Sunday, 17 March 2019 00:00

ቃለ ምልልስ የአዲስ አበባ ውዝግብ እንዴት ነው የሚፈታው?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የህገ መንግስቱ አንቀፅ 49 ስለ ርዕሰ መዲና እንዲህ ይደነግጋል፡፡ ንዑስ አንቀፅ 1፤ “የፌደራሉ መንግስት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው፡፡” ይላል፤ ንዑስ አንቀፅ 2 ደግሞ፤ “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን ይኖረዋል፡፡ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል” ይላል፡፡ ንዑስ አንቀፅ 3፤ “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግስት ይሆናል” ይላል፡፡ ንዑስ አንቀፅ 4 ደግሞ፤ “የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዚህ ህገ መንግስት በተደነገገው መሰረት፣ በፌደራሉ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ይወከላሉ” ይላል፡፡ ከእነዚህ ግልፅ ድንጋጌዎች ቀጥሎ በንዑስ አንቀፅ 5 የተቀመጠው ደግሞ፤ “የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፤ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል” ይላል፡፡
እነዚህ ድንጋጌዎች በህገ መንግስቱ ላይ ባሉበትና ምንም ዓይነት ማሻሻያ ባልተደረገበት ሁኔታ በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ ላይ ለምን የተካረረ ውዝግብ ተነሳ? የሚለው የወቅቱ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ምንም ዓይነት ችግሮች ቢሆኑ መፈታት ያለባቸው በሰከነ ውይይትና ንግግር ነው ብለን እናምናለን፡፡ስለዚህም እንደተለመደው በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ ሃሳቦችንና አመለካከቶችን ለማንሸራሸር እንሞክራለን፡፡ በዚህም ዓላማ መሰረት፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ያነጋገራቸው ታዋቂ ምሁራንና ግለሰቦች የሰነዘሯቸው ሃሳቦች እንደሚከተለው ተጠናቅረው ቀርበዋል፡፡



                          “የአዲስ አበባ ጉዳይ በሰከነ አኳኋን መታየት አለበት”
                                አያልነህ ሙላት (ገጣሚና ጸሃፌ ተውኔት


          በአዲስ አበባ ጉዳይ በሁለቱም ፅንፍ ያሉ ቡድኖች አደብ ገዝተው፣ ሁሉንም ነገር በትዕግስትና በጨመተ የችግር አፈታት ዘዴ ነገሩን ማየት አለባቸው፡፡ በህብረተሰቡ ውስጥ ባሉ ባህላዊና ልማዳዊ የችግር አፈታት ዘዴዎችም ነገሩን ማየት ይገባል፡፡ እነዚህ ሁለት ኃይሎች ተቀምጠው የሚወያዩበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ በሌላ በኩል፣ አሁን ያለውን አመራር ከአንድ ወገን አድርጎ ከመፈረጅ ይልቅ ጊዜ ሰጥቶ፣ የተፈጠረውን ችግር በሰከነ መንገድ እንዲፈታ እድል መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ደርግ እኮ ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም ብሎ ሲነሳ፣ እኔ ራሴን ጨምሮ፣ ምሁሩ ወገን፣ ያለ ደም ሶሻሊዝም አይሳካም ብለን ጮኸንበት፣ወደማይፈለገው መንገድ ገፍተን አስገብተነዋል፡፡ ያኔ የምሁሩ ጥፋት ብዙ አሳጥቶናል። አሁንም ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንዳንገባ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ ያ ታሪክ እንዳይደገም፣ በድንገት ብዙ ነገሮችን ፈንቅሎ የወጣውን፣ ብዙም ልምድ የሌለው፣ ገና ጫጩት የሆነውን አመራር፣ ይሄን አምጣ ያንን አድርግ እያሉ ከወዲያም ከወዲህም መጫን የሚፈጥረው ነገር አስቸጋሪ ነው፡፡ አመራሩን ወደ ሌላ ፅንፍ ሊያስገባው  ይችላል፡፡ አንደኛ፤ እኛ ራሳችን ሰከን ብለን ጉዳዩን የምናይበት መንገድ ያስፈልጋል፡፡ ዞሮ ዞሮ የተነሳው ጥያቄ፣ የትም ሊያደርስ የማይችል መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ጥያቄው በራሱ ጥቂት ችግሮች ይዞ የተነሳ አይደለም፡፡ ዋናው ችግር ከፊታችን ነው ያለው፤ እሱም ምርጫ ነው፡፡ ያለ ምንም ጥይት ኢትዮጵያውያንን ወደ ዲሞክራሲ ሊያሸጋግር የሚችል ምርጫ ይካሄዳል አይካሄድም የሚለው ነው ትልቁ ችግር፡፡ ዛሬ በማይሆን ጉዳይ የማይረባ አጀንዳ ይዞ ከመጨቃጨቅ ይልቅ ይሄን ምርጫ እንዴት እናሸንፍ በሚለው ላይ ነው ፖለቲከኞች እርብርብ ሊያደርጉ የሚገባው። በዚህ አጀንዳ ሃገርን ለመበታተን መሞከሩ ተገቢ አይደለም፡፡
ዛሬ የኛ ትልቁ ጭንቀት፤ ችግርና ችጋር  ነው፡፡ ችግርን ማጥፋት ችጋርም እንዳይኖር ማድረግ ነው፤ ትልቁ ፈተና፡፡ ይሄን ከባድ የህልውና ፈተና ሳናልፍ ነው በማይረባ ጉዳይ የምንነታረከው። ለአፍሪካውያን በዚህ ረገድ ምሳሌ ሆነን፣ ትልቅ ሃውልት ገንብተን ማለፍ የምንችልበትን ዕድል ነው በማይረባ ጉዳይ ፅንፍ እየያዝን ያለነው፡፡ ይሄን ትልቅ ጉዳይ ጥለን ነው፣ ትንሽ አጀንዳ ላይ ተወሽቀን ለመጠፋፋት የቋመጥነው፡፡  
ሌላው የልዩ ጥቅም ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ ይሄ ነገር ያስፈልጋል አያስፈልግም? የሚለውን ለማወቅ ጥናቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ባህር ዳርም፣ አሶሳም፣ ሃዋሳም የየክልሉ ዋና ከተማ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ልዩ ጥቅም መስጠት አለባቸው ከሆነ፣ አስቸጋሪ ነው፡፡ አዲስ አበባን ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? የኢትዮጵያ ከተማ አይደለችም እንዴ? ምን ማለት ነው ልዩ ጥቅም? መሬት የህዝብና የመንግስት ነው ተብሏል። ታዲያ እንዴት ነው በህዝብና በመንግስት መሬት ላይ ልዩ ጥቅም የሚጠየቀው? ይሄ በሚገባ ውይይት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡   

_________________


                                         “አዲስ አበባ አለማቀፍ ከተማ ነች”
                                                ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ (የኢኮኖሚ ባለሙያ)


        አዲስ አበባ አለማቀፍ ከተማ ናት፡፡ የተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫ  ከተማ ናት፡፡ በሌላ በኩል፣ በአለም ላይ አለማቀፍ ማህበረሰብን በማስተናገድ፣ አዲስ አበባ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ የአፍሪካ የዲፕሎማቲክና የፖለቲካ ዋና ከተማ ናት፡፡ እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ፣ አዲስ አበባ የአንድ ብሔረሰብ ናት የሚባለው ተገቢ አይደለም፡፡ ሁሉም ሊኖርባትና ሁሉም  ባለቤት ሊሆንባት የምትገባ ከተማ ናት፡፡ በህገ መንግስቱም አዲስ አበባ ራሱን የቻለ መስተዳድር ነው፡፡ እንደ  አንድ ክልል የተቀመጠ ነው፡፡ እነዚህን ክልሎች የራሣቸው የተወካዮች ም/ቤት አስተዳደር እንዲኖራቸው ተደርጐ ነው የተቀመጠው፡፡ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ አሁን ግርግር የሚፈጥሩት ለውጡን ለማበላሸት የሚሞክሩ ሰዎች ሴራ ካልሆነ በስተቀር ወደሌላ ጉዳዩ የሚያስገባ አይደለም፡፡
በከፍተኛ አመራር ላይ የተቀመጡ ሰዎች፣ አዲስ አበባ አለማቀፍ ከተማ፣ ትልቅ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ማዕከል መሆኗን በየጊዜው መንገርና ግልጽ አቋም ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡ “አዲስ አበባ የኔ ነች፣ ያንተ ነች” በሚል ብጥብጥ ቢነሳ፣ ለዚህ መንግስትና በአጠቃላይ ለሀገሪቱ ሃፍረት ነው የሚሆነው፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች የማትሻሉ ተብለን ነው አንገታችንን የምንደፋው፡፡ ህግን የማስከበር ሃላፊነት የተጣለባቸው የከተማዋን ህግ ማስከበር አለባቸው፡፡ አስተዳደሩ መጠናከር አለበት፡፡ የዲሞክራሲ ምህዳሩ መስፋቱ እንዲቀጥል ከተፈለገ፣ አስተዳደሮች መጠናከር አለባቸው፡፡ የበዳይና ተበዳይነት አካሄድ መኖር የለበትም፡፡ አሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተስፋ የሚከተሉና የሣቸውን ስራ ለማበላሸት የሚጥሩ ሁለት ተቃራኒ አካላት ነው ያሉት፡፡ መንግስት ራሱን አጠናክሮ፣ በውስጡ ያሉትን  አጥፊዎች መስመር ማስያዝ  አለበት፡፡ በማናቸውም ውዝግብ በሚነሳባቸው ጉዳዮች ላይ ምሁራን አጥኚዎች  የተካተቱባቸው ውይይቶች መደረግ አለባቸው። ጽንፈኝነትን በዚህ መልኩ ማርገብ ያስፈልጋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን በማስተካከል ላመናቸው ህዝብ ጠንክረው መስራት አለባቸው፡፡  
አዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም የሚለው ጉዳይ፣ በሌሎች ሀገሮች ያልተለመደ ነገር ነው፡፡ በርካታ ፌደራላዊ ሀገራትን ብንመለከት ይሄ ነገር የለም። ልዩ ጥቅም የሚለው ሃሳብ ከየት እንደመጣ አላውቅም። ናይጄሪያ ፌደራል አስተዳደር ነው ያላት፡፡ ዋና ከተማዋ ላይ የመጣ የልዩ ጥቅም ጥያቄ የለም፡፡ አዲስ አበባ ትንሽ ለየት የሚያደርጋት፣ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአለምና የአፍሪካ መንግስታት የዲፕሎማቲክና የፖለቲካ ማዕከል መሆኗ ነው።  
ይሄን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ልዩ ጥቅም የሚባለው ከዚህ አንፃር ምን ያህል ያሻግራል የሚለውንም ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ አዲስ አበባን የበለጠ አለማቀፍ ከተማ ማድረግ እንጂ ወደ ትንሽነት መቀየር መልካም አይደለም፡፡
የኢኮኖሚ መስፋፋትና እድገትን ነው የበለጠ ማየትና ማስተዋል የሚገባው። ወጣቱ ከብሔር ብሔረሰብ ወጥቶ ጠንካራ የሃሳብ ባለቤት መሆን የሚችልበትን ነው ማለም ያለበት፡፡

__________________


                                   “ርዕሰ ከተማ ከተማ ማለት የሁሉም የሀገሪቱ ህዝብ መናኸሪያ ማለት ነው”
                                       ዶ/ር ንጋት አስፋው (የዩኒቨርሲቲ መምህር)


           ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም ይገባታል የሚል አንቀጽ በህገ መንግስቱ ተቀምጧል፡፡ ይሄ እስከ ዛሬ ድረስ ተግባራዊ አልሆነም፡፡ አንዱ ጥያቄ ለምንድነው እስከ አሁን ተግባራዊ ያልተደረገው የሚለው ነው፡፡ መቼም ሁሉም ሀገር የራሱ ርዕሰ ከተማ አለው፡፡ በዚያ ርዕሰ ከተማ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚያ ሰዎች የዚያ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው፤ የሀገራቸው ባለቤትም ናቸው፡፡ ይሄ አስተሳሰብ ሰፍቶ መቅረብ አለበት፡፡  
እኔ በርካታ የአለም ሀገራት ተሞክሮን ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ እንዲህ ያለ የከተማ ይገባኛልና ልዩ ጥቅም ጉዳይ አላጋጠመኝም፡፡ ታሪክ እንደሚያስረዳን፤ በሰው ህይወት መስተጋብር ውስጥ ከተማ ይፈጠራል፡፡ ያንን ከተማ የሚፈጥረውና የሚያስፋፋው በውስጡ ያለው ህዝብ ነው፡፡ እኛ የዛሬ 100 አመት አንኖርም እንጂ ብንኖር ምናልባት አምቦ፣ አዳማ፣ ደብረብርሃን የመሳሰሉት የአዲስ አበባ አካል ሆነው ልናገኛቸው እንችላለን፡፡ ከ100 አመት በኋላ ብንመለስ፣ በ150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያሉ አካባቢዎች በሙሉ፣ የአዲስ አበባ አካል ሆነው እናገኛቸው ይሆናል፡፡ የዚህ ከተማ ባለቤት ደግሞ በውስጡ የሚኖረው ህዝብ ነው፡፡ ርዕሰ ከተማ ማለት የአንድ ጐሣ ወይም ብሔረሰብ ከተማ ማለት አይደለም፤ የሁሉም የሀገሪቱ ህዝብ መናኸሪያ ማለት ነው፡፡ ቀዳሚ አለማቀፍ እውቅና ያለው ከተማ ማለት ነው፤ ርዕሰ ከተማ፡፡ አዲስ አበባ  ትልቅ የፖለቲካ ከተማ ነች፡፡
ነገር ግን ይሄ ሁሉ ችግር የሚመጣው ከህገ መንግስቱ ጉድለት ነው፡፡ ህገ መንግስቱ በጽንፈኛ ሀይሎች ወያኔና ኦነግ የተረቀቀ በመሆኑ ነው ዛሬ ብዙ የተጣመሙ ነገሮችን የምናይበት፡፡ ስለዚህ ይሄ ህገ መንግስት በእርጋታ መታየት ይገባዋል፡፡ ፌደራላዊ አወቃቀሩም  በሚገባ መፈተሽ  አለበት፡፡
በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን በሚመለከት ከየትኛውም አካል የሚወጣ መግለጫ ጥሩ አይደለም፡፡ በተለይ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ከሚመራው ኦዴፓ መግለጫ መውጣቱ ተገቢ አይደለም፡፡
ጉዳዩ ከመግለጫ ጋጋታ ይልቅ ወደ ውይይት ነው መምጣት ያለበት፡፡ ሚዲያዎችም ይሄን ጉዳይ ሲያነሱ፣ ነገሩን ሰፋ አድርገው መመልከት አለባቸው፡፡ ያልተገባ ቅስቀሳ ከማድረግ ተቆጥበው ወደ ውይይት ነው መግባት ያለባቸው፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ነች፤ ይሄ በህገ መንግስቱ ተቀምጧል፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን ህገ መንግስቱ የፈጠራቸውን  ግድፈቶች ማረም  የሚቻለው ህገ መንግስቱን በማሻሻል ነው፡፡


_________________



                            “መንግስት የአዲስ አበባን ጉዳይ ለውይይት ማቅረብ አለበት”
                                 አቶ ክቡር ገና (የግል ቢዝነስ መሪ)


          አንዱ ትልቅ ችግር በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ውይይት የመካሄድ እድሉ የጠበበ መሆኑ ነው፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማነቷ በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠ ጉዳይ  ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ ኦሮሚያ የኔም ዋና ከተማ ናት ይላል፡፡ እነዚህ ሁለት ጉዳዮች በህግ በደንብ መለየት አለባቸው፡፡ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ስትሆን ምን ማለት ነው? መብቱ እስከ ምን ድረስ ነው? በኦሮሚያ ዋና ከተማነት መብቷ የሚጠበቀው እንዴት ነው? የኢትዮጵያም ዋና ከተማ  ስትሆን መብቷ እስከ ምን ድረስ ነው የሚጠበቀው? የሚለው እስካሁን ድረስ ምንም ውይይትና ንግግር ያልተደረገበት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ክፍተት ማምጣቱ ሊደንቀን አይገባም፡፡ ይሄ ችግር ሊፈታ የሚችለው እንግዲህ አንደኛ፣ የህዝብ ውይይት በማድረግ ነው፡፡ አሁን ትልቁን  ችግር እየፈጠረ ያለው ኢህአዴግ በቀድሞ የፓርቲ አወቃቀር ላይ አለመሆኑ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚሉት ነገር እየላላ መምጣቱ፣ የተወሰኑ ሰዎች፣ ስልጣንን ያለ አግባብ ወደ መጠቀም ሳያስገባቸው አይቀርም፡፡   
የልዩ ጥቅም ጉዳይን በተመለከተ በልዩ መልኩ ነው መታየት ያለበት፡፡ በዋናነት ጉዳዩ ወደ ፓርላማ ነው መቅረብ ያለበት፡፡ ፓርላማውን በማሳመን ነው መወሰን የሚገባው፡፡ ምንም እንኳ በህገ መንግስቱ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ዝርዝሩ ግን ለውይይት መቅረብ አለበት፡፡  እንግዲህ አንዱ የዚህ ሁሉ ችግር ምንጭ፣ አንድ ትልቅ ከተማ ብቻ ያለን መሆኑ  ነው፡፡ ሌሎች ሀገራት እንደ ዋና ከተማ ተመሳሳይ፣ አንዳንዴም ከዋና ከተማው ሰፋ ያሉ ጠንካራ ከተሞች አላቸው፡፡ እኛ ግን  የለንም፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የኛ ውዝግብ ከድህነት አስተሳሰብ የመነጨ  እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ ስለዚህ ይሄ አጀንዳ ለውይይት ቀርቦ፣ በጊዜ መፍትሔ ማግኘት አለበት፡፡ መንግስት ጉዳዩን ለውይይት ማቅረብ አለበት፡፡ አንድ አካል ተነስቶ “ከተማዋ ያንተ አይደለችም፤ ማንም ወደዚህ ዝር ማለት አይችልም” እያለ ሲያስፈራራ ተጠያቂ የሚሆነው፣ ጉዳዩን በዝምታ የተመለከተው መንግስት ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር መፍትሔው  ጉዳዩን ለውይይት ሙሉ ለሙሉ ክፍት ማድረግ ነው፡፡
የአዲስ አበባን ጉዳይ በተመለከተ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ኮሚቴው ከህዝብ ጋር ውይይት አድርጐ፣ ጉዳዩን ለህዝብ ሪፈረንደምም ማቅረብ ይቻላል፡፡  

Read 1224 times