Print this page
Saturday, 23 March 2019 12:26

የለውጡ የአንድ ዓመት ጉዞ በምሁራን እየተገመገመ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በለውጥ አመራርነት ወደ ስልጣን ከመጡበት ያለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስክ የተመዘገበው ለውጥ በምሁራን እየተገመገመ ነው፡፡
ትናንት (አርብ) ረፋድ የጀመረውና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አዘጋጅነት የሚካሄደው የግምገማ መድረኩ ዛሬም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን 17 ያህል ምሁራንና ፖለቲከኞች በተለያየ ዘርፍ የግምገማ ጥናት ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
“አዲስ ወግ” የመቻቻልና የመከባበር ውይይት በሚል በተሰየመው የግምገማና ውይይት መድረክ ላይ በትናንት ውሎው፣ “የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ጉዞ፣ ታሪካዊ ዳራና ወቅታዊ ተግዳሮት” በሚል ርዕስ የታሪክ ተመራማሪና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተመራማሪው ዶ/ር ዲማ ነገኦ፣ የፖለቲካ ፍልስፍና መምህርና ተመራማሪ አክራም መሃመድ፣ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪና መምህር ዶ/ር ሰሚር የሱፍ የየራሳቸውን ምልክታ አቅርበዋል፡፡
“የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲና የአፍሪካ ተሳትፎ” በሚል ርዕስ ላይ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የቀድሞ ረዳት ዋና ፀሀፊ ሂሩት ገ/ሥላሴ፣ የአፍሪካ ህብረት አማካሪ አብዱል መሃመድ፣ የተባበሩት መንግስታት አማካሪ አምባሳደር ህሩይ አማኑኤልና የአፍሪካ የሰብአዊና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽን አተያይ በመድረኩ አቅርበዋል፡፡
በዛሬው የቅዳሜ ውሎም የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት፣ የምጣኔ ሃብት እድገት፣ ስራ ፈጠራና ማህበራዊ አካታችነትን በተመለከተ የማክሮ ኢኮኖሚ ተመራማሪና መምህር ዶ/ር ሰኢድ ኑሩ፣ የ “ብሉሙን” ኢትዮጵያ መስራች ዶ/ር እሌኒ ገ/መድህን፣ የህብረት ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርና የፋይናንስ ባለሙያ አቶ ዛፉ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ እንዲሁም የመሬት ስሪት ተመራማሪና የጥናት ባለሙያው አቶ ደሳለኝ ራህመቶ ጥናታቸውን ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ በኢትዮጵያ ተግዳሮቶችና ቀጣይ አካሄዶች ላይም የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ሌንጮ ለታ፣ የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የፖለቲካ ተንታኝና አራማጅ ዮናታን ተስፋዬ፣ የኦጋዴን ህዝብ ነፃነት ግንባር የአዲስ አበባ ተጠሪ አቶ ሐሰን ሞአሊን እና የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ምልከታቸውን እንደሚያቀርቡ ከመጣው ዝርዝር መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል፡፡  

Read 6961 times