ ሲልም የታሪክ ትርክትንም አምጥቷል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ የጋራ ታሪክ ነበረን፡፡ አሁን እያንዳንዱ ብሔር ላለፈ ዘመን ማንነትና ታሪክ፣ የየራሱን ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ብሔርተኝነት አሁን የመጨረሻው አስከፊ ጫፍ ላይ ይገኛል። ይሄንን ለማስተዳደር ደግሞ የተዘጋጀ ግልፅ አቋምና ፅናት ያለው አመራር ሥልጣን ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡ ሁኔታዎችን ተጠቅሞ በቀጭን ገመድ ላይ እየተራመደ፣ መሻገር የሚፈልግ አመራር ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ አሁን ያለው አስተዳደር ግልፅ አቋም ለመያዝ የተቸገረ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ነው ብሎ እውቅና ከሰጠ፣ ከኦሮሞ ብሔርተኞች ተቃውሞ እንዳይነሳ ይሰጋል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞችን አቋም በቀጥታ ከደገፈና እውቅና ከሰጠ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ድንገተኛ ተቃውሞ ይፈራል፡፡ ስለዚህ በቀጭን ገመድ ላይ እየተራመደ፣ ዝም ብሎ ሁኔታዎችን እያባበለ፣ መልስ ሳይሰጥ፣ አሳድሮ መሻገርን እንደ ስልት የሚከተል  አመራር ነው ያለው፡፡ በሁሉም ጉዳዮች ይሄን መንገድ ነው የሚከተለው፡፡ ለምሳሌ የሲዳማን ጥያቄ ብንመለከት፣ ለሲዳማ መልስ ብሰጥ፣ ሁሉም ብሄሮች ተነስተው ክልል ልሁን ይሉኛል፤ ሲዳማ ክልል መሆን አይችልም ካልኩ ደግሞ የሲዳማ ህዝብ ተቃውሞ ይፈጥርብኛል የሚል ስጋት ስላለው፣ በውጥረቱ መሃል ችግሮችን ለነገ እያሳደረ  መጓዝን የመረጠ መንግስት ነው፡፡ በአማራና በትግራይ መካከል ያለው የወልቃይት ጉዳይም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ብዙ ነገሮችን አቋም ሳይዙ እያባበሉ ለነገ እያሳደሩ፣ መጓዝን ምርጫው ያደረገ መንግስት ነው አሁን ያለው፡፡
ይሄ ችግሮችን  ለነገ እያሳደሩ የመሄድ ጉዳይ፣ ምን ውጤት ያስከትላል ይላሉ?
አንድን ችግር በበቂና በወቅቱ መፍታት ካልተቻለ፣ ማዕከላዊ መንግስቱ እንደ መንግስት መቆም እንዳያቅተው እፈራለሁ፡፡ ሁሉም ጥያቄያችንን አሁን መልስ ይላሉ፡፡ ከዚህ የተነሳና በማሳደሩ ምክንያት ከሚመጣ መናድ ለመዳን፣ ለጥያቄዎች በመርህ ላይ የተመሰረተ ምላሽ መስጠት ያለበት ይመስለኛል፡፡ እሱን ለማድረግ ደግሞ በመጀመሪያ ተከፋፍሎ ያለውን ገዥ ፓርቲ፣ ወደ ሃሳብ አንድነት ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ያለፈውን ችግር በጋራ ወስዶ፣ የወደፊቱን መፍትሄ በጋራ መፈለግን ይጠይቃል። ይሄን ማድረግ ካልቻለ ግን ማዕከላዊ መንግስቱ አጠቃላይ ቀውስ ውስጥ ይገባል። አንዳንድ ሃገሮች ያጋጠማቸው ከባድ ቀውስ ማስተማሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ዩጎዝላቪያ ያሉ ሃገሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ብሔርተኝነቱና አክራሪነቱ እየበረታ ሲሄድ፣ ወደ በቀልተኛነት ተገብቶ፣ የከፋ ሁኔታ እንዳይገጥመን ያሰጋል። አሁንም ለራሳችን ችግር የራሳችንን መፍትሄ መፈለግ ይቻላል፡፡ ዲሞክራሲው መጀመር ያለበት ገዥው ፓርቲ መዋቅር ውስጥ ነው፡፡ ይሄ ካልተጀመረ ሁሉም ለየራሱ የጎበዝ አለቃ እየሆነ ነው የሚሄደው፡፡ ይሄ አደገኛ አዝማሚያና ውጤትን ነው ይዞ የሚመጣው፡፡
አክራሪ ብሔርተኛ ሃይሎች መንግስት የሚሆኑበት  እድል ይኖራል ብለው ያስባሉ?
አክራሪ ብሔርተኛ ሃይሎች ማዕከላዊ መንግስቱን ተቆጣጥረው፣ ኢትዮጵያን መምራት እንደማይችሉ እነሱም ያውቁታል፡፡ ምናልባት ከሁሉም የተውጣጡ አክራሪ ሃይሎች፣ ግንባር ወይም ቅንጅት ቢፈጥሩ፣ የሚያጋጥማቸው ተቃውሞ ሊጠብላቸው ይችል ይሆናል፡፡ አሁን እርስ በእርሳቸውም ልዩነት አላቸው። ለምሳሌ የኦሮሞ አክራሪ ብሔርተኞች ወደ ስልጣን እንምጣ ቢሉ፣ ከሁሉም ተቃውሞ ነው የሚጠብቃቸው፡፡ ስለዚህ በስልጣን ላይ ፀንተው መቆየት አይችሉም፡፡ አሁን ኢትዮጵያዊነትን ሳይዙ በስልጣን ላይ መቆየት አይቻልም፡፡ እርግጥ ነው የብሄር ፖለቲካን በዚህ ዘመን ሙሉ ለሙሉ መጣል አይቻልም፤ ነገር ግን የግለሰብን የብሄርን ማንነት አብሮ ይዞ፣ ኢትዮጵያዊነትን ፕሮጀክት ማድረግ ይቻላል። ብሔርተኝነትን አክብሮ፣ ብሔር የለኝም የሚለውንም አክብሮ የሚሄድ የፖለቲካ አውድ መፍጠር ከተቻለ፣ ኢትዮጵያዊነት እንደ አዲስ መነሳትና መቀጠል ይችላል፡፡ መንግስት አሁንም ስላለፈ ማንነታችን፣ ዛሬ ስለቆምንበት፣ ወደፊት ስለምንሄድበት ሁኔታ ግልጽ አቋም ሊኖረው ይገባል፡፡ ምሁራን ባለፉ ታሪኮቻችን መከራከር መወያየት ይችላሉ፤ መንግስት ግን ግልጽ አቋም ይዞ ነው መሄድ ያለበት፡፡
አሁን የሃገሪቱ ፖለቲካ ከተስፋ ወደ ስጋት እያመራ ነው ከዚህ ስጋትና አጣብቂኝ የመውጫ መንገዶች ምንድንናቸው?
በመጀመሪያ ኢህአዴግ የርዕዮተ አለም ቀውስ ውስጥ መግባቱን መረዳት አለበት፡፡ ርዕዮተ አለማዊ አስተሳሰቡ ልክ ነበር ወይ? ልክ ካልነበረ የቱ ጋ ነው ስህተቱ? የሚለውን ማየት አለበት። ስትራቴጂዎችን ስናስፈጽም ምን ጉድለት ገጠመን? የሚለውን መገምገም ይኖርበታል። በሌላ በኩል፣ በራሱ ውስጥ  ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ግንኙነት መፍጠር ያልቻለ ፓርቲ የሀገር አንድነት ሊያመጣ አይችልም፡፡ ከኢህአዴግ ግንባር ውስጥ ለውጡን በተለያየ መንገድ የማይቀበሉ ሃይሎችን እያራገፉ በሃሣባዊ አንድነት የተጣመሩ የለውጥ ሃይሎችን ይዞ መሄድ መቻል ያስፈልጋል፡፡ ችግራችን ምን ነበር? ወዴት ነው የምንሄደው? አሁን ምን ላይ ነን? በሚለው ላይ ግልጽ የሆነ ፍሃተ ካርታ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ ሚካኤል ጐርባቾቭ እኮ ሊያመጡ ስለሚፈልጉት ለውጥ፣ ስለሚሄዱበት አቅጣጫ ግላስኖስ እና ፕሪስቶሪካ በሚል ግልጽ አቅጣጫ ነበረው፡፡ ግላስኖስ የዲሞክራሲ ሪፎርም ነው ፕሪስቶሪካ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሪፎርም አቅጣጫ ነበር፡፡ ያንን ሁሉ አድርገው ነው ሚካኤል ጐርቫቾቭ አልተሳካላቸው፡፡ አሁን ደግሞ እኛ ከተወሰኑ መፈክሮች ያለፈ ምን ነበር የተበላሸው? ምንድን ነው የምንፈልገው በሚለው ላይ ብያኔ ያለው የአስተሳሰብ ሁኔታ የለም፡፡ የዶ/ር ዐቢይ አመራር በመጀመሪያ ይሄን በማጥራት ላይ ነው መሄድ ያለበት፡፡
ይሄን ቢያደርጉ ነው ሀገር ማዳን የሚችሉት። ሀገሩን እየመራ ያለው ድርጅት ሽፈራው ሀገሩን ይዞ ሊጠፋ ይችላል፡፡ ዲሞክራሲ ደግሞ በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ ከጀመረ ሀገርን ማዳን ይችላል፡፡ እኔ ይሄን የምለው ኢህአዴግ ፍቅር ስላለኝ አይደለም፡፡ ማን ነው የሚረከበው ብዬ ሳስብ ነው፡፡ ኢህአዴግ በውስጡ ያለውን ችግር ፈትቶ ራሱን ማጥራት ሲጀምር የሀገሪቱ ችግርም እየተቃለለ ይሄዳል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በራሱ የተመመ ፓርቲ ግን ለሌሎች ጤንነት ያመጣል ብዬ ለማመን ይቸግረኛል፡፡ አሁን ፀረ ዲሞክራሲያዊነት ያለው በኢህአዴግ ውስጥ ነው፡፡ ፀረ ዲሞክራሲየዊነት አምባ ለአምባ ሆኖ ለመታኮስ መቋመጥ ነው፡፡ ፀረ ዲሞክራሲያዊነት መሽጐ መካሰስ ነው አሁን በድርጅቱ ውስጥ እየታየ ያለው፡፡
በዚህ ሁኔታ በቀጣይ ምርጫ ራሱ ኢህአዴግ እንዴት እንደሚቀርብ አላውቅም፡፡      

Read 806 times