Saturday, 23 March 2019 12:36

የአገሯን ፖለቲከኞች የምታወዛግብ መዲና - አዲስ አበባ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)

  - ኦነግ “ፊንፊኔ የኦሮሞ አንጡራ ሃብት ናት” ይላል
           - አረና ገና አቋም አልያዘም፤ በቅርቡ ይይዛል
           - ኦዴፓ የአዲስ አበባን የኦሮሞ ባለቤትነት ለማረጋገጥ እሰራለሁ ብሏል
           - ኦዴፓ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናት ባይ ነው
                  
           አዲስ አድማስ በአዲስ አበባ ጉዳይ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ድርጅቶች አዲስ አበባ አሁን ባለው የህገመንግስቱ አንቀፅ 49 (ስለ አዲስ አበባ) በሚደነግገው መሠረት መገዛት እንዳለባት አመልክተዋል፡፡
አዲስ አበባ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 49 ላይ በተደነገገው መሠረት፤ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ እንዲሁም የራሷ አስተዳደርና የህዝብ ተወካዮች ያሏት ከተማ ናት ያለው አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ፤ ይሄን ህገመንግስታዊ ድንጋጌ ጥሶ ወዳልተገባ ሂደት መግባት ተገቢ አለመሆኑን ጠቁሟል፡፡
የንቅናቄው የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፤ የአዲስ አበባን የባለቤትነት ጉዳይ ለመቀየር የሚፈልግ መጀመሪያ ህገ መንግስቱን መቀየር ነው ያለበት፤ ህገ መንግስት ደግሞ የሚቀየረው የሁሉም ኢትዮጵያውያን ፍላጐት ሲታከልበት ብቻ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ኢራፓ በበኩሉ፤ አዲስ አበባን በተመለከተ በህገመንግስቱ የተደነገገው መጽናት አለበት፤ አዲስ አበባ ትንሿ ኢትዮጵያ ናት፤ የማንም ሳትሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ከተማ ናት” ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን እንደሆነች ሁሉ፣ አዲስ አበባም የሀገሪቱ ዋና ከተማ እንደመሆንዋ፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንጂ የአንድ አካል ብቻ አይደለችም - ብለዋል የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ተሻለ ሠብሮ፡፡ የከተማዋ አስተዳደርን በተመለከተም፣ የፌደራል ቻርተር ከተማ መሆን አለባት ብሏል - ፓርቲው፡፡
ተመሳሳይ አቋም የሚጋራው መኢአድ፤ “አዲስ አበባ የሁሉም ከተማ ናት፤ በህገመንግስቱ ድንጋጌ መሠረት አስተዳደሯ መቀጠል አለበት” ይላል፡፡
የህገመንግስቱ ድንጋጌም እስከ መጨረሻው ፀንቶ መቆየት እንዳለበትና አዲስ አበባ ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብቷ መጠበቅ እንዳለበት ፓርቲው አቋሙን ገልጿል፡፡
ከመኢአድ ጋር ተመሳሳይ አቋም ያንፀባረቁት ኢህአፓ፣ የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ህብረት፣ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ፣ የአፋር ህዝቦች ዲሞክራሲዊ ፓርቲ፣ የአፋር ነፃነት ፓርቲና የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳትሆን የመላ አፍሪካውያን መዲና ስለሆነች፣ በአዲስ አበባ ላይ የሚነሳ የተናጠል የባለቤትነት ጥያቄን አጥብቀን እንቃወማለን ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችንም መንግስት ህገመንግስቱን ባገናዘበ መልኩ መመለስ እንዳለበት አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገልፀዋል፡፡
አረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉአላዊነት፤ በአዲስ አበባ የባለቤትነትና አስተዳደር ጉዳይ ላይ በሚነሳው ውዝግብ እስካሁን የራሱን ግልጽ አቋም እንዳልያዘ ጠቁሞ በቅርቡ ተወያይቶ አቋም እንደሚይዝ አስታውቋል፡፡  
የፓርቲው ምክትል ሊ/መንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ በግላቸው በሰጡት አስተያየት፤ “አዲስ አበባ የኦሮሞም የኢትዮጵያውያንም ናት፤ ከተማዋ የኦሮሞንም ሆነ የሌላውን ኢትዮጵያዊ ባህልና ቋንቋ አቻችላ የምትሄድ መሆን አለባት” ብለዋል፡፡
በፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) በበኩሉ፤ ህገመንግስቱ በስራ ላይ ባለበት ሁኔታ የአዲስ አበባ ጉዳይ ማንንም ሊያወዛግብ አይገባም ብሏል፡፡ የአዲስ አበባ ጉዳይ በህገመንግስቱ በተቀመጠው አግባብ ብቻ መታየት እንዳለበት የጠቆመው ፓርቲው፤ መንግስት ከህገ መንግስት ድንጋጌ ውጪ ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቋል፡፡ አዲስ አበባ በ1983 በሽግግሩ ወቅትም በክልልነት ነፃሆና መደራጀቷን በመጥቀስ፣ ራሷን የቻለች ህጋዊ ከተማ መሆኗን መገንዘብ ያስፈልጋል ብሏል፡፡
በፕ/ር መረራ ጉዲና የሚመራው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ደግሞ፤ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፣ የፌደራል መንግስትና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗን ገልፆ፤ ነገር ግን በኦሮሚያ መሀል ስለምትገኝ የኦሮሚያና የኦሮሞ አንጡራ ሃብት ነች ብሏል፡፡
በህገ መንግስቱ የተደነገገው፤ የልዩ ጥቅም ጉዳይም እንደማይቀበለው አዲስ አበባ ልዩ የከተማ አስተዳደር ሆና፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በህግ መታቀፍ አለባት ብሏል፡፡
የኦፌኮን አቋም ለአዲስ አድማስ የገለፁት የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ኢትዮጵያ የመኖርና ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው እንደሚባለው ሁሉ፣ አዲስ አበባም መኖር የሚፈልግ ሁሉ በዚህ አግባብ መኖር የሚችልባት ከተማ መሆን አለባት ብለዋል፡፡
“የኦሮሞ ህዝብ ፊንፊኔ ላይ ተፈጥሮአዊ፣ ታሪካዊና ጥንታዊ የባለቤትነት መብት አለው” ያለው ኦነግ በበኩሉ፤ በኦሮሚያና በፊንፊኔ መካከል የሚኖረውም ድንበር ሳይሆን አስተዳደራዊ ወሰን ነው” ብሏል፡፡ “ከተማዋ የኦሮሚያ እምብርትና ዋና ከተማ ነችም” ሲልም አቋሙን ገልጿል፡፡
የአማራ ክልላዊ መንግስትን የሚያስተዳድረውና የኢህአዴግ አባል ፓርቲ የሆነው የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፤ አዲስ አበባ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ብሔር አይደለችም ይላል፡፡ “አዲስ አበባ አንድ ብሔር በባለቤትነት የሚይዛት ሳትሆን የመላ ኢትዮጵያውያን ነች” ሲል አዴፓ አቋሙን አሳውቋል፡፡ የኦሮምያን ክልላዊ መንግስት የሚመራው የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) በበኩሉ፤ የአዲስ አበባን የኦሮሞ ባለቤትነት ለማረጋገጥ እሠራለሁ ብሏል፡፡

Read 13913 times