Print this page
Wednesday, 20 March 2019 00:00

ኒውዮርክ በቢሊየነሮች ብዛት የአለማችንን ከተሞች ትመራለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የከተማዋ 84 ቢሊየነሮች 469.7 ቢ. ዶላር ሃብት አፍርተዋል

       በፈረንጆች አመት 2019 ከአለማችን ከተሞች መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸው ቢሊየነሮች መኖሪያ በመሆን ኒውዮርክ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንና በከተማዋ 84 ቢሊየነሮች እንደሚገኙ ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡
የአሜሪካዋ ቁጥር አንድ ግዙፍ ከተማ ኒውዮርክ፣ ቴክኖሎጂና ሪልእስቴትን ጨምሮ በተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙት እነዚሁ 84 ቢሊየነሮች በድምሩ 469.7 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት እንዳላቸውም የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም ቁጥር ከአውስትራሊያ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት እንደሚበልጥም አመልክቷል፡፡
የተጣራ ድምር የሃብት መጠናቸው 355.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ የተነገረላቸው 79 ቢሊየነሮች መኖሪያ የሆነቺው ሆንግ ኮንግ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ የሩስያዋ መዲና ሞስኮ 336.5 ቢሊዮን ዶላር ባፈሩ 71 ቢሊየነሮቿ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
የቻይና መዲና ቤጂንግ በ61 ቢሊየነሮች፣ የእንግሊዟ መዲና ለንደን በ55 ቢሊየነሮች፣ የቻይናዋ ሻንጋይ በ45 ቢሊየነሮች፣ ሳንፍራንሲስኮ በ42 ቢሊየነሮች፣ ሌላኛዋ የቻይና የንግድ ከተማ ሼንዜን በ39 ቢሊየነሮች፣ የደቡብ ኮርያዋ ሴኡል በ38 ቢሊየነሮች እንዲሁም የህንዷ ሙምባይ በ37 ቢሊየነሮች እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውም ተነግሯል፡፡
ቻይና የበርካታ ቢሊየነሮች መቀመጫ በመሆን ከአንደኛ እስከ አስረኛ ደረጃ በተቀመጡት ከተሞች ዝርዝር ውስጥ ሶስት ከተሞቿን በማስመዝገብ ቀዳሚነቱን ይዛለች፡፡
በ2019 የፈረንጆች አመት የፎርብስ መጽሄት የአለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት 2 ሺህ 153 ቢሊየነሮች መካከል 551 ያህሉ በ10 ከተሞች ውስጥ እንደሚኖሩ የጠቆመው ዘገባው፣ እነዚህ ቢሊየነሮች ያፈሩት ጠቅላላ የተጣራ ሃብት 2.3 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚደርስም አክሎ ገልጧል።

Read 2056 times
Administrator

Latest from Administrator