Saturday, 23 March 2019 12:57

ቃለ ምልልስ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው - በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 • የትግራይና አማራ ህዝቦች ወደ ግጭት እንዲገቡ ማድረግ የለየለት እብደት ነው
            • በቴሌቶኑ ኢትዮጵያዊ ፍቅርንና አንድነትን የሚያጎላ ድጋፍ ተደርጓል
            • አዴፓ እና ኦዴፓ ሆድና ጀርባ ሆነዋል የሚባለው ምኞት ነው  

            ከ10 ዓመት በላይ የአማራ ክልላዊ መንግስትን ያስተዳደሩትና ከለውጡ መሪዎች አንዱ የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ላይ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው ይታወቃል፡፡ የማንበቢያና የማሰቢያ ጊዜ እንደሚፈልጉ የሚናገሩት አቶ ገዱ፤ከሥልጣን ቢለቁም ለውጡ እንዲሳካ ከመሥራት ወደ ኋላ እንደማይሉ ጠቁመዋል፡፡ አሁን በእረፍት ላይ የሚገኙት የቀድሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር፤ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር በተለያዩ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ላይ፣ በአዴፓና ኦዴፓ ወቅታዊ ግንኙነት፣ በወልቃይትና ራያ ውዝግብ፣ እንዲሁም በአማራና ትግራይ ክልል ፍጥጫ ዙሪያ ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡


            የአገሪቱን ወቅታዊ  የፖለቲካ ትኩሳት እንዴት ይገመግሙታል?
አገሪቱ ሁለት ዓይነት የፖለቲካ ገፅታ ባለው ሁኔታ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ በተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በአንድ ዓመት ይሰራል ተብሎ የማይገመት ብዙ ሥራ ተከናውኗል። የአገሪቱን የቆዩ ችግሮች ለማስተካከል ብዙ ውሳኔዎችና የማስተካከያ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ይሄ የፈጠረው በጎ ነገር አለ። በአገራችን ውስጥ የነፃነት ስሜት እንዲዳብር፣ ዜጎች የመሰላቸውን ሀሳብ በፅሁፍ፣ በቃልና እነሱ በፈለጉት መንገድ የሚገልፁበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይሄ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አኳያ ትልቅ እርምጃ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡ ማንኛውም በአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ዜጋ አስተዋፅኦ ያበርክት የሚል ጥሪም ተደርጓል፡፡ በዚህ ጥሪ መሰረት ተሰዶ የነበረው ተመልሷል፣ ተደብቆ የነበረው ወጥቷል፣ ታስሮ የነበረው ተፈትቷል፡፡ በተለይ አንቺም እንደምታውቂው፣ ሚዲያ አካባቢ ብዙ የተጨናነቁ ነገሮች ነበሩ፤ አሁን የተስተካከሉበት መንገድ አለ። በአጠቃላይ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፊ እንዲሆን፣ የለውጡ እንቅስቃሴ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል። ከዚህ ተነስቶ ነፃነት ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡ ያሳደረው ተስፋ አለ፡፡ አገራችን ከቆየው ፖለቲካዊ ችግሮቿ ትላቀቃለች የሚል ተስፋ ዜጎች አሳድረዋል፡፡ እርግጥ ዴሞክራሲ ተቋማዊ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር መልካም አጋጣሚ ነው፡፡
በሌላ መልኩ ይህንን መልካም አጋጣሚ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ከመምራት አኳያ ብዙ ተግዳሮቶች ተፈጥረዋል፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች የሚመነጩት በአገራችን ውስጥ የፖለቲካ ባህላችን በጣም ዝቅተኛና ኋላቀር በመሆኑ፣ ይሄ የወለደው ከጥላቻና ከዘር ፖለቲካ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያዊያን በጋራና በአንድነት ለማደግ ከማሰብ ይልቅ ሁሉም የየራሱን ጥግ እንዲይዝ ለረጅም ጊዜ የተሰራ የጥላቻ ፖለቲካ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይሄ ደግሞ የወለደው የፅንፈኝነት አመለካከት አለ፡፡ ይህ ጉዳይ አገሪቱን ፈተና ውስጥ የከተተበት ሁኔታ በግልፅ ይታያል። ለዴሞክራሲ ባህል ማደግ እንቅፋት የሆነው ይኸው ፅንፈኝነት፤ ሰዎች በሀሳባቸው፣ ባላቸው አመለካከትና አቋም የሚመዘኑበት ሳይሆን በአብዛኛው በብሔር መነጽር የሚታዩበት ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ በዚህ ምክንያት ለሰው ልጆችና ለሰብአዊነት ያለው አክብሮት የማነስ፣ የመኮሰስና የመጥበብ ደረጃ ላይ አድርሶታል። አገሪቱን ወደፊት የሚያራምድ የጋራ አጀንዳ ይዞ ከመንቀሳቀስ ይልቅ የብሔር ቀሚስ ውስጥ የመደበቅ፣ የጠበበ አመለካከት የአገሪቱ የወቅቱ ፈተና ሆኗል፡፡ እንዲህ ዓይነት ተግዳሮት የአገር ችግሮችን ለመፍታት የማስተካከያ እርምጃ በሚወሰድበት የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ማጋጠሙ አይቀሬ  ነው። ግን ይሄ ተግዳሮት  ለረጅም ጊዜ  እንዳይቀጥልና ሀይል እያሰባሰበ እንዳይሄድ፣ አገራዊ መግባባትና እርቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡  
የለውጡ መሪዎች እየተባሉ ስማቸው በጋራ የሚጠራው  የአማራው አዴፓ እና የኦሮሞው ኦዴፓ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግንኙነታቸው እየሻከረ መምጣቱንና ሆድና ጀርባ የመሆን አደጋ እንደተጋረጠባቸው የሚናገሩ የፖለቲካ ተንታኞች  አሉ፡፡ እርስዎ  ምን ይላሉ?
የአዴፓና ኦዴፓ ጥምረት መሰረቱ፣ የጥቂት አመራሮችና ኃላፊዎች ፍላጎት ብቻ አይደለም። ከዚያም በላይ የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ግንኙነት በታሪክም ረጅምና ሰፊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩም ጠንከር ያለ በመሆኑ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ እነዚህ ሁለት ህዝቦች ከማንኛውም ህዝብ በላይ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸውና በብዙ ነገር የተጋመዱ ሆነው እያሉ፣ የነበረው የፖለቲካ የተሳሳተ እይታና ፕሮፓጋንዳ፣ ሁለቱን ህዝቦች በጥርጣሬ ውስጥ እንዲወድቁ ያደረገ ሁኔታ እንደነበር ሁላችንም የምንገነዘበው ነው፡፡ አሁን የሁለቱ ህዝቦች አመራሮች፣ ዋነኛው ትስስራቸው፣ ከፓርቲና ከፖለቲካ ጉዳያቸው ባሻገር፣ እነዚህ ሁለት ህዝቦች እውነተኛና ተፈጥሯዊ የሆነው ግንኙነታቸው፣ በትክክለኛ ገፅታው እንዲገነባና ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር ምስል እንዲያሳዩ ማድረግ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ህዝቦች፣ የኢትዮጵያ አብዛኛውን ህዝብ ቁጥርም የያዙ  ናቸው፡፡ የእነዚህ ህዝቦች ጤናማ ግንኙነት መዳበር፣ የኢትዮጵያን ችግር ከመፍታት አኳያ፣ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ፓርቲ ለፓርቲ ብቻ ሳይሆን ህዝብ ለህዝብ ያለው ግንኙነት፣ በተዛባና በተረት ተረት ትርክት ላይ ተመስርቶ፣ ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቁ የሚደረግ አካሄድ መቀየር አለበት የሚል እምነት ስለተያዘ፣ ያለፉ ታሪኮች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተጠንተው፣ ግንኙነታቸውን ማጎልበት ይቻላል፡፡ ለሰፊው የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ካለፈው በላይ የወደፊቱ አብሮነትና አንድነት ነው የሚበጃቸው፡፡ እነዚህ ህዝቦች በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው፣ በተፈጥሮ ሀብታቸው ጭምር ኢትዮጵያን ወደፊት ለማሻገር ትልቅ አቅም አላቸው፡፡
እነዚህን ህዝቦች ወደ ጠንካራ አንድነት የማምጣት ጉዳይ ነው ይበልጥ ሊተኮርበት የሚገባው፡፡ ታዲያ ይህ ትልቅ ሀሳብ ሲወጠን፣ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ምክንያቱም የቆየውን ታሪክ እናንተም ታውቁታላችሁ፡፡ ሲሰራ የነበረውም ጉዳይ አለ፡፡ እናም ከዚህ ተነስተን ነው የአማራ ዴሞክራቲክ ፓርቲና የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ወይም የቀድሞዎቹ ብአዴንና ኦህዴድ አመራሮች፣ በጥምረት ተግባብተን ለመስራት፣ የጋራ አቋም ይዘን ስንንቀሳቀስ የቆየነው፡፡ ይህ ሁኔታ አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡
በእርግጥ ይህ ግንኙነት እንዲሻክር ሆን ብለው የሚሰሩ አካላት እንዳሉ አውቃለሁ። ኦሮሞ ሳይሆኑ በኦሮሞ ስም፣ አማራም ሳይሆኑ በአማራ ስም ተደራጅተው፣ በየጊዜው ስሜታዊ የሚያደርጉ አጀንዳዎችን በማንሳትና በመቀስቀስ፣ በሁለቱም ህዝቦች ውስጥ ያሉ ፅንፈኞችን እንዲናቆሩ በማድረግ፣ በህዝቦቹና በፓርቲዎቹ መካከል ጥርጣሬ እንዲያድር የሚያደርጉ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ ነው። በእኛም በአመራሮቹ ድክመት፣ በተለያዩ አፈፃፀሞች የሚደረጉ ክፍተቶችን በመጠቀም፣ ግንኙነቱ እንዲሻክር፣ የፈጠራ ፕሮፓጋንዳዎች እየተፈበረኩ የሚነዙበት አጋጣሚ አለ፡፡ የሆነ ሆኖ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አሁንም በጋራ ነው የምንሰራው፤ እኔ አስከማውቀው ድረስ እንደ ኢህአዴግም ሆነ በሁለቱ ፓርቲዎች አመራር  ደረጃ፣ ዋና ዋና የሚባሉ ውሳኔዎች በጋራ ነው የሚወሰኑት፡፡ እየተመካከሩ አቅጣጫ በማስቀመጡም በኩል በጋራ ነው እየሰሩ ያሉት፡፡ እናም አዴፓና ኦዴፓ ሆድና ጀርባ ሆነዋል የሚለው አባባል ምኞት ነው፡፡ ሁለቱን ድርጅቶች ሆድና ጀርባ ሊያደርግ የሚችል አጀንዳም የለም፡፡
በነገራችን ላይ የአማራንና የኦሮሞን ህዝብ ሊያናቁር የሚችል ምንም አጀንዳ የለም፤ ሆን ተብሎ ካልተፈጠረ በስተቀር፡፡ የሁለቱ ህዝቦች ዋነኛ አጀንዳ ከድህነት መውጣት ነው፡፡ የህዝቡ ፍላጎት፣ የኢትዮጵያን የህዝብ የሚያከብር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ማድረግ ነው፡፡ ፓርቲዎቹም የህዝቦቹ ነፀብራቆች ናቸው፡፡ በሂደት ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፤ በምክክርና በውይይት ይፈታሉ፡፡ ከዚህ ውጭ ፓርቲዎቹ ሆድና ጀርባ ይሆናሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህ ምኞት ሊኖር ይችላል፤ ግን የሚሳካ ምኞት አይደለም፡፡
በአሁኑ ወቅት የአማራና ትግራይ ክልል የጦርነት ፍጥጫ ላይ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ የአማራ ክልል የደህንነትና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ጀነራል አሳምነው ፅጌም፤ “የትግራይ ክልል ጦርነት ሊያውጅብን ነው” ብለው እስከ መናገር ደርሰዋል፡፡ እርስዎም ስልጣንዎን ባስረከቡበት ዕለት “ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው፤ ታሪክና ባህል የሚጋሩ ናቸው፤ የትኛውም አካል ጦር ከመማዘዝ መታቀብና ወደ ውይይት መቅረብ አለበት” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ የሁለቱ ክልሎች ፍጥጫ መንስኤ ምንድነው? ከአወዛጋቢዎቹ የወልቃይትና ራያ ጉዳይ ውጭ ሌላ  ችግር አለ እንዴ?
አሁንም አበክሬ መግለፅ የምፈልገውና ሁሉም የሚገነዘበው፣ የአማራና የትግራይ ህዝብ በታሪክ፣ በሃይማኖትና በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኢኮኖሚ ትስስርና በበርካታ ጉዳዮች ሊገለፁ የሚችሉ መልካም ግንኙነቶች ያላቸው ህዝቦች ናቸው። እነዚህ ህዝቦች ወደ ግጭት እንዲገቡ ማድረግ የለየለት እብደት ነው፡፡ ይህንን ጤናማ አዕምሮ ያለው ሰው ያደርገዋል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም እነዚህ ህዝቦች በጦርነት መከራ ያዩ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ ከጦርነት አትራፊነትም የለም፡፡ ጦርነት ሰው ይበላል፤ ጦርነት ኢኮኖሚ ያወድማል፣ ጦርነት በአሁኑ ብቻ ሳይሆን በቀጣዩ ግንኙነት ላይ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል፡፡ እነዚህ መልካም ግንኙነት ያላቸው ህዝቦች በዚህ ረገድ ጦርነት ውስጥ ይገባሉ ብዬ አላምንም። በህዝቡ መካከል ለጦርነት የሚያበቃ አጀንዳ የለም፡፡ አንቺም እንዳነሳሽው ከወልቃይትና ከራያ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ። እነዚህ ደግሞ በጦርነት የሚፈቱ ችግሮች አይደሉም። የወልቃይትና የራያ ጉዳይ የፖለቲካ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ፖለቲካዊ ችግሮችም ናቸው፤ ለነዚህ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችና ችግሮች ዘላቂ መፍትሄው፣ ፖለቲካዊ ውሳኔና ፖለቲካዊ መልስ እንጂ ጦርነት መፍትሄ ሊሆን አይችልም። የመጀመርያው ጉዳይ፣ ህዝቦቹ እያሉ ያሉት ምንድን ነው የሚለው ነው፡፡ እስኪ ነፃነት ሰጥተን እናድምጣቸውና ፍላጎቸውን እንረዳ፡፡ ይህ ጉዳይ የሁለት አገር ህዝቦች ችግር አይደለም፤ በአንድ አገር ያሉ ሁለት ወገኖች ችግር እንጂ፡፡ ይሄ ጉዳይ የሁለቱን ህዝቦች ፍላጎት መሰረት አድርጎ፣ መፍትሄ የሚያገኝ እንጂ ጦር የሚያማዝዝ ጉዳይ አይደለም፡፡
ታዲያ ለምንድን ነው ውጥረቱን ማርገብ ያልተቻለው?
በተካሄደው የለውጥ እንቅስቃሴ ተጎድተናል ብለው የሚያስቡ ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች  የሚያራምዱት የስጋት መንፈስ አለ፤ እናም የትግራይን ህዝብ “የአማራ ህዝብ ሊወርርህ ነው” በማለት ህዝቡ በስጋት ውስጥ እንዲወድቅ የሚያደርግ ቅስቀሳና ግፊት እንዳለ እናውቃለን፡፡ ሁለተኛው ከወደኛም በኩል ያልተገሩ፣ በሽፍትነት የቆዩም፣ ዝም ብለው  የሚናገሯቸው ነገሮች አሉ፡፡ የትግራይን ህዝብ ወደ ስጋት ሊያስገቡ ይችላሉ፡፡ ከወዲያ በኩል የአማራን ህዝብ ስጋት ውስጥ የሚጥሉ ቅስቀሳና የፕሮፓጋንዳ ስራዎች አሉ፤ መታረም አለባቸው። በኛ በኩል ጉዳዩን አንስቶ የሚተነኩስ አካሄድ መታረምና መቆም አለበት ብለን በይፋ ደጋግመን ገልፀናል፡፡ በዛኛው በኩል ጦርነት የሚፈልግ ወይም በግጭት ውስጥ ራሱን ማቆየትና ማትረፍ የሚመኝ ቢኖርም፣ በህብረተሰብ ደረጃ የትግራይ ህዝብ፣ ከኤርትራ ጋር በምን ዓይነት ሁኔታ እንደቆየ እናውቃለን፡፡ አሁን ደግሞ ከወንድሙ ከአማራ ህዝብ ጋር ልታጋጩን ነው ወይ የሚል በጎ አመለካከት በህብረተሰቡ ውስጥ እንደሚንፀባረቅ እናምናለን፡፡ የአማራ ህዝብ ከትግራይ ህዝብ ጋር ጦርነትም ግጭትም አይፈልግም፡፡ ምናልባት በትንንሽ ቅስቀሳዎችና ትንኮሳዎች፣ ከወንድማችን የትግራይ ህዝብ ጋር እንዳንጋጭ እያልን፣ ሁልጊዜም በየመድረኮቻችን እናሳስባለን፡፡
የሁለቱ ህዝቦች የፖለቲካ አመራሮች የአመለካከት ልዩነት ሊኖረን ይችላል፡፡ በለውጡ አካሄድ ላይም ያለን አመለካከት የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ ምንም ችግር የለውም፡፡ በክርክር በውይይትና በመሰል መድረኮች ንግግር እየተደረገ የሚሆነው ይሆናል፡፡ ከህዝቡ 55 እና 56 በመቶው፣ ከድህነት ወለል በታች ነበር። ባለፉት 20 እና 25 ዓመታት በተሰራ ስራ፤ ይሄ ቁጥር በሁለቱም ክልሎች ወደ 25 እና 26 በመቶ ወርዷል፤ ነገር ግን አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ድሆች አሉ፡፡ ዋናው አጀንዳ ከድህነት መውጣት ነው፡፡ ከድህነት ለመውጣት ደግሞ አስተማማኝ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ከሰላም ሁለቱም ህዝቦች ይጠቀማሉ፡፡ በሚጠቅመው ላይ አትኩሮ መስራት ተገቢ ነው፣ ይሄ ደግሞ ለሁለቱ ህዝቦች ይጠፋቸዋል ብዬ ስለማላስብ፣ ወደ ጦርነት ይገባሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡
በህገ መንግስቱ አንቀጽ 49፤ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ መሆኗ የተደነገገላት አዲስ አበባ፣ የወቅቱ የውጥረት መንስኤ ሆናለች። “አዲስ አበባ የኛ ናት” በሚል ከኦሮሚያ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች የሚደረገው  ወከባና ጫና፣ በመላ አገሪቱም ሆነ በውጭ የተለያዩ ንቅናቄዎችን አስነስቷል፡፡ እንደ አዴፓም ሆነ እርስዎ በግልዎ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ አቋማችሁ  ምንድን ነው?
አዲስ አበባ፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ በጥረታቸው የገነቧት ከተማ ናት። በሌላ በኩል፤ ይህቺ ከተማ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ ናት፤ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ማዕከልም ነች። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሁሉም ህዝቦች ተቀላቅለው የሚኖሩባት ትንሿ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በአዲስ አበባ ላይ “ይገባኛል፣ የእኔ ናት” በሚል የሚፈጠር ውጥረትን የምመለከተው፣ እንደ ኋላቀር የፖለቲካ አመለካከት ነው፡፡ እንደ እኔ እምነት፤ አዲስ አበባ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ግንባታ በሞዴልነት የምታገለግል፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ተቃቅፈውና ተደጋግፈው በሰላም የሚኖሩባት እንዲሁም ህዝቡ በሚመርጣቸው መሪዎች የምትመራ፣ ሰላም የሰፈነባትና የህግ የበላይነት እውን የሆነባት የአገራችን መዲና ብቻ ሳትሆን የአፍሪካም መዲና ናት፡፡ ከዚህ ውጭ “ከተማዋ የእንትና ናት፣ የእኔ ናት” የሚለው ጉዳይ በአግባቡ መታየት የሚገባው ነው፡፡ እኔ አጀንዳ መሆን አለበት ብዬም አላምንም፡፡ በህገ መንግስቱ ለኦሮሚያ የተቀመጠ መብት አለ፡፡ ይሄ ደግሞ አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሀል ላይ በመሆኗ፣ ክልሉና ከተማ አስተዳደሩ የሚኖራቸው ግንኙነት ምን መሆን አለበት በሚል በጥልቅ የተደነገገ ድንጋጌ ነው። ይህ ድንጋጌ ሁለቱን ተጠቃሚ የሚያደርገው በምን መልኩ ነው በሚለው ላይ መመካከር ይቻላል፡፡ በከተማ አስተዳደሩና በክልሉ መካከል ወደ ቅራኔ የሚያስገባ የጥቅም ግጭት አለ ወይ? ብሎ ትዕግስት በተሞላበት አካሄድ፣ ህግና ሥርዓትን መሰረት አድርጎ መታየት አለበት። በተረፈ ነገሮችን ማጯጯህ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ይሄ ጉዳይ አዴፓም፣ ኦዴፓም፣ ኢህዴግም እንደ ፓርቲና ሌሎች ፓርቲዎችም ስለሚመለከታቸው በምክክር መፍታት እንጂ “አዲስ አበባ የእከሌ ናት፤ የእንትና ናት” እያሉ ነገር ማራገብ ለፅንፈኝነት ፖለቲካ እውቅናና ድጋፍ መስጠት እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም። ሳጠቃልለው፤ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ህዝቦች በላባቸው የገነቧት፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብሮነት ማሳያና የአገራችን የኢኮኖሚ ማዕከል ናት፤ አስተዳደሩም አካሄዱም ለዚህ የሚመጥን መሆን አለበት ብዬ ነው የማምነው፡፡
በመላ አገሪቱ በርካታ የዜጎች መፈናቀል ተከስቷል። በአማራ ክልል የተፈናቀሉ ቁጥራቸው 93 ሺህ ያህል ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን 1.5 ቢ. ብር ለማሰባሰብ፣ ባለፈው ቅዳሜ በሸራተን ቴሌቶን አዘጋጅታችሁ ነበር፡፡ ውጤቱ እንዴት ነው? ቴሌቶን ያዘጋጃችሁት ተፈናቃዮቹን መልሶ ማቋቋም፣ ከአማራ ልማት ማህበር (“አልማ”) እና ከክልሉ አቅም በላይ ሆኖ ነው?
በአማራ ክልል ውስጥ የመፈናቀል ችግር የገጠማቸው ወገኖቻችን አሉ፤ እውነት ነው። እንዳልሽው ቁጥራቸውም 93 ሺህ ያህል ነው፡፡ በአገራችን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ የመፈናቀል ችግር ያልደረሰበት የለም፡፡ ይሄ እንግዲህ የፖለቲካችን በሽታ ውጤት ነው፡፡ በህብረተሰቡም ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ ግልፅ ነው፡፡ ለመፈናቀሉ ዘለቄታዊ መፍትሄ ይሆናል ብዬ የማምነው፣ የጥላቻን ፖለቲካ ከስሩ የምንነቅልበትን መንገድ ስንሰራ ብቻ ነው፡፡ የጥላቻ ፖለቲካ ካልተወገደ፣ የአሁኖቹን መልሰን ብናቋቁም፣ ነገ ሌላ ተፈናቃይ መኖሩ አይቀርም፡፡ ተፈናቃዮቹን በተመለከተ የአማራ ክልል ተፈናቃዮች፤ ከተለያየ ቦታ የተፈናቀሉ ናቸው፡፡ የተወሰኑት በጊዜያዊ መጠለያዎች፣ ግማሾቹ ከዘመዶቻቸው ተጠግተው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ይህ መፈናቀል በተፈጠረበት ጊዜ የክልሉ መንግስት ወዲያውኑ በሚችለው የምግብ፣ የውሃና የጤና አገልግሎት አቅርቦት ለመስጠት ጥረት አድርጓል፤ አሁንም እየተደረገ ነው ያለው። መፈናቀል በተለይ በእኛ ክልል በተለያየ ጊዜ ይከሰታል፡፡ አንዳንዶቹን ከተፈናቀሉባቸው ክልሎች አመራሮች ጋር በመመካከር ወደነበሩበት ስንመልስ፣ ሌሎቹን በክልላችን ስናቋቁም ቆይተናል፡፡ ባለፈው አመት በተለይ ከቤኒሻንጉልና ከምዕራብ ኦሮሚያ ነበር የተፈናቀሉት፡፡ የሚመለሱትን አስተማማኝ ሰላም መኖሩን አረጋግጠን ስንመልስ ቆይተናል፤ ያልተመለሱም ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ በዋናነት በክልሉ በነበረው ግጭት በርከት ያሉ ተፈናቃዮች መጥተዋል። እነዚህ ወገኖች ከሞቀ ቤትና ኑሯቸው  ሲፈናቀሉ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋልና የክልሉ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ ሲሰጥ ነው የቆየው፡፡ ፌደራል መንግሥትም ለሌሎች ክልል ተፈናቃዮች እንደሚያደርገው፣ ድጋፍ የሰጠበት ሁኔታ አለ። በዚህ መልኩ ሲሰራ ነው የቆየው፤ ይሁን እንጂ በተለይ አንዳንዶች ቤታቸው የወደመባቸው አሉና፣ በመንግስት በጀት ብቻ ሁሉን ማድረግና ማሟላት አይቻልም፤ ህብረተሰቡ በዚህ ጉዳይ መሳተፍ ስላለበት፣ የንግዱ ህብረተሰብን ጨምሮ ሁሉም ለወገኖቹ አለሁላችሁ ብሎ በሞራልም በቁሳቁስም፣ በገንዘብም ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለን ስላመንን፣ ቴሌቶኑን አዘጋጅተናል፡፡ ይሄ በአንድ በኩል መንግስትንም ማገዝ ነው፡፡
“አልማ” ይህንን ከባድ ችግር ይሸከማል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እስካሁንም የክልሉ መንግስት ነው ድጋፍ ሲያደርግ የነበረው፡፡ አልማ በቴሌቶኑ ላይ እንደ አንድ ተቋም፣ ህዝቡን በማንቀሳቀስ በኩል ከፍተኛ ስራ ሰርቷል እንጂ ይህንን ሸክም መሸከም አይችልም፡፡ በቴሌቶኑ ከማህበረሰቡ የተገኘው ምላሽ በጣም አስደሳች ነው፡፡ እነዚህን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም፣ በተለይ ከክልሉ ለተፈናቀሉት ወሳኝ ድጋፍ ነው፡፡ አሁን ላይ ክልሉ የተረጋጋ በመሆኑ በአንድ ጊዜ መልሰው እንዲቋቋሙ እየተደረገ ነው። ለቤት መስሪያም ሆነ ምግብና ውሃ ክልሉ እያቀረበ ይገኛል፡፡ እንደ ግብ የተያዘው ተፈናቃዮቹ የእርሻ ስራ ከመጀመሩ በፊት ቶሎ ወደ ቀያቸው ተመልሰው፣ አርሰው በቀጣዩ ምርት እንዲሰበስቡ ማድረግ ነው፤ ይሄ ይሳካል። በዕለቱ 610 ሚ. ብር መሰብሰቡ ተረጋግጧል። ከዚያ በኋላም ገንዘብ መሰብሰቡ መቀጠሉንና አንዳንድ አካባቢ ፕሮግራሙ በድጋሚ ይዘጋጅ የሚል ጥያቄ መቅረቡን ሰምቻለሁ፡፡ በቴሌቶኑ ኢትዮጵያዊ ፍቅርንና አንድነትን የሚያጎላ ድጋፍ ከሁሉም አቅጣጫ ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ህዝብ እንድንኮራ ያደረገን ፕሮግራም ነበር፡፡ በአንድ አካባቢ ችግር ሲከሰት መተባበርና መደጋገፍ የቆየና የምንታወቅበት ባህል ነው፡፡ እኛም ባደረግነው ጥሪ የተሰጠው ምላሽ፣ ይህንኑ ባህል ያጎላ ነው፤ እናመሰግናለን። በሌሎች ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖችም ተመሳሳይ ጥሪ ተደርጎ፣ ብዙ ችግርና ጉስቁልና ሳይደርስባቸው መልሶ ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡
በወልቃይትና በራያ ጉዳይ ላይ ቁርጥ ያለ አቋማችሁ ምንድነው?
ቁርጥ ያለ አቋም ማለት ምን ማለት ነው… አንቺኑ ልጠይቅሽ እስኪ? ቁርጥ ያለ አቋማችን እኮ በተደጋጋሚ ጊዜ የተገለፀ ነው፡፡ ወልቃይትና ራያ ላይ ነዋሪዎቹ ያነሱት ጥያቄ አለ፡፡ “እኛ አማራ ነን፤ ወደ አማራ ክልል መካለል አለብን” ብለው ያምናሉ። ይሄ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ፣ ከአካባቢ አልፎ፣ የአማራም የትግራይም ክልል አጀንዳ ሆኗል። ምናልባትም የኢትዮጵያ አጀንዳ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ይሄ የህብረተሰብ ፍላጎት በአግባቡ መስተናገድ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ ማን ነው ምላሽ መስጠት ያለበት ካልን መንግስት በተመቸ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የህዝቦቹን ፍላጎት መጠበቅ አለበት፡፡ ህዝቦች እንዲወስኑ ነፃነት ማግኘት አለባቸው፡፡ እነሱ የወሰኑት ውሳኔ መከበር አለበት፡፡ ከህዝብ ውሳኔና ፍላጎት ውጪ በግራም በቀኝም በሚደረግ ተፅዕኖ የሚመጣ ዘለቄታዊ ውጤት የለም፤ አይኖርምም፡፡ እናም በሀገራችን ህገ መንግስትም ሆነ በየትኛውም ቦታ እንዲህ አይነት ችግሮች በሚያጋጥሙ ጊዜ የሚፈቱት በህዝብ ፍላጎት ላይ ተመስርተው ነው፡፡ ጉዳዩ ያን ያህል ውስብስብ አይደለም‘ኮ፡፡ ዞሮ ዞሮ ችግሩ ህግና መርህን ተከትሎ፣ የህዝብን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ነው መፈታት ያለበት፡፡ ይሄ መቼም ግልፅ ነገር ነው፡፡
የአቶ በረከት ስምኦንና የአቶ ታደሰ ካሳ የእስር ክስ የሙስና ነው ቢባልም፣ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ዓላማ እንዳለው፣ በፍርድ ሂደቱም ላይ ችግር  እያጋጠማቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ የእርሰዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ይሄ በፍ/ቤት የተያዘ ጉዳይ በመሆኑ ብዙ ማለት አልፈልግም፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ግን የአማራ ክልል፣ የፍትህ ተቋማት፤ ፍ/ቤትም ሆነ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና እንዲሁም ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሚያዘውና በሚፈቅደው አግባብ ብቻ ግለሰቦቹ እንዲታዩና እንዲዳኙ ያደርጋል እንጂ ከዚያ ውጭ ፍርድ ቤት በስሜት ወይም በሆነ ግፊት ላይ ተመስርቶ ይወስናል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ ፍርድ ቤታችን በተነፃፃሪነት ሲታይ የተሻለና ህግን መሰረት አድርጎ የሚሰራ እንደሆነ እምነት አለኝ፡፡ የግለሰቦቹ ሁኔታም በዚህ አግባብ የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡ እርግጥ ከውጭ የተለያዩ ግፊቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ የተለያዩ አዝማሚያዎችም ሊኖሩ ይችላሉ፤ በእርግጠኝነት መናገር የምችለው፣ አፌን ሞልቼ የምገልፀው፣ ከህግ ውጭ በተለየ መንገድ በባለስልጣናት፣ በፖለቲከኞች ወይም በሌላ አካል ተፅዕኖ ፍትህ ይዛባል የሚል ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ይሄን አሁንም በእርግጠኝነት የምናገረው ጉዳይ ነው፡፡
በመጨረሻ ከእርስዎ ጋር የተገናኘ ጉዳይ ላንሳ። የምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ወይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሹመት ሊሰጥዎ መሆኑ ተወርቷል፡፡ እውነት ነው?
እኔ እንግዲህ እንዲህ ዓይነት ያልተጨበጡ ወሬዎች ጎጂዎች ናቸው ብዬ ነው የማምነው። አገርንም ህዝብንም ሆነ ተቋማትን ይጎዳሉ፡፡ በእኔ በኩል በየትኛውም መልኩ፣ በየትኛውም ቦታ ተሰልፌ፣ አገርና ህዝብ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡፡ በተለይ አሁን አገሪቱ ላይ የመጣው ለውጥ ከዳር እንዲደርስ የበኩሌን አስተዋፅኦ አደርጋለሁ፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ እዚህ ቦታ ትመደባለህ የሚል በይፋ የተነገረኝ ነገር የለም፡፡ ሰው ዝም ብሎ የራሱን መላምት እያስቀመጠ፣ ውዥንብር ባይፈጥር ደስ ይለኛል። ሁሉንም የሚያውቀው መንግስት ነው። እኔ ግን ለማንበብም ሆነ የተሻለ ሀሳብ ለማፍለቅ በሚያስችለኝ፣ ቀለል ያለ ቦታ  ብመደብ እመርጣለሁ። አሁን ለጊዜው እረፍት ላይ ነው ያለሁት፡፡

Read 2361 times