Saturday, 23 March 2019 12:39

“የሚያባርረኝ ጣሊያን እንቅፋት መቶት በሞተ፤ ጀግና ነው ብለው አሰሩኝ እንጂ፤ እኔስ አርበኛ አይደለሁም!”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ይህን ወግ፤ “we told it earlier as no one listened we shall repeat it again” ይላል ቮልቴር፡፡ እኛም ከዕለታት አንድ ቀን ብለነው ዛሬ የሚሰማ ሰው እንዳጣን ስለተገነዘብን ልንደግመው ተገደድን!
ከዕለታት አንድ ቀን ገበሬ ቀኑን ሙሉ ዘር ሲዘራ ውሎ ወደ ቤቱ እየተለመሰ ነው፡፡ ጦጢት ዛፍ አናት ላይ ሆና ገበሬው የሚዘራውን እህል፤ መቱንም፣ ፈሩንም ስታስተውል ቆይታለች፡፡
አሁን ገበሬው ወደ ቤቱ እየተመለሰ ነው፡፡ ጦጢት ሄዳ የዘራውን ሁሉ እየበረበረች እንደምትበላበት ያውቃል - ገበሬው፡፡ ጦጢትም ምንም ጥያቄ ብትጠይቀው ቀና መልስ እንደማይመልስላት ታውቃለች፡፡
ገበሬው ጦጢት ያለችበት ዛፍ ስር ደረሰና፤
“እንደምን ውልሃል ገበሬ?” ስትል ሰላምታ አቀረበች፡፡
“ደህና፡፡ አንቺስ ደህና ከረምሽ?”
“እኔ በጣም ደህና ነኝ”
ገበሬ የሚቀጥለውን ጥያቄ በመገመት መልስ አዘጋጅቷል፡፡
“ገበሬ ሆይ፤ ዛሬ ምን ዘራህ?” አለችው፡፡
ገበሬም የጦጣን ተንኮል ያውቃልና፤
“ተልባ፤ ተልባ ነው የዘራሁት”
ጦጣ የማትፈለፍለውንና የሚያሟልጫትን እህል እንደጠቀሰና፤ ተስፋ እንድትቆርጥ እንደሆነ ገባት - ጦጣ ናትና!
ጦጣ፤
“አይ ደህና፤ ወርደን እናየዋለን!” አለችው፡፡
***
“ነገሩ አልሆን ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር፣
ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር” ይለናል አንበሳው ገሞራው፡፡ የዱሮ ትግል ስሜት ግጥም ነው፡፡ የዛሬ መሪዎች ለዚህ አልታደሉም፡፡ ቢታደሉና በየግጥሙ ጉባኤ ቢታደሙ ደስ ባለን። ምክንያቱም ቢያንስ “እረኛ ምናለ?” ከሚል ዘይቤ ይገላግለን ነበር፡፡ ወትሮ ግጥምና ሥነ ፅሁፍ አንዱ ዕውነት የመናገሪያ መንገድ ነበር፡፡ ጃንሆይን አስቀይሞ ነበር ቢባልም፣ መንግስት መለዋወጡን ባይተውም፣ ግጥምም የራሱ የደረጃ አካሄድ አለው፡፡ ሚዛኔ አገርና ህዝብ ነውና! ከአገርና ከህዝብ መንገድ ሲወጣ ዲሞክራሲ ፌዝ ነው፡፡ ፍትህ ተራ ሙግት ነው፡፡ እኩልነት እኩል ያለመሆን ልማድ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር፣ መልካም አስተዳዳሪ በሌለበት “የደረባ  - ደረብራባ” ጨዋታ ነው፡፡ የሰው ኃይላችንን አቅም እንመርምር! የሰው ኃይላችንን ሥነ ምግባርና መልካም ግብረገብነት እናጢን!
ስለ ንፁህ መንገዳችን በብርቱ አውርተናል፡፡ ንፁህ አለመሆናችንን ግን ልባችን ያውቀዋል! መሄዳችንን እንጂ መድረሻችንን አለማወቁ አንዱ ታላቅ እርግማናችን ነው፡፡ መታመማችንን በቅጡ ሳናውቅ ሐኪም ፍለጋ መዳከር ክፉ ልማድ ሆኖብናል፡፡
ዱሮ፤
“የእኛ ተግባር
መማር፣ መማር፣ መማር!” እንል ነበር - ሌኒን ባለው እየተመራን፡፡ ዛሬስ? የማንም መፈክር ስለሌለን ለምንምነታችን እጃችንን ሰጥተናል፡፡ ስለዚህ ብዙ ጥያቄዎች አናታችን ላይ ይንቀዋለላሉ። እንደምን?
ለምሳሌ፤
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አካሄድ ተመቸን፤ እኛ እኛ ነን፤ ግን እሱ ተመችቶች እየገዛን ነው?
ከእሱ በኋላ (ኦህዴድ፣ ደህንነትና መከላከያ፣ እንደሆነ ሳንረሳ፤ ብጥብጥ ለምን በዛ/አሁንም የወደቁት ዛፎች ላይ ምሳር ሳናበዛ ራሳችንን እያየን ብንነጋገር፣ ወደ መፍትሄው እንቃረብ ይሆናል። አለበለዚያ በተለመደው አባዜያችን ስንረጋገም መኖራችን ነው (ነብሱን ይማረውና አሰፋ ጫቦ “ውሃ ወቀጣ!” ይለው ነበር!”)
አንድ ጊዜ ጓድ ሊቀ መንበር መንግስቱ ኃ/ማርያም “የምንለውን ብለናል፤ የምናደርገውን እንጀምር” ብለው ነበር፡፡ የወቅቱን እሳቸውን የማድነቅ ግዴታ ባይኖርብንም፣ አነጋገራቸው ግን ዕውነቱን የሚያንፀባርቅ ነበረ! ዛሬም ከንግግር አባዜ (Rhetoric) ወጥተን መሬት ብንይዝ፣ ቢያንስ “አይ መሬት ያለ ሰው?!” የሚል መሬት ያለ ሰው አይኖርብንም!
ዋናው ጉዳይ ግብረገብነታችንን ወደ ቆራጥ ተግባር እንለውጠው ነው! እርምጃ እሚያስፈልገውን አናስታምም! To satisfy all is to satisfy none! የሚለውን አባባል ለአንዲት ደቂቃም አንርሳ! (‹ሁሉንም ማርካት ማንንም አለማርካት ነው› እንደማለት ነው)
ምቀኝነት ያለባቸው አያሌ ናቸው፡፡ ቢችሉ በአካል አሊያም በመንፈስ ሊያኮላሹን የሚሹ ተዘርዝረው አያልቁም! ያም ሆኖ ሁሉም ቤት ያፈራቸው ናቸውና በጥንቃቄ መቀበል ግድና ዋና ነገር ነው፡፡ ከሀገራችን ዋና ዋና ችግሮች አንዱ፣ ወንጀል ወንጀሉን ሌሎች ላይ መላከክ ነው፡፡
“የአብዬን እከክ እምዬ ላይ ልክክ” እንዲል ማለት ነው፡፡ ወንጀለኞቹና ሴረኞቹ ሌላ ቦታ፣ ተወንጃዮቹ ሌላ ቦታ ናቸው፡፡ የሚሰጠው ሰበብም እንደዚያው፡፡ ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት ፀጋዬ ገብረመድህን፤
“የሚያባርረኝ ጣሊያን እንቅፋት መትቶት በሞተ፣ ጀግና ነው ብለው
አሰሩኝ እንጂ እኔስ አርበኛ አይደለሁም” የሚለን ለዚሁ ነው፡፡  

Read 9153 times