Sunday, 17 March 2019 00:00

እግዜር ሞጋች ግጥሞች

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(3 votes)

ግጥም በሠማይና በምድር መካከል የተሰነቀረች ህይወት ጩኸት ናት፡፡ ወቅት (የትኛውም ሀይል) የማይቋቋመው ሞገድ ናት፡፡ ሰውነት ሙሉ ትጥቅ የሚላበሰው በእሷ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ደግሞ የግለሰብ ተብሰልስሎት ነው፡፡ አረረም መረረም የህብሩ ልክ መስፈሪያ ናት፡፡ ጎባባውን ሰማይ የምንፈትሽበት ሚዛን ናት፤ ለእኛ (ለሰው)፡፡ ይህ ደግሞ በጥልቅ ስሜት የተሞሸረ ነው፡፡ ካልሆነማ የተመጠጠ ሸንኮራ መሆኑ አይደል?
“ፍልስፍና እና ስነ-ግጥም እኩዮች ናቸው፤ ኸረ እንዲያውም ተቀናቃኞች ናቸው” ያለው ማን ነበር? ለማበላለጥ መሞከሩ ስህተት ባይሆንም አቻነታቸው ግን ከተፈጥሮ ጋር “የሰመሩ” መሆናቸው ይመስለኛል። ለዚህ ሳይሆን ይቀራል “ገጣሚ ውበትና ሀሳብ ሲያስስ የሚኖር ፍጡር ነው”  -- የሚባለው? ተፈጥሮ መንፈስ የተሸከመች በመሆኗ፣ ከአካላዊ ግዝፈቷ ባሻገር የምትናገረው መልዕክት ይፈተሽበታል - ግጥም፡፡
ግጥም የነፍስ ኑዛዜ ነው፤ የመንፈስ መታወክ ሀቅ ያፈጠጠበት፡፡ እነሆ፡-
እግዜር መሬት ወርዶ፣
አምላክ መሬት ወርዶ፣ አንድቀን አግኝቸው፤
ቀጭን ዘንጌን ይዤ፣ ሞግቸው ሞግቸው፤
እሱም ዘዴኛ ነው አይወርድም እምድር
ሁሉም ሰው ደመኛው ማን ቤት ገብቶ ሊያድር፡፡
 (የእረኛ ግጥም)
በማህበረ- ባህላችን የግጥም ቦታ ከፍ ያለ ነው፡፡ የህልውና ቋጠሮ የሚፈታበት ብርቱ ጥበባዊ ግንዛቤ ነው፡፡ ማህበረሰብ ሲታመም የህመሙን ጠገግ ፅንፍ አፈፍ የሚያደርግበት መዳፋ ነው -- ለከያኒ፡፡
ግጥሙ በእግዜር እና በሰው መካከል ያለውን የሞራል ትስስር ያሳየ ነው፡፡ ሙግቱ የህልውና ውል ነው፡፡ በእጃዙር ገላጩም ተገላጩም ሰው ነው፡፡
[ቀታሪ÷ ስሩ ቀተረ ነው፡፡ ቀተረ÷ እኩል ለመሆን ተከታተለ÷ ተቀታተረ÷ ተመለካከተ÷ ተወዳደረ÷ ተተካከለ÷ ተመዛዘነ÷ ተፈካከረ÷ ተፈላለገ (አስ) ከባለ ቀትር አትቀታተር፡፡ ( ከሣቴ ብርሃን ተሠማ÷ የዐማርኛ መዝገበ ቃላት÷ ገፅ ፫ ፻ ፹ ፬÷2008 ዓ.ም)  ግጥም ምንጬ ህይወት ነውና (ቋንቋው (መንገዱ) አዕምሮን፣ ስሜቱ ልብን እና መልዕክቱ ልቦናን ይቀትራል፡፡) አዕምሮን ፣ ልቦናንና ልብን የቀተረ ከምናብ የሚፈለቀቅ የፀነነ የጥበብ ውጤት ነው። መቀተሩ ከልማድ ጋር የሚደረግ ግብግብ ነው፡፡ ፈጠራ ደግሞ ልማድን መሻገር ይጠይቃል፡፡ ከልማድ ያልተሻገረ ግጥም ነፃ አያወጣም፡፡ አይታኘክም- የተመጠጠ ነውና፡፡]
* * *
 ቁጥር-4
ቃላዊ ግጥሞች ለእንጉርጉሮ የቀረቡ ናቸው፡፡ በጥልቅ ቁዘማ ከምናብ የሚፈለቀቁ በመሆናቸው ነፍስን (ስሜትን) ይቀትራሉ፡፡ የቃላቱ ምትሀታዊ ሀይል ምንጩ ቅፅበት ነው፡፡ የማይኮረኮር ማዕዘን የለም-- በቋንቋው፡፡ የህልውናችን መስፈሪያ ነው -- ዘዴው፡፡ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል ዳንቴ፤ “ግጥምን የማያውቅ እግዜርን አያውቅም” የሚለን። የእግዜር (የፈጣሪ) መልክ ህብር የሚገለጥበት ኪነ - ስፌት ነው -- ያለ ይመስለኛል፡፡ እዚህ ላይ ገጣሚ በድሉ ዋቅጅራ፤ “ግጥም ተፈጥሮ እራሷን የቆለፈችበትን ቁልፍ ያስቀመጠችበት ሙዳይ ነው” ያለበትን ምክንያት እንደ ማለዘቢያ መጥቀስ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በፍጡርና በፈጣሪ መካከል የሚምዘገዘግ የሀቅ በትር ነው -- ግጥም፡፡
በቅርቡ የካቲት 12 የሰማታት ሀውልት ዳርቻ፣ አንድ እናት ተቀምጠው እንዲህ ሲያንጎራጉሩ ሰምቻለሁ፦
እስኪ ላነሳሳው የፈጠረኝን
ከጓደኛ በታች ያደረገኝን
ከጥቂት ፋታ በኋላ እንዲህ ቀጠሉበት፦
እናንተ ምታዩኝ እኔ ማላያችሁ
የብርሃን አበባ አይርገፍባችሁ፡፡
አይናለም አይናለም
ላንድቀን ይከብዳል እንኳን ለዘላለም፡፡
ጥልቅ ቁዘማ ነው፤ህልውና የተሰፈረበት፡፡ የህመሙ ብርታት ይነዝራል፡፡ ይቀትራል፡፡ ስሜቱ እረፍት ስለሚነሳ ያቅበጠብጣል፡፡ በህይወት መገፋት ከፈጣሪ ጋር ያላትማል፡፡ ለምን ? የሚል ጥያቄ ወጥሮ ይፈታተናል፡፡ ከተፈጥሮ በደል የበለጠ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ችላ ሲሉን ህመሙ ይበረታል፡፡ ለዚህ ይሆን
“እናንተ ምታዩኝ እኔ ማላያችሁ
የብርሀን አበባ አይርገፍባችሁ”
የሚሉን፤ የማየትን ውብ ፀጋ በ“አበባ” በመመሰል። አጃኢብ ነው! ይቀትራል፡፡
ባንድ ወቅት ጎዣም ውስጥ በሰሞነ ህማማት ቁዘማ ስትብሰለሰል የሰነበተች ሴት፣ የእየሱስን ከመቃብር መነሳት የህመሟ መስፈሪያ በማድረግ እንዲህ ገልፃዋለች፦
“ስትታመም ታማ ስትሞት ተቀበረች
አንተ ስትነሳ የኔ እናት የታለች!?”
በንፅፅር የቀረበ ነው፡፡ ንፅፅሩ ደግሞ ሲቃይ፣ ህመም ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የእናቴ እና ያንተ (እየሱስን መሆኑን ልብ ይሉዋል) ስቃይ ልዩነቱ አልታይሽ አለኝ! ያለች ይመስለኛል፡፡ ያው ሁለታችሁም በህመም ስቃይ ውስጥ ነበራችሁ -- እንደማለት ነው፡፡ ታዲያ በእኩል ሚዛን ያለፈ መጨረሻው ለምን ተለያየ? መለኮታዊ ሀይል ለምን  አድሎ  አደረገ? የሚሉ ጥያቄዎች የህመሟ መነሻ ናቸው፡፡ “ህይወት ያለ ስነ-ፅሁፍ ገሀነም ነው” ይለናል፤ ቡከውስኪ፡፡ የማይታየውን የማሳየት ብቃት አለው -- እንደማለት ነው፡፡ የመጀመሪያው ስንኝ የእየሱስን የስቃይ ወቅቶች የሚወክል ነው። ምንም እንኳ ስለ እናቷ የቀረበ ቢሆንም ማንፀሪያ ነው፡፡ ሁለተኛው ስንኝ ደግሞ የታምራት እሳቤን (ተለምዷዊ የሆነውን) የሚፈታተን ነው፡፡ ማለትም “ታምራዊነት የእየሱስ ከሞት መነሳት ሳይሆን የሞተን  ማስነሳቱ ላይ ነው” የሚል ይመስላል፡፡
ግጥሙ ቅኔያዊ ነው፡፡ ለተደራራቢ ፍቺ የተጋለጠ ነው፡፡ ድድር ነው፡፡ ልክ እንደ ሽንኩርት፡፡ ስለ ፍትህ፣ ስለ ታምራዊነት፣ ስለ ስነ-ምግባርና ስለ ህልውና ጉዳዮች ፍንጭ ይሰጣል፡፡ እናቴም ሆነች አንተ (እየሱስ) የመለኮት ልጆች ናችሁና እንዴት ሳትነሳ ቀረች? የሚለው አንዱ ማሳያ ይሆነናል፡፡ ተራኪዋ (ገጣሚዋ) ምዕመኑን፣ እናት ደግሞ እየሱስን ወክለው ነው የቀረቡት -- በግጥሙ፡፡ ስለሆነም ንፅፅሩ ያቻነት ነው፡፡
ልጇ በጠና የታመመባት እናት በየፀበሉ፣ በየሀኪም ቤቱ፣ በየአዋቂ ቤቱ  ደጅ ጠንታ የላቧና የምልጃዋ ውጤት ከንቱ ሆኖ አንድዬ  ልጇን በሞት ብትነጠቅ እንዲህ ብላ አንጓራጓረች፡፡
“አስር ታድናለህ አንድ ትገላለህ
የሴት ልጅ ነህና መቼ ፍርድ ታውቃለህ”
እራሷን ከጓረቤቷ አስር ልጅ ካላት እናት ጋር በማነፃፀር ታንጓራጉራለች፡፡ ቀታሪ ነው፡፡ መቀተሩ ከሀቅ ጋር የሚደረግ ግብግብ ነው፡፡ ቀድሞውኑ ሰውነትን የሸረበችበት ፈትል ሲውሸለሸል አልተዋጠላትም፡፡ ጎረበጣት፡፡ የህመማችን ልክ ድንበር ሲያጣ የመለኮት ቦታ ዳብዛው ይጠፋብናል። አቅም ፍለጋ እንቃትታለን፡፡ በዚህ መንቶ ግጥም የሆነው ይህ ነው፡፡
በደርግ ዘመንም የሆነው ይኸው ነው፡፡ በሰፈራ እንቅስቃሴው ሰለባ የነበረ የወሎ ገበሬ ምልጃውን እንደሚከተለው  አንጓራጓረ፡፡
ቀና ብየ ባየው ሰማዩ ቀለለኝ ፣
አንተንም እንደኛ ሰፈራ ወሰዱህ መሰለኝ፡፡
በማለት ፍርድ መሻቱን በመንቶ ስንኝ ቋጠረ። የህልውና ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ ከራስ፣ ከማህበረሰብ፣ ከባህልና ከተፈጥሮ ጋር ያላትመናል። ከፍ ሲልም ከፈጣሪ (ከመለኮት) ጋር ያፋጥጠናል፡፡ መፍትሄ ማጣት ያቅበዘብዘናል፡፡
የትኛውንም ባህል የሚሻገሩ አተያዮች በግጥሞቹ ተሞሽረው ቀርበዋል፡፡ እይታዎቹ የኑሮ ሒስ የቀረበባቸው ናቸው፡፡ ለዚህ ይሆን፤ “ስነግጥም በስነግጥማዊ እውነትና ውበት ላይ የተመሰረተ የህይወት ሒስ ነው” የሚለን፡፡ ሒሶቹ  መለኮት (አምላክ )ላይ ያነጣጠሩ ቢሆኑም በሰው ልጅ ፍቅር የተነደፉ፣ ጥብቅና የቆሙ ናቸው፡፡ ዋና ጉዳያቸውም ሰውና ሰው ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡-  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2878 times