Sunday, 17 March 2019 00:00

ፍልሚያ - ፍራሽ ሜዳ - (ወግ)

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

 ልዋጭ ልዋጭ ልዋጭ! ... ቦሌ ቦሌ ቦሌ...!  ፍራሽ አዳሽ!
እህኔ ፍራሽ አዳሹ ምስጋና ይግባውና፤ ዬኔታ ምስሉ ትዝታውን ጠቅልሎ ስንቅር አለብኝ። ስብሀት ለአብ! አልኩ፡፡ የአንድ አጭር ልቦለዱ ትውስታ መጣ፡፡ በስጋ የሳቸው ያልሆነውን ልጅህ ነው ተብለው የተሰጣቸውን ብላቴና፣ ከልጄም ልጄ ብለው ስሙን እኔ ብለው የሰየሙት ፍራሽ አዳሹ አቶ ደጀኔ፤ ‹‹ልጃቸው››ን - እኔ ደጀኔን ትራስ ሰጥተው ‹‹በለው!›› ይሉታል፡፡ እሳቸው የሰፉትን አዲስ ፍራሽ ደሞ ‹‹ስንት ጉድ ታስተናግድ ይሆን!›› እያሉ በአርምሞ ያጠይቁታል፡፡ ፍራሽ አዳሽ በዚህ ምሽት እንዴት ስል፣ የመንገድ ላይ የግርግዳ ግጥም ሻጩ ንባብ  . . . ውረድ እንውረድ ተባባሉና . . . ብሎ ጀመረና የግጥሙ መድፊያ በሲኖትራክ ጡሩምባ ተዋጠ፡፡ ሌላ ስንኝ ቀጠለ . . .
‹‹አይሽ አይሽና ይመጣል እንባዬ
አንቺም ወይ እድልሽ እኔም ወይ እጣዬ!››
አምጣው እሱን ለኔ ስጠን አሉ፣ አንድ ጃኬታቸውን በአሮጌ መናኛ ቦርሳ ላይ ያንጠለጠሉ ተስፈኛ ተራማጅ ዜጋ . . .
ፍራሽ ሜዳ ሽው ሲል የኔታ ስብሀት ወጎች ትውስታ አብሮ ከች ይላል፡፡ ለምሳሌ ስፒዲ ጎንዳሌዝ! እሱ እንኳ ፍራሽም አያሻው፤ በቁም ነው አመሉ፡፡ ብቻ ግን መኮንኑ ጎንዳሌዝ ምርኮ ቀንቶት ድል ባደረገበት ሁሉ የመጀመሪያ ተግባሩ ገዢውን ከነሚሽቱ አስቀርቦ ጥያቄ ማቅረብ ነው፡፡ ምላሹን ከማግኘቱ በፊት ግን እነሆ በረከት ብሏል፡፡ ይህንን ፍጥነቱንም ሲያደንቅ የገዢው ሚሽት ጉንጯ ላይ ያረፈችውን ዝምብ እሽ ብላ ሳትጨርስ ጎንዳሌዝን ባቷ ውስጥ ማግኘት የተለመደ ነው ይለናል። ምናልባት ታላቁ እስክንድር አዲስ የማረከውን ግዛት በእጁ ማስገባቱን ለማረጋገጥ ንግስቷን ጉያው ወሽቆ እንደሚያድረው አይነት ነው፡፡ እርግጥ ነው በኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ህንደኬ የወረራ ሙከራው በለስ አልቀናውም፡፡ ታላቁ እስክንድር ኩም! ብሏል። በቀረ እግሩ በረገጠበት ሁሉ ከሄዋን ዘር ማን ተረፈው! እስክንድር እኮ ራሱን የአምላከ አማልዕክቱ የዜዩስ ልጅ መሆኑን ነው እሚያምን፡፡ እንኳንስ እርሱ ፈረሱ ቡሴፋለስም ቢሆን፡፡ እህህም አለ ፈረስ! ግጥምና ዜማ ደራሲው ታላቁ እስክንድርን ‹‹አንት ከንቱ! ትቢያ... ይህ እንደሚሆን አስቀድመህ ማወቅ አልነበረብህምን?!›› እያለ፤ ለንግሥት ህንደኬ ይሆናላ  ‹‹ወይዘሪት ኢትዮጵያ›› ብሎ የተቀኘላት . . . ‹‹እንከን የሌለብሽ፤ ከእግር እስከ ራስሽ፤ ሴትን አስከባሪ፤ እኔ ነኝ ባይ ማነሽ?” ስንኝን የቋጠረው . . . ፍፁም ኢትዮጵያዊት . . .
የኔው ቤት ወለሉ ጣራና ማገሩ
በብርሀን ተነድፈው በጮራ የተዋቀሩ፤
ቤት እየጀመሩ መሰረት ሳይሰሩ
ማሩ ሳይቆረጥ እንጀራው ሲቆረስ
ቀፎ ማፈላለግ እንደ ዘላን ንብ ነፍስ . . .
ብሎ በቀለም ቀንድ እያጠቀሰ ጥቅልል ብራናው ላይ የትዝብቱን እውነታ ያሰፍርም ይሆናል፤ በአዲሱ ሽምጥ ደንገላሳ ጋላቢ ፈረሰኛ ብላቴና ንግሥቲቱን ከግዛቱ ጋር የተነጠቀው ምርኮኛ ንጉሥ ዜና መዋዕል ጸሐፊ በበኩሉ፡፡ የቀረው ከአፍ አፍ ይዘራል፡፡ እንጂ የሚቀር የለ የፍራሽ ሜዳ ፍልሚያ ገድል፡፡
ወራሪውን መንገድ እየመራች እንዲወስዳት ያመቻቸች የንግሥት ገድልም አይጠፋውም፤ የአለም የፍራሽ ሜዳ ታሪክ መዝገብ፡፡ ልፊያው ሲያበቃ ወደ ቀድሞ አጋሯ ትመለሳለች፡፡ ለሁለተኛ ሶስተኛ ጊዜም ትደጋግመዋለች፡፡ ምናልባትም አዘውትራው በባህርይዋ ግብሯን መስላለች - ሆናለች፡፡ ከጎብኚዎቿ አንዱ ለዘለቄታው የኔ ብቻ እንድትሆኚ ነው እምፈልገው አላት፡፡ እና ምን ላድርግልህ ውዴ ሆይ አለች፡፡ እርሱ በህይወት እያለ ምንስ እናደርግ ዘንድ እንደ ምን ይቻለናልን አንቺ ሴት! እርሱንም ለዘለቄታው ማስወገድ ነዋ! ሹክ አላት ምኞቷ፡፡ ሰው እያወቀም ይሁን ሴጣንም እንኳን ሳያውቅ ሲጥ! አደረገችው - ያላንዳች ሀፍረት - የልጆቿን አባት፡፡ ወደ ጎብኚዋ እቅፍ አበባ ይዛ ሄደች፤ምንጣፏን አበባ ነስንሳ ጠበቀችው፡፡ አሁን ያለ ገደብ ያንተ ብቻ ነኝ ብላ በሀሴት እየተፍለቀለቀች የምስራቹን አበሰረችለት፡፡ አሽኮለሌና እልልታም አክላበት፡፡ እርሱስ? አላት፡፡ ‹‹መላ ዘይጄ ሸኘሁታ! ገደልኩት! እኛ ነፃ እንድንሆን!›› አለችው በኩራት። ‹‹እና የልጆችሽን አባት ለመግደል ያላመነታሽ ነገስ ለኔ የምትመለሺ ነሽ ብዬ እማስብ ይመስልሻልን!›› አላት - ኩም! ብስራቱ ስብራትና መርዶ ሆነ፡፡ አበቦቹ ደረቁ፡፡ እሽንደረሬዋ ከሰመ፡፡ እልልታዋ በሙሾ ተቀየረ፡፡ አይኗን በጨው አጥባ መሸነቷን ካደች፡፡ ስሜንም እንዳይጠራ ከልክየው ነበር! እሚል መገበዝ አክላበት፡፡ መርማሪ ፖሊሱ ‹‹እሱን ስትገረፊ ታወሪዋለሽ!›› እያለ ምስክሮች በተሰበሰቡበት ባደባባይ ተሳለቀባትና ባፍርሳታ ቃልዋን እንድትሰጥ ቀጠሮ ሰጣት፡፡ ከቀጠሮው ቀን በፊት በራሷ እጅ ምስኪን የቀድሞ ባሏን ተከተለችው፡፡ አሉ፡፡ የመንገድ ላይ የግርግዳ ግጥም ሻጩ ድምጽ . . .
ብቻ ወንድምዬ ነጋችን አይጉደፍ እንጂ ሁሉም ይቅር
አንተ ዠግና ተባል እኔ የእናቴ ልጅ ፈሪ እማቀረቅር፤
መቼ ከለከልኩህ እጀ ጠባቤንስ መጎናፀፊያዬን ወስደኸው ሽቅርቅር?
ራስ ወዳድ ሰው ባልሆን ነፍሴንስ ብሰጥህ ስለ ወንድም ፍቅር ፤
እና ሁሉም ይቅር . . .
‹‹እሱንም ስጠኝ!›› አሉ የቀድሞው ሰውዬ ከፈሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ መቸም ለየጉዳዩ መላ አያጣም አይደል? . . .አባ መላ ተብሎ እሚያስጠራ፡፡ ለመሰል ገጠመኞችም እንዲሁ ... እየሰማን ያደግነው። ፊታውራሪ ከዘመቻ ሲመለሱ ሚሽታቸውን (ፈቅዳው) ፍራሽ ሜዳ ያወረደ ታማኝ ወታደራቸው ከግንድ ጋር ተጠፍንጎ ታስሮ አገኙትና፤ የተፈፀመው ክብረ ነክ ነውር ሁሉ በዝርዝር ተነገራቸው፡፡ ፊታቸው ላይ ምንም ስሜት አልታየም ነበር አሉ፡፡ እንደ ፑቲን፡፡ ይልቅስ ሌላ አስቸኳይ ጉዳይ መኖሩን ነግረው ድግስ አስደገሱ፡፡ ጠላው ሲደርስ እንጀራ እስጋግረው ወዳጅ ዘመድ ጠሩና ሚሽታቸውን ከፈቀዱት ከወደዱት ከወታደሩ ጋር ድል ባለ ድግስ ዳሯቸው፡፡ እ...፡፡ እፎይ፡፡ ለስሜ ብለው በምስጢር ከመያዝ ይህን መረጡ፡፡ የፍራሽ ሜዳ አለም ምን ምስጢር አለውና! የመንገድ ላይ የግርግዳ ግጥም ሻጩ ድምጽ ምንጭ ጠቅሶ አነበበ. . .ሌላ ባለ ራዕይ ገዛው . . .
ከፍልስምናም ገጽ መላምት ክዕሌቱ የፍጥረት አብዮት
ከአዳም የአሜን ሚስት ከሌሊት መነሁለል ፍቺን መለየት
አክንፎ ካስቀራት አዲስ ህልምን መሻት የሌት አለም ማየት
የንጋት ኮከብ ጥቅሻ መቀነቷ ጥምጥም ከቅዠቷ ግልድም የጥላዋ ጥለት . . .
ሁለት መኮንኖች ደግሞ ለአመታት ፍልሚያ ለመግጠም በየሀገሩ በብርቱ ሲፈላለጉ ኖረው ኖረው፣ ድንገት ተገናኙና ከእኩለ ሌሊት በፊት ፍልሚያቸውን ለማድረግና አንዱ ድል ሊጨብጥ፣ አንዱ በክብር ወደ ሞት ሊሸኝ፤ ሻምላቸውን እየወለወሉ፡ ‹‹እሰይ! ስንት ጊዜኮ ነው ስፈልግህ የኖርኩ፤ ዛሬ ቀናኝና ተገናኝን›› እያሉ ለፍልሚያ ቋምጠው፣ ቀይና ነጭ ወይን በጠርሙስ ሲገባበዙ፤ ድንገት መሸተኛዋ አንደበቷን እያለሰለሰች፣ ቀሚሷን እየነሰነሰች መሀላቸው ገብታ ‹‹ጀግኖቼ በእኔ ምክንያትማ በፍፁም ፀብ ማንሳት የለባችሁም!›› እየተወራጨች ስትለምናቸው ተበሳጩ፡፡ እናም አንደኛው በዐይኑ ቂጥ እንኳ ሊያያት የማይሻው በተለይ፤ ወደፊት ለምን ሰላሳ አርባ አመት አይሆንም ስፈልግህ እኖራለሁ እንጂ ዛሬ ግን በፍፁምም አንፋለምም፡፡›› አለ፡፡ ለምን ቢለው - ‹‹ፍልሚያችን ከአመታት በፊት ጀምሮ ስንጠብቀው የኖርነው የጀግንነታችን መሻት ነዋ፡፡›› አለውና ሻምላውን ወደ ሰገባው መለሰ፡፡ አሁንም ደግሞ ‹‹እኮ ለምን ነው ዛሬ እማንፋለመው?›› ቢለው፤ ‹‹በእሷ የተጣላን እንዳይመስላት ነዋ!›› ብሎ እብስ ወደ ቤቱ፡፡
መሸተኛዋም፤ ከቢጤዎቿ ዘመን እማይተካት የባለክራሯ ድምጽ አየሩን ሰንጥቆ ‹‹የአሣ ሽማግሌ አቀበት ይዋኛል፤ አትከፋ ልቤ ወይ ይበልጥ ይገኛል›› እያለ ሲያስተጋባ እየሰማች፤ ስለምን አብሬው እሄዳለሁ? ወይስ ብወደው ኖሮ ከመሄድ አላንገራግርም ነበርን? እያለች፤ እንደ ሱላማጢስ ወዲህ ጸጸት እየደፈቃት ወዲያ ራሷ ለመጽናኛ ያደራጀችው ሀሳብ እየናጣት፤ ‹‹ውዴ እንደ ቁራ ጥቁር ነው›› ስትል ‹‹የለም መሻትሽስ ጆፌ አሞራ ነው!›› እያላት ልቧ፤ ከቀረው ጋር አቶ ደጀኔ በሰፉት አይነት የመስክ ያክል የተንጣለለ ሰፊ ፍራሽ ሜዳ ላይ በእቅፉ ሆና በምኞት ሰመመን እየቃዠች፣ በቁም ህልም እየተናጠች፣ አይኖቿ ግን ሩቅ ያማትራሉ፤ ልቧ ከሄደው ጋር ነጉዷል፤ በዱላው በቅናት እርር ድብን እቅድ የተስተጓጎለበት መአልት ውጥንቅጡ ሲወጣ ቁልጭ ብሎ እየታያት፣ ባልተሳካው ውጥን ሁለመናዋ ተንኮታኩቶ ግራ መጋባት እያጠላበት፣ ወዲህ ደግሞ ከቶም ያልጠበቀችው ወለፈንዲ ግጥምጥሞሽ ፊቷ የገተረው ግዘፍ የነሳ ቁመና ... እንዲህ አይነተኛ እርካታን የተራቆተ ቀልቧ ሁለት ቤት ተጥዶ ባለበት ወለፈንዲ ስሜት ውስጥ ስትባዝን ሳለችም፣ በዚያው ቅጽበት ‹‹እኔስ ሌላው የናቀው ምኔ ነው!›› በማራኪና ፍልቅልቅ ድምፁን ያላት ይመስላታል - ያደረ አፋሹ። አሁንም አሁንም አሁንም ኩም! ኩም! ኩም!. . . የመኪና ጡሩምባ ከመሸታው ቤት ዳንኪራ ጋር ተቀይጦ ይሰማል፡፡ ከርቀት  - ልዋጭ ልዋጭ ልዋጭ! ቦሌ ቦሌ! ቦሌ ቦሌ . . . ፍራሽ አዳሽ . . .!!! የመንገድ ላይ የግርግዳ ግጥም ሻጩ የንባብ ድምጽ ጎላ ብሎ ተሰማ . . .
ስሜትማ ሟች ነው በቃ ተቀበረ ማን በማን ይፈርዳል
ፍቅር ግን ህያው ነው በይቅርታ አብቦ አዲስ ቀን ይወልዳል፡፡
‹‹እሱን ለኔ ስጠኝ!››
‹‹ለኔም!››
‹‹ለኔም!››
‹‹ለኔም!››
‹‹ለእኛም! ለእኛም! ለእኛም!›› !!!
ሁሉሙ ከፈለ፡፡

Read 1438 times