Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 26 May 2012 13:16

ቴዲ አፍሮ የዘመኑ ጥቁር ሰው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የለሰለሰ ኢትዮጵያዊ መልክና ህብረ ብሔራዊ ዜማ፤ ከዛሬ በላይ ነገ ከነገ ወዲያ ሲሰሙት እያሸተ፤ እየጐመራ ውስጥን በሀሴት እየኮረኮረ የሚሄድ - የቴዲ አዲሱ አልበም!ከዜማው ግጥሙ፣ ከግጥሙ ቅንብሩ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እድሜና ፆታ ሳይለይ የሚያግባባ፣ የሚገባ፣ ታሪክን ከባህል አጣምሮ ከትልቁ የህይወት ክብ ውስጥ ትንሹን ነጥብ መዝዞ” በዚያም ረጅሙን የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል በፍቅር የሚተርክ፡፡ ዘላቂ ጭብጦችን (ፍቅር፣ ጥላቻ፣ ፀብ…) ለዛ ባለው ቋንቋ መጥኖ ለጆሮ ያደረሰ “ጥቁር ሰው አልበም”፡፡ “ከሚገባሽ በታች ከምችለው በላይ!” አቤት በእነዚህ ሁለት ሀረጋት መካከል ያለው ርቀት! በብዙ ክንድ ይሰፈራል፡፡ በጣም ወዷትም አልረካ፣ ይህን ያህል ቃትቶም ለእሷ ውበት፣ ስብዕናና ሴትነት አልመጠነለትም…

“ጥቁር ሰው” የቴዲ አዲሱ አልበም ስም! ማነው ጥቁር ሰው? ገራገር አድማጭ ምኒሊክ ነው ቢል እውነቱን ነው፤ መስሎታላ፡፡ ሲመስለው ደግሞ አይምሰልህ አይባልም፤ መሰለኝ ደግሞ አያስጠይቅም፡፡ ይሁን እንጅ ይህን አባባል ከመረመርነው ትዕምርትነቱ (Symbol) ጐልቶ ይሰማናል፡፡ የአንድ ህብረተሰብ ባህል፣ ቋንቋ፣ ስነጽሑፍ ባጠቃላይ የማንነቱና የምንነቱ መግለጫ ነው ትዕምርት፡፡

መስቀል በአመተ ፍዳ ዘመን የቅጣት፣ በአመተ ምህረት ደግሞ የድህነት ምልክት ነበር/ነው፡፡ በሰዎች ዘንድም በዘመናቸውም ሆነ ከዘመናቸው አልፈውም እንደልዕለ ሰብ የሚታዩ ወይም የሚዘከሩ አሉ፡፡ አርአያ ሰብ ልንላቸው እንችላለን፡፡ አርአያነታቸውም በክልላቸው ብቻ ላይወሰን ይችላል፡፡ የልዕልናቸው ብርሃን ለሀገራቸው ለአህጉራቸው ከዚያም ከፍ ሲል ለዓለም ይተርፋል፡፡ ታዲያ ቴዲ ምኒልክን ጥቁር ሰው ቢላቸው” ለአገራቸውና ለአህጉራቸው እንደትዕምርት ቢመለከታቸው ነው ቢባል ያስኬዳል፡፡ ቴዲ “ለአፍሪካ ልጆች ድል ቀና” የሚለው በነጭ ቅኝ ገዥዎች ላይ ጥቁሮች ድል የተቀዳጁበት፣ የመላ አፍሪካዊያን ኩራት፣ ታሪክና ድል በመሆኑ ነው፡፡ምኒልክን፣ ጣይቱን፣ ባልቻን፣ ሀ/ጊዮርጊስንን፣ አሉላን፣ መንገሻን…ወዘተ ከድፍን ኢትዮጵያ አሰባስቦ አድዋ ላይ ያስከተመው ቴዲ፣ በዚያ ዘመን የተፈፀመን አንድነት፣ ሀቅ እና ፍቅር ሲዘክር እናያለን፡፡

አድዋ ሲሄድ ምኒልክን ኑ ካለ

አይቀርም በማሪያም ስለማለ

ታዲያ ልጁስ ሲጠራው ምን አለ

ዎይ!

ምኒልክ ወደ አድዋ ለመዝመት ሲዘጋጁ መስከረም 1895 ዓ.ም ያደረጉት የክተት አዋጅ በከፊል እንዲህ የሚል ነበር:-

ሀገርንና ሃይማኖትን የሚያጠፋ ጠላት ባህር ተሻግሮ መጥቷል፡፡ እኔም ያገሬ ሰው መድከሙን አይቼ እስካሁን ብታገሰውም…ያገሬ ሰው ጉልበት ያለህ ተከተለኝ፤ጉልበት የሌለህ በፀሎትህ እርዳኝ … ማሪያምን አልምርህም!

ቴዎድሮስ ካሳሁን ይህን መጥቀሱ አይደለም የሚገርመው፡፡ “ታዲያ ልጁስ ሲጠራው ምን አለ?” ብሎ ራሱ ይጠይቅና “ወይ” ብሎ ነው በአራት ነጥብ የሚዘጋው፡፡ ቴዲ አይንዛዛ፤ አያንዛዛ፡፡ “ወይ” ውስጥ ያለው ታሪክ ግን አንድ የታሪክ ድርሳን ይሆናል፡፡ ትንሽ ወረድ ብሎ  ያልታሰበ ሌላ ነገር ይመዛል፡፡

ወይ ሳልለው ብቀር ያኔ (2 ጊዜ)

እኔን አልሆንም ነበር እኔ

”” ”” ”” (4 ጊዜ)

”” ”” ””

የስንኞቹ መደጋገም ለአጽንኦት ነው፡፡ እውነት አባቶቻችን ወይም አያቶቻችን ያኔ ወይ ባይሉ ኖሮ እኛ እኛን እንሆን ነበር? ይህን ግጥሙን ገልብጠን ካነበብነው

ምንሊክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ

ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ

የሚል ለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ዘመንና ቃላቱ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዳራው ቢለያይም የተመሰረተበት ጭብጥ አንድ ነው፡፡ ይሄ ለጣይቱም ነው! እሷም “ለምን ነገ ጠዋት አትመጣም” ብላለቻ! ጦር መርታ ተዋግታለቻ፡፡ ለዚህ ነው ጥቁር ሰው ለምኒልክ ቁመተ ስጋ ብቻ የተለካ ስም አይደለም” ወኪል ነው የምለው፡፡ የሀገራችን ከፍ ብሎም የአፍሪቃን ጥቁርነት በውስጡ የያዘ የዚች አህጉር ትዕምርት (Symbol) ነው፡፡ እሱ ወኪል ልዕለ ሰብ ነውና!

ሁለተኛው “ስለፍቅር” በሚል ሀረግ የቀረበ ዜማ ነው፡፡ በርግጥ በተቃራኒ ጾታ ላይ የተመሰረተ ግጥም አይደለም፡፡ ያ ባያቅተውም ይሄኛው ግን “እንደ ባቢሎን ግንበኞች በቋንቋ ልንግባባ አልቻልንም” ነው የሚለው፡፡ የስነጽሑፍ ባለሙያዎች ይህን አይነቱን የአገጣጠም ስልት አያዋ (paradox) ይሉታል፡፡

የሚጋጭ የሚመስል፤ ከዘወትሩ የማህበረሰብ ልማድ ያፈነገጠ፣ ግን ግን ሲመረምሩት ዕውነት የሆነ እንደማለት ነው፡፡ ለዚህ አይነቱ ስልት ዋቢ እንስጥ ከተባለ የኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) በረከተ መርገም፣ የፈቃደ አዘዘ እየሄድኩ አልሄድም በዋናነነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ በቀደመው አልበሙ ቴዲ ራሱ ያነሳው እያነቡ እስክስታም ሌላ ዋቢ ነው፡፡ እግር እያለን አለመራመዳችንም የዚሁ ስልት አካል ነው፡፡

መርገም እንደበረከት፣ በእስክስታ ላይ እንባ” እየሄዱ አለመሄድ እና እግር ኖሮ አለመራመድ የሚገርምም የሚያሳዝንም ነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ አንድ ላይ ሆኖ መለያየትም አለ” በእርግጥ አብሮ ሆኖ ከመለያየት ተለያይቶ አንድ መሆን ይሻላል፡፡

ስለፍቅር ሲባል ስለፀብ ካወራን ተሳስተናል!

የመጣነው መንገድ ያሳዝናል

…………

እግር ይዞ እንዴት አይሄድም

ሰው ወደፊት አይራመድም

አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ

ለምን ይሆን የራበው ሆዴ

ትልቅ አባባል ነው! ይሄ እኮ በትዳርም፣ በስራ ቦታም፣ በማህበራዊ ግንኙነትም፣ ከፍ ሲልም በአገር ፖለቲካ ላይ ሲከሰት የሚታይ ዘወትራዊ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ አሏ! ይህን የመሰለ አገር ይዘን መራባችን፣ የዚህን ያህል ዘመን ታሪክ ይዘን “የአባቶቻችን ልጆች፣ የአያቶቻችን ወላጆች” እንዳለው ፀጋዬ” ዕድገታችን እንደካሮት ቁልቁል መሆኑ የማያሳዝነው ኢትዮጵያዊ ቢኖር ራሱ ያሳዝናል፡፡

የአንድ ሀገር ወይም ህዝብ እድገት በስልጣኔም ሆነ በኑሮ ከፍ ያለ ቦታ ለመድረስ ቅድመ አያቱ በሰራው ላይ አያቱ፣ ከዚያ አባቱ ቀጥሎም ልጆቹ” እሱ ደግሞ ለመጪው በማሰብ ሲኖር መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ቴዲ እንዳለው እንኳ ከፋሲል እስከ እኛ ካለው ታሪክ ብንነሳ

የት ጋር እንደሆነ ይታይ የእኛ ጥበብ መሰረቱ

የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ

ሳይራመድ በታሪክ ምንጣፍ

ሰው አይደርስም ከዛሬ ደጃፍ፡፡

የጥበባችን መሰረት የት ጋ እንደሆነ የጠፋብን ትውልዶች መሆናችን ነው፡፡ ድምጻዊው እንፈልገው ማለቱም ይህን ዱካው የጠፋበት አንድ ፈለግ (pattern) መከተል ያልቻለውን ዝንቅ ህብረተሰብ ነው፡፡ ትላንትናችንን ረግጠን ካጠፋነው የዛሬ ደጃፍ ላይ የደረስነው በተሳሳተ ጐዳና መጥተን ነው ማለት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን እንኳ ብንነሳ የትኛው መንግስት ለየትኛው መንግስት ነው እዚህ ድረስ አምጥቻለሁ” አንተ ደግሞ በተራህ ዱላውን ተቀበለኝና ድንበርህ ድረስ ሮጠህ ለሌላው ስጥ ያለ? አጼ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ምንሊክ፣ ኢያሱ…እያልን መመልከት እንችላለን፡፡ በአንዱ ስራ ላይ ሌላው አክሎበት የምንጓዘው መቼ ይሆን? የሚል ይመስላል ቴዲ!

አንተ አብረሃም የኦሪት ስባት

የነ እስማኤል የይስሃቅ አባት

ይህን በማለት አንድነታችን ከአንድ የዘር ምንጭ እንደሚቀዳ ይገልጻል፡፡ አያይዞም ውስጤን በፍቅር እሳት አሙቁት በማለት ይማፀናል፡፡ እሱ ውስጡን የሚያመው አንድነት፣ ፍቅር፣ መተሳሰብና መተዛዘን ሲጠፋ ነው፡፡ ያኔ “ወዮ” ይላል፤ አመመኝ ይላል! ይጮሃል - ይህ እስኪፈፀም ድረስ፡፡

ሰው ለመውደድ ካልኩኝ ደከመኝ

ያኔ ገና ውስጤን አመመኝ

አመመኝ አመመኝ…

አትድከም፣ አትዛል፣ ልቤ ሁሌ ቀና ሁን… ብሎ የገሰጸው ልቡ ለፍቅር የሚደክም ከሆነ “አመመኝ” ሲያንሰው ነው፤ ሲያንሰን ነው፡፡

 

 

Read 4942 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 13:18