Saturday, 23 March 2019 12:48

ሚያዚያ 27 አዲስ አበባ ላይ እንገናኝ!

Written by  አያሌው አስረሰ
Rate this item
(0 votes)

 “ጉዞ አድዋ” ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ ተኪዷል፡፡ በዚህ አመት በተደረገው ጉዞ፤ ከሐረር የራስ መኮንን ጦር የተጓዘበትን መንገድ ይዘው የገሠገሡ፣ ወረኢሉን የረገጡ ብቻ ሳይሆን ከትግራይ የራስ አሉላን መንገድ የተከተሉም ተቀላቅለውት፣ 123ኛውን የአድዋን የድል በዓል፣ አድዋ ላይ አክብሯል፡፡
እግረኞቹ የአድዋ አስታዋሾች የማጠናቀቂያ ሥነ ስርዓት ረቡዕ መጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ.ም በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል አክብረዋል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ የመገኘት እድል ገጥሞኛል፡፡ በሁለት ነገር ደስ ተሰኝቻለሁ፡፡ አንደኛው፤ የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ፣ በጦርነቱ ላይ የሀገራቸውን ነፃነት ለማስጠበቅ መስዋዕትነት ለከፈሉና ነፃነት ሊገፉ አገር ሊያስገብሩ መጥተው በጦርነቱ ለተገደሉ፤ በጋራ አገላለጽ ለገዳይም ለሟችም፣ የሥነ ሥርዓት ተካፋዩ ሕዝብ የህሊና ፀሎት እንዲያደርስ ማድረጋቸው ነው፡፡ ድሮም የምኒልክ ሠራዊት ያደረገው እንዲህ አይነት ቸርነት ነው፡፡ ምርኮኛውን ጣሊያን አዲስ አበባ ድረስ ያመጣው በቅሎ እያሰጠ ወይም ከበቅሎው እየወረደ እያሳረፈ ሲደክም እያፈናጠጠ ነው፡፡
ሁለተኛው፤ ሙዐዘ ጥበብ ዲያቆን ዳንኤል ከብረት፣ አድዋን ምልክት አድርገን እንድንቀበለው እንድናሳድገው ያቀረበው ማሳሰቢያ ነው፡፡ ድሉ ከአዲሰ አበባ ውጪ በሌሎች ክልሎች ያለውም ቦታ ከትናንቱ ዛሬ እየተሻሻለ የመጣ በመሆኑ፣ እሱን አንድ መገናኛ ምልክት አድርጐ ሕዝብን ማሰባሰብ፣ ለእድገትና ለልማት እንዲነሳሳ መቀስቀሻ ማተጋጊያ አድርጐ መጠቀም የተገባ ነው፡፡ እንደ ልመና በሬ ወደየመጣበት እየተጐተተ ላለው የዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ፤ ወደ መሐል ሊስበው ሊሰበስበው የሚችል ነገር በመሆኑ መጠቀም ብልህነት እንጂ የዋህነት ወይም ቂልነት አለመሆኑን በአጽንኣት ማስገንዘብ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
የአድዋ ተጓዦች፤ “ወደ አድዋ የምትመጡ ከሆነ የሬሳ ሳጥናችሁን ይዛችሁ ኑ” የሚል ማስጠንቀቂያ በማህበራዊ ሚዲያ እንደደረሳቸው ነግረውናል። እኔም አንብቤያለሁ - የወላጅ ቅጣትና ምርቃት የጐደለው ዋልጌ መሆን አለበት፡፡
ያሳዘነኝም ነገር አለ፡፡ አድዋ ድረስ  በባዶ እግሩ የተጓዘው ኤርሚያስ የተባለውን ልጅ በዚህ ፕሮግራም ላይ አላየሁትም፡፡ ይህ ልጅ እንደ እሱ በባዶ እግር የሚጓዙ መቶዎች ቢመጡ መደሰት መኩራት ነበረበት እንጂ መቅናት አልነበረበትም፤ አለመታደል ይሏል ይህንን ነው፡፡
ወደ ነገሬ ልመለስ እንደ አድዋ ድል ሁሉ ከወደቀበት የሚያነሳው የሚፈልግ፣ እንዲያውም ከአድዋ በላይ  የአድዋ ድል የነፍስ አባት የሆነ፣ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ድል ቀን አለ - ሚያዚያ 27 የነፃነት ቀን፡፡ የአድዋ ተጓዦች በሚያዚያ 27 ነፃነት ባይገኝ ኖሮ፣ አድዋ ሊታሰብ የሚችል ጉዳይ አለመሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ የአሸናፊነት ዋጋ የሚላከው መጨረሻ አሸናፊ  በመሆን መሆኑ ጨርሶ ከልባቸው ሊርቅ አያስፈልግም፡፡ እድሜ ለሚያዚያ 27 ማለትም አለባቸው፡፡
የሚያዚያ 27 ድል፤ እንደ አድዋ ድል በአንድ ቀን፣ በአንድ አካባቢ በተወሰነ የሰው ኃይል የተገኘ ድል አይደለም፡፡ ወረራው በሶስት አቅጣጫ እንደተጀመረው ሁሉ የመከላከሉ ጦርነት በሶስቱም አቅጣጫ ማለትም በሰሜን፣ በደሎና በኦጋዴን ግንባር ተካሂዷል፡፡ ግን አሸናፊ መሆን አልተቻለም። በአድዋ ጦርነት የአፄ ሚኒልክ ሠራዊትና ወራሪው የጣሊያን ጦር የተቀራረበ ትጥቅ ማለትም የጦር መሣሪያ የነበራቸው ሲሆን፤ በ1928 ግን የኢትዮጵያና የጣሊያን ትጥቅ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ፣ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ከሰናድር አምበዛም አልራቀም ነበር። ጣሊያኖች ግን በገፍ የታጠቁ ከመሆናቸው በላይ የአየር ኃይላቸው የሚያዘንበው የመትረየስ ጥይት ቦምቦና የመርዝ ጋዝ፣ ለመግለጽ እንኳ የሚከብድ ነበር፡፡ በወቅቱ የተነሱ በመርዝ ጋዝ ተለብልበው ውሃ ቋጥረው የምናያቸው የእጅ ጣት ፎቶዎች የሚመሰክሩት ያንን የጦርነቱን አስከፊነት ነው፡፡
የማይጨው ጦርነት ኢትዮጵያውያን እጅግ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለው ድል ያጡበት፣ በቀጣዩ አምስት አመትም የሚጠብቃቸው ፈተና በግልጽ የታየበት መሆኑ መጠቀስ አለበት። ፈተና ያልሁት ከመንግሥቱ ሠራዊት ጐን ተሰልፎ፣ የሀገሩን ጠላት መዋጋት የነበረበት ወገን፤  ለጠላት መሣሪያ  ባንዳ ሆኖ፣ በራሱ ወገኖች ላይ የዘመተበት በመሆኑ ነው፡፡
ድሉን ማይጨው ላይ የተነጠቀው ሕዝብ፣ ንጉሡ ወደ አውሮፓ ቢሰደዱም ከእንግዲህ ምን ቀረኝ ብሎ እጅን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ይልቁንም የሚያውቀውን አካባቢ፣ ማለትም የጐጃሙ አርበኛ ጐጃምን፣ የትግሬው ትግሬን፣ የወሎው ወሎን፣  የሸዋው ሸዋን፣ የወለጋው ወለጋን  ወዘተ የጦር ሜዳ አደረገው፡፡ ጣሊያን እንደ መጀመሪያው በአይሮፕላን በሚደበደበው የተከማቸ ጦር አሰጣው፡፡ በተለይ ከየካቲት 12 ቀን 1928 በኋላ ድሮ ለጣሊያን ያሸረግድ የነበረ ከተሜ ሳይቀር በጣሊያን ላይ ፊቱን በማዞሩ፣ አርበኛው እንደ ልብ መረጃ ማግኘት ቻለ፡፡ ጣሊያን ለማጥቃት መንገድ ሲገባ በአርበኛው እየተቀደመ ወይም ቀለበት ውስጥ እየገባ መከራውን ማየት ጀመረ፡፡
እዚህ ላይ ደጃዝማች በላይ ዘለቀን ማስታወስ ይገባል፡፡ ደጃዝማች በላይ፣ ጣሊያን ግንባር ቀደም አድርጐ የሚያሰልፈው ሠራዊት ባንዳውን መሆኑን በየጊዜው ባደረጉት ውጊያ ተመልክተዋል፡፡ ከኋላ የቀረው ጣሊያን ወደፊት የቀደመውን ባንዳ፣ ለሞት ያጋፍጣል እንጂ እሱ አይሞትም፡፡ ;;; ከፊት ሞት ከኋላም ሞት ስለሚጠብቀው ባንዳ ነፍሱን ለማዳን ይዋጋል። ይህን የተመለከቱት ደጃዝማች በላይ ዘለቀ “ጥዝጥዝ” ተብሎ የሚታወቀውን የውጊያ ስልታቸውን ጀመሩ፡፡ በዚህ የውጊያ ስልት ከኋላ ሆኖ ጦሩን የሚመራው ጣሊያን እየተመረጠ የመጀመሪያ ሟች ተደረገ፡፡ መሪው ሲሞት ባንዳ ደግሞ እግሬ አውጪኝ ይሸሻል፡፡ ይህ የሚጠብቃቸውን ውጊያ ክብደት እንዳቀለለው ይነገራል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ በስደት ከኖሩበት እንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሱበት፣ እንግሊዝ በጦር ጓደኝነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጐን በተሰለፈችበት ጊዜ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የጣሊያን ጦር፣ በከተሞች የተሰባሰበበት ገጠሩ፤ ከሞላ ጐደል በአርበኞች ቁጥጥር ሥር እንደነበር በአጽንኦት ማስታወስ ይገባል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለሥላሴ መጡ መጡ በተባለበት ጊዜ ደግሞ ጣሊያን ፍርሃትና ሥጋቱ በዝቶ፣ ኃይሉን ወደ ዋና ዋና ምሽጐች እያሰባስበ ነበር፡፡
እዚህ ላይ አስቀድሞ ማስገንዘብ የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ ከአንዳንድ አርበኞች ጋር መቃቃር ቢኖርም፣ ንጉሡ በየአካባቢው ከነበሩ አርበኞች ጋር በየጊዜው መልዕክት ይለዋወጡ ስለነበር፣ በአርበኛውም በሕዝቡም ዘንድ ንጉሥነታቸው ተቀባይነት ያለው መሆኑና ራሳቸውም በነፃ አውጭነትም ሲጠበቁ የነበሩ መሆናቸው ነው። ሌላውን አካባቢ እንተወው፡፡ እንግሊዞች ኤርትራ መሬት የገቡት “ንጉሠ ነገሥታችሁን ይዘንላችሁ መጥተናል” በማለት ሰብከው መሆኑ መጠቀስ ይኖርበታል፡፡
ኦሜድላ ላይ የመጀመሪያውን የነፃነት ምልክት የሆነውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የሠቀሉት ንጉሠ ነገሥቱ፣ አብሯቸው ያለው ሠራዊት እንደ ፍላጐቱና እንደመቻሉ ባይሆንም በአዝጋሚ ጉዞ ደብረማርቆስ ገባ፡፡ ከፊሉ ጦር ወደ ጐንደር፣ ከፊሉ ወደ ወለጋ ተጓዞ ንጉሠ ነገሥቱ ደብረማርቆስ ላይ ለጥቂት ቀናት ቆይተው ሚያዚያ 27 ቀን 1933 አዲስ አበባ ገቡ፡፡
ንጉሡን ተከትሎ የገባው ከጐጃም አብሯቸው የመጣው፣ ሰላሌ ላይ የተቀላቀለው የአካባቢው አርበኛ እንዲሁም  እንግሊዞች ይገባ ዘንድ የፈቀዱለት የራስ አበበ ጦር ነበር፡፡
ሚያዚያ 27 የነፃነትና የድል ቀን፣ እንደ አድዋው ሁሉ ዛሬ ተቆርቋሪ ያስፈልገዋል፡፡
በባንዳዎችና በፀረ ኃይለሥላሴ አስተሳሰብ በተለከፉ ሰዎች ላለፉት አርባ አራት አመታት፣ እንደ ክርስቶስ መስቀል የፖለቲካ ቆሻሻ ሲደፋበት የኖረው ይህ ቀን፤ ተገቢውን ቦታ ሊያገኝና ሊከበር ይገባል።
ድሉ የንጉሠ ነገሥቱ ድል ብቻ አይደለም፤ ድሉ በዱሩ በገደሉ መከራቸውን ያዩ የአርበኞች ድል ነው። ድሉ የእውነተኛ ኢትዮጵያዊ ድል ነው፡፡ መከበር ያለበትም አፄ ኃይለሥላሴን በመውደድና በመጥላት ሳይሆን በተከፈለው መስዋዕትነት ትልቅነትም  ነው። አገር ሚያዚያ 27 አዲስ አበባ ላይ እንገናኝ የሚሉ የነፃነት ተቆርቋሪ ትፈልጋለች፡፡
የላቀ ክብር ለሚያዚያ 27!!            


Read 1735 times