Sunday, 17 March 2019 00:00

ሲደጋገሙ እውነት የመሰሉ አዲስ አበባ ተኮር ተረኮች

Written by  መስከረም አበራ
Rate this item
(6 votes)


           አዲስ አበባ የወቅታዊ ፖለቲካችን የልብ ትርታ እየሆነች ነው፡፡ ለወትሮው የሃገራችን ፖለቲካዊ አሰላለፍ የዜግነት ፖለቲካና የዘውግ ፖለቲካ የሚራመድበት ተብሎ በሰፊው ለሁለት የሚከፈል ነበር፡፡ ሁለቱም የፖለቲካ ሰልፈኞች አዲስ አበባን መዲናቸው አድርገው የሚያስቡ ናቸው፡፡ ከዘውግ ፖለቲከኞች ውስጥ ‘ትልቅ ነን፣ ሰፊ ነን፣ ፍላጎታችንን ለማስጠበቅ የምችል ክንደ ብርቱ ነን’ ባዮቹ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች ደግሞ በአዲስ አበባ ላይ በለጥ ያለ ባለቤትነት አለን ይላሉ፡፡ ይህንንም በግልፅ ሲያስቀምጡት፤ “አዲስ አበባ ንብረትነቷ የኦሮሞ ሆና፣ ሌላው ሰውም በከተማዋ መኖር ይችላል” ይላሉ፡፡

መኖር ሁሉ መኖር ነው?
እዚህ ላይ ዋናው ጥያቄ፤ “አዲስ አበባ የኦሮሞ ንብረት በሆነችበት ከባቢ ውስጥ መኖር ትችላለህ የተባለው ኦሮሞ ያልሆነው ኢትዮጵያዊ የሚኖረው እንዴት ነው?” የሚለው ነው፡፡ መኖርማ ኢትዮጵያዊ የትም ይኖራል፡፡ መኖር ከተባለ በየመንም፣ በሊቢያም፣ በደቡብ አፍሪካም፣ በአፍጋኒስታንም፣ በቤሩትም ከፖሊስ ጋር አባሮሽ እየገጠመ ይኖራል። መኖር ሁሉ ግን መኖር አይደለም! የሆነ ምድር ባለቤት ነኝ ያለ፤ “በችሮታው” እንዲኖሩ የፈቀደላቸውን ህዝቦች እንዴት ሊያኖር እንደሚችል የሚጠፋው የለም፡፡ በሰው ቤት ሲኖሩ ሁሉን እሽ ብሎ፣ አጎንብሶ፣ ከክብርና መብት ጎድሎ ነው። ለዛውም ባለቤት ነኝ ባዩ የፈለገ ዕለት፣ አጎንቦሶ ተለማምጦ መኖርም ላይቻል ይችላልና፣ በሰው ግዛት ዋስትና የለውም፡፡  
“ሌላው ኢትዮጵያዊ መኖር ይችላል፤ እኛ ግን ባለቤት ነን” የሚሉት የኦሮሞ ብሄርተኞች፣ የተመኙት ሰምሮ ባለቤት ቢሆኑ ሰውን እንዴት እንደሚያኖሩት ዶ/ር ዐቢይ ስልጣን እንደያዙ መንግስታቸው በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ ያደረገውና  የሰሞኑ ይዞታቸው ፍንጭ ሰጭ ነው፡፡ ሰሞኑን የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር እንዲችል ለመምከር ተሰብስቦ ሲመለሰ፣ ተኩስ ተከፍቶበት የታሰረ ሰው ነበረ፡፡ ይህ የወደፊቱ የሚብስ እንደሆነ የሚያመላክት ነው። ዛሬ ባለቤትነቱ ሳይረጋገጥ፣ ምኞቱን ተከትሎ ብቻ እንዲህ ያደረገ አካል፤ ነገ የተመኘውን ባለቤትነት ቢያገኝ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ማሰብ ነው። ነገሩን በሰፊው እንየው ከተባለ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦች እየገጠማቸው ያለውን ችግር ብናስተውል፣ የኦሮሞ ብሄርተኞች “ሌላው መኖር ይችላል” ሲሉ በምን መንገድ ሊያኖሩ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡
በታሪክ ገፅ የተመዘገቡ በኦሮሚያ ክልል፣ በሌሎች ህዝቦች ላይ የተደረጉ በደሎችን ሳናነሳ፣ በዚች ቅፅበት የሚደረገውን ብቻ ብናነሳ እንኳን በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጌዲኦዎች፣ በቄሮና በታጣቂው ኦነግ “ከሃገራችን ውጡ” ተብለው መከራ እያዩ ነው። ይህ ዓለም ሁሉ የዘገበው፣ በባዕዳን ሁሉ ዘንድ ትዝብት ላይ የወደቅንበት ገበናችን ነው፡፡ በገዛ የሃገራቸው ሰዎች በጭካኔ ከቀዬአቸው ተባረው፣ ምግብ አጥተው፣ የከሳ ሰውነታቸውን እያሳዩ ስለ ጌዲኦ ተፈናቃዮች የሚዘግቡ የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን የሚነዙት ገበና የሚያመለክተው፣ የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች “የእኛ” ባሉት ምድር ኦሮሞ ሳይሆኑ መኖር ምን እንደሚመስል፣ ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል ነው፡፡
በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት በቄለም ወለጋ በ1977 ዓ.ም (ምናልባትም ዛሬ ባለ ሃገር ነን ብለው የሚያፈናቅሉት ቄሮዎች ሳይወለዱ) ወደ ስፍራው ያቀኑ የአማራ ክልል ተወላጆችና የልጅ ልጆቻቸው አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ እየተገደዱ ነው፡፡ በዚህ ማስገደድ ውስጥ ቄሮ፣ የክልሉን መንግስት የሚመራው የኦዴፓ ባለስልጣናትና የክልሉ የፀጥታ ሃይሎች በትብብር እንደሚሰሩ ተጎጂዎቹ ተናግረዋል፡፡ በነዚህ የአገር ባለቤት ነን በሚሉ ሃይሎች፣ አማራ በመሆናቸው ብቻ ሴቶች ይደፈራሉ፣ ወንዶች እግራቸው ወደመራቸው ጫካ እየገቡ እንደሆነ ነው እማኞች ለኢሳት የተናገሩት። ክልሉን የሚያስተዳድረው “የለውጥ ሃይል ነኝ” ባዩ ኦዴፓ ታዲያ በቦታው ደርሶ ሰዎቹን ከመታደግ ይልቅ ችግሩን ሽምጥጥ አድርጎ መካድን መርጧል። ጭራሽ ነገሩን የዘገበውን ጣቢያ ኢሳትን እከሳለሁ እያለ ነው፡፡
በጉጂ ዞን የሚኖሩ ጌዲኦዎችንና በቄለም ወለጋ የሚኖሩ አማሮችን ጉዳይ ወቅታዊ ስለሆነም አነሳሁት እንጂ ኦሮሞ ሳይሆኑ በኦሮሚያ ክልል መኖር ያለው ፈተና ብዙ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በየቀኑ የሚንቆለጳጰሰው ወያኔን የጣለው ትግል አካል በሆነው የቄሮ እንቅስቃሴ ወቅት በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ወገኖች በትልቅ ችግር ውስጥ እንደነበሩ የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ንብረት ከሆነች በኋላ መኖርን አንከለክልም” የሚለው የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች ስብከት፣ አጓጉል ማስመሰል እንደሆነ ለገጣፎን፣ ሰበታንና ቡራዩን ያየ ሁሉ መረዳት የሚችለው ነገር ነው፡፡  
አዲስ አበባ የኦሮሚያ ንብረት ስትሆን አዲስ አበባን ሊያስተዳድሩ የሚመጡት እንደ ለገጣፎዋ ከንቲባ ወ/ሮ ሃቢባ ሲራጅ ያሉ በግፍ የተፈናቀሉ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን እንኳን እንዳይጠለሉ የሚያደርጉ “ግፍ ልብሱ” የሆኑ፣ ህወሃትን የሚያስከነዱ ዘረኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰብዓዊነት በዞረበት ያልዞሩ ሰዎች የተሾሙት መልአክ ናቸው በሚባሉት አቶ ለማ እና ሙሴ የሚባሉት ዶ/ር ዐቢይ በሚመሩት ኦዴፓ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በፊት በስህተት ተሹመው ይሆናል ከተባለም፣ ይህን ሁሉ ግፍ ከሰሩ በኋላም እዛው ስልጣን ላይ መቀመጣቸው፣ አዲስ አበባን ንብረቴ ላድርግ የሚለው ኦዴፓ፤ ለሰለጠነ የከተሜ ፖለቲካም ሆነ ለአዲስ አበባ እንደማይመጥን ነው። አዲስ አበባን የሚመጥናት በማህጸኗ ተወልዶ ያደገ/የኖረ፣ ችግሯን በውል የሚረዳ፣ የሰለጠነው ዘመን ውስብስቦሽ ሰውን በዘሩ ብቻ ለመተመን እንደማያስችል የሚያውቅ፣ ከሁሉም በላይ የከተማውን ህዝብ ይሁንታ ያገኘ ሰው ነው፡፡ መሆን ያለበት ይህ ሆኖ ሳለ “አዲስ አበባ ለኦሮሞ ከፈጣሪ የተሰጠችን እርስት ነች” እንደማለት የሚሞክረው ነገር፣ ከኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች ዘንድ እየተደመጠ ይገኛል፡፡
አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ እነዚህ ሃይሎች አዲስ አበባ ለእነሱ እንደምትገባ ሲከራከሩ በዋናነት የሚጠቅሱት ታሪካዊና ህገ-መንግስታዊ ማስረጃዎችን ነው፡፡ ከሁለቱም ማስረጃዎች የሚበረታው ግን የደመነፍስ ለእኔ ብቻ የሚያስብል ጉጉታቸውና ሌላውን ገፍትሮ ራስን ብቻ የማስቀደም አስገማች አካሄዳቸው ነው፡፡ ከታሪክ አንፃር አዲስ አበባ የኦሮሞ የግል ንብረት የምትሆነው አለም የተፈጠረው፣ ታሪክ የተቆጠረው ከአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ቢሆን ነበር። በህገ-መንግስቱም ቢሆን አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ ዋና ከተማና ራሷን የምታስተዳድርበት ምክር ቤት ያላት ከተማ እንጂ በጨፌ ኦሮሚያ ስር የምትተዳደር ከተማ ነች አልተባለም፡፡ አዲስ አበባን ለመውሰድ የሚቋምጠው የኦሮሞ ብሄርተኛ ሁሉ ይህን አይክደውም፤ ያምታታዋል እንጂ!
ማምታቻ አንድ ፡ የመቀመጫ እና የመዲና ተረክ
የኦሮሞ ብሄረተኝነት ልሂቃን፣ አዲስ አበባ የኦሮሞ ለመሆኗ ታሪክና ህገ-መንግስት ምስክራችን ነው ይበሉ እንጂ ታሪክንም ሆነ ህገ-መንግሰቱን ተንተርሰው ጠበቅ አድርገው የሚያስረዱት ብርቱ ክርክር አያመጡም፡፡ ምክንያቱም ታሪክም ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ያልፋል፤ ህገ-መንግስቱም አዲስ አበባ ባለቤቷ ጨፌ ኦሮሚያ ነው አይልምና ነው፡፡ ይህ ነገር ሩቅ እንደማያስኬዳቸው ያወቁት፣ ለአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ሲሆን ብቻ የሚስማሙት የኦሮሞ ብሄርተኛ ልሂቃን፣ ሌላ አዳዲስ ግማሽ እውነቶች እያመጡ፣ ጥያቄያቸውን ትክክለኛ ለማስመሰል  እየሞከሩ ነው፡፡
አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መዲና እንደሆነች ስሜት ውስጥ ገብቶ ማውራት ሰሞኑን ከመጡ ማምታቻዎች ዋነኛው ነው፡፡ ይህ  ቅጥፈት በዚህ አያበቃም፡፡ ጭራሽ አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ፣ የኦሮሚያ ክልል ደግሞ መዲና እንደሆነች መላልሶ በማውራት እውነትን ከታች ወደ ላይ ገልብጦ፣ በሃሰት የመተካት ሃፍረተ-ቢስ አካሄድ ተይዟል፡፡ የባሰው ሲመጣ ደግሞ አዲስ አበባ የኦሮሚያ መዲና  መሆኗ የማያከራክር፤ መቀሌ የትግራይ፣ ባህርዳር የአማራ ክልል ዋና ከተማ ከመሆኗ ጋር እያወዳደሩ ምሳሌ ማድረግ ነገሬ ተብሎ ተይዟል፡፡ እውነቱ ግን ተቃራኒው ነው፡፡
አዲስ አበባ የኦሮሚያ መዲና ነች የሚል ህግ ሆኖ የወጣ ብሄራዊም (ፌደራላዊ) ሆነ ክልላዊ ህገ መንግስት የለም፡፡ የፌደራሉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 49/1 አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ ርዕሰ ከተማ እንደሆነች በግልፅ ያስቀምጣል። በ1994 የተሻሻለው የኦሮሚያ ህገ-መንግስት አንቀፅ 6 ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መዲና አዳማ እንደሆነች በግልፅ ይደነግጋል፡፡ ይህ የተሻሻለው ህገ-መንግስት የፀደቀው ራሱ በአዳማ ከተማ እንደሆነ በመጀመሪያዎቹ ገፆች ላይ አስቀምጧል፡፡ ይህ የሆነው አሁን ኦሮሚያ የአዲስ አበባ ጌታ እንደሆነች ታሪክም ህገ-መንግስትም ምስክር ነው የሚለው የአቶ ለማ ኦዴፓ/ኦህዴድ በሌለበት አይደለም፡፡ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ እንደሆነች የሚደነግገው አቶ ለማ በምስክርነት የሚጠሩት ህገ-መንግስት የቱ እንደሆነ የት ተገኝተው ይጠየቃሉ?
ይህ ከሃቅ ጋር የማይመሳከር የግፋኝ ክርክር ለደምፍላት ፖለቲከኞች መንደርደሪያ ሆኖ፣ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዘዝ የምትለው የአማራ ክልል በባህርዳር ላይ ልዘዝ እንደሚለው ወይም የትግራይ ክልል በመቀሌ ላይ ልዘዝ እንደሚለው ነው ተብሎ ቁጭ አለ፡፡ ይሉኝታቢስነት፣ ቅጥፈት፣ ግማሽ እውነት በአደባባይ ሲናገሩት የማያሳፍርበት፤ አይነ-ደረቅነትና የአደባባይ ውሸታምነት ቅሌት እንደ ጉብዝና የሚታይበት ዘመን ስለሆነ፣ ይህ ነገር እንደ እውነተኛ ነገር ተቀጥሎበታል፡፡ እውነቱን ተናግሮ ለማለፍ ግን አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ ዋና ከተማ፤ የኦሮሚያ ክልል ደግሞ መቀመጫ ነች፡፡ መቀመጫ እና መዲና ይለያያል፡፡ መቀመጫ ማለት ተቀማጩ (በዚህ ሁኔታ የኦሮሚያ ክልል መንግስት) በከፊል መስሪያ ቤቶቹን አዲስ አበባ አድርጎ ስራውን ይሰራል ማለት ነው፡፡
በዚህ መሰረት የኦሮሚያ ክልል መስሪያቤቶች በአብዛኛው አዲስ አበባ ሲሆኑ የክልሉ ምክር ቤት አዳማ ከትሟል፡፡ የገልማ አባገዳ የተንጣለለ አዳራሽ በአዳማ ከተማ የተገነባው ለዚህ ነው። የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የማንኛውም መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ህግ አውጭው የመንግስት ክንፍ/ፓርላማው ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልልን የሚመራው ኦዴፓ(የቀድሞው ኦህዴድ) የፓርላማ መቀመጫውን ያደረገው አዳማ ላይ በተገነባው ገልማ አባገዳ ነው፡፡ አሁን ክልሉ የሚመራበት በ1994 የተሻሻለው ህገ-መንግስት የፀደቀው በራሱ በህገ-መንግስቱ የክልሉ መዲና ተብላ በተጠቀሰችው አዳማ ላይ በተደረገ ስብሰባ እንደሆነ እዛው ህገ-መንግስቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ንብረቴ ነች የሚለው ኦዴፓ፤ በአንድ ወቅት በአቶ መለስ ትዕዛዝ ጓዙን ጠቅልሎ አዳማ ገብቶ አንደነበር ታሪክ መዝግቦታል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጓዙን ጠቅለሎ ወደ አዳማ ከትሞ የነበረውም ሆነ ዛሬም ቢሆን በከፊል መስሪያቤቶቹን አዳማ ላይ ያደረገው ያለ ምክንያት አይደለም- አዳማ የኦሮሚያ ክልል ህጋዊ (ህገ-መንግሰታዊ) መዲናዋ ስለሆነች እንጂ፡፡
ባህርዳር የአማራ ክልል፤ መቀሌ የትግራይ ክልል መዲና እንደሆነችው ባለ የህጋዊነት መጠን አዲስ አበባም የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ነች የሚለው የኦሮሞ ልሂቃን ክርክር ልክ ቢሆን ኖሮ፣ አዲስ አበባ የምትመራው በጬፌ ኦሮሚያ በሚወጡ ህጎች ሆኖ ማየት ነበረብን፡፡ ምክንያቱም ባህርዳር የምትመራው በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት በሚወጡ ህጎችና ደምቦች ነው፡፡ መቀሌም እንደዚያው በትግራይ ክልላዊ መንግስት ፓርላማ በሚደነገጉ ህጎች ትተዳደራለች፡፡ አዲስ አበባ ግን የራሷ ፓርላማ ያላት፣ በራሷ ምክር ቤት የምትተዳደር ከተማ እንጂ በኦሮሚያ ክልል በተመረጡ አንደራሴዎች በሚወጡ ህጎች አትመራም፡፡ ይህን ቄሮም ሆነ አለቃው፤ ኦህዴድም ሆነ ኦነግ የአዲስ አበባ ባለቤትነት አምሮት ከቁጥጥራቸው ውጭ ሆኖ ስላዋተታቸው የማይቀይሩት ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ አይቀየር የማለቱ ጥብቅና የሚበረታው ደግሞ በእነርሱው ስለሆነ፣ ሲመችም ሳይመችም ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ማክበር ግድ ይላቸዋል፡፡      
አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል.....
ኦሮሚያ ክልል የሚመራበት ህገ-መንግስት በግልፅ የክልሉ መዲና አዳማ ነች ሲል በደነገገበት ሁኔታ፣ የኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባን መቀመጫው ያደረገው በምን የህግ መሰረት እንደሆነ ኦህዴድም ሆነ እውቀት ከእኔ በላይ ላሳር የሚሉ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ሲያስረዱ አጋጥሞኝ አያውቅም። በርግጥ እነሱ የማያስረዱት ጠያቂ ስለጠፋም ይሆናል። የኦሮሚያ ዋና ከተማ አዳማ መሆኗ በህግ ተደንግጎ ሳለ፣ የክልሉ መንግስት አዲስ አበባ የተቀመጠው፣ ደግሞ ወደ አዳማ የሄደው፣ ከ1997 ወዲህ ደግሞ መልሶ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ የመጣው በአቶ መለስ ትዕዛዝ እንደሆነ ግልፅ ነገር ነው፡፡
አቶ መለስ ለምን ይህን አደረጉ ለሚለው ጥያቄ ደግሞ መልሱ በ1997 ምርጫ በአዲስ አበባ ህወሃት መራሹ መንግስት በደረሰበት ሽንፈት ሳቢያ በመበሳጨቱ በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ የውዝግብ ችግኝ መትከሉ ነው፡፡ ይሄው ችግኝ አድጎ ነው ዛሬ እያነታረከን ያለው፡፡ በተጨማሪም “ህወሃት እኔ ስልጣን ከለቀቅኩ ሃገሪቱን ለኦነግ አስረክቤ ነው የምሄደው” ባለው መሰረት፣ ወዶ ስልጣኑን በግልፅ ኦነግ ነኝ ለሚል አካል ባያስረክብም እየሆነ ያለው ግን ህወሃት በተመኘው መንገድ ነው፡፡ የሃገሪቱን ስልጣን በተቆጣጠረው ኦዴፓ ውስጥ ገዥው ሃሳብ የኢትዮጵያ መኖር ያለመኖር ግድ የማይሰጠው የኦነግ ሃሳብ ነው፡፡ ዛሬ ሃገሪቱንም ሆነ አዲስ አበባን የሚያሰጋት፣ በተለያየ ስም በሚጠሩ የኦሮሞ ፓርቲዎችና ግለሰብ አክቲቪስቶች ያደረው የኦነግ መንፈስ ነው፡፡
ሲጠቃለል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እንደ ዘሃ ዘጊ ከአዲስ አበባ አዳማ የሚያደርገው ምልልስ ደራሲው፣ የእኩይ ፖለቲካ ሊቁ አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ በሌላ ህግም ሆነ አዋጅ ሳይደገፍ በአቶ መለስ ቀጭን ትዕዛዝ ብቻ አዲስ አበባ የከተመው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ነው እንግዲህ የአዲስ አበባ ባለቤት ነኝ የሚለው፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ ራሷን በራሷ እንድታስተዳድር የሚታገል አዲስ አበቤ ሁሉ ካልገዛኋችሁ ሞቼ እገኛለሁ ለሚለው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ማንሳት ያለበት ጥያቄ፤ “የአዲስ አበባ ባለቤትነቱ ቀርቶ መቀመጫነቱን የደነገገው ህግ የቱ ነው?” የሚል ነው፡፡ የመለስ ተንኮል ህግ ሆኖ ተጠቅሶ አያከራክር መቼም! ዘመኑ እፍረት የጠፋበት ነውና የአዲስ አበባ ብቸኛ ባለቤት ያደረገን መለስ ነው ከተባለም፣ መለስ ጌትነቱ ጠፍጥፎ ለሰራቸው ፓርቲዎች እንጂ ለአዲስ አበባ ህዝብ አይደለምና ነገሩ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡  
ሌላ ነገር እንበርብር ከተባለም፣ በሽግግሩ ወቅት አዲስ አበባ ሯሷን የቻለች ክልል 14 እንጂ አሁን እንደሚወራው በዘመን መካከል ሁሉ ከኦሮሚያ ጋር የተሰፋች ርስት አይደለችም፡፡ ነገሩ አሁን እንደሚወራው ቢሆን ኖሮ ኦነግ አድራጊ ፈጣሪ በነበረበት የሽግግሩ ወቅት አዲስ አበባ እንዴት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ሆና ሳትደለደል ቀረች? የሽግግሩ ወቅት የታሪክ አካል ነው፡፡ አቶ ለማ የታሪክና የህግ ምስክር ጠርተው አዲስ አበባ የኦሮሚያ ንብረት መሆኗን ሲያስረዱ፣ የሽግግር ዘመኑ የታሪክ እውነታ የሚቆመው ግን በተቃራኒያቸው እንጂ በጎናቸው አይለም፡፡ ከዛ በፊት ያለው ታሪክም ቢሆን ክርክራቸውን አይደግፍም፡፡ ከዚህ አይነት የክህደት ክርክር የሚገኘው ትርፍም ትዝብት ብቻ ነው፡፡
ማምታቻ ሁለት፡ ተበታተንኖ እና
ተሰባስቦ የመኖር ነገር
የኦሮሚያ ክልል በውስጡ የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎችን መብት አያከብርም የሚል በተግባር ማሳያ ያለው ትችት ይቀርብበታል፡፡ ሌሎች ክልሎች ለምሳሌ የአማራ እና የደቡብ ክልል በውስጣቸው ለሚኖሩ የተለያዩ ብሄረሰቦች፣ የልዩ ዞንና ልዩ ወረዳ የአስተዳደር መልክ ሰጥተው ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ይፈቅዳሉ፡፡ የኦሮሚያ ክልል ይህን ለምን እንደማያደርግ የሚጠየቁ የኦሮሞ ምሁራን፤ ኦሮሚያ ይህን የማያደርገው በክልሉ የሚኖሩ ሌሎች ህዝቦች የራሳቸውን ልዩ አስተዳደር ለመከለል እንዲመች ሆነው በአንድ ቦታ የማይኖሩ ይልቅስ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ተሰባጥረው የሚኖሩ ስለሆኑ፣ ክልሉ ልዩ ወረዳና ዞን ለመስጠት ተቸግሮ እንዳለ ይገልፃሉ፡፡ ይህን ባሉበት አፋቸው ደግሞ ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦች ተሰባስበው በአንድነት የሚኖሩበትን፣ በህገ-መንግስት የኦሮሚያ ክልል አካል ያልሆነውን  የአዲስ አበባ ከተማን ካላስተዳደርን፣ በግዛቱም ላይ ባለቤት ካልሆንን ብለው የህዝቡን ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት በዱላ ጭምር ለመጋፋት ይሞክራሉ፡፡
በክልላቸው ውስጥ ያልሆነውን፣ በአንድ ውስን አካባቢ የሚኖር ህዝብ፣ የግል ንብረቱ ለማድረግ የሚያንቧትረው የኦሮሚያ ክልል፤ በክልሉ ውስጥ ያሉ ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦች በአንድ ላይ ቢኖሩም፣ ልዩ ዞን ወይም ወረዳ ሰጥቶ፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ያደርጋል ማለት የማይታመን ነገር ነው፡፡ ክልሉ ይህን አደርጋለሁ ካለ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ደራ በምትባለው የኦሮሚያ ክልል ምድር ላይ የሚኖሩ አማሮች የሚያነሱትን የልዩ ዞንነት ጥያቄ መልሶ ያሳይ፡፡  
ማምታቻ ሶስት፡ የማዕከልነት ጥያቄ
ሌላው የኦሮሞ ልሂቃን ክርክር አዲስ አበባ ለእኛ ትገባናለች የምንለው ዙሪያዋን በኦሮሚያ ተከባ  በመሃል የምትገኝ ስለሆነች ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ላይ አዲስ አበባ ቀደምት ነዋሪዎች ኦሮሞዎች ነበሩ፣ ከተማዋ ስትቆረቆር በግድ ተፈናቅለው ነው የሚል ክርክር ይደርባሉ፡፡ የአዲስ አበባ ቀደምት ነዋሪዎች ኦሮሞዎች ነበሩ የሚለውን ልብ አውላቂ ክርክር  አይረቤነት ከዚህ ቀደም በሰፊው ስላነሳሁ ለአሁኑ  ከ15ኛው ክፍለ ዘመን በፊትም ዘመን ነበረ፣ ሰው ነበረ በሚለው ብቻ ልለፈው፡፡ ወደ ፊተኛው ክርክር ማለትም አዲስ አበባ በኦሮሚያ እምብርት ላይ ስለምትገኝ ለእኛ ትገባለች ወደ ሚለው ክርክር ስንመለስ፣ አጭሩ መልስ፣ የአንድን ግዛት ዙሪያውን መክበብ ብቻ ባለ እርስት እንደማያደርግ የሌሴቶንና የደቡብ አፍሪካን ካርታ አፈላልጎ ማየት ነው፡፡ ሌሴቶ በደቡብ  አፍሪካ ግዛት መሃል ላይ የምትገኝ ግን ራሷን የቻለች ሃገር ሆና የምትኖር ሉዓላዊት ሃገር ነች፤ደቡብ አፍሪካም “ስለከበብኩሸ ልዋጥሽ” ሳትላት እስከ ዛሬ በጉርብትና ይኖራሉ፡፡ ዙሪያዋን በጣሊያን ግዛት ተከባ ግን በመንፈሳዊ መሪ የምትመራዋ የቫቲካን ግዛትም እንዲሁ የጣሊያን መንግስት “ንብረቴ ነሽ” ብሏት አያውቅም፡፡
በአጠቃላይ የኦሮሞ ብሄርተኞች በአዲስ አበባ ላይም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚያሳዩት እንደ ልጅ ሁሉም ለእኔ ይገባኛል የሚለው አካሄድ ጠላት ያበዛባቸው ይሆናል እንጂ የሚያሳኩት ምኞት አይመስልም፡፡ እንዲህ ያለ የፖለቲካ እሳቤ የሚንጠው፣ የራሱን ምኞት እንኳን መግራት ያልቻለ ቡድን ስልጣን ላይ መሆኑ ደግሞ ችግሩን ሃገራዊ ስፋት ይሰጠዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የሃገሪቱን የፖለቲካ አሰላለፍ ያመሳቅለዋል፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኞች ሁሉን ለእኔ የሚል አካሄድ፣ የሃገሪቱን ፖለቲካ አሰላለፍ እንዴት ያደርገዋል የሚለውን ጉዳይ ለማንሳት ሳምንት ልመለስ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ የጸሃፊዋን አመለካከት
ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡

Read 2366 times